የካህናት እልልታ የምዕመናን እሪታ (ከበርን – ስዊዘርላንድ)
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በተክልዬ ልጆች መከፈል ከልቡ ያዘነ፣በሚነዛው አሉባልታ ልቡ የበገነ የሰበካ ጉባኤ አባል ነው፡፡ ውሸታሞች ውሸታቸውን ማቆም አለባቸው ብሎ ስለሚያምን ውስጠ ነገሩን ለማወቅ ለሚጨነቅ ሁሉ አቅጣጫ ለማስያዝና ፍጹም በማይገኘው የበርን ችግር ጅማሬ እና ፍጻሜ ላይ የስዊዝ ምዕመናን መጠነኛ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተደረገ ሙከራ ነው፡፡ ጉዳዩ ማህበራዊ ሆነና እኛ እያለ ለመጻፍ ቢገደድም በጽሑፉ የሚዳሰሱ ነገሮች በሙሉ ከእውነት ያልወጡ ጸሐፊው በግሉ ኃላፊነት የሚወስድ መሆኑን ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡ ስለዚህም እኛ ብዬ ልጀምር፡፡
እልልታው ይቀጥል ጉሮ ወሸባው ይድራ
የአባ ተጋድሎ በስዊዘርላንድ በራ፡፡
ካህናት ዲያቆናት ተባብረው በአንድነት
የተክልዬን መንጋ ከፈሉት ለሁለት፡፡
እልል እልል ዲያቆኑ!! እልል እልል ቄሱ ካህኑ!! እልል እልል መነኩሴ!!
እንደዛሬው በመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ሳንጥለቀለቅ፣ በትዳር ተጣምረን ወደ ሚስጢር ህይወት ሳንጠልቅ፣ በልጆች ተከበን በተድላ በደስታ ሳንፍለቀለቅ ያኔ፣ ያኔ ምንም ባልነበረን በዚያች የመከራ ወቅት በአንድ ሀሳብ በአንድ መንፈስ የተክልዬን መሰረት በሶሊኮፈን /Zollikofen/ ስንጥል ያሰባሰበን ክርስቶስ በደሙ የመሰረታት አንዲቷ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነታችህ እንደነበረች የማይረሳ ነው፡፡ በዚያ ወቅት አንተ የአባ ___ አንቺ የአባ __ የሚል የዘመኑ አማርኛ በመሀከላችን የመስተናገድ ቦታ አልነበረውም፡፡
በክርስቶስ ፍቅር ተሰባስበን የአመለክነው አምላካችን ትንሽ በትንሽ አሳድጎን በቁጥርም ከቀን ወደ ቀን አብዝቶን ከሩቅ ኮሊሎፈን / Zollikofen / ወደ መሃሉ በርን ሲያመጣን ከጉባኤ በኋላ በመከራ ተለይተን ቀጣዩን የምንገኝበትን ቀን ከመናፈቅ ውጭ እንኳን ለዲያብሎስ ለነፋስም ቦታ አልነበረም፡፡
የመነኩሴው ተንኮል የዲያቆኑ ሸር
በአንድ አንደበት ሆነን እንመክር ነበር፡፡
ድብቁ ዓላማ የአባ ተልኮ
በመሰሪው ዲያቆን እንዳይገባ ሾልኮ
ጥብቅ ነበር በሩ አጥሩ ብረት
አባ እንደ ዛሬው ላይሰባብሩት፡፡
የነውጡ ጅማሬ፡
የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ አንድ ጳጳስ ከአዲስ አበባው ሲኖዶስ የምዕመናኑ ፍላጎት በመነኩሴው፣ በዲያቆኑና በጥቂት ግለሰቦች አቀናባሪነት ወደ በርን ሰበካ ጉባኤ ከመጡበተ ከዚያች የተረገመች ቀን ጀምሮ ሰላችን ተነጠቀ፤በሀሳብ መለያየት ተጀመረ፤ መተማመን ጓዙን ጠቅልሎ ወጣ፤ ላንጠገን ተሰበርን፡፡
