የወያኔ ‘የከፋ ግፍ ፅዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ነው’ – መድረክ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ትላንት ከሰዓት በኋላ በፅ/ቤቱ “አምባገነኑ ስርዓት በህዝብና በሀገር ላይ የሚያደርሰው የከፋ ግፍ ፅዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ነው” በሚል ርዕስ በሰጠው መግለጫ ኢህአዴግ ህዝባዊ አመፅ ሳይገነፍልበት በፊት መሠረታዊ ለውጦችን እንዲያደርግ ጠየቀ፡፡

መድረክ በመግለጫው መጀመሪያ ላይ ወያኔ/ኢህአዴግ «ኢትዮጵያ የአለም ሀገሮች ወደደረሱበት የዕድገት ደረጃ ሊያደርሳት የሚያስችላትን ዕድልና አጋጣሚ ሁሉ ሆን ብሎና አውቆ እንደተሰራ በሚያስመስል መልኩ አበላሽቶታል፡፡» ካለ በኋላ እንዲህ ለማለት ያስቻሉትን የገዢው ፓርቲ ጥፋቶች ዘርዝሯል፡፡ ከዝርዝሩ ውስጥ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ማድረግ፣ አሳፋሪውን የአልጀርስ ስምምነት መፈረም፣ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ጋር በተያያዘ የገደላቸው ንፁሀን ሰላማዊ ሰልፈኞች ጉዳይ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም ባላስከበረ መልኩ መሬትን ለውጭ ኢንቨስተሮች መስጠትና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

በመቀጠል የመድረክ መግለጫ ከ1997 ምርጨ ወዲህ ኢህአዴግ በህዝብ ፍቃድ ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችል ስለተረዳ ሁለንተናዊ የአፈና ስርዓት መዘርጋቱን ከገለፀ በኋላ የአፈና ስርዓቱ ውጤት ኢህአዴግ ባለፈው ምርጨ እንዳገኘው የሚገልፀው የ99.6% ድምፅ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ኢህአዴግ አስመዝግቤዋለሁ የሚለውን የኢኮኖሢ ዕድገት “የወረቀት ላይ ፕሮፓጋንዳ” በማለት የገለፀው የመድረክ መግለጫ መንግስት በቅርቡ ያወጣውን የዋጋ ተመን በተመለከተ የገበያ ትርምስ ከመፍጠር ውጭ ፋይዳ የሌለው መሆኑን አስምሮበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የመድረክ መግለጫ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከምንጊዜውም በበለጠ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እየተጣሱ መሆኑን ጠቅሶ መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት በፍፁም እንደሌሉም አስታውቋል፡፡

መግለጫው ሰሞኑን በኦሮሚያ 12 ዞኖች ኢህአዴግ በተቃዋሚ አባላት ላይ የወሰደውን አስራትና የሰብአዊ መብት ረገጣ ከዘረዘረ በኋላ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ጨቋኝ ስርዓቶች ላይ የነደደው የህዝብ ቁጣ ስላስደነገጠው የፈፀመው መሆኑን አስረድቷል፡፡ ሆኖም ይህ እርምጃ ለኢህአዴግ እንደማያዋጣ የሚገልፀው የመድረክ መግለጫ ከዚህ ይልቅ ገዢው ፓርቲ ያሰራቸውን ዜጎች መፍታት፣ ብሔራዊ የውይይት መድረክ መጥራትና መሰረታዊ ለውጦችን ማካሄድ እንደሚኖርበት አስታውቋል፡፡

