በቃ ስንል! እምብዮ ሲሉ!

በሳምሶን ውብሸት

ባለፉት ሁለት ወራት በሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ የተስፋፋው የለውጥ እንቅስቃሴ በአመዛኙ የ20ኛውን ክ/ዘመን መለያ የሆነውን አምባገነንነት ወደ ታሪክ መዘክር የመጣል ሂደት የመጨረሻ መጀመሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የለውጥ ማእበል በአምባገነን ገዥዎችም ሆነ በምእራባውያን ሸሪኮቻቸው ዘንድ ያልተጠበቀ ክስተት ነበርና ሊቆጣጠሩት አልቻሉም፡፡

በመሆኑም ሕዝብን ረግጦ በጭካኔ መግዛት የኋላ ቀር የፓለቲካ ሥርዓት በተንሰራፋባቸው አገሮች ሊያበቃለት ነው፡፡ በእነርሱ እግር በምእራባውያን ተወልውሎ ወይም ተገጣጥሞ የሚቀመጥ አገዛዝ ማስፈንም እንደቀድሞ የሚቀል አይመስልም፡፡

በመስጠም ላይ ያለ ያድነው መስሎት አረፋም ቢሆን ይጨብጣል እንዲሉ ለአሥርት ዓመታት ህዝባቸውን ቀጥቅጠው የገዙ አምባገነን መሪዎች ይህን የታሪክ ሱናሚ ሊያቆሙ ቢወራጩም የቆሙበት መሬት ሸሽቷቸዋል፡፡ የቱኒዚያ፣ ግብጽ መሪዎች በተስፋ፣ በጥገናና በጉልበት የማእበሉን አቅጣጫ ለማስለወጥ ቢሞክሩም አንስቶ ወስዷቸዋል፡፡ አእምሯቸው መታወኩ የሚነገርላቸው ኮ/ል ጋዳፊም በገዛ ሀገራቸው ከአገራቸው ህዝብ ጋር ‘’የግድ ትወደኛለህ’’ ብለው ጦርነት ገጥመዋል፡፡ ምናልባት ይህ ጽሁፍ ሲነበብ ጋዳፊ ከሊቢያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ተባረው ይሆናል፡፡

ቁም ነገሩ ግን በሰሜን የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች የምናስተውለው ሕዝባዊ አመጽ በዘርና ሃይማኖት ላይ ያልተመሠረተ ወይም በቋንቋ ልዩነት የመጣ ሳይሆን በይዘት ለተሻለ ህይወትና የፖለቲካ ነፃነት መገኘት የተለኮሰ በመሆኑ የአረብ ሃገሮች መለያ እንዳልሆነ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም በአረብ ሀገሮችና ሙስሊም ተከታዮች መካከል የነበረ የግፍ አገዛዝ ተመሣሣይነት በመካከላቸው ያሉ የሃይማኖት፣ ቋንቋና ባህል ግንኙነት አንዱ ጋር የተለኮሰ የትግል ችቦ ወደሌላኛው በፍጥነት ተጉዞ ለማቀጣጠል መርዳቱን መካድ አይቻልም፡፡

የአንድ ሥር ነቀል የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ግን ቁንጮዎቹን አባሮ ከጀርባ የነበሩትን ወደፊት በማምጣት የሚያበቃ አይደለም፡፡ ስለዚህም የቱኒዚያና የግብጽ ፕሬዝዳንቶች መባረራቸውና የጋዳፊም እጣ ከዚህ ውጭ አለመሆኑ የአብዮቱን እመርታ ያመለክት እንደሆን እንጂ መሳካቱን ገና አያሳይም፡፡ አለበለዚያ ለአሮጌ ጅብ አዲስ ስም እየሰጡ ሥልጣን ላይ ማውጣት ትግሉንና መስዋእትነቱን ማራከስ ይሆናል፡፡

ስለዚህም የግብጽ፣ ቱኒዝ፣ ሊቢያ፣ ባህሬን፣ የመንና ሌሎች ሕዝባዊ አመጽ የጋመባቸው ሀገሮች በቃ ማለት ያለባቸው ግለሰቦችን በተናጠል ሳይሆን ሥርዓቱን በሙሉዕነቱ መሆን አለበት እንላለን፡፡

