በዋሽንግተን ዲሲ፡ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ አሸንፎ ዋለ
194 ሰዎች የተገኙበት የመክፈቻና፡ የትውውቅ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ
ከትኬት ሽያጭና ከስፖንሰርሺፕ ባንድ ምሽት 27 ሺህ 300 ብር ተሰብስቧል
ንፋስ የቀላቀለ ሀይለኛ ዝናብ ሳይጠበቅ መጥቶ የተወሰኑ ትኬት የገዙ ሰዎችን ቢያስቀራቸውም፡ ንፋስና ዝናብ ሳይበግራቸው በወጡና የኢትዮጵያዊነት ፍቅር በሚያቃጥላቸው 194 ከዲሲና አካባቢው እንዲሁም ከአትላንታ፡ ሂውስተን፡ ሎስአንጀለስ፡ ኦታዋና ሲያትል የመጡ ሰዎች በተገኙበት፡ የኢትዮጵያዊያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብእ የመጀመሪያ የመክፈቻ፡ የእራት እና የትውውቅ እንዲሁም የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ገለጹ።
እንደኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር፡ ትናንት ቅዳሜ፡ ግንቦት 6፡ 2003 (እንደ ፈረንጆቹ ደግሞ ሜይ 14 ከምሽቱ 8 ሰዓት ጀምሮ) በ6000 ጂዮርጂያ በተካሄደው በዚህ የኢትዮጵያዊነት ውርስና እሴት ተንከባካቢ ድርጅት የመክፈቻ ዝግጅት ላይ፡ ወጣቶች፡ አዛውንቶች፡ ምሁራን፡ ሴቶችና አረጋዊያንም፡ የጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተው የመጪውን አመታዊ ፌስቲቫል ናሙና ከግሩም እራት ጋር የተቋደሱ ሲሆን፡ በዳምጠው ወርቁ በሚመራው ታዋቂው የቅኝት የባህል ሙዚቃ ቡድን የባህላዊ ጭፈራዎችና ሙዚቃዎችም ቀርበዋል።
ነዋሪነቱ በሲያትል የሆነው የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ሼክስፒር ፈይሳ ስለኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብእ በሰሜን አሜሪካ ምስረታ ታሪክና አላማ እንዲሁም ስለአጭርና ረጅም ግዜ እቅዶቹ ንግግር አቅርቧል። አቶ ሼክስፒር ፈይሳ፡ የኢትዮጵያዊነት ውርስ ድርጅት ዋንኛ ዓላማ ኢትዮጵያዊነትን መታደግ አንደሆነ ገልጾ፡ በአጭር ግዜ የመጪው ፌስቲቫል፡ በረጅም ግዜ ደግሞ በዋሽንግተን ዲሲ ታላቅ የኢትዮጵያውያን የባህል ማእከል መገንባት የድርጅቱ ግብ አንደሆነ ተናግሯል።
በዚሁ ዝግጅት ላይ፡ ሁለት ታላላቅ ኢትዮጵያዊን ተሳታፊውን የመሰጠና የማረከ ታሪካዊ ንግግር ቅርበዋል። ለላፉት 50 አመታት ለኢትዮጵያ ሙዚቃና ኪነጥበብ እድገት ታላቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱት፡ አንጋፋው የኪነጥበብ ሰው፡ አቶ ተስፋዬ ለማ፡ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ያለፈበትን የሀምሳ አመት ጉዞ በአጭሩ አቅርበዋል። አቶ ተስፋዬ ለማ፡ በ1960ዎቹ መጀመሪያና፡ እንደገናም ባለፈው መንግስት ግዜ የህዝብ ለህዝብን የሙዚቃ ቡድን በቡድን መሪነት ይዘው የመጡ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው። አቶ ተስፋዬ ህመምና እድሜ ሳይበግራቸው፡ በአረጋዊያን መጦሪያ እየኖሩ ያዘጋጁትንና በቅርቡ የሚታተመውን ከአጼ ምኒሊክ እስከ 1983 ዓ.ም. ያለውን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ መጽሀፍ ቅጂም ለህዝቡ አሳይተዋል።
ሁለተኛዋ ተናጋሪ ከአብዮቱ በፊት ትምህርታቸውን ቀንቀን እየተማሩ ማታ ማታ በበነርሲንግ ሙያ እየሰሩ ጨርሰው ወደሰሜን አሜሪካ የመጡትና ከደላዌር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያቸ ድግሪያቸውነ በነርሲንግ፡ የድህረ ምረቃ ድግሪያቸውን በህዝብ አስተዳደር ያገኙትና በቨርጂኒያ ክፍለግዛት ጤና ጥበቃ ሚ/ር መስሪያ ቤት ከሀያ አመት በላይ ያገለገሉትና The Unheard Voice, a collection of poems and essays፤ The Common Peoples Voice of Ethiopia፤ A Mother’s Eye View፤ Hear Me Now የተሰኙ ስራዎችን ለህትመት ያበቁት ወ/ሮ ለምለም ጸጋው ናቸው። ወ/ሮ ለምለም የኢትዮጵያን ባህላዊ የጋብቻ፡ የግብርና፡ የልጆች አስተዳደግና የኢትዮጵያዊነትን ክብርና ማእረግ የተመለከተ ሁሉንም ተሰብሳቢ ወደትዝታ የከተተ ማራኪ ንግግር አድርገዋል።
በዚሁ ዝግጅት ላይ በድርጅቱ አነስተኛ እድሜ ያለው መስራች አባልና ረዳት ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወጣት ልኡል ወንድፍራውም ኢትዮጵያዊነትን የተመለከና ታዳጊዎችና ወጣቶች ለምን መሳተፍ እንዳለባቸው የሚያስረዳ ንግግር አቅርቧል። ከሂውስተን የመጡትና በተመሳሳይ መድርክ ውስጥ የረጅም ግዜ ልምድ ያላቸው አቶ ሀይሌ ተፈራ የማህበሩን የስፖንሰርሺፕና የቢዝነስን እቅድ የተመለከተ ባህላችንን ማእከል ያደረገ እቅድ አቅርበዋል። በመጨረሻም ከህዝቡ መካከል የተወሰኑ ሰዎች አስተያየትና ጥያቄ አንስተውና ውይይት ተደርጎበት፡ በቅኝት ሙዚቃ ቡድን አባል፡ በድምጻዊ ሰጠኝ ተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ጣእመ ዜማዎች ቀርበዋል።
በእለቱ ከተገኙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብ የአባልነት ቅጽ የሞሉ ሲሆን፡ ሁሉም ለመጪው ሰኔ መጨረሻና ሀምሌ መጀመሪያ ላይ በዋሺንግተን ዲሲ ለሚደረገው ፌስቲቫል መሳካት ለመረባረብ ቃል ገብተው የዝግጅቱ ፍጻሜ ሆኗል። በዲሲ የሚገኘው ፋሲል ሬስቶራንት፡ ሀበሻ ሬስቶራንት፡ ዘላለም እንጀራ፡ የቀድሞ አየር ሀይል፡ ኢህአፓዲና ሌሎች ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች የቅዳሜው ዝግጅትና የመጪው ፌስቲቫል ስፖንሰር ሆነዋል። በእለቱ መገኘት ያልቻሉ ብዙ የድርጅቱ ደጋፊዎች ከያሉበት ስቴትና ከተማ ለእለቱ የተዘጋጀውን ባለመቶ ብር ቲኬት በመግዛት ለድርጅቱ ያላቸውን ድጋፍና አጋርነት ያሳዩ ሲሆን፡ በጠቅላላው ከ27 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡ ታውቋል።