እንዲያው የኛ ነገር – ተስፋዬ ለማ

ከተስፋዬ ለማ

በአንድ ዘመን ዝና የነበራቸው ኳስ ተጫዋቾች በተለያዩ ጊዜያት አሜሪካ መጥተው እነሱም እንደሌላው ህብረተሰብ በየስራው ተሰማርተዋል፡፡

የአዲስ አበባን ስታዲዮም ትዝታ ለመወጣት በየዓመቱ July 4 የአሜሪካንን የነፃነት በዓል በማስታከክ የጀመሩትን አመታዊ የስፖርት ዝግጅት እየተለመደ በመምጣቱ ብዙ ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባስብ በዓል ሆኖ ቆይቷ፡፡

እድሜ ለሶስተኛ የአፍሪካ ዋንጫ 40 ዓመት ሆነው፡፡ ከዚያ ወዲህ በግል ሮጦ ከማሸነፍ በቀር የህብረት ስፖርት አልዋጣ ብሏል፡፡

አንድ አዛውንት አበሻ ተለያይቶ መኖር አይችልም፤ ተቀራርቦ ቁም ነገር መስራትም አይሆንለትም ብለው የሰጡት ትዝብታዊ አስተያየት እውነት ይመስላል፡፡

አለምንም ግዴታና ተፅዕኖ በራሱ ፍቃድ ብቻ ከሃያ ሺ በላይ ህዝብ ይሰበሰባል፡፡

ምክንያቱ የእግር ኳስ ስፖርት ቢሆንም በሜዳው ላይ ቀን ቀን ኳስ፤ ጨዋታው ዙሪያውን ደግሞ ምግብ፣ የተለያዩ የእጅ ስራዎች፣ መፅሔቶች፣ ስዕሎች፣ ፎቶግራፎች፣ ጌጣ ጌጦች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የቤተክርስቲያን ማስታወቂያዎች፤ ማታ ማታ ደግሞ የተለያዩ ዘፋኞችና ሙዚቀኞች ለሳምንት በሚዘልቅ ዝግጅት ህብረተሰቡ እየተገኘ በዚህ መልክ መሰባሰብን ከተያያዘ ከ25 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡

ለዚህ ሁሉ ምክንያት የሆኑትን ስፖርተኞች ህብረተሰቡ ያመሰግናቸዋል፣ ያደንቃቸዋል፡፡ በሌላ በኩል እንደዚህ ብዙ ህዝብ መሰባሰቡ ካልቀረ ከፍተኛ ቁም ነገር ሊሰራ ወደሚችልበት ደረጃ መሸጋገር ነበረበት፡፡

በአሜሪካ የሚኖረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በኢኮኖሚ፣ በሶሻል፣ በባህልና በፖለቲካ በሚደረገው እንቅስቃሴ ምን ያህል ጠንካራና ብልህ መሆኑን ለወደፊቱም በአሜሪካ ኢኮኖሚና ባህል ሊጫወት ስለሚችለው ሚና ያለውን ራዕይና ጥረት የሀገሩ ህዝብና መንግስት በቅርቡ እንዲረዱ ወደ ህብረተሰቡ በመዝለቅ ከማስተዋል ይልቅ ስፖርቱም ሙዚቃውም ሌላውም ንግድ አበሻ ለአበሻ ሆነ፡፡

ትላንት ከኛ ኋላ ተነስተው የአፍሪካ፣ ከዚያም አልፈው የዓለም ሻምፒዮን ውድድር ውስጥ የገቡትን፣ አልፎ ተርፎም አሸናፊ ለመሆን የቻሉትን እንደ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ካሜሮን የሌሎችን የአፍሪካ ሀገሮች የእግር ኳስ ስፖርት እድገት ተመልክተን በአንፃሩ የሀገራችንን ሰናይ ሁኔታው አሳዛኝ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ቁጥራቸው አስር ሺ የማይደርስ የሌሎች ሀገር ስደተኞች በየሚኖሩበት ክፍለ ሀገር ወይም ስቴት ከፍተኛ የኢኮኖሚ የትምህርትና የባህል ተቋም ከመገንባታቸው ሌላ ድርጅታቸውም የባለ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ትርፋማ ነው፡፡

ሃያ አምስት ዓመት ያሳለፍንበት ከሃያ እድከ ሰላሳ ሺ ሆነን የምንሰባሰብበት ይህ በዓል የፈጠረው ነገር ቢኖር በየስቴቱ ለሚገኙ የአሜሪካ ሆቴሎች፣ የመጠጥና የእቃ ፋብሪካዎች ገንዘባችንን አስረክበን ለመበታተን ካልሆነ በቀር ሌላ ትርጉም አልኖረውም፡፡

ይህን ዝግጅት የሚያቀርበው ፌዴሬሽን የባለሚሊዮን ዶላር ትርፋማ መሆን ቀርቶ ለዓመታዊ በዓል ማዘጋጃ ገንዘብ የሚያገኘው ከግለሰቦች በመበደር ነው ይባላል፡፡

እንዲያው የኛ ነገር ስፖርታችን የውሸት፣ መሰባሰባችን የውሸት፣ ፖለቲካችን ውሸት ኪሳራችን ብዙ ትርፋችን ዜሮ!

(”አንድ ወቅት በአሜሪካ” ከሚል አርዕስት ከታተመው የደራሲ ተስፋዬ ለማ መጽሃፍ የተወሰደ።)