የምዕመናኑ ፍቅር ጥንካሬ፤የህፃናቱ ምስጋና ዝማሬ ያቃጠለው ዲያብሎስ አመቺ ቀዳዳ ተፈጠረለት፡፡ በተፈጠረው ቀዳዳ አባን ተከትሎ ገባ፡፡
ችግሩን ለመፍታት ጉባኤ ተቀምጠን፤ ግርግር የሚወዱት መነኩሴ ከጄኔቭ እየበረሩ መጡ፡፡ ፖለቲከኞች በማለት ግለሰቦችን ለማስገለል ተጣጣሩ፡፡ የበርን ፍቅር መሰረቱ ጠንካራ ነበርና ያቀነባበሩት ሴራ ሳይሳካላቸው አፍረው በንዴት ወደ መጡበት ተመለሱ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርን አባ ጥርስ ውስጥ ገባ፡፡
በወቅቱ የተወሰዱ እርምጃዎች፡
ለተፈጠረው ችግር ወደፊትም ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ ይሆናል ተብሎ በማሰብ የበርን ሰበካ ጉባኤ መተዳደሪያ ደንብ በቄሱ፣ በዲያቆኑ እና በኮሚቴው ተረቆ ለምዕመናኑ ቀርቦ፣ ትምህርት ተሰጥቶበት ያለምንም ተቃውሞ ፀደቀ፡፡ ለዚህም ምስክሮቹ ሁላችንም ምዕመናን ስንሆን ይህንን ክዳን ለምንዋሽ ሁሉ ዳኞችን በቤታቸው፣ በፊታቸው ያደረግነውን የታዘቡ ፃድቅ አቡነ ተክለሃይማኖት እንደሆኑ እናረጋግጥላችኋለን፡፡ በዚህ መተዳደሪያ ደንብ እስከ ዛሬ ሲሰራበት ጓዳ ለጓዳ ከሚናፈስ አሉባልታ ውጭ ማንም በጽሑፍ የተቃወመ የለም፡፡ በደንባችን መሰረት በበርንም በጠቅላላ ስዊዘርላንድ በአገልግሎት ስንተጋ ኖረናል፡፡
ስውሩ እጅ፡
በየደረሱበት ሁለት ዓመት ታገሰናቸው ሲሉ የሚደመጡት መነኩሴ ስውር እጃቸው እና የተቀነባበረ ተንኮላቸው በርንን ተለይቶ አያውቅም፡፡ አሉባልታን በማስወራትና ሰውን በሰው ላይ በማነሳሳት ካህኑና ዲያቆኑ ያቀነባበሩት አመፃ እያደረገ መጥቶ በጉባኤ መዘላለፍና በልጆች ፊት መሰዳደብ ተደጋገመ፡፡ መነኩሴውም በቅዳሴ በአደባባ ወጥተው ወንጌልን ያስተማሩ በማስመሰል ቂመኞች አድመኞች፣ በነጠላቸውና በቀሚሳቸው ስር ኃጢያታቸውን ይዘው የሚቆረቡ… በማለት በበርና ላይ ያነጣጠረ ትምህርት ሰጡ፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል የበርንን ፍቅር እንደ ቀደሙ ለመመለስ ጥረቱ አልተቋረጠም፡፡ ወንድማማቾችን እርስ በርሳቸው ይቅር አንዲባባሉ ተጥሯል፤እህትማማቾች ወደ ቀደመው ፍቅራቸው እንዲመለሱ ተሞክሯል፤ የሰላም ቀን ታስቧል፤ የሰላም ጉዞ ተካሂዷል፤ የሰላም ወረቀት ተበትኗል፤ የሰላም ሲዲ ተሰራጭቷል፡፡ ምዕመናኑ እሳቱን ለማጥፋት ሲደክሙ ኃላፊነት ያለባቸው መነኩሴ፣ ካህናትና ዲያቆን ግን ቤንዚን በማርከፍከፍ ሲያቀጣጥሉ ከረሙ፡፡ ለነገሩ ቄስ እና መነኩሴ የቋጨውን ማን ሊፈታው ይችላል?