ገዢው ፓርቲ እነዚህን ለውጦች ካላካሄደ የሚፈራዉ የህዝብ አመፅ እንደማይቀር ያስገነዘበው የመድረክ መግለጫ የመፍትሄ ሀሳቦችን ያካተቱ 5 ጥያቄዎችን ለኢህአዴግ መንግስት አቅርቧል፡፡ ከመግለጫው በኋላ መድረኩን ለውይይት ክፍት ያደረጉት የመድረክ አመራሮች ከሀገር ውስጥና ከውጭ ጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው መልስ ሰጥተውባቸዋል፡፡ “የኢትየጵያ መንግስት ሰሞኑን ኤርትራን አስመልክቶ የሚሰጣቸው መግለጫዎች ጦርነት ሊጀመር መሆኑን የሚያሳዩ ይመስላችኋል ወይ? ከተጀመረስ የእናንተ አቋም የሚሆነው ምንድነው?” ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄ መልስ የሰጡት የመድረክ ሊቀመንበት አቶ ገብሩ አስራት “ሻዕቢያ ኢህአዴግ እንደሚለው ኢትዮጵያን የማፈራረስ አቅም የለውም፡፡ ይህንን የሚለው እውነታውን ሳይረዳው ቀርቶ ሳይሆን ሰው በስጋት ተውጦ በሰብአዊ መብትና የኑሮ ጥያቄዎች ላይ እንዳያተኩር አቅጣጫ ለማስለወጥ ነው፡፡ ጦርነት ቢነሳ ለሚለው እኛ ከአሁኑ አቋም አንወስድም፡፡ ሁሉንም ነገር ከኢትዮጵያ ጥቅም አንፃር በማየት በተለይ ደግሞ የባህር በራችንን ልናስመልስ የምንችልባቸውን መንገዶች በጥልቅ እንመረምራለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለዚሁ ጥያቄ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ደግሞ ዶ/ር መረራ ጉዲና “ፓርላማ በነበርኩበት ጊኬ ከሶማሌ ጋር የነበረውን ጦርነት በተመለከተም የአብዛኞቻችን ተቃዋሚዎች ጥያቄ የነበረው ጉዳዩ ምን ያህል የሀገር ጉዳይ አለበት የሚለው ነበር፡፡ ሀገርና ድንበርን መከላከል ከሆነ ከናንተ ጋር ነን፡፡ አለበለዚያ ይቸግረናል ነበር ያልነው፡፡ ኢህአዴግ በሱማሌው ጦርነት ምን የህል ገንዘብ እንዳወጣና ስንት የህዝብ ልጅ ደም እንደፈሰሰ ለህዝቡ ሪፖርት አላቀረበም፡፡ ጦርነቱን እንዳካሄደበት የነገረን አላማም ግቡን አልመታም፡፡ አሁንም አቋማችን ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን ያመጣው የህዝን ጥያቄ ለማፈን ይሆናል፡፡ ካልሆነና ጦርነት ሊደረግ ከሆነም የጦርነቱን መንስኤ ጨምሮ ብዙ የምንመረምራቸው ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ኢህአዴግ ስላለ ብቻ የሚሆን ነገር አይኖርም፡፡ ከሻዕቢያ ይልቅ እኛ ለኤርትራ ህዝብ እንበጀዋለን ሲሉ የነበሩ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ነበሩና ምናልባት ጦርነቱ እኛንም የኤርትራ ህዝብንም ለመግዛት የሚደረግ መሆንና አለመሆኑንም ማየት ይኖርብናል” በማለት ጋዜጠኞቹን አስፈግገዋቸዋል፡፡

የኢህአዴግ የንግድ ተቋማትን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ሲሆኑ “ተቋማቱ የኢህአዴግ business empires ናቸው፡፡ መጀመሪያ ላይ ኢህአዴግ ተቋማቱ እንደሌሉ አድርጎ ሲክድ ቢቆይም በኋላ ላይ ግን endowment ናቸው፡፡ በትግሉ ጊዜ ያፈራነውን ገንዘብ የት እናድርሰው? የሚል አጉል ጥያቄ ጀምሯል፡፡ የንግድ ተቋማቱ የሚያስገኙት ትርፍ እዚች ሀገር ካዝና ውስጥ የማይገባና የሀገሪቱ ኦዲተር ጄኔራል የማያውቀው ነው፡፡ ድርጅቶቹ ሪፖርቶቻቸውን የሚያቀርቡት ለኢህአዴግ ነው፡፡ ይሄ በአንድ ሀገር ውስጥ የሁለትዮሽ ኢኮኖሚን የመፍጠርና ፍትሀዊ ውድድርን በማጥፋት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚጎዳ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንገድ እንደማይችሉ ከሚደነግገው የሀገሪቱ ህግ አንፃር ሲታሰብም ህገወጥነት ነው” ብለዋል፡፡

“የሰሜን አፍሪካው አመፅ በሀገራችን ይከሰታል ወይ? የናንተ አቋምስ በዚህ ላይ ምን ይመስላል?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጡት የመድረክ አመራሮች በኢትዮጵያ እየታየ ያለው አይነት ቀውስ እንዲመጣ እንደማይፈልጉ ገልፀው በሰላማዊ ውይይቶች ኢህአዴግ ችግሮችን እንዲፈታ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዳዩን አስመልክቶ “ህዝቡ እንደተራበ ሲነግሩት ለምን ኬክ አይበላም? እንዳለችው የፈረንሳይ ንግስት የኛም መሪዎች የህዝቡ ብሶት ሊገባቸው አልቻለም፡፡ ያኔ የሚበላው ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል ያልኩት ኢህአዴግ ለካድሬና ለካቢኔ እየቀለበ የኢትዮጵያን ህዝብ በማስራቡ እንዲታረም ነበር፡፡ አልታረመም፡፡ ኢህአዴግ ሳይታረም ጐረቤቶቻችን የህዝብ ነውጥ እያስተናገዱ ነው፡፡ ለመታረም ከፈለገ አሁንም የሚቀርብለትን የድርድር ጥያቄዎች ለማስተናገድ ሰዓት አለው” የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት ሌላው የመድረክ ተወካይ አቶ ገብሩ ገ/ማርያም “ወጣቱ አርሰናልና ማንችስተርን ቸል እያለ አልጀዚራን መከታተሉ የሚሰጠው መልዕክት አለ፡፡ እኛ ህዝብ እናነሳሳለን አላልንም፡፡ ህዝቡ ስለተበደለ ግን እኛ ባናነሳሳውም አይቀርም፡፡” ብለዋል፡፡

ከሳቸው በመቀጠል መድረኩን የተረከቡት የኦፌዴን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዋጋ ፋሪሳም “ሰሞኑን በኦሮሚያ ዞኖች ኢህአዴግ እያደረሰ ያለው ግፍም ይኸው ፍርሀት የወለደው ነው እንጂ የታሰሩት ሰዎች እንደተባሉት መሳሪያ ያከማቹ አልነበሩም፡፡ ሰዎቹ ስንቅም ጠበቃም እንዳያገኙ ተደርገዋል፡፡ ኢህአዴግ ኦሮሞነትን ችግር አድርጎታል፡፡” ብለዋል፡፡

ችግሩ በኦሮሚያ ይባስ እንጂ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችንም እየነካ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ገብሩ አስራት ሲሆኑ በትግራይ አቶ ተክላይ አርአያ የተባሉ የአረና አባል አመፅ የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችን በሞባይል የስልክ መልዕክት አስተላልፈሀል በሚል እንደታሰሩ ገልፀው ሌሎች የፓርቲው አባላትም በስቃይ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

መድረክ በዕለቱ ለኢህአዴግ ያቀረበውን የድርድር ጥያቄም በተመለከተ ከጋዜጠኞች “ኢህአዴግ መድረክ የስነምግባር ኮዱን እስካልፈረመ ድረስ ምንም አይነት ድርድር አይኖርም” በሚል እየገለፀ ባለበት ሁኔታ የድርድር ጥያቄ በማቅረባችሁ ጥያቄያችሁ ከጥያቄነት የዘለለ እንደሚሆን አታስቡም ወይ?” በሚል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ “የስነ ምግባር ኮድ አለመፈረማችን ኢህአዴግ ከኛ ጋር እንዳይደራደር ምክንያት አይደለም፡፡ ፓርላማ ገብቶ ህግ ሆኖ የፀደቀ ነገር ላይ የኛ መፈረምና አለመፈረም ምን ለውጥ ያመጣል፡፡ ህጉን የማክበር ግዴታ አለብን፡፡ ከዚህ ውጭ የሀገሪቱ ህግ ሆኖ የወጣን ነገር እኛ ስላልፈረምነው ለድርድር አለመቅረብ ምን ማለት ነው? እንድንፈርም የምንገደደውስ ለምንድነው? በፍጥጫና በማስገደድ ለመግዛት ከሚያምን ወገን የሚቀርብ ዝም ብሎ ምክንያት እንደሆነ ይገባናል፡፡ በመሆኑም ምንጊዜም አንቀበለውም” የሚል መልስ ሲሰጡ አቶ ገብሩ ገ/ማርያም በበኩላቸው “የስነ ምግባር ኮድ የፈረሙትስ ምን የፈየደላቸው ነገር አለ?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ጋዜጣዊ መግለጫው ከሁለት ሰዓታት በላይ የቆየ ሲሆን የመድረክ መሪዎች ከዚህ በፊት ሲሰጧቸው ከነበሩ መግለጫዎች ይልቅ ጠንከር ያለ ይዘት እንደነበረው ተስተውሏል፡፡