የመሸበት መንገደኛ አንቀበልም!

ለአንድ ሃገር ልማት ከዜጐቿ በላይ የሚጨነቅ የለም፡፡ ሃገር ውስጥም ሆነ ውጭ ያሉ ሁሉ ጥረው ግረው ያገኙትን በሃገራቸው ግንባታና በራሳቸው ህይወት መሻሻል ላይ ቢያውሉት የበለጠ ይመኛሉ፡፡

ቁም ነገሩ ግን ይኸ መልካም ምኞታቸው ብቻ ሳይሆን ለእውቀት ለሃብትና ገንዘባቸው እንዲሁም ለራሳቸው ደህንነት አስተማማኝ ሁኔታ በሃገራቸው መኖሩ ጭምር ነው፡፡ ይህ ካለ ደግሞ ከቤተ-መንግሥት መግለጫ፣ በካድሬዎች ቅስቀሳና የልዑካን ገለጣ አያስፈልጋቸውም፡፡

የልማት ተሳትፎን የፓለቲካ ወገናዊነት በሚወሰንበት ሃገር፣ ከመልካም አስተዳደር ይልቅ የክልል ባለሥልጣን በህልሙ አይቶ በሚቀማበት ምድር ቤት፣ ሠርተህ ግንባታ መሥርተህና ንግድ አደራጅተህ ‘’ጠቅመህ ተጠቀም’’ ቢባል ነገ በሚሆነው እርግጠኛ ላልሆነ ዜጋ አይዋጥለትም ፡፡ ምክንያቱም የላቡንና የእውቀቱን ፍሬ አየር በአየር አላገኘውምና፡፡

ትላልቅ የልማት እቅዶች ቀርቶ፣ ቤት መሥራት ዘውጉ በሚኖርበት ክልል እንዲሆን እየተደረገ ኢትዮጵያዊነቱን ለማመን የተቸገረ ጥቂት እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ በሚሊኒየም ዋዜማ ‘’ልዮ አጋጣሚ ተፈጠረልህ’’ ተብሎ የደከመበትን ቋጥሮ አገሩ የሄደና ገንዘቡን ያፈሰሰ ኢትዮጵያዊ በቢሮክራሲያዊ ጥልፍልፍና ፓለቲካዊ ሸር ባዶ እጁን የቀረ እንዳለም መቁጠር ይቻላል፡፡ በአካባቢው ቋንቋ አፍህን አልፈታህም ተብሎ ጨርቁን ሳይቀር ጥሎ የተባረረ ጥቂት አይደለም፡፡ በቅርቡ በአዋሳ ቤት ገዝተው ወይም ሠርተው ለመንግሥት የሚፈለግባቸውን እየገበሩና ማስረጃ እያቀረቡ ሳለ፣ በላያቸው ላይ እንዲፈርስ መደረጉንም እናውቃለን፡፡ ይህን ለመቃወም ሲወጡም የክልሉን ተወላጆች በተናጠል ሰብስበው ‘’ከነፍጠኛ ጋር አታብሩ’’ መባላቸውን ምሥክርነት የሰጡባት ሃገር ናት፡፡

በመሆኑም አገራችን ውስጥ ለሀብትና ንብረታችን የተረጋገጠ ሕጋዊ ዋስትና አለማግኘታችንና ስንበደል እንኳ ጉዳያችን በነፃነት አይቶ ፍትህ የሚሰጥ ዳኝነት አለመኖሩ ከሃገራችን ልማት ተሳተፉ ከሚሉን በላይ ያሳስበናል፡፡ እኛ በመልካም አስተዳደር ጥንካሬና ህልውና ነፃ በሆኑ የፍትህና የደህንነት አካላት ጥንካሬና ህልውና የምንተማመን እንጂ ከተቋማት በፊት በግለሰቦች የምናምን አይደለንም፡፡