በአጠቃላይ ግን ሕዝባቸውን በድህነት እያማቀቁ ሃብት የሚያጋብሱ አገዛዞች፣ የዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱን ረግጠው በጭቆና የሚገዙ መሪዎች የትምሆኑ የትም ጊዜው በቃ! እያላቸው ነው፡፡ በተረገመ አስተዳደር ሥር በፍርሃት ተሸብበው በኃይል የሚገዙ ህዝቦች በቃ! ይቻላል! የሚል መፈክር አንግበው ለለውጥ እየተነሱ ነው፡፡ ይህ ሂደት ለለውጥ በበሰለች አፍሪካ ውስጥም በአንዳንድ ሀገሮች የቅርብ ጊዜ እውነታ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ያለእኩልነት አንድነት፣ ያለፍትህ መልካም አስተዳደር፣ ያለነፃነት እድገት ሊኖር አይችልምና ራሱን ወገኑንና አገሩን የሚወድ ሁሉ ወደአዲሱ ነፃነት ትግል መቀላቀሉ አይቀሬ ነው፡፡ የአገራችንም እጣ ፈንታ ከዚህ የበቃ አመጽ የተለየ አይሆንም፡፡

የበቃ ነገር ከተነሳ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የበለጠ የሚበቃው ያለ አይመስለንም፡፡ በቃ! ለሀገራችን ለሕዝባችን ከቃላት ያለፈ ጽንሰ ሀሳባዊ ይዘትም ሆነ ፍቺ አለው፡፡ ይህንንም አልፎ የተግባር መፈክር ነው፡፡ በቃ ስንል ግን ማፍረስ ብቻ ዓላማችን ሆኖ አይደለም፡፡ በምትኩ የምናንፀውን በሚገባ እናውቃለን፡፡ አጋሮቻችንም በቃ ስላልን በወቅታዊ መፈክርነት እንጂ በመዳረሻነት ወይም በስትራቴጂያዊ ዓላማ እንዳያዩብን እንፈልጋለን፡፡

የአንድ ሀገር አንጡራ ሀብቱ ሕዝቡ ሆኖ ሳለ ይህን ሕዝብ በቋንቋ፣ በጐሣና፣ በሃይማኖት ነጣጥሎ እንደመግዛት አስነዋሪ ተግባር የለም፡፡ የሃገሪቱን ሉዓላዊነት በጋራ መስዋእትነት ያስጠበቁ ዜጐቿን የልዩነት ሽብልቅ ከመክተት አልፎ መተማመን ፍቅርና አንድነትን እንደማሳጣት እኩይ ድርጊት የለም፡፡

የዚህ ሁሉ ድምር ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን መናድ መሆኑ ማብራሪያ አያሻውም፡፡ ለኢትዮጵያውያን በቃ! ማለት በጐሣ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ነጣጥሎ ሊያፋጀን ከሚጥረው አገዛዝ እንሰነባበት ማለት ነው፡፡

እያንዳንዱን ዜጋ እኩል ሆኖና የፖለቲካ ነፃነቱ ተረጋግጦ የወልና የግል መብቱ ተከብሮ ባህሉን፣ ቋንቋውና፣ ትውፊቱ ዳብሮ ራሱን በፈለገውና በመረጣቸው ወኪሎች የሚያስተዳድርበት አዲስ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲገነባ እንፈልጋለን፡፡ ይህ እንዳይሰምር ደግሞ ከተወላጅነታቸውና ስማቸው ሌላ ኢትዮጵያዊ ግብርን የማናይባቸውን እንግዴ ልጆች በቃ! ማለት ግድ ሊሆንብን ነው፡፡

በ21ኛው ክ/ዘመን 20 ዓመት ቀላል ጊዜ አይደለም፡፡ ምናልባትም በድሮ ጊዜ 200 ዓመት ያህል ሊሰላ ይችል ይሆናል፡፡ ወያኔ ርኩሳንን ሰብስቦ በኢህአዲግ ካባ ውስጥ ከወሸቃቸው ጊዜ ጀምሮ የአገራችን የግዛት አንድነት ተናግቷል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ክር እንዲሰልል ተደርጓል፡፡ አንድ ትውልድ ከመንደሩ ባሻገር ሀገር ምን እንደሆነ እንዳይረዳ ተኮትኩቷል፡፡ በዓለም ታሪክ አስደናቂ ቦታ ያለውን የኢትዮጵያን ታሪክ እንዳያውቅ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አልፎ የብሔረሰቡንም ቢሆን ስያሜውን ካልሆነ በቀር ታሪኩን እንዳያውቅ ተደርጓል፡፡ ይህ የሆነውም የእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሔረሰብ ታሪክ ከሌላው ጋር የተያያዘና ከሀገረ ኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ መነጣጠል ስለማይቻል ነው፡፡ በቃ የምንለውም ክህደትንና ይህንን ታሪካዊ ማንነታችንን ለማስመለስና ለማስጠበቅ ስለምንፈልህ ነው እነርሱ ደግሞ እምቢዮ የሚሉት የአጥፍቶ ጠፊ ተልእኮአቸው እስኪሳካ ድረስ ነው፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት በሀገራችን አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ ቆይቷል፡፡ የአገር አንድነት ለማስከበር የተካሄዱ ተከታታይ ጦርነቶች አልነበሩም፡፡ አሜሪካና የምእራብ መንግሥታትም ቢሆኑ እንደዘንድሮው በገንዘባቸው ቸር ሆነው አያውቁም፡፡ በውስጥም ቢሆን የሰው፣ የገንዘብና የማቴሪያል ክስረት የሚጠይቅ ሁነኛ ውዝግብ አልነበረም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሃገራችን አሁንም በእንፉቅቅ እየዳኸች ነው፡፡ ረሃብና ርጥባን ተለይቶን አያውቅምና የመኖር ፍቺ የጠፋባቸው ወገኖች በየብስ፣ በባህርና በአየር በ10ሺዎች አገር ለቀው ወጥተዋል፡፡ ፍልሰቱን ዘመነኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ሽንገላ አልገታውም፡፡

