ወያኔ የተቃውሞ ይዘት ያላቸውን መፅሐፍት ከቤተ-መፅሐፍት ማውጣት ጀመረ

ገዢው ፓርቲ ወያኔ የተቃውሞ ይዘት ያላቸው መፅሐፍትን በተለይ ከአንደኛና ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ቤተመፅሐፍት ውስጥ ሰብስቦ በማውጣት ላይ መሆኑን ምንጮቻችን ገለፁ፡፡ ይኸው የወያኔ ድርጊት የወጣቶች ማዕከላት ተብለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከፈቱ ማዕከላት ቤተመፅሐፍት ውስጥም ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል፡፡ እንደምንጮቻችን ገለፃ ገዢው ፓርቲ ይህንን በማድረግ ላይ ያለው መፅሐፍት የመለወጥ ሀይል ስላላቸው በተለይ ወጣቶች ወደማይፈልገው አቅጣጫ እንዳይሄዱ ካለው ስጋት በመነጨ ነው፡፡

ሰሞኑን ከተጠቀሱት ቤተመፃሐፍት ውስጥ ተሰብስበው ከወጡ መፅሐፍት መሀከል “ባህልና አገዛዝ” በሚል ርዕስ በቅርቡ የታተመው የፕ/ር መስፍን ወልደማርያምና የደራሲ ይስማዕከ ወርቁ መፅሐፍት እንደሚገኙበት ተረጋግጧል፡፡

መፅሐፍትን የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ ያለው በየወረዳው ባሉ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች አማካኝነት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሀላፊዎቹ በየቤተመፅሐፍት ቤቶቹ እየዞሩ መፅሐፍት ቤቶቹ የያዟቸውን መፅሐፍት የመገምገምና መፅሐፍቶቹን የገዟቸውን ሰዎች ስም የመመዝገብ ስራ እያከናወኑ መሆኑንም የምንጮቻችንዘገባ ያስረዳል፡፡

በአንድ የወጣት ማዕከል ቤተመፅሐፍት ውስጥ በመስራት ላይ ያለች አንዲት ወጣት በጉዳዩ ላይ ያላትን ገጠመኝ «አንድ ቀን አንድ ሹም መጣና ዴርቶጋዳንና አዲሱን የፕ/ር መስፍን መፅሐፍትን ምን ያህል ወጣቶች እንደተዋሱት የሚገልፅ ዳታ እንድሰራለት ጠየቀኝ፡፡ በማግስቱ መጣና መፅሐፍቶቹ ከማዕከሉ ሀላፊ ጋር በመሆን እንዲሰበሰቡ አደረገ፡፡ አሁን ወጣቶቹ መፅሐፍቶቹን ሲጠይቁኝ ሌላ ሰው ተውሷቸዋል እያልኩ ነው፡፡ እስከመቼ ይሄ መልስ እንደሚያስኬደኝ አላውቅም፡፡ መንግስት እንዳይነበቡ የሚፈልጋቸውን መፅሐፍት ለምን እንዲታተሙ እንደሚያደርግ አይገባኝም» በማለት ገልፃልናለች፡፡

ወያኔ/ኢህአዴግ ከዚህ በተጨማሪም ከአሁን በኋላ ፓርቲውን የሚተቹ መፅሐፍት ወደቤተመፅሐፍቶች እንዳይገቡ ለመከላከል ያመቸው ዘንድ የመፅሐፍት ግዢ ኮሚቴዎችና የመፅሐፍት ግዢ የሚመለከታቸው ሌሎች አካላት በሙሉ በፓርቲው ታማኝ አባላት እንዲተኩ እያደረገ መሆኑንም ምንጮቻችን ጨምረው ገልፀዋል፡፡