ስለዚህም ነው የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግና ራሱን ለማሻሻል ያፈራነውን ጥረት አገራችን ላይ ማፍሰስ ብንፈልግም ነፃነት የጐደለው ልማት መሰናክል ሆነብን የምንለው ስለዚህም ነው በሃገራችን ኢትዮጵያ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ዲሞክራሲና ነፃ የፖለቲካ ሥርዓት እንካልተዋቀረ ድረስ በልማት ስም የምናስገባው የውጭ ምንዛሬ የወገኖቻችንን ሰቆቃ በማራዘም የአገዛዙን እድሜ ከመጨመር የተለየ ፋይዳ የለውም የምንለው፡፡ ለመሰደዳችን ምክንያት የሆነው የፖለቲካ ጭቆናና የኢኮኖሚ ኢ-ፍትሃዊነት እስካልተወገደ ድረስ የትኩረታችን አቅጣጫ ወደ ሥርዓት ለውጥ ነው የምንለው፡፡

ከውጭ ያለነውን ይተውንና እስቲ እዚያው በሃገር ቤት የንግድና የቢዝነስ ተቋማት በማን ቡድን ሞኖፖሊ እንደተያዘ ያስረዱን አቧራቸውን አራግፈውና ሰንደላቸውን ጥለው እነማን ናቸው፡፡ በአጭር ጊዜ ሚሊየነሮች የሆኑት ባንኮች ኢንሹራንሶች አስመጪና ላኪዎች የአዳዲስ ትርፋማ የማምረቻ ተቋሞች ባለቤቶች እነማን ናቸው? የገዥው ፓርቲ መሪዎች ቤተሰቦቻቸው ጀሌዎቻቸው አይደሉምን? ይህን አንስቶ ተው! የሚል ደግሞ በጐጠኞች በሚመሩት የመከላከያ የደህንነት፣ የፓሊስና ዳኝነት አካላት አይቀጡ ቅጣት ይቀጣል፡፡ ታዲያ ይህን እየሰማና እያየ ማን ሰው ነው ኢንቨስትመንት ቢሉት የሚገባው? ለምንስ ብሎ በሌላ ያዋለውን ገንዘቡንና ሀብቱን ለማዳን በሕግና በተደላደለ ሥርዓት መተማመኑ ቀርቶ የፓርቲ አባልነት ፎርም መሙላት የሚገደደው? ለምንስ ብሎ ዛሬ መሮት እየከዳው ከሄደ አገዛዝ ጋር በመተባበር ነገ ጠዋት የሚጠየቀው? እንኳን ተምሮ ያገኘውን እውቀት በሥራ መስክ እንዲያውል ለቅጥርና እድገት የፓርቲ አባልነት ግድ እየሆነ የመጣበት አገር እኮ ነው ያደራጁልን!!

እኛ በውጭ የመኖር እድል የገጠመን ኢትዮጵያውያን በአንድ ሃገር ውስጥ መልካም አስተዳደር፣ ነፃነት ሕግና ፍትህ መኖር ለህብረተሰቡ የተረጋጋ ኑሮ ያላቸውን ወሣኝነት በገቢር ለማየት ችለናል፡፡ ከዚህ መለስ ከዚህም ወዲያ የምንመኘው የለንም፡፡ ይህ ካለ ያለንን ጉልበት እውቀት ገንዘብና ሃብት እንደአቅማችን እዚያው አገራችን ላይ እናፈሳለን፡፡ ለዚህ ደግሞ በራሪ ወረቀትም ጥሪም ሰበካም ሆነ ሴሚናር አያሻንም፡፡ እነዚህ ተቋማት ከሌሉ ግን ከሕዝባችን ጋር እንዲፈጠሩ እንታገላለን እንጂ በምንም መንገድ ሕዝቡን በዘር፣ ሃይማኖት፣ ክልልና ቋንቋ ነጣጥለውና አጋጭተው ለሚገዙ ከፋፋዬች ሕልውና መራዘም በኢንቬስትመንት ስም አስተዋጽኦ አናደርግም፡፡ ሕዝባችን ባለውለታችን እንጂ ደመኛችን አይደለምና የሕሊናና የታሪክም ተወቃሽ አንሆንም፡፡

በApril 13 በተጠራው ስብሰባ ምናልባት የምንገኝ ከሆነ ይህንኑ እናረጋግጣለን፡፡ አገራችን እንድታድግ መጀመሪያ ሥልጣን ወደሕዝቡ ትራንስፎርም ይደረግ፡፡

ለኢንቨስትመንት መስፋፋት አስተማማኝ የሆነ ሕዝባዊ የፓለቲካ ሥርዓት!