የወያኔ ምህረትና የደርግ ባለስልጣኖች
ምንም ቢሆን ምህረትን የማይወድ ፍጥረት ያለ አይመስለኝም። ሰው ይሳሳታል፤ አውቆም ሳያውቅም ያጠፋል ይቅር መባባል ከሰው ልጅ መልካም ባህሪ አንድ ነው። የወያኔን ለቀድሞ ባለስልጣናት ምህረት ማድረግ የተቀበልኩት በተቀላቀለ ስሜት ነው። ደርግ ሃገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ ላይ እንድትሆን ለወያኔና ለሻብያ ካመቻቹት ሃይሎች ቀዳሚው ነው። ለውድ ሃገራቸው በቅንነትና በጀግንነት የሚፋለሙትን ሁሉ በየምክንያቱ በማስርና በመግደል የሠራዊቱ ጉልበትና ያመራር መዋቅር እንዲላላና እንዲፈራርስ በማድረግ ዛሬ ወያኔ በአዲስ አበባ ሻብያ በአስመራ እንዲፈነጥዙ የረዳው የደርግ ጭፍን አመራር ነው። ያ ከሃያ ዓመት በፊት የሆነው ነው። እስኪ አሁን ወደ ዛሬው እንመለስ። የኤርትራው መሪ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ የለገሷት ያሁኒቱ ኢትዮጵያ የወያኔ መጭፈሪያ ከሆነች እንሆ ሃያ ዓመት አለፈን። በእነዚህ ዓመታት ሃገሪቱ በዘርና በጎሳ ተከፍላ አንገት አልባ ቆማለች። ትላንት የኤርትራን ነጻነት እወቁልኝ በማለት በዓለም ዙሪያ የለፈፈውና ሃገራችንን ያለ ባህር በር ያስቀረው ወያኔ ዛሬ በአስመራ የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ የጦር መሳሪያ በመሽመት ላይ ይገኛል። ቅማልን የት ትሄጃለሽ ቢሏት መተማ። ትደረሻለሽ? ልብማ እንዳሉት ተርት ነው። ለፍላፊው ወያኔ በህዝባችን ላይ መቀለድ የጀመረው ገና በበረሃ እያለ ነው።
አሁንም እንሆ ለቀድሞ የደርግ ባልስልጣኖች የተደረገው ምህረት ህዝባችንን ለመከፋፈልና ለውጭ ሃገር የወሬ ፍጆታ ብቻ ነው። ወያኔ በየቀኑ በማፈን፤ በመግደልና በማሰር የህዝባችንን ስቆቃ እያባባሰው እንደሆነ በምድሪቱ የሚተራመሱት ዘጠና ሚሊዪን ሃበሾች ይረድታል። የሃገሪቱ የጦር ሃይል የተዋቀረው በአንድ አናሳ ጎሳ ብቻ ነው። የሃገሪቱ ሃብትና ንብረት እንካቹህ የሚባለው ለወያኔ አባልና ለተለጣፊው ድርጅት ብቻ ነው። ለመኖር ትገላለህ፤ ታስራለህ፤ታፍናለህ፤ትሰርቃለህ። ሲበቃቸውም ጣዕሙ እንዳለቀ የሽንኮር አገዳ አክ እንትፍ ይሉሃል።
ታዲያ አሁን ከሃያ ለሚበልጡ የቀድሞ ደም አፍሳሾች ምህረት አረኩ ሲለን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ጉዳይ አለ። በደርግ ሥር በክፍለ ሃገር፤ በአውራጃና በወረዳ በስልጣን ላይ ሆነው እስከ ዛሬ በእስር ያሉትን ምህረት የሚያረግላቸው ማን ነው? ከዚህም በላይ ወያኔ በድብቅ እስር ቤቶች ያከማቻቸውን የሃገሪቱ ዜጎችን የሚፈታው? የሃገሪቱን ለም መሬት ስብዕና ለሌላቸው ቻይናና ህንድ ማስረከቡን የሚያቆመው? የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እንደማስከበር የጠረፍ ድንበርና ከተሞችን ለባዕድ መንግሥት አሳለፎ መስጠቱ የሚገታው መቼ ነው?
በመሰረቱ የምህረት ግማሽ ጎን የለውም። የቀድሞዎቹ የደርግ ባልስልጣናት ከታገቱበት ስፍራ ተለቀው ለቤታቸው ቢበቁ ደስ ይለኛል። ያዘው ጥለፈው እያልን ለዘመናት ኑረናል። ያለሞከርነው ነገር ምህረትን ምህረት ለማይገባቸው እንካቹህ ማለት ነው። ስንገዳደል፤ ስንወነጃጀል ኖረናል። ወያኔ በየስርቻው አፍኖ የያዛቸውን የድብቅና የስውር እስረኞች ሁሉ መልቀቅ ይኖርበታል። ፍትህ የሌለው መንግሥት ቀን ሲለወጥ መደበቂያ የለውም። ወያኔ ልብ ገዝቶ ህዝባችንን ማዋከቡን በማቆም ስልጣንን ህዝብ ለመረጠው እስካላስረከበ ድርስ አወዳደቁ የሮም አወዳደቅ ነው የሚሆነው። የዛሬው ድንፋታ ቀን ሲጨልም አይገኝም።
ሰንብተን እንይ
አደፍርስ ተሰማ