የአባይ ግድብና የኢትዮጵያ ህዝብ – “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ”
ከደምስ በለጠ
በውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ልማት ላይ ለመሳተፍ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆነም በ ወያኔ ስርአት የተፈተነ ተለምዶው የተነሳ ተቃውሞውን ሲያሰማ ቆይቶአል:: ወያኔዎቹ እንደሚሉት ዳያስፖራው በጋጠወጥነት አደባባይ እየወጣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በጎደለው መንገድ የሚቃወምም አይደለም :: ሰሞነኛው የአብይ ግድብ ኡኡታ በተለይ በአገዛዙ በኩል እየታየ ያለው የሚዲያ ያዙኝ ልቀቁኝ እጅግ አስገራሚ ሆኖአል:: ህዝቡ እጅ እጅ እስከሚለው ድረስ ነው ሚዲያዎቹ እያሰላቹት ያሉት:: ዳያስፖራው የሚለው ፍትህና ርትእ ይቅደም ዜጎች በመጀመሪያ መብታቸው ይከበር: መድልዖ ይቁም:ከቁሳዊ ልማት በፊት ሁሉንም ያማከለ መሰረታዊ ነጻነት ይቅደም ነው:: በሃገሪቱ ወስጥ የዜጎች እኩልነት እስካልተረጋገጠ ድረስ የልማት ስራዎች የሚባሉት ሁሉ ለሙስናና ለንቅዘት የተጋለጡ ናቸው:: ዳያስፖራው በሚኖርባቸው አገራት ከነዚህ ሁኔታዎች የፀዳ አገልግሎት ያገኛል አገሩም ላይ እንዲሁ እንዲሆን ይመኛል:: ይህን መጠየቁ ደግሞ ፀረ ልማት ሊያሰኘው አይችልም።
ዛሬ በሃገራችን ለአባይ ግድብ መዋጮ ርብርቦሽ እየተደረገ ነው:: ህዝባዊው ተሳትፎ ሁለት አይነት ባህርያት ይስተውለውበታል:: አንደኛው ህዝቡ በፍላጎቱ የሚያደርገው መዋጮ ሲሆን ይህም አገራዊ ስሜቱ ላይ ተመርኩዞ ያለ አንዳች ተፅእኖ የሚያደርገው ነው:: ሁለተኛው ደግሞ ያቶ መለሰን ሰሞነኛ ቃለ-መጠይቅ አባባል ልዋስና “ቁርስ የማይበላው ህብረተሰብ” በየመስሪያ ቤቱ የደሞዙን አንድ አስራሁለተኛ በወር የሚለቅበት ሲሆን :ይህም ለቤት ኪራይ ለመብራት ለውሃ እና ለትራንስፖርት ወጪ እንዲሁም ሌሎች ጥቃቅን ወጪዎች ተደማምረውበት የዛሬው ኑሮ ወደነት ተጨምሮ እሱም ሆነ ቤተሰቡ ምሳቸው ወይ ራታቸው ተቀነሰ ማለት ይሆናል:: በኔ አስተያየት ልጆቹንና ራሱን አስርቦ ኑሮውን ደፋፍቶ አንድ አስራሁለተኛ ደሞዙን የሚለቅበት ምክንያት ምንድነው ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ይሆናል:: በየመስሪያ ቤቶቹ የተሰገሰጉት የወያነ አባላት ፍጥጫና ግልምጫ አንዱ ምክንያት ሲሆን ቤቴን ደፍቼ አላዋጣም ቢል የመንግስትን ትራንስፎርማሽን ፖሊሲ ተቅውመሃል ተብሎ ጠቅላላ ስራውንም ሊያጣ ይችላል:: ሌላው በየገጠር ከተማው ስራ እየቆመ የሚደረገው ሰልፍ አስደንቆኛል:: ከአንድ አስራ ሁለተኛ ደመወዝ ለቀቃ ቀጥሎ በከፍተኛ ደረጃ የአባይ ግድብ ድጋፍ ሰልፍ በየትናንሿ ከተማ ወስጥ እየተደረገ ነው:: በፍላጎቱም ሆነ ያለፍላጎቱ እያዋጣ ያለው ህብረተሰብ ተማሪው ከስራ ቀርቶ ሰራተኛው ስራውን ትቶ ነጋዴው ሱቁን ዘግቶ ሰልፍ ውጣ ይባላል :: ይህ ለምን አስፈለገ ብየ ስጠይቅ ያገኘሁት መልስ የአምባ-ገነን መሪዎች ምስ መሆኑን ነው በሹመኞቻቸው አማካይነት ህዝቡ ብቁጥጥራቸው ስር መሆኑን ይገመግሙበታል:: በነገራችን ላይ አቶ መለስ ከሁለት ቀናት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለመለለስ ላይ የታዘብኩተን