ያሁኑ ትውልድ ዛሬም እንደቀድሞቹ ትውልድ በጨለመ ሀገር ውስጥ መኖር አይሻም፡፡ ከዱር ተነስተው ሚሊየነር የሆኑ ግለሰቦች ጥጋብ አንጀቱ ላይ ጠብ አይልም፡፡ ስለዚህም በቃ ብሎ ተነስቶ ፍትሃዊና የዳበረች ሀገር መገንባት ይፈልጋል፡፡ በቃ የምንለው ኋላቀርነትን ጭምር ነው!!

ሀገራችን ሁሉም በእኩል የሚሳተፍበት የፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖራት እንጂ ትግላችን አንዱን ዘረኛ ቡድን አንስቶ ሌላውን ትምክተኛ ወይም ጠባብ ቡድን ማንገሥ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እስካለች ድረስ አንዱ ብሔረሰብ ተጠቃሚ ሌላኛው ተጐጂ ይሆናል ብሎ ነገር የለም፡፡ እንደምናየው ዛሬ የሚጠቀሙት በስሙ የሚነገዱትና ከአንተ ወርቅ አብራክ ተወለድን የሚሉት ጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ብቻ ናቸው፡፡ ታዲያ እሸቱን እየበሉ አረሙ እንኳ የማይደርሰው ወገን እንዴት የገዥነት ስሜት ሊኖረው ይችላል? እንኳን የእንግዴ ልጅ የምታዳላ እናት ልጆቿን ማበጣበጧ ይቀራል? ለዚህ ነው ዘበርጋ፣ ፈትለወርቅ፣ ማዴቦ፣ መገርሳ መሀመድ ወይም ሌላ ሥልጣን ያዘ ማለት የተወለደበት ብሔረሰብ ሁሉ ነገሠ ማለት አይደለም የምንለው፡፡ ለዚህ ነው የተወለደበትን ብሔረሰብ አስጨንቆና ከሌላው ጋር አቃቅሮ በሥልጣን መቆያ መሣሪያ ሊያረገው የሚፈልገውን በቃ እንበለው የምንለው፡፡ በቃ ስንል በተራ እንገዛዛ ሳይሆን በጋራ የምናስተዳድርለት ያለፍርሃትና ጥርጣሬ የምንኖርበት አዲስ ኢትዮጵያን እንፍጠር ማለታችን ነው፡፡ በቃ ስንል የትግራይ ወንድምና እህቶቻችን በስማችሁ የሚነግደውን ወያኔን እናንተም ከእኛ ጋር በቃ በሉት የሚል ጥሪ ማቅረባችንም ነው፡፡ በእኛ እምነትና ፍላጐት የበቃ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ችቦ አዲስ አበባ ላይ ሳይሆን መቀሌ ላይ መለኮስ የሚገባው ነው፡፡

ጠ/ሚ/ር መለስ ከ19 ዓመት በፊት ሕዝቡ በቀን ሶስቴ የሚበላበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለው ነበር፡፡ እርሳቸውና የአገዛዙ ተጣቢዎች ከሶስትም አልፈው መክሰስ ሲጨምሩበት አሁንም አንዴ እንኳ መብላት የተሣነው ወገን ብዙ ነው፡፡ በዚያች ዘፈን ግን 19 ዓመት ቆይተውበታል፡፡