ሉዘርን፣ አራው፣ ሰንጋለል… የሚሰባስባቸው እና የሚያስተምራቸው አጥተው ሲበታተኑ የእኛ አባ ወንጌልን እየተዘዋወሩ እንዲያስተምሩበት ምዕመናኑ ከዕለት ጉርሲ ቆርሶ በቆረጠላቸው የዓመት መጓጓዣ ትኬት እግራቸውን እስኪቀጥን በርን በመመላለስ በመጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ስድስት ከቁጥር 16-19 የተጠቀሰውን የእግዚአብሔር ነፍስ አጥብቃ እንደምትፀየፈው በወንድማማቾች መካከል ጠብን መዝራት በተራቀቀ ሁኔታ ፈጸሙት አስፈጸሙት፡፡
ገድል ሆኖ ይፃፍ በአባታቸው ዘንድ
የአደረጉት ጥረት ቤቱን ለመናድ፡፡
ስዊዝ ለአባ ጳውሎስ ከገበረላቸው
ሺህ ነፍስ ቢጠፋ ምን ጉዳይ አላቸው፡፡
የሰኔ ጾምና የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ፡
ታስቦበትና ታቅዶ በሚያስመስለው መልኩ በየወቅቱ የጾም መጀመሪያ የጭቅጭቅና የክስ አጀንዳ የክስ አጀንዳ ቀርጣ እኩል ከጾሙ ጋር የሚያሲዙን መነኩሴ ዘንድሮም እንደተለመደው በሰኔ ጾም አስጀመሩን፡፡ የአሁኑ ግን የሚያሳዝነው የሰኔ ጾምን ለቄስ ብለው በጾሙ ያልተሳተፉ የበርን ክርስቲያኖች የዓለምን ዋንጫ አጣጥመው ለማየት አለመታደላቸው ነው፡፡ በርን ውስጥ አርዕስተ ዜናው፡
የሰኔ ጾምና የዓለም ዋንጫ
የበርን ምዕመናን እና የካህናቱ ፍጥጫ ነበረ፡፡
ስደት ማህበራዊ ኑሮና ማህበራዊ ትስስት ነውና በምዕመናኑ ላይ የተጀመረው ጡጫ በርትቶ ወሬው የዓለም ዋንጫ ሳይሆን የበርን ፍጥጫ ሆኖ ከረመ፡፡
ፍረዱን መናፍቅ ተባልን፡
በተደጋጋሚ በጉባኤው እንደተለመደው ስለ ካህን ክብር ተነግሮን ማንኛውም ጾም በካህን በኩል ማለፍ እንዳለበት ተገለጸልን፡፡ ይህም የተለያዩ ጥያቄዎች ስላስነሳ በአዋጅና ከማህበር ጾም ሌላ የፈቃድ ጾም እንዳለ ምዕመናን ገለጹ፡፡ ቄሱ ግን የግል ጾም የለም አይደረግም አሉ፡፡ በነገሩ ግራ የተጋባች እህት ተነስታ ‹‹ በአንድ ወቅት እስር ቤት ሆነን ሶስት ቀን ጾምን ፀልየን ተፈታን ስለዚህ እግዚአብሔር ጾማችንን ተቀብሏል›› አለች ፡፡ በመሀከል አንዱም‹‹ያዳነሽ ምግብ ማቆምሽ ሳይሆን እምነትሽ ነው…›› በማለት ማብራራት ጀመረ፡፡ በመቀጠልም ‹‹በገጠር ዝናብ ጠፍቶ የአካባቢው ሽማግሌዎች እግዚአብሔርን በፀሎት ለመለመን ሲሰበሰቡ አንዱ ከመሀከላቸው ሻንጥላ ይዞ ሄደ ይህ ሰው ከቤቱ ሲወጣ እግዚአብሔርን አምኖ ስለወጣ…›› በማለት መዳን በዕምነት ብቻ እንደሆነ ቤቱን ላመሳመን ተጣጣረ፡፡ በዚህ ኦርቶዶክሳዊ ባልሆነ የተዛባ ትምህርት ምዕመናኑ ሲጨቃጨቁ ዲያቆኑም ሆኑ ቄሱ ይህን ከባድ ስህተት ለማረም አልሞከሩም፡፡ በዲያቆኑ ባልሆነ የተዛባ ትምህርት ምዕመናን ተመስተህ ተናገር ብለው ቢያፋጥጡት ይብስ ያንኑ ስህተት የሚያጠናክር ‹‹አስራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴት ጨርቁን ብነካ አድናለሁ ብላ ስላመነች ድናለች›› ስለዚህ ልጁ ትክክል ነው ብሎ አጠናከረው፡፡ ውድ ምዕመናን ዲያቆኑም ሆነ ቄሱ ይህን አደገኛ ስህተት አጥተውት አይደለም፡፡ ነገር ግን ማብራሪያውን የሰጠው ሰው የተክልዬን ቤት ለመበተን በሌላ ጎራ ያዘጋጁት ሰው ስለነበር ሊያስቀይሙት ስላልፈለጉ ብቻ ነው፡፡ በዚያ ወቅት ይህ የተሳሳተ ትምህርት ይዘው ለሚሄዱ ምዕመናን አልተጨነቁም፡፡
በበጎ ስራና በጾም በምፅዋት ያልተደገፈ ዕምነት
ከንቱ ነው ይለናል የተዋህዶ ትምህርት
ዲያቆኑ ባለበት የኮሌጅ ምሩቅ
ካህኑ ባለበት የኦርቶዶክስ ሊቅ
መዳን በዕምነት ብቻ ተብሎ ሲዘራ
የቄሱ ዝምታ የዲያቆኑ መልስ ምነው አያስፈራ
ፍረዱን ይህን በተከራከርን በተደጋጋሚ በሚሰጠው ትምህርቶች ጥያቄ በጠየቅን እንደ መናፍቅ ወንጌል ወንጌል የሚሉ በማለት ስም ተለጠፈልን፡፡ ለእውነተኛዋ የኦርቶዶክስ ትምህርት መሟገት መናፍቅ ያስብላልን ይባስ ብሎ ቄሱ እኔ ገድል እንጂ ወንጌል አላስተምርም እስከ ማለት ደረሱ፡፡ በእውነት እኛ የአባታችንን ገድል እንጠላለን ወንጌልና ገድልስ ይለያያሉን ወንጌልስ የእኛ አይደለምን ለመናፍቅስ ማን ሰጣቸው ፍርዱን ለአንባቢ…
የሰኔ 13 ቀን 2010 ውርደት
13 ቁጥር በፈረንጆች የክፉ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህም በእኛ ላይ ተረጋገጠ፡፡ በዕለቱ በምንጠቀምበት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ላሉ ስዊዞች ሃይማኖታችንን፣ ሀገራችንን እና ባህላችንን የምናስተዋውቅበት ፕሮግራም ተዘጋጀቶ በድምቀት ተካሄደ፡፡ በጸሎት፣ በያሬዳዊ ዜማ፣ በወረብ፣ እንዲሁም የሃይማኖታችንን ቅዱሳን ቦታዎች በሚያሳይ የግማሽ ሰዓት ፊልም የተዝናኑት እንግዶቻችን በአዘጋጀነው ምሳ ተደስተው አመስግነው ገና ወጥተው አላለቁም፡፡ ከኋላ አካባቢ ጭቅጭቅ ተጀመረ፡፡ ቀስ በቀስ ስድብ፣ ሃይለ ቃልና መጯጯህ በዛ አይ ውርደት ምነው እንግዶቻችን እስኪርቁ እንኳቢጠበቅ፣ በሌለና ባልተያዘ ፕሮግራም ከጁን 19 ቀን የያዝኩትን የኮሚቴ ስብሰባ ሰረዙብኝ በማለት ቄሱ ላዘጋጁት ሰው ነግረው ክብሪቱን ለኮሱት፡፡ በጾሎት በምስጋናና በዝማሬ የዋልንበትን ቦታ የጦርነት ቀጠና አደረጉት፡፡ ጊዜአችንን ሰውተን፣ መዝሙር ወረብ ተለማምደን፣ እህቶቻችን በገዛ ገንዘባቸው ምግብ አዘጋጅተው ሃይማኖታችንን እና ሀገራችንን ባስተዋወቅንበት ቦታ ይህን ግጭትና ረብሻ አንድ ቄስ ሲያስጀምርና ሲያስፈጽም ይገባ ነበርን መልሱን ለአንባቢ ትተናል፡፡
ከውርደት መልስ
