አምባገነኖች ከአንድ ባሕር(ይ) ይቀዳሉ

ከይነጋል በላቸው

ከጥቂት ቀናት በፊት አመፀኛው የኮትዲቩዋሩ ሎራን ባግቦ ሃያ በመቶው የሀገሪቱ ከተሞችና ክልሎች በሕጋዊው ተመራጭ ዕጅ ገብተው እርሱና ጥቂት ግብረ አበሮቹ በራሱ በባግቦ መኖሪያ ቤትና በተወሰኑ አካባቢዎች ተወስነው በነበረበት ወቅት በተወካዩ አማካይነት አንድ መልዕክት አስተላልፎ ነበር – አላሳን ዋታራ ከነደጋፊዎቹ ዕጁን በሰላም እንዲሰጥና ሀገሪቱ በልማትዋ እንድትቀጥል የሚያትት፡፡ ባግቦ አለ – ‹ ክቡር አላሳን ዋታራ፣ ለሰላም የዘረጋነውን ዕጅ ሳናጥፍ ከነሠራዊትህ በሕዝብ ለተመረጥኩት ሕጋዊው የኮትዲቮዋር ፕሬዚደንት ለሎራን ባግቦ ዕጅህን በአስቸኩዋይ ስጥ፡፡ በከንቱ ከምትለፋና በግጭቱም ሕይወትህ ከምታጣ ዕጅህን በሰላም ሰጥተህ የልማታችን ተባባሪና ተጠቃሚ ሁን፡፡ ይህን ዕድል ሳትጠቀምበት ቀርተህ ለሚደርስብህ ጣጣ ተጠያቂው አንተና አንተ ብቻ ነህ፡፡… › ግሩም ማስጠንቀቂያ! ከግሩም ባዶ ጭንቅላት ወጣ ታላቅ የዓመቱ የሰላም ጥሪ!

ይህ በተባለ በሳምንት ገደማ አስጠንቃቂው አይወርዱ ውርደት ተዋርዶ ከነሚስቱ ተያዘ፡፡ የዓለም ታሪክም በሳምንታት ልዩነት ውስጥ የቅሌታም አምባገነኖችን ማፈሪያ የመጨረሻ ክንውኖችን እየመዘገበ ጉዞውን ቀጥሎኣል – ጥርሱን ጉራማይሌ ተነቅሶ እየሳቀና እየተሳለቀባቸው፡፡ እኛም ቀጣዩ ተረኛ ማን እንደሚሆን በጉጉት እየጠበቅን የአብሮነት ጉዞዋችንን ቀጥለናል፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው ይባል የለም? የአምባገነኖች ንግግርም ሆነ አጠቃላይ ነገረ ሥራ ግን አንዳችም ሳይዛነፍ አንድ ዓይነት መሆኑ በጣም የሚገርም ነው፡፡ ለወትሮው እሚባለው ‹ባልና ሚስት ከአንድ ምንጭ ይቀዳሉ› ነበር፡፡ አሁን ያ ቀርቶ ሌላ ዘፈን ተተክቶ ‹አምባገነኖች ከአንድ ባሕር(ይ) ይቀዳሉ› ወደሚል ፍጹም እውነት የተሸጋገርን ይመስለኛል፡፡ አንዱን ዐይተን ሌላውን ስናይ ከመልካቸው መለያየት በስተቀር ባሕርያቸውና ምግባራቸው ፍጹም ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን አንድ ዓይነት ነው፤ ተማሩ አልተማሩ ለውጥ የለውም፡፡ ትናንትን ጭራሽ የሚዘነጉ ተላላዎች፣ ዛሬን ከትናንት ማገናዘብ የማይችሉ የብስለት ድውያን፣ ነገ ምን እንደሚያስከትልባቸው ምንም የማይገምቱ የግንዛቤ ስንኩላን ፣ አስተሳሰባቸው ከአፍ እስከ አፍንጫው ሊሆን ቀርቶ ከላይኛው የፊት ጥርሳቸው እስከታችኛው የፊት ጥርሳቸው ድረስ እንኩዋን የማይዘልቅ የአእምሮ ሥውራን፣ የአንጎላቸው አጠቃላይ ይዘት እንመራዋለን ከሚሉት ሕዝብ የመጨረሻውን ዝቅተኛ ዜጋ (ቦዘኔም ይሁን ማጅራት መቺ) ያህል እንኩዋን ሊሆን የማይችል መናኛዎች፣ በጥቅሉ የለየላቸው ወፈፌዎችና ዕብዶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ የአፍሪካ አምባገነኖች በጣም አሣፋሪና — አሁን የሌላው ዓለም ሕዝብ እነሱን በሚያይበት ዐይን ይሆን እኛንም የሚመለከተንና ‹መሪዎቻቸው እንዲህ ከሆኑ ተመሪዎቹ ምን ይሆኑ ይሆን›? — በሚል ጭንቀት ጤነኞች ነን የምንል ወገኖችን በሀፍረት አንገት የሚያስደፉን ናቸው፡፡

የኛኑ ማፈሪያ መለስንም ስንመለከት ከዚሁ የተለየ ታሪክ የለውም፤ የሱ እንዲያውም ከሁሉ የባሰ ነው፡፡ እናም መጨረሻው ከባግቦና ከሳዳም የተለየ እንደማይሆን ከሁኔታዎች በመነሳት አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡ የማስጠንቀቂያ ጋጋታ የትኛውንም አምባገነን ከሚደርስበት የመጨረሻ አሰቃቂ ዕጣ አድኖት አያውቅም፡፡ ሳዳም ሁሴን አሜሪካዎች በሁለተኛው የባህረ ሰላጤው ጦርነት ባግዳድን እየከበቡ በነበሩበት ጊዜ ‹ግዴለም፤ ስንዝር ይጠጉና ባግዳድ መቀበሪያቸው ትሆናለች!› እያለ ዓለምን ሲያስቅ አንዳንዶቻችንንም ‹ይህ ሰው የተለየ መሣሪያ ይኖረው ይሆን ሲጠጉለት ድምጥማጣቸውን የሚያጠፋበት?› በማለት እንድንጠራጠር ሲያደርገን ከቆየ በሁዋላ በመጨረሻው እግር አውጪኙን አምልጦ እንደገናም በመጨረሻው መጨረሻ በሁለት ካሬ ሜትር ጉድጉዋድ ውስጥ እንደቀበሮ ከተሸጎጠበት በቅሌት ወጥቶ በውርደት ተሰቅሎ የማይቀር ሞቱን አስተናግዶዋል – ብዙ ሺህ ሊትር የሰው ደም በእጆቹ ነበራ! እንኩዋን የሰውን ደም የውሻን ደም በከንቱ የማያስቀረው ፈጣሪ ማንም የጁን እንደማያጣ ያሳየናል የታሪክ አካሄድ፡፡ እሱስ ተገላገለ፡፡ ይብላኝ ለነመለስና ለነባግቦ እንዲሁም ለነጋዳፊና ለነሣለህ – በሰው ደም እየዋኙ የእርኩሳን መናፍስቶቻቸውን ቀረቤታ ይለማመኑ ለነበሩና አሁንም ሥልጣን ላይ ተቀምጠው በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ የልቀቁ አንለቅም ጣር ላይ ለሚገኙ፡፡ እነሱም ፍርዳቸውን በሚገባ ያገኙታል፤ አሁን ቶሎ ቶሎ ይሥፈሩ፤ የነሱንም ቁና አንድዬ እያበጀላቸው ነው፡፡