የኬንያ አዲስ ህገ-መንግሥት በፕሬዚዳንቱ ፊርማ ጸደቀ

(DW) — የኬንያው ፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪ፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ድምፅ በመስጠት ብዙኀኑ የፈቀዱትን አዲስ ሕገ-መንግሥት ፤ ዛሬ ናይሮቢ ውስጥ በተካሄደ ደማቅ ሥነ -ሥርዓት በፊርማቸው አጸደቁት። በሥነ ሥርዓቱ ላይ ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያንና በዛ ያሉ አፍሪቃውያን መሪዎች ተገኝተዋል። ርእሰ ብሔር ምዋይ ኪባኪ ፤ ስለአዲሱ ህገ-መንግሥት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ስለመሆኑ እንዲህ ነበረ በአዋጅ ያስታዋወቁት—

« እኔ ምዋይ ኪባኪ የኬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንትና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ከዛሬ ነሐሴ 21 ቀን 2002 ዓም አንስቶ አዲሱ ህገ መንግስት የፀና መሆኑን አውጄያለሁ »

በናይሮቢው ህገ-መንግሥት የማጽደቅ ሥነ-ሥርዓትም ሆነ ክብረ በዓል ላይ ከተገኙት መካከል አንዱ፣ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዖማር ሐሰን ኧል በሺር ናቸው። ኬንያ ፣ በደን ኻኽ ኔደርላንድ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች መርማሪ ፍርድ ቤት ውል ፈራሚ አገር እንደመሆኗ መጠን፤ ፕሬዚዳንት በሺርን ይዛ ማስረከብ ነበረባት ሲሉ የዜና አውታሮች አስታውሰዋል። ዖማር ሐሰን ኧል በሺር በምዕራቡ የአገራቸው ጠ/ግዛት የጦር ወንጀልል በመፈጸም ህዝብ በመጨፍጨፍ መወንጀላቸው አይዘነጋም።

አዲሱ የኬንያ ህገ-መንግሥት ፣ የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን የሚገድብና የዜጎችን መብት የሚያሰፋ ነው ተብሏል።