እስክንድር ነጋ ምን ነካው? ዲን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
ሰሙኑ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከወደ ቃሊቲ እስር ቤት ለኒውዮርክ ታይምስ “Letter From Ethiopia’s Gulag” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ በጻፈው ደብዳቤ እ.አ.አ ጁልይ 24, 2013 ለህትመት በበቃ ጽሑፍ “I am confident that America will eventually do the right thing. After all, the new century is the age of democracy primarily because of the United States” የምትለዋን ዓረፍተ ነገር በአንዳንድ አጨብጫቢዎችና ከበሮ መቺዎች ዘንድ ለብቻዋ ተቀንጭባ ሲያራግቧት ስትራገብ ሰንብታለች። እንደው “ታድያ ምን ችግር አለበት?” በማለት ነገሩን አቅልለው ያዩት ይሆን ይሆናል። ቁምነግሩ/ፖለቲካዊ አንድምታው ያለው ወዲህ ነውና ልብ ብለው “ይከተሉኝ”።
የጽሑፉ ይዘትና ዓላማ፥
ጽሑፉ በይዘቱ ሁለት ክፍሎች ሲኖሩት ቀዳሚው ክፍል የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መልእክት ከደብዳቤው ሙሉ ይዘት በማጉደል እንደ መፎክር እያውለበለቡ ለሚገኙ ነፍስ ያልዘሩ አዳማቂዎች እርምትና ማስተካከያ ለመስጠት የተጻፈ ሲሆን ተከታዩና ሰፊው ክፍል ክፍል ሁለት ደግሞ በእስክንድር ነጋ አባባልና ብዕር “After all, the new century is the age of democracy primarily because of the United States” ተብላ የተወደሰችው ሀገረ አሜሪካ ዲሞክራሲ ምን መልክ እንዳለው ለአንባቢያን ማስተዋውቅና የሚተረጉም ክፍልም ይሆናል። መልዕክቱን ለሚያነቡ ሁሉ ሰላም ይሁን!
ሐተታ፥
የምዕራባውያን ነገር በተለይ ከሦስተኛ ዓለም ሀገራት ያላቸውን ግኑኝነት በተመለከተ ፖለቲካዊ ጣልቃ በመግባት ሳይቀር “ይህን ብታደርጉ አለንላችሁ!። የለም! ያላችሁ እንደሆነ ግን ቀረባችሁ!” ዓይነት መልዕክት ያዘሉ መልዕክቶችና መግለጫዎች የምንሰማበት ሰዓት እንገኛለን። ታድያ እንዲህ ባለ ፈታኝ ወቅት (የሀገር ሉዓላዊነት በተመለከተ ማለቴ ነው) ተቃዋሚ አካልም ቢሆን “የቀረ ይቅር እንጂ ኢትዮጵያ ኬንያ አይደለችም!” በማለት ለሀገሩ ሉዓላዊነትና ለሕዝቡ ክብር የማይቆምበት ምክንያት እጅግ ያሳስበኛል። የትኑም ያክል በሥልጣን ላይ ያለው/የሚገኘው መንግሥት ብንቃወም የጋራ ስለሆነችው ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በተመለከተ ግን እንደ አንድ ሰው በአንድ ልብ መቆም እንደሚገባን ምንም ሊያደራድረን ባልተገባም ነበር። ለሀገራችን ሉዓላዊነት መቆምና ጠብቆ የማስጠበቅ ጉዳይም እንዲሁ በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት ብቻ ግዴታ አይደለም። ጉዳዩ የዜጎች ሁሉ ግዴታ ነው። ሀገራዊ ግዴታችን መወጣት ማለት ደግሞ በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት ከመውደድና ከመጥላት ጋር አንዳች የሚያገናኝ ነጥብ የለውም። ምን ነው ቢሉ ኢትዮጵያ ስልጣን ላይ የሚገኙ የባለ ስልጣናት (መንግስት) ርስት አይደለችም። ሀገር የሁላችን ናት!