አሁን ደግሞ እድገትና ትራንስፎርሜሽን በሚል ያልተማረው በእድገት የተማረውን በትራንስፎርሜሽን ቃል እንዲማልል ሲዲ አውጥተዋል፡፡ ያው በሥልጣን ሙጭጭ ብሎ የመቆያ ስልት እንጂ እቅዱ ተምኔታዊ መሆኑ እነርሱም ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ ምክንያቱም የምጣኔ ሃብት እድገትና የፈጠራ እምብርት የሆነ ነፃ የፖለቲካ ሥርዓት በዘመኑ ህብረተሰብ የተቆላለፉ ናቸውና፡፡ ይህ እንዳልሆነ ቻይናን እየጠቀሱ የሚሟገቱን ቢኖሩም፣ ቻይኖች ያለፖለቲካ ነፃነት ትንሽ ሄዶ ባፍጢሙ የሚደፋ እድገት ሂደት ላይ መሆናቸውን ያለጠንቋይ ልንነግራቸው እንወዳለን፡፡ ምክንያቱም እድገቱ የተወሰነ ደረጃ ላይ ሲደርስ የፖለቲካ ሥርዓቱ እስካልተለወጠ ድረስ ለቀጣይነቱ ማነቆ መሆኑ ስለማይቀር ነው፡፡ ያኔ ቻይኖችም በቃ ሊሉ ነው! ለነገሩማ አሁንም አላረፉም፡፡ ይህ እንግዲህ የቻይናን ታሪክ፣ ነባራዊ ሁኔታና የለውጥ ሂደት ለማስረጃ ሳንነካካ ደረቅ ሐቁን ብቻ ጠቁመን ለማለፍ ነው፡፡ መቋጫችን ግን ማህበራዊ ፍትህ የተዛባበትና የሕዝቡ ኑሮ እየከፋ የሄደበትን የኢህአዴግ አገዛዝ በቃ! እንበል ነው፡፡

በመጨረሻ እስካሁን የዘረዘርኩትን ማሰር እፈልጋለሁ፡፡ በመግቢያዬ እንደጠቆምኩት በቃ! ቃል ብቻ አይደለም፡፡ በቃ! የማንፈልገውን በማስወገድ የምንፈለገውን እንድንተካ ጐህ የሚቀድልን መሪ መፈክራችን ነው፡፡ በመሆኑም በቃ! ስሜትንና ብሶትን መግለጫ /Abstract/ መፈክር አይደለም፡፡ በቃ የጊዜ ሠንጠረዥ አለው፤ በቃ የምንለው ዛሬ ነው! ይበቃል ብለን መነሳት ያለብን አሁኑኑ ነው!

ዛሬ የአገራችን ችግርና የሕዝባችን ብሶት ልክ ያጣበት ለአምባገነኖች የማይመች ውጭያዊ የፖለቲካ ሁኔታ ተፈጥሮ እንቅልፍ ያጡበት ጊዜና፣ ወዳጆቻችን የሚሏቸው እየተንጠራሩ ሌላ ወዳጅ የሚፈልጉበት ወቅት ላይ ነንና በጋራ ከተን የነፃነት ቀንን ማቅረብ ይጠበቅብናል፡፡

መቼም ይሁን መቼም የወያኔን አገዛዝን ያለመስዋእትነት ማስወገድ እንደማይቻል ከተማመንን፣ መስዋእትነቱ የሚቀልበትን ጊዜና ስልት መምረጥ የእኛ ፈንታ ነው፡፡ ጥረታችን ህዝቡን በትግሉ ማገዝ እንጂ መተካት ባለመሆኑ በወቅታዊ መፈክር ሥር እንዲሰለፍ ማነሳሳት አለብን፡፡ በዚህ ወቅት ማነው የሚቀድመው? ጋሪ ነው ፈረሱ? ጐታቹ ማነው? በሚል እሰጥ አገባ ወቅቱን ካሳለፍን ምናልባት ታሪካዊ አጋጣሚው ያመልጠንና እንደ 1997ቱ ቢሆን ኖሮ ….. ልንል ነው፡፡ በታሪክም በህሊናም ተወቃሽ ልንሆን ነው፡፡

ወያኔ በህዝቡ ውስጥ የፈጠረው የልዩነት ስሜትና ክፍፍል የማያሳስበው አገር ወዳድ የለም፡፡ የበለጠ የሚያሳስብ ሆኖ የመጣው ግን አገዛዙ በቆየ ቁጥር ክፍፍሉን እንዳባባሰው ሁሉ፣ በሚቆይ መጠን አደጋውን የበለጠ አደገኛ እያደረገ መሄዱ ነው፡፡ ስለዚህም የአንድነትና ዲሞክራሲ ኃይሎች ልዩነቶችን አቻችሎና ተግባብቶ የጋራ የትግል ማእከል መፍጠር ያለባቸው አሁን ነው፡፡ በቃ! ማለት መለስተኛ በሆኑና በሚቻቻሉ ልዩነቶች ተለያይቶ መታገል ያክትም ማለትም ነው፡፡ ተቀራርቦ በመነጋገርና የጋራ መግባቢያ ሃሳቦችን በማንጠር፣ በዚያ ዙሪያ ተሰባስበን እንታገል ማለት ነው፡፡

በቃ! ገዬ! በስ! የአክል! ወታንደም! ዲትሃ! አሎኒ! ገዲስ! … ብለን ከተነሳን፣ ከተሰባሰብንና የጋራ ክንዳችንን ካስተባበርን የወያኔን እድሜ በእርግጠኝነት እናሳጥራለን፡፡