ወያኔ ግንቦት 20 (May 28) ሰልፍ ለማዘጋጅት እይተሯሯጠ ይገኛል

ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር ወያኔ/ኢህአዴግ በሕዝብ ፍቅር መጥገቡን በተለያየ መንገድ አስመስሎ በመዋሸት በሃገር ውስጥ ያሉትን ሞኞች፤ በውጭ ያሉትን በርቀታቸው ከለላነት፤ ዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ በማያውቀውና በሃገር ውስጥ ያሉትም ኤምባሲዎች እያወቁ በሚሸፍጡት እውነታ በማለባበስ ላይ ከተሰማራ ከረመ፡፡

የዘንድሮው የአባይ መገደብ በሚያስደንቅ ፍጥነት ተጠና ተብሎ ሙያቸው ባልሆነ ምላሰኞች ጥናቱ ተግባራዊ እንዲሆን በመለስና በአጫፋሪዎቻቸው ጉሮ ወሸባዬ ሲዘፈንለት ከርሞ ለመደምደሚያው ደሞ በወያኔው አሽቃባጭ እቁባይ በሚመራውና በአገልጋዩ ሠራዊት ፍቅሬ እስክስታ የሚመታበት የጥበብ ሰዎች ታግተው በሰላም አውቶቡስ ወደ አባይ ሂደው ጮማ ቆርጠው ጠጅ ተንቆርቁሮላቸው የበሉት ሥጋና የጠጡት ጠጅ አፈናቸው መሰል እስካሁን ምንም የለም፡፡

አሁን ደሞ ግንቦት 20ን አስመልክቶ ሕዝቡ ከኛ ጋር እንደሆነ ማሳየት አለብንና በዕለቱ አንድ ሚሊዮን ተሰላፊ በመስቀል አደባባይ በማውጣት እንደ ሚያዝያው የቅንጅት ሰልፍ ማሳየት አለብን፣ የፋብሪካ ሰራተኞች፤ የቀበሌ ታዛዦቻችን፤ ነጋዴዎች እንደተለመደው ካልወጡ የሚከተለውን የመረረ ውሳኔ በመንገር፤ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ምሳ እራትና የኪስ ገንዘብ በመስጠት፤ተማሪዎች ከየትምህርት ቤቱ ሊደረግላቸው የሚችለውን ድጋፍና ጥቅም በማስረዳት፤ የየማህበራትን አባላት በችግራቸው በመግባትና በማግባባት፤ የሚፈለገውን ቁጥር ማግኘት ያስፈልጋል በሚል ትዕዛዝ ሁሉም ወረዳ አስተናባሪ ተመድቦለት በመሯሯጥ ላይ ነው፡፡

ለሙዚቃ ተውኔት ሰአሊያን ማሕበር ሠራዊት ፍቅሬና እቁባይ ከየሙያ ማሕበራቱ አባላት አመራሮች ጋር ሲመደቡ፤ ለንግዱ ሕብረተሰብ ደግሞ በቅርቡ ተውጣጥቶ የተቋቋመውና እነ አብነት ገብረመስቀል ሼህ አላሙዲን ወክለው የተገኙበት ኮሚቴ ተመድቧል፡፡ እነ አቶ የሱስወርቅ ዛፉና ሌሎችም ለዚህ ተግባራዊነት ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው እየተሯሯጡ ነው፡፡

እንግዲህ ትላንት በየጓዳው ከአባይ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥላጣን ዘመን ይገደብ ያለ ሁሉ ቃሉን ውጦ ለግንቦት 20 ሰልፍ ሊወጣ ነው፡፡

ለዚህ የሚሆን ደሞ ለማግባቢያና ለአንዳንድ ጉዳይ ማስፈጸሚያ ወፈር ያለ ገንዘብ ወጥቷል እነሰራዊት ፍቅሬም ይህን የሕዝብ ደም የሆነውን ገንዘብ ሊበሉ ዝግጅታቸውን ፈጽመዋል፡፡ ግንቦት 20 ደርሶ አይተነው ጊዜ፡፡