በነገሩ ያዘንን ጠቅላላ ስብሰባ ተደርጎ በችግራችን ለመወያየት አሰብን፡፡ ለዚህም አስራ ዘጠኝ ሰዎች በፊርማ ሌሎች በቃል የተስማሙበትን ደብዳቤ ለኮሚቴው ቀረበ፡፡ በነሐሴ ሰባት ቀን ጠቅላላ ስብሰባ ተጠራ፡፡ በመሀከል ከስዎዝ አስተባባሪ ኮሚቴ ተብዬው የበርንን ህዝብ ስብሰባ መጥራቱ ተሰማ፡፡ በግልም በኮሚቴም የበርን ችግር ለመፍታት የራሳችንን ፕሮግራም ስለያዝን እንዲታገሱ ተነገራቸው፡፡ የእነርሱ ጣልቃ ገብነት ሁላችንንም ሊበታትነን ስለሚችል የራሳችንን ችግር በራሳችን እንፍታ ብለን ለመንን፡፡ የሚያዳምጠን አጣን፡፡
ታላቁ ስህተት
ለቤተ ክርሲቲያን ቅን የሆኑ ሰዎችን ከነቤተሰቦቻቸው ለማጥፋት በመነኩሴው፣ በካህኑና በዲያቆኑ የተቀነባበረው ሴራ በስዊዝ አስተባባሪ ኮሚቴው አጋዥነት፣ ከየሰበካው በመጡ ሰዎች ተካሄደ፡፡ የበርን ሰበካ ምዕመናን አብዛኛው በስብሰባው ባይገኝም በጥቂት የመነኩሴ ድብቅ ዓላማ አስፈፃሚዎች፣ በማያውቁት ነገር ተታለውና ተወናብደው በሄዱ ጥቂት አባሎቻችን፣ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኗ ፈፅመው የማይታወቁ ሰዎች የተካሄደው ስብሰባ የመጀመሪያ ስራው እዚህ ላይ ልብ በሉ በምዕመናንና በበርኑ ቄስ በኩል ስለተፈጠረው ችግር መወያየት መፍትሄ መፈለግ ሳይሆን የበርን መተዳደሪያ ደንብን ውድቅ ማድረግ እና ተመራጩን ኮሚቴ የሚተካ በስዊዝ ኮሚቴ ሞግዚትነት የሚያገለግል ሌላ ኮሚቴ መሾም ነበር፡፡ ልክ እንደ አፍሪካ መፈንቅለ መንግስት አብዛኛው አባላት ባልተገኘበት ይህን ማድረግ ይቻላልን?
ደንባችንን ለመለወጥ ከአባቱ ሦስት አራተኛው መስማማት እንዳለበት በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የኮሚቴው ምርጫ ለማድረግም ያለው ኮሚቴ የስራ ዘመን ሪፖርቱን እያዘጋጀ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ይኽ ሁሉ ግርግር ለምን አስፈለገ በተለያዩ ሰበካዎች መነኩሴው በግልፅ እንንገራችሁ… አይቻልም!!! አንቀበለውም!!! አባ ድብቁን ተልኮ እንደ ደበቁት ይኑሪ፡፡ በግልፅ ቪዛ አግኝተው የመጡት በስደትም ሆነ በተለያዩ ምክንያት በስዊዝ ለሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርሲቲያኖች ወንጌል ማስተማር ነው፡፡ በቃ አበቃ ሌላ ስራ የለዎትም፡፡ እንዴት እንደምንተዳደር ለእኛ ይተዉልን፡፡
በህጋቹ የምትከተሉት ኢትዮጵያ ያለውን ሲኖዶስ ነው፡፡ ከሌላ የመጣ ካህን፣ ሰባኪና መዘምራንም አትቀበሉም ፡፡ ስለዚህ ወገንተኛ ልትባሉ ስለማትችሉ የፓትያርኩን ስም የመጥራት የህግ ግዴታ አለባቸው ፡፡ የፓትርያርኩን ስም አንጠራም መንፈሳዊ እንጂ ሌላ መመሪያ አንቀበልም እያላችሁ የምታምታቱትና ግልፅ እንድታደርጉ እንጠይቃችኋለን፡፡
