ወያኔ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ በአባል ተማሪዎቹ አማካኝነት ሊቆጠጠር ነው

ገዢው ፓርቲ ያለፈው ቅዳሜና እሁድ በትምህርታቸው ከ1ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ የወጡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ሰብስቦ እንደነበር በስፍራው የተገኙ ምንጮቻችን ገለፁ፡፡ እንደ ምንጮቻችን ገለፃ ከሁለትና ከሶስት ት/ቤቶች የተውጣጡት ጐበዝ ተማሪዎች አማካይ ሊሆን በሚችል አንድ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ እንዲሰበሰቡ ቢደረግም ከተለያዩ ትቤቶች የመጡ ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ የተገናኙት ግን በፕላዝማ የሚተላለፉ ገለጻዎችን ለመስማት ብቻ እንደነበር ታውቋል፡፡ ለተማሪዎቹ በፕላዝማ ገለፃ ካደረጉት የመንግስት ባለስልጣናት መሀከል በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴንና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዲላም ኦቶሬ ይገኙበታል፡፡

ገዢው ፓርቲ የስብሰባውን አላማ እንደተለመደው ከመማር ማስተማር ጉዳይ ጋር ለማየያዝ ቢሞክርም ተማሪዎቹ አጀንዳው ትምህርት አለመሆኑን በቀላሉ ደርሰውበት በዕረፍት ሰዓታቸው ሲነጋገሩበት እንደነበር ታውቋል፡፡

ተማሪዎቹ የገዢውን ፓርቲ ድብቅ አጀንዳ የተረዱት ከ1ኛ እስከ 10ኛ የወጡ ተማሪዎችን ብቻ የሚመለከት ስብሰባ እንደሚደረግ ከተነገራቸው ጊዜ አንስቶ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ገዢው ፓርቲ በማስፈራርያና በመደለያ ጎበዝ ተማሪዎችን በሙሉ አባል ማድረጉ ነው፡፡ እንደ ተማሪዎቹ ገለፃ ተማሪዎቹ የስብሰባውን አላማ አስቀደመው መገንዘባቸውን የተረዳው ገዢው ፓርቲ አጀንዳው ትምህርት ላይ ያተኮረ እንዲመስል ብዙ ጥሯል፡፡ በስብሰባው መጀመሪያ ተማሪዎቹ መምህራኖቻቸውን፣ አስተዳዳሩንና አጠቃላይ የየት/ቤቶቻቸውን ሁኔታ እንዲገመግሙና እንዲወያዩበትም አድርጓል፡፡ በዚህ ወቅት ተማሪዎቹ አስተማሪዎቻቸውን በተመለከተ ግልፅ ውይይት ቢያደርጉም ርዕሳነ መምህራኖቻቸው ራሳቸው አወያይ በመሆናቸው እነሱን በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን የሰጠንና በድል በር ት/ቤት ስብሰባውን የተከታተለ አንድ ተማሪ ሁኔታውን ‹‹የኢህአዴግ አባልነት ፎርም ያስሞሉን ዳይሬክተሮቻችን ናቸው፡፡ ስለዚህ የኢህአዴግ ደንበኛ አባል ናቸው ማለት ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ብለን እነሱን ለዛውም እነሱው ባሉበት የምንገመግመው?›› በማለት አስረድቷል፡፡

ከግምገማው በመቀጠል መንግስት እየተከታተለ ያለውን የ70 በ30 የትምህርት ፖሊሲ በተመለከተ ለተማሪዎች ማብራሪያ ከመሰጠቱም በላይ ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ላይ እንዲያተኩሩም ተመክሯል፡፡ በዚህ ወቅት የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ላይ ተማሪዎች እንዲሳቡ ለማድግ ተብሎ ሊሰጥ የነበረው ትንተና የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርቶችን ያንኳሰሰና አደገኛ እንደነበር ተስተውሏል፡፡

በጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ወቅት ተማሪዎች ከጥያቄ ይልቅ አዲሱ መፅሐፍ ሳይደርሳቸው የሚፈተኑት ፈተና በውጤታቸው ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ የተመለከተ አስተየየት በብዛት ሲሰጡ የነበረ ቢሆንም የተሰጣቸው መልስ ግን ተማሪዎቹን አስገርሟቸዋል፡፡ ከመንግስት ሀላፊዎች ለተማሪዎቹ ስጋት መቅረፊያ ተብሎ የቀረበው ምላሽ ‹‹የተማሪዎቹ ውጤት ላይ አስተያየት እንደሚደረግ›› የሚያስረዳ በመሆኑ ተማሪዎቹ ፈፅሞ ያልጠበቁት ምላሽ ሆኖባቸዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ወደ ዋናው አጀንዳ የገባው ከላይ የተጠቀሱትን ሽፋኖች ከተጠቀመ በኋላ ነበር፡፡

እያንዳንዱ ተሰብሳቢ ጐበዝ ተማሪ በስሩ አራት ተማሪዎችን እንዲይዝና የተማሪዎቹን አጠቃላይ ሁኔታ በየጊዜው ሪፖርት እንዲያደርግ እንደሚፈለግ በመጨረሻ ለተማሪዎቹ ተነግሯቸዋል፡፡

‹‹የተለየ አይነት እንቅስቃሴ የሚያደርግ ወይም ረብሻ ለማስነሳት የሚፈልግ ተማሪ ካለ በህይወታችሁ እየቀለደ ነውና ሙሉ ስሙን መዝግባችሁ ስለ ድርጊቱ አሳውቁን›› መባላቸውን የገለፀችልን አንዲት ተማሪ አስተያየቷን የዘጋችው ‹‹ትምህርቴን ልማር ነው ወይስ ተማሪዎችን ልከታተል›› በሚል ስጋት አዘል ጥያቄ ነበር፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡን መምህራንና ወላጆች ተማሪዎቹን የሰበሰቡበትን ምክንያት የአመፅ መጀመሪያ ት/ቤቶች በመሆናቸው ይህንን ለመከላከልና ከተነሳም በቀላሉ በቁጥጥሩ ስር ለማዋል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ተማሪዎቹ በስብበባው መጨረሻ 50 ብር አበል እንደተሰጣቸው ታወቋል፡፡