ለሞፈክር ወዳጆች ቁምነግሬን በአጭሩ እንደሚከተለው ነጥብ በነጥብ ላስረዳ/ላስቀምጥ፥
- አንደኛ፡ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጥቅሟን የምታስከብርበትና የምትጠብቅበት እንዲሁም ከሌሎች ሉዓላዊ ሀገራትና መንግስታት የምትገናኝበት ሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች መስመሮችና ግኑኝነቶች ለመኖሩ ማናችን ብንሆን እንስተዋለን የሚል እምነት ባይንረኝም በምድሪቱ ውስጣዊ ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁ አሜሪካ ጨምሮ ማናቸውም ምዕራባውያን ሀገራት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ምን ማድረግና የትኛው መንገድ ተከትለን መሄድ እንዳለብን የማዘዝም ሆነ ቀጭን መምሪያ የመስጠት አንዳች ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ሥልጣን የላቸውም።
- ሁለተኛ፡ ኢትዮጵያ እንደ ማናቸውም የበለጸጉ ምዕራባውያን ሀገራት ከነድህነትዋ እኩል ሉዓላዊት ሀገር ናት! ዕልል ያለ ነጭ ድህነትዋም እንደሆነ ከዚህ ክብር/ሙላት “የሰናፍጭ ቅንጣት” ታክል አያጎድላትም።
- ሦስተኛ፡ የኢትዮጵያ መጻኢ/ዕጣ ፈንታ ፓለቲካዊ/ሀገራዊ ጉዳይ በተመለከተ የሚበጀውን አውቆ ውሳኔዎችን የማስተላለፍና የማጽደቅ ባለ ሙሉ መብት የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ድርሻ ብቻ እንጂ የባዕድ ሀገራት ስልጣንም አይደለም።
በነገራችን ላይ አንድ ዜጋ የሀገሩን ሉዓላዊነት አሳልፎ ከመስጠትና ከሟንቃሸሽ በላይ ሌላ ምንም ዓይነት የከፋ ሀገራዊ ክህደትና ወንጀል ሊፈጽም አይችልም። ወጣም ወረደ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ልዩነቶቻችን እንደ ተጠበቀ ሆኖ የሀገራችን የሉዓላዊነት ጉዳይ፣ የሕዝባችን ክብር ስለ መጠበቅ ግን ልዩነታችንን በማጥበብ እንደ አንድ ሰው ማሰብና መቆም ይገባናል። በተረፈ ግን በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የማያምን የፓለቲካ መሪ፣ የሚድያ ተቋም እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅቶችና “የሲቪክ ማኅበራት” ስለ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት አፉ/አፋቸው መልቶ/ተው የመሟገትም ሆነ የመናገር መብት የለውም/የላቸውም። ምን ነው ቢሉ ሉዓላዊት የሆነች ሀገር ስትኖር ነው ስለ ሀገር፣ ስለ ተገፉ ዜጎች መናገርም ሆነ ጠበቃ መሆን መቆምም የሚቻለውና። ለሀገሩ ሉዓላዊነት ልብም ሆነ ስፍራ የሌለው ግለሰብ ሆነ ድርጅት ግን እሱ ታዳጊ/ነጻ አውጪ ሳይሆን የበግ ለምድ የለበሰ በላተኛ አውሬ ወንበዴም ነው።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ምን ነካው?
በሀገሬ ሳለሁ ከአንዴም ሁለቴ በእስር ያለፍኩ ግለሰብ እንደመሆኔ መጠን ለዛሬ ጽሑፌ መነሻ የሆነም በእስር የሚገኘው ግለሰብ በመሆኑ ይህን ጽሑፍ ለንባብ ሳበቃ በግለሰቡ ሁኔታ “በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” ለመሆን ቃጥቶች ሳይሆን እስክንድር በእንግሊዝኛ ቋንቋ “ለኒውዮርክ ታይምስ” ጻፈው በተባለ ደብዳቤ ውስጥ የተሰነጠረችው ተንተርሼ ግላዊ “ፖለቲካዊ” ትንታኔ ከመስጠት ያለፈ ጽሑፉ ሌላ ምንም ዓይነት ዓላማም ሆነ ተልዕኮ እንደሌለው ስገልጽ በአክብሮት ነው።
እስክንድር ከቃሊቲ ጻፈው ተብሎ ለንባብ የበቃ ጽሑፍ በይዘቱ የጸሐፊው የእምነቱ ነጸብራቅና የግለ ህይወቱ አቋም እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። የጻፈውን የሚያምነውን ነው። የተጻፈም መልእክት ለማስተላለፍ ነው። ምን ዓይነት መልዕክት? ለሚለው ጥያቄ ግን ነገሩ ከጸሐፊው እጅ ይወጣና ለመቀበልም ላለመቀበልም እኔን ጨምሮ ተደራሲው ወገን/አንባቢን ሁሉ የሚያሳትፍ ይሆናል። ስለሆነም አንድ የምዕራብ ዜጋ ሌላ ሀገር፣ ቋንቋና ባህል በምድር የሌለ እስኪመስል ድረስ በሀገሩና በዜግነቱ እንደሚኮራ ሁሉ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ያበረከትኩት ተፈጥሮአዊ አስተዋጽኦ ባይኖረኝም እንደ ሰውኛ አነጋገር ሀገር አለኝ ማለቴ ካልቀረ ኢትዮጵያ ከነድህነትዋ ሀገሬም ክብሬም ናት! በማለት የተሳሳተ እንዲታረም: አውቆ ለሚያጠፋ ደግሞ መልስ ብጽፍ ምን ይለኛል?