ስለዚህም ሀገራችንን ፣ ወገኖቻችንን ፣ቤተ ሰቦቻችንን ጥለን ሳንወድ በግድ በምንኖርባት ሀገር፤ የሰው ልጅ መብትና ነፃነት በተከበረባት በሰዊዘርላንድ የእምነት ነፃነት የሚጋፉ ለአምላክ ሳይሆን ለሰው አንገት የሚያስደፋ በሶስቱ ትናንሽ ንጉሶች የፀደቀውን ህግ መቼም ቢሆን እንደማንቀበለው እንገልፅላችኋለን፡፡ ይህንን ከሚከተሉት ጋር ህብረት አይኖረንም እንላለን ፡፡
ለቅዱስ ገብርኤል ንግስ ሦስት ንጉስ፡
በትላልቅ በዓላት በሀገራችን ኢትዮጵያ በሾም መሷሷም የተለመደ ቢሆንም የእኛ መነኩሴና ካህናት በስህተት ኢትዮጵያ ያሉ መስሏቸው አልተቀበሉም እንጂ ንግስናቸውን አወጁ፣ በወረቀት አሰራጩ፡፡
በአንድ ወቅት የበርኑ ቄስ በጉባኤ ላይ ልብና ኩላሊትን የሚመረመር አንድ እግዚአብሔር ነው የሚለውን አምላካዊ ቃል ለራሳቸው በመውሰድ ‹‹ እያንዳንድሽ አውቅሻለሁ ኦፕራሲዮን አድርጌ መርምሬሻለሁ›› በማለት በአደባባይ የዘለፉንን በቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል ላይ በሎዛን የተበተነው ወረቀት አስታወሰን፡፡ በውስጡ ያዘለው አንባገነናዊና ጫና ‹‹ውስጣችሁን መርምረናል ምን ታመጣላችሁ›› ከሚለው የካህናቱ ትዕቢት የመነጨ ይመስላል፡፡
ለመሆኑ በአዲስ ህጋችሁ ላይ ማንም ካህን ወደዚህ አገር ሲመጣ ማወቅና መመርመር እንዳለባችሁ ገልፃችኋል፡፡ ይህ ህግ ለእናንተም መስራት አለበት ብለን ለምዕመናን በመጀመሪያ ራሳችሁን እንድታስመረምሩ እንጠይቃችኋለን፡፡ እንቢ ካላችሁ እናስገድዳችኋለን፡፡ ሌላው ደግሞ ህግን በአደባባይ እያፈረሳችሁ ስለሌላ ህግ ለማውራት ብቃት የላችሁም፡፡
በህጋቹ የምትከተሉት ኢትዮጵያ ያለውን ሲኖዶስ ነው፡፡ ከሌላ የመጣ ካህን፣ ሰባኪና መዘምራንም አትቀበሉም ፡፡ ስለዚህ ወገንተኛ ልትባሉ ስለማትችሉ የፓትያርኩን ስም የመጥራት የህግ ግዴታ አለባቸው ፡፡ የፓትርያርኩን ስም አንጠራም መንፈሳዊ እንጂ ሌላ መመሪያ አንቀበልም እያላችሁ የምታምታቱትና ግልፅ እንድታደርጉ እንጠይቃችኋለን፡፡
ስለዚህም ሀገራችንን ፣ ወገኖቻችንን ፣ቤተ ሰቦቻችንን ጥለን ሳንወድ በግድ በምንኖርባት ሀገር፤ የሰው ልጅ መብትና ነፃነት በተከበረባት በሰዊዘርላንድ የእምነት ነፃነት የሚጋፉ ለአምላክ ሳይሆን ለሰው አንገት የሚያስደፋ በሶስቱ ትናንሽ ንጉሶች የፀደቀውን ህግ መቼም ቢሆን እንደማንቀበለው እንገልፅላችኋለን፡፡ ይህንን ከሚከተሉት ጋር ህብረት አይኖረንም እንላለን ፡፡
ነሐሴ 7 ቀን 2010
በዕለቱ በስብሰባችን አንድም ካህን አንድም ዲያቆን አልተገኘም ፡፡ ምን አለ ለፍርድ እንዲመቻቻው ሁለቱንም ወገን ቢያዳምጡ? እዚህ ላይ ሳንጠቀስ የማናልፈው ፍቃድን ሳንጠይቅስሟን መፃፍ አላስፈላጊ ሆነ እንጂ በሁለቱም ወገን ስብሰባ ተካፍላ እውነትን ለማወቅ ለጣረችው እህት የቅዱስ እግዚሐብሔር ምስጋና ይድረሳት እንላለን ፡፡ ካህናት ያላደረጉትን አድርጋለችና ፡፡
ካህናት ዲያቆን ሆነው ወገንተኛ
