የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ህዝብ እያማረረ ነው
ያለፈው እሁድ ተግባራዊ የተደረገው የነዳጅ ጭማሪ ህብረተሰቡን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እያማረረ ነው፡፡ ይህ የሆነውም ከዚህ በፊት በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት ይደረጉ ከነበሩት የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪዎች በሙሉ የአሁኑ የበዛ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ታውቋል፡፡
በአሁኑ የዋጋ ጭማሪ 1፡15 የነበረው የጉዞ ታሪፍ ወደ 1፡25 ሲያድግ 2፡35 የነበረው ደግሞ ወደ 2፡60 ከፍ ማለቱ ታውቋል፡፡ እንዲሁም 3፡25 የነበረው የጉዞ ታሪፍ 3፡70 ሲደረግ 5፡30 የነበረው ደግሞ 6፡10 መግባቱ ታውቋል፡፡ ጉዳዩን በማስመልከት ያነጋገርናቸው የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች እንደነገሩን ታክሲ ይጠቀሙ የነበሩ ሰዎች አውቶብስ መጠቀም ሲጀምሩ አንዳንዶቹ ደግሞ ግማሹን መንገድ በእግራቸው በመጓዝ ወጭያቸውን ለመቀነስ እየሞከሩ ነው፡፡
ጭማሪው ያማረረው ተሳፋሪዎችን ብቻ ሳይሆን ሹፌሮችና ረዳቶቻቸውን ጭምር መሆኑንም በየታክሲው ውስጥ በጭማሪው ተበሳጭተው ሲነጋገሩ ከሚደመጡት ሹፌሮችና ረዳቶች ቃለ ምልልስ መረዳት ይቻላል፡፡ 17፡25 የነበረው የቤንዚን ዋጋ 21 ብር ከመሆኑ በተጨማሪ እሱንም ቢሆን ማግኘት እየቸገረ መሆኑም ታውቋል፡፡ በዚህ ምክንያት ታክሲዎች ለረጅም ሰዓት በየቤንዚን ማደያው ወረፋ በመጠበቅ ላይ በመሆናቸው ተሳፋሪዎች የፈለጉት ቦታ ባሰቡበት ሰዓት መድረስ አቅቷቸዋል፡፡
ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለው የሌሎች የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪም ነዋሪውን አስግቶታል፡፡