በእስክንድር ነጋ ተጻፈ ተብሎ ለንባብ የበቃ ደብዳቤ ሀገር ተረካቢው ትውልድ ስለ ሀገሩ ሊኖረው የሚገባ አመለካከትና ክብር እጅግኑ የሚያጎድፍ: ራዕይ የለች: ደንታ ቢስና ነህዘላል ትውልድ በማፍራት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክት በአስቸኳይ ሊታረም የሚገባ አመለካከት ሆኖ አግኝቸዋለሁ። እውነት ነው መንግስት ከሚከተለው ፖሊሲም ሆነ ከሚያራምደው ፖለቲካዊ አቋም የተነሳ አለመግባባት/ልዩነት ሊኖረኝ ይችላል። ደግሞም የሃሳብ ልዩነት ያለ ነው። በበኩሌ በደፈናው ሳይሆን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲዎችና ፖለቲካዊ መርህ የሃሳብ ልዩነት ያለኝና በጽኑ የምቃወም ግለሰብም ነኝ። ዳሩ ግን ሀገርን ከጊዜያዊ የፖለቲካ ባለ ስልጣናት በማገናኘት በሀገሬ ሉዓላዊነት የሚደራደር አእምሮ የለኝም። ሀገርን ከጊዜያዊ የፖለቲካ ነጥለህ አለማየት ደግሞ መጨረሻው የማያምር ልክፍት ለመሆኑ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ይስተዋል የሚል እምነት የለኝም።
ችግር አለ ወይ የለም? ችግር አለ! ታድያ በሀገሪትዋ አለ የሚባለውን ችግር ሊፈታ የሚችለው የሀገር ሉዓላዊነት አሳልፈህ በመስጠት ነው ወይ? እስክንድር የኢትዮጵያ ችግር ሊፈታ የሚችለው በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ነው ብሎ የሚያምን ከሆነ እጅግ ተሳስተዋል። ስህተት መስራቱ ብቻም አይደለም ድርጊቱ እጅግ አሳፋሪ ነው። የኢትዮጵያ ችግር በኢትዮጵያውያን ትግል መሆኑ ቀርቶ በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ወይም ጡንቻ ነው የሚፈታ ብሎ የሚያምን ከሆነ በእውነቱ ነገር እዚህ ሁሉ አሁን የሚገኝበት ሁኔታ ውስጥ መግባት አይጠበቅበትም ነበር። እስክንድር የሚሰማው ካገኘ እውነት ነው “አሜሪካ ሆይ! ለኢትዮጵያ እርዳታ አትስጡ” በማለት ጥሪውን ማቅረብ ይችላል። ከዚህ ያለፈ ግን አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንድትገባ ጥሪ የማቅረብ መብት ግን የለውም። የጻፍኩትን ጽፌአለሁ የሚል ከሆነ ደግሞ ይህ ደብዳቤ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የሚያሳየው እስክንድር የአቋም ለውጥ ማሳየቱ ብቻ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ያለውን የወረደ አቋም የሚመሰክር ነው። ከሚገኝበት ሁኔታ ለመወጣት የመጸጸት መንፈስ እያሳየና ጥፋተኛም ነኝ ብሎ የሚያምን ከሆነ “ተጸጽቻለሁ ይቅርታ ይደረግልኝ” በማለት አቤቱታውን ማሰማትና ማቅረብ የሚገባው ላሰረው አካል እንጂ ለአሜሪካ መንግስት አይደለም። አሜሪካ ፈርጣማ ወታደራዊና አስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ አቅም ስላላት ብቻ በደካማዋና ድሃዋ አገር ኢትዮጵያ ያሻትን ታደርግ ዘንድ ጥሪ ማቅረብም ሆነ የወደደችውን ማድረግ ትችላለች ብሎ ማሰብ በራሱ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው።