ከነ ልጆቻችን ቢጨክኑ በእኛ ፤
አንድ ሴት ተገኝች እውነትን ፍለጋ
ደስታ ሰላም ጤና ይሁንላት ዋጋ፡፡
መነኩሴው ሶስት ፓለቲከኞች በበርን ቤተ ክርስቲያኑን ሊበትኑ ነበር፡፡ አስወገድናቸው እያሉ የዋሹበት አስተባባሪው ኮሚቴ የተታለለበትና የየካንቶኑ ሰበካ ጉባኤ አባላት የተወናበዱበት ስለነበር ስለተሰራው ስህተት እንድንመረምር የተገደድንበት ቀን ነበር፡፡ በወንጌል እየሱስ ክርስቶስ ዘጠና ዘጠኙን በጎች ጥሎ አንዱን ፍለጋ እንደሄደ የሚያስተምሩን አባት ሶስት ሰዎች ነበሩ አስወገድናቸው ሲሉ መስማት እርሳቸው ስለየትኛው ነፍስ እንደሚጨነቁ እንድንመረምር አስገድዶናል ፡፡ የስብሰባው ተካፋዮች በካሰህናት ምክንያት በየካንቶኑና በየቤቱ አኩርፈው ከቤተ ክርስቲያን እንደራቁት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ቤት ላለመለየት ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ የተገደዱ፤ በመንፈስ አንድ የሆኑ ሰዎች ስለነበሩ ርጋታው መደማመጡ እና መንፈሳዊነቱ በግልፅ የታየ ነበር፡፡ በዕለቱ ስብሰባ ከተገኙት የጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ተወካይ በሁለቱም ስብሰባ ተገኝተው እንዳረጋገጡት ልጆችን ሳይጨምር በአዋቂ የሁለቱም ቁጥር እኩል እንደነበር መስክረዋል ፡፡ ስለዚህም ጥቂት ፖለቲከኞች በማለት የሲዊዝ ሰበካዎች አስተባባሪ ኮሚቴውን ፤የስዊዝን ሰበካ ጉባኤዎች አባላትና ምዕመናንን በማጭበርበር የበርን ቤተ ክርስቲያን እንድትከፍል ያደረጉ ካህናት እና ጥቂት ምዕመናን መሆናቸውን ለሲዊዝ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ሁሉ እናስውቃለን ፡፡
እኛስ አንቀርም በሰው አኩርፈን
ተክልዬ ቤት ማነው የሚለየን ፡፡
በተክልዬ ቤት ውስጥ ተወልደው ያደጉ
ለመዝሙስ ምስጋና ሁሌም የሚጓጉ፡፡
አሉን ህፃናቶች የእግዚአብሔር ልጆች
የኦርቶዶክስ ዕምነት የኛ ወራሾች ፡፡
የአባ—– የአባ—– እያልን ስንካሰስ
መፍትሔ ለሌለው አንዱ አንዱን ሲወቅሰ
ልጆቹ ያድጋሉ ቆመው አይጠብቁ
መሠረት ሳንጥል እግዚርን ሳያውቁ፡፡
ነሐሴ 13 ቀን 2010 ላይጠገን ተሰበረ
በጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን አደራዳሪዎች ከሁለቱም ሦስት ሦስት ሰው ተወክሎ እንዲነጋገር ተደረገ፡፡ በስምምነት መሠረት ሦስት ሰዎች ላክን ፡፡ ካሁኑ ዲያቆኑ ሕዝቡ ከእኛ ጋር ነው እነርሱን አባራችሁ ቦታውን ለእኛ ስጡን የሚሉት ከተወሰነላቸው በላይ ቄሱንና ዲያቆኑን ጨምረው አምስት ሆነው ተገኙ፡፡