ላካፍላችሁ:: አቶ መለስ በተደላደለ ቢጫማ ሶፋ ላይ ተደላድለው ተቀምጠዋል:: ጋዜጠኛው ወይም ጠያቂው በሌላ የተለቭዥን ዝግጅቶች ላይ አወያይ እየተባለ ሲቀርብ አይቸዋለሁ ከአቶ መለስ ትይዩ አንዲት ነጠላ ወንበር ላይ እግሮቹን ከታች በኩል አጠላልፎ ከወንበሩ ስር ቀብሮአቸዋል:: ቃለ መጠይቁን ሲያቀርብ እስከአጋማሹ ድረስ እጆቹ ይንቀጠቀጡ ነበር:: ይህ ፍርሐት በውስጡ የተፈጠረበት ምክንያት ምን ይሆን? ብየ ራሴን ጠይቄአለሁ::የተረዳሁት ነገር ቢኖር ከተሌቭዥን ድርጅቱ ለቃለመጠይቅ ሲላክም ሆነ ቤተመንግስት ሲገባ የተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች ሳይረብሹት አልቀሩም:: የህም አምባ-ገነን መሪዎች በሚፈጥሩትና በሚታወቀው ጨካኝ ባህሪያቸው የተነሳ ሌሎች ሰዎችን የስነ-ልቡና ሽብር ወስጥ ይከቱአቸዋል:: በጠያቂውም ላይ የታየው መንቀጥቀጥ ከዚህ የተነሳ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል::
ሌላው ጠያቂው ያነሳቸው በተለይ ህዝቡና አገዛዙ መካከል ተፈጠረ የሚላቸውን መቀራረቦች በተለይ ህዝቡ እያሳየ ያለውን መነሳሳት አስመልክቶ ላቀረበው ጥያቄ አቶ መለስ የሰጡአቸው መልሶች ሁለት ባህርያት ተስተውለውባቸዋል:: አንደኛው ሀዝቡን እያደረገ ላለው ርብርቦሽ ምስጋና መስጠት ተገቢ የነበረ ሲሆን ይህም ህዝብን አክብሮ ራሰን ማስከበር ሲቻል ሳያደርጉት ሁለትና ሶስት ጊዘ እድሉ አልፎአቸዋል:: ባለማወቅ የተደረገ ነው እንዳይባል መለስ የዝንብ:ይቅርታ የንብ ልጃገርድ ከሩቅ የሚያውቁ መሆናቸውን የማያውቅ የለም:: የሚገርመው ባህሪያቸው ህዝብ ላይ ተቀምጠው ሁለት ነገሮች ካፋቸው ማውጣት ይቸግሯቸዋል:: ይኅውም ህዝብ ላደረገው ተሳትፎና ቀና ቀረቤታ ምስጋና ማቅረብ የምጥ ያህል ታስቸግራቸዋል የህም ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በሗልም ታይቶአል ዛሬም ላይ ተደገመ:: ሌላው ከአቶ መለስ አፍ የማትሰሙት ቃል የኢትዮጵያ አንድነት የሚለውን ነው: የአገሪቱ አንድነት ጥያቄ ሲነሳ ሁልጊዜ ሉአላዊነት በሚል ማደናገሪያ ቃል አውሸልሽለው ያልፉታል::የኢትዮጵያ አንድነት ግን በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በዛሬው ቀንና ሰአት እየተገለጸ ነው:: ኢትዮጵያዊው ከዳር እስከዳር የተነሳሳው እየተረባረበም ያለው ናፍቆት የነበረውን አንድነቱን የሚገልፅበት ብቸኛ መንገድ በማግኘቱ ነው:: አማራ ትግሬ ጉራጌ ኦሮሞ ከንባታ ሃድያ ጋምቤላ ሶማሌ ሳይል ባንድነት መነሳሳቱ::
እንዲያውም እንደ አቶ መለስ የቃለ መጠይቅ መልስ ይህ ህዝባዊ መነሳሳት ህዝቡ በፍላጎቱ ያመጣው ሳይሆን እሳቸውና መንግስታቸው ባደረጉት ቆራጥ አመራር የተነሳ የተገኘ ውጤት ነው::
ሌላው ቃለ መጠይቁ ላይ የተነሳውና በሌሎችም ሁነታዎች እየተገለጸ የሚገኘው ኢትዮጵያ ማንንም የማትጎዳ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የአባይ ፍጆታዋን ለመጠቀም የምትፈልግ አገር ናት የሚለው ሲሆን መሰረተ ሃሳቡ መልካም ሆኖ ሳለ የተወስኑ የግብፅ ላኡካን አዲስ አበባ መጥተው ራትና ምሳ እየተጋበዙ ስለገለፈጡ ለግብፅም ሆነ ለለሎች ሃገራት የውሃ ተመራማሪዎች ግንባታችንን መጥተው እንዲመረምሩ እንፈቅዳለን ማለት ምንድነው? የወያኔ መንግስት በ1993 ከግፅብጽ ጋር አድርጎት የነበረው ስምምነት አንቀፅ 4 ላይ ኢትዮጵያ ግዛቷ ውስጥ በሚገኙ በአባይና በአባይ ተፋሰስ ወንዞቿ ላይ የምትገነባውን ማንኛውንም ፕሮጀክት በግብፅ ባለሙያውች ታስመረምራለች ከሚለው ስምምነትስ በምን ይለያል:: ሳይጠይቁንስ የለሎች አገራት የውሃ ጠበብትን መጋበዝ ምን አመጣው? በዚህ የግብጾቹ ልኡካን ቡድን የዲፕሎማሲ የበላይነቱን ተቀዳጅቶ ሄዷል:: ምን ማሌቴ ነው አሁን ግብፅ የተረጋጋ መንግስት ስለሌላት ፋታ ስጡንና የተረጋጋ መንግስት ከመሰረትን በኋላ እንነጋራለን ማለት ነው:: መንግስታቸው በእግሩ ሲቆም ምን አይነት አቋም ሊይዙ እንደሚችሉ ገና መናገር አንችልም:: አብሮ ራት በተበላ ቁጥር ይህን እናረግላችኋለን ያን እንፈፅምላችኋለን እያሉ ቃል መግባትስ ምን አመጣው? ግብፅ ደግሞ የምትናቅ አገር አይደለችም ጠንካራ እኮኖሚና ጠንካራ ወታደራዊ ሃይል ያላት አገር ነች አባይ ደሞ ትንፋሿ ነው::
የለሎች አገራትስ የውሃ ተመራማሪውች ምን አገባቸው “እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል”እንዲሉ ራሱ በመረጣቸውና ደሞዛቸውን ይከፍላቸው በነበሩ ዳኞች በአልጀርሱ ስምምነት ስንት ደም የተከፈለበትን ሃገር እንድናጣ የተፈረደብን ሰዎች ሳይጠይቁን ጋብዘን ወደፊት ግብፅ ንትርክ ብታመጣ መሰክሮች ለማቅረብ ምቹ እንዲሆንላት ማዘጋጀትስ አይሆንም ወይ? ይህ የዲፕሎማሲ አልብቃት ነገ ግብጽ አሻፈረኝ ብትል ለሚነሱ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ጥቃቶች በቀላሉ አገራችንን አያጋልጣትም ወይ?
ሌላው ግድቡ ሲገነባ የምንደርስበት ይሆናል::በተለያየ ጊዜአት የልማት እቅዶች እየተባሉ የተሰጡ መመሪያዎች ህዝባችንን በየደረጃው የተለያየ ዋጋ አስከፍለውታል ለምሳሌ በፊት የማኔጅመንት ስትራቴጂክ ዕቅድ (SPM)፣ በኋላ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (BPR) ቆይቶ ደግሞ ውጤት ምዘና (BSC)፣ አሁን ደግሞ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP) እየተባለ ቁም ስቅሉን አይቷል ግማሹ ከስራ ተባሯል ሌላው ቤቱ ተበትኗል ልጆቹ የጎዳና ተዳዳሪ ሆነዋል:: በነዚህ ምክንያቶች በተለያየ ደረጃ ዋጋ ከፍሏል አሁን ደግሞ የትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የሆነው የአባይ ግድብ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተደምሮ ድሮም ከጠፋው ቁርሱ ጋር ምሳው ወይ ራቱ በአንድ አስራሁለተኛም መዋጮ ምክንያት ከጠረጴዛው ላይ ተወስዶበታል:: ይህን ስል ታዲያ ሰርቶ የሚገባውን ብቻ ነው ያን ባጋጣሚ ጉሮሮውን ዘግቶ የሚቀጥለው ምግብ መቼ እንደሚገኝ የሚያልመውን ወገኔን አይጨምርም::
በዚህ የአባይ ግድብ ዙሪያ እነአቶ መለስ የአመራር ብቃታቸው ህዝባዊ ርብርቦሹን አመጣው ብለው ሲሞካሹ እኛ ደግሞ ለንከስትላቸው የሚገባ አንድ ኅቅ አለ ይኅውም ሕዝባችን የአባይ ግድብ ስራ ርብርቦሽን የታፈነው የአንድነት ድምፁ መገለጫ እንዲሆነው አድርጎታል:: የምትፈሩት አንድነትም እንዲህ እየተገለጸ ነው: ስለዚህ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ሆኖባችኋል::
ከደምስ በለጠ