ሌላው የእስክንድር አቀራረብ የአሜሪካ መንግስት ሆድ ያባባል ወይ? ለሚለው ጥያቄ ለጊዜው ነገሩን ለአሜሪካ ባለ ስልጣናት እንተወውና መሬት ላይ ያለውን አንድ የተገለጠ እውነታ አንስተን እንወያይ። ይኸውም: ውዳሴ ታክሎበት አፈር በሚያንከባልሉ ቃላቶች ቢጻፍም ነገሩ ለአሜሪካ የሚያስገኘው ጥቅምና ትርፍ እስከሌለ ድረስ የአሜሪካ ባለ ስልጣን ጊዜያቸው የሚያጠፉበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌላቸው አሜሪካ የምትከተለው የውጭ ፖሊሲ በጥንቃቄ ማጥናትና ማወቅን ይጠይቃል። አሜሪካ ስለ ሰብዓዊ መብት የሚገዳት አገር ብትሆን ኖሮ አሁንም ድረስ ሴቶች ሙሉ ሰው መሆናቸው ቀርቶ እንደ ግል ንብረትና እንደ ግማሽ ሰው የሚታይባቸው ሀገራት ይቅር ወዳጅነት ልትመሰርትና የኢኮኖሚ አጋር ልትሆን ልትወስደው የምትችለውን እርምጃ ይታይዎት። መንግስታቱ የተጠየቁት ሳያንገራግሩ በዝግታ እስከገበሩ ድረስ ግን አሜሪካ “የለም! ይህን ነገራችሁ አስተካክሉ” በማለት አፍ አውጥታ የምትናገርበትና የምትገስጽበት ምንም ዓይነት ምክንያት የላትም።
እስክንድር “After all, the new century is the age of democracy primarily because of the United States” ሲል ወደ ጻፈው እንመለስ። የ17 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ትራይቮን ማርቲን በግፍ መገደናልና ገዳዩ ነጭ አሜሪካዊ ዚመርማን በነጻ መለቀቅ፤ የኤድዋርድ ስኖውደን የሀገሩ የአሜሪካ የጸጥታና የደህንነት ቢሮ ከፍተኛ ምስጢራዊ ሰነዶች ይዞ ወደ ሆንግ ኮንግ ከዚያም ወደ ራሽያ ማቅናቱን ተከትሎ የአሜሪካ ባለ ስልጣናትና ከፍተኛ የመንግስት ሹማምንት የወጣውን ለመመለስ የሞከሩትን ሙከራ ዓለምን አስደምመዋል። እነዚህ ሁለት ክስተቶች ከዚህ ቀደም በግላጭ በአደባባይ ታይቶ የማይታወቅ የአሜሪካ ገጽታ ፍንው አድርገው ለዓለም ያሳዩና አሜሪካ በዓለም መድረክ ያራቆቱ ክስተቶች ሲሆኑ “የዲሞክራሲ” ትሩጓሜም ደብዛው አጥፍተውታል። ወይስ እስክንድር ስኖውደንን ጥገኝነት ስለ መስጠት ተከትሎ የአሜሪካ ሕግ አውጪው አካል ኢኳዶር ይህን የዋለችው እንደሆነ ምትርዋን ወደ አሜሪካ በመላክ ከአሜሪካ የምታገኘውን 23 ሚልዮን ዶላር ይቀርባታል በማለት ሲዝቱ ይህን የሰማ የኢኳዶር መንግስት ደግሞ በበኩሉ ሳይውል ሳያድር ስለ ሰብዓዊ መብት ለግንዛቤ ማስጨበጫ የሚውል ዓመታዊ 23 ሚልዮን ዶላር በርታዳ መልክ ለአሜሪካ መንግስት ማበርከትዋን አልሰማ ይሆን?