በዕለቱ የነበረውን ውይይት ማውራት የተወካዮች ኃላፊነት ሲሆን የሲዊዝ ምዕመናን ማወቅ ያለበት በተቀነባበረው ተንኮል ሲተጉበት የነበረው የመከፋፈል ሴራ ተሳክቶላቸው ቄሱና ዲያቆኑን ባስደሰተ መልኩ የበርን ቤተ ክርስቲያን በነሐሴ 13 ቀን 2010 ለሁለት መከፈሏ በአደራዳሪዎች ተረጋገጠ፡፡
ይህ አሳዛኝ ክስተት በምዕመናኑ ዘንድ የማይረሳ ጠባሳ ሆኖ የኖራል፡፡
በዚህ ዕለት እስከሚቀጥለው ጥር ወር ድረስ ቤተ ክርስቲያኗንና ተራ በተራ እንድንጠቀምበት የሚያስችል የ 2010 ፕሮግራም ለሁለቱም ወገን ወጣ፡፡
እንባችን ፈሰሰ እኛስ አለቀስን
ተታለው ለሄዱት ለቄስና ካህን፡፡
ማጠቃለያ
የሆነው ይኸ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ጦርነት ዋና አላማ አሁን በተግባር አባ ተልኳቸውን ለመፈፀምና ለማስፈፀም ያደረጉት ተጋድሎ ነው፡፡ ተሳክቶ ይህን?
በተረፈ የተክልዬ ፕሮግራም / ጉባኤው፣ቅዳሴው፣ዝማሬውና የህፃናት ምስጋና / ይቀጥላል፡፡የተክልዬን ዓመታት በዓል በ ነሐሴ 29 ለማክበር በብዙ ውጣ ውረድና ለእግዚአብሔር በሚያስደስት ነገሮች ውስጥ ስለነበርን ቅዳሴው ይለፈን ብለናል፡፡ ነገር ግን በዕለቱ በዚህ አገር ሰዓት አቆጣጠር ከ12 ሰዓት ጀምሮ በጸሎት ፣በመዝሙር፣እና በህጻናት ምስጋና በጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን እናስባቸዋለን ፡፡ በራችን ለማንም ክፍት ነው፡፡ በአዲስ ካህን በመስከረም 12 በኦሰተርሙንዲገን /ostermundigen/ ቅዳሴ እናደርጋለን ፡፡ ግብዣችን ለመላው ስዊዝ ምዕመናን ይሆናል፡፡
ከዚህ በታች ያለችውን ለዲያቆኑ ፣ለቄሱ፣ ለመነኩሴው የቅዳሴ ትርጉሙ ላልገባቸው ሁሉ በማስተላለፍ መልዕክቴን አበቃለሁ፡፡ በርን ውስጥ በተካሄደው ሁለት የፀብ የጭቅጭቅ የሀሰት የመከፋፈል ስብሰባዎች ማግስት የቅዳሴ ፣ሥጋወ ደሙ መቀበል ማቀበል….እንዴት ያዩታል?
አንብቦ ለመረዳ እውነትን ለመመርመር እግዚአብሔር ይርዳቹሁ፡፡ መፅሐፍ ምዕ.6 ቁጥር 16-19 እግዚአብሔር የሚጣላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፡፡ ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትፀየፋዋለች፡፡
ትዕቢተኛ ዓይን ፣ ሀሰተኛ ምላስ፣ ንጹህ ደም የምታፈስ እጅ፣ ክፉ ሀሰትን የሚያበቅል ልብ ፣ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር ፣ በሀሰት የሚናገር ሀሰተኛ ምስክር ፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚዘራ፡፡
አማን አማን ብለው አባ ቢያወድሱ
ቂም በቀል ታቅፈው ቢቀድሱ ፤
በወንጌል ተፅፏል በካህን ምክንያት
በሯ ትዘጋለች መንግስተ ሰማያት፡፡
ይህ ነው ውጤቱ ጎዶሎ ዕምነት
በንስሀ እናልቅስ ለዚያች ለገነት፡፡
ወሰብሐት ለእግዚአብሔር!!!
ከበርን ምዕመን