ለማንኛውም በእስክንድር አእምሮ ዲሞክራሲ ሲተረጎም ምን ማለት እንደሆነ ይህ ነው ለማለት ባልደፍርም በተወሰነ መልኩ ግን ቁም ነገሬን እንደሚከተው አሰፍራለሁ።
- ዲሞክራሲ ማለት መንግስት የሕዝብ ይሁንታ በሌለበትና በህገ ወጥ መንገድ ራሱን አደራጅቶ ዜጎቹን መናጥና ማድቀቅ ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም ምስጢራዊ ፍርድ ቤት በማቋቋም ሕዝብ መውቀር ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም የሰው ሀገር በቦንብ አያፈንዳህ፣ ሕዝብ ፈጅተህና አፋጅተህም ስታበቃ አጀንዳህን የሚያስፈጽምልህ መንግስት መሾምና መጫን ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም ድምጹን ሰጥቶ ወደ ስልጣን የሚያወጣህን ሕዝብ በስውር መሰለል ማለት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም ሕገ መንግስታዊ መብቱ ተጠቅሞ እውነቱን የሚናገር ስመ ዝክሩ ከምድረ ገጽ ለማጥፋትና ለመደምሰስ እንቅልፍ ማጣት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም እኔ በምለው ነገር ካልተስማማችሁ ከእኔ ጋር ካልቆማችሁና ካላበራችሁ ሊገጥማችሁ የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይታያችሁ በማለት ሉዓላውያን ሀገሮችና መንግስታት ማስፈራራትና መዛት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም ሕዝብ በፖለቲካ መሪዎቹ እምነት ማጣት ማለት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም የፖለቲካ የመንግስት ባለ ስልጣናት ማለት ከሕግ በላይ ናቸው ማለት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም የፖለቲካ የመንግስት ባለ ስልጣናት በሚሰሩት ጥፋትና በሚፈጽሙት ወንጀል በህግ አይጠየቁም ማለት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም መንግስት የሀገሪቱ ሕገ መንግስት በመጣስ የወደደውን ማድረግ ይችላል ማለት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም ለህገ መንግስት የቆመ ዜጋ ማደንና ማሳደድ ማለት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም ወንጀለኛን ወንጀለኛ ያለ በወንጀል መፈረጅ ማለት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም በጨለማ ላይ ብርሃን ያበራ ዓለም በቃኝ ማውረድና መቆለፍ ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም መንግስትን መጠየቅ በመንግስት ጥርስ የሚያስገባ ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም ስልጣን የሕዝብ መሆኑን ቀርቶ ስልጣን የባለ ስልጣናት ነው ማለት ከሆነ፤
- ዲሞክራሲ ሲተረጎም ሕዝብ ድምጹን ሰጥቶ ያስቀመጠው/የሾመው መንግስት የሚሰራውን ስራ የማወቅ መብትየለውም ማለት ከሆነ እስክንድር አልተሳሳትክም። “እውነት” ብለሃል። ግን ደግሞ የጻፍከው ደብዳቤ ከራስህ ጥቅም አንጻርና ግለ ሁኔታህን ብቻ ያማከለ ከእውነታ የራቀ እንደሆነ በተጨማሪም ቅንነትና እውነት እንደሚጎድልብህም በአደባባይ ስገልጽ በአክብሮት ነው።
ቀደም ሲል “After all, the new century is the age of democracy primarily because of the United States” ተብሎ የተጻፈ የምልጃ ደብዳቤም “After all, the new century is the age of violence and political chaos primarily because of the United States” በሚል ዓረፍተ ነገር ጸሐፊው ራሱን አስተካክሎ እንዲመጣና ራሱን እንዲያርምም ባልገፋው ይህን ጽሑፍ የሚያንብ አንባቢ ዜጋ ሁሉ ግን ቢያንስ ቢያንስ አንድ ቁምነገር ራሱን ያስተምራል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ።
በመጨረሻም ኢየሱስ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” እንዲል ሁሉም ነገር በብልሃት ነውና የሀገሬ መንግስት ሲገፋኝ ተቀብላ፣ ልዩ ከፍተኛ የትምህርት ዕድል ሰጥታም አስተምራ አሁን ለምገኝበት ደረጃ ላበቃችኝ ሀገረ አሜሪካ ያለኝ ክብርና የላቀ ልባዊ ምስጋናዬን በዚህ አጋጣሚ በመግለጽ ጽሑፌን እዚህ እቋጫለሁ።
“If there is no struggle, there is no progress. Those who profess to favor freedom, and yet depreciate agitation, are men who want crops without plowing up the ground. They want rain without thunder and lightning. They want the ocean without the awful roar of its many waters. This struggle may be a moral one; or it may be a physical one; or it may be both moral and physical; but it must be a struggle.” ወያኔ፥ ጸሐፊ፥ ፖለቲከኛ፥ አንደበተ ርቱዕ ጥቁር አሜሪካዊ ፍረደሪክ ዶግላስ
የሀገር ሉዓላዊነት አሳልፈህ በመስጠት የሚፈታ የሀገር ችግር የለም!
ዲን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E-mail: [email protected]
United States of America
August 2013