የመለስ ዜናዊ መንግስት የባለስልጣናቱ የሰሜን አሜሪካ ተልእኰ

በሀገርና በንፁሃን ወገኖቻችን ደም እየነገደ፣ቀኑ እየመሸበት ያለው የመለስ ዜናዊ መንግስት የባለስልጣናቱ የሰሜን አሜሪካ ተልእኰ ዋና አላማ ለልማት? ወይስ እኛን በሆድ ከፋፍለው የነርሱ የጥቅም ምርኮኞች ሆነን፣ የሕልም እንጀራ እየበላን፣ ለለውጥ እንዳንጮኽ ፀጥ ረጭ አድርገው ዘላለም ለመግዛት ነው?

በአህጉራችን በሰሜን አፍሪቃና በሌሎች መካከለኛ ምስራቅ ሀገሮች በህዝባዊ አመፅ በተናወጡበት ሰዓት በግልፅ እንደታየው ሁሉ እንደነ ሙባርክና ቢን ዓሊ የመሳሰሉ ፈላጭ ቆራጭ መሪዎች ከገቡበት አዘቅት ለማምለጥ ሲሉ የመጨረሻ ቀናቸው ሲደርስ የጥግና ለውጥ እናመጣለን፣ ሀገር እናለማለን፣ ለውጥ እናመጣለን በማለት የተነሳውን የህዝብ ቁጣ ለማብረድ፣ የትግሉን አቅጣጫ ለመቀየርና ብሎም ለማኮላሸት ሲሉ የቀቢፀ ተስፋ የኑዛዜ ቃላትና የማጭበርበር ስራ እንደጀመሩ፣ ሳይሆንላቸው ሲቀር ደግሞ “ከኔ በኋላ ሰርዶ አይብቀል” እንደሚባለው ሁሉ ህዝቡን እርስ በርሱ እንዲናቆር በማድረግ አጥፍቶ ለመጥፋት እንደሚፍጨረጨሩ በግብፅ፣ በቱኒዝያ፣ በሊቢያ፣ በየመንና በሌሎች ሀገሮች የተደረገውን አስነዋሪ ድርጊት በጋሃድ ዓይተናል። ሰምተናል። ታዝበናል።

ዛሬ በጎረቤት ሀገሮች እየተቀጣጠለ ያለውን የሰደድ እሳት ውሎ አድሮ የማይቀርላቸው መሆኑን በውል የተረዱት የወያነ ሸማምንትና አምባ ገነን መሪዎችም በአፈ ሙዝ ታፍኖ ያለውን የህዝብ ብሶት ዛሬ ነገ ይፈነዳ ይሆናል በሚል ስጋት የፍርሃትና የጭንቀት ምጥ ከያዛቸው ውለው አድረዋል። ከዚህ የተነሳም የህዝቡ የዳቦ፣ የፍትሕ፣ የነፃነትና የለውጥ ጥያቄ ለማዳፈን፣ የህዝቡ የትግል ወኔ ለመግደልና ብሎም ከፋፍሎ በመግዛት የስልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዛም ሲሉ ትናንት እጃቸው በንፁኃን ደም የታጠቡ፣ በሀገራችን አንጡራ ሃብት የቀለዱ፣ በሙሱና የተዘፈቁ፣ ዘራፊና ሰው በላ መሪዎች እኖሆ ዛሬ ባለቀ ሰዓታቸው እኛን ሊያመኙና የሕልም እንጀራ ሊያበሉን የልማትና የትራንስፎርመሽን ሃዋሪያ ሆነው መጥቷል። መሰሪ አላማቸው ተግባራዊ ለማድረግም አፕሪል 9 እና 10 ቀን 2011
ዓ.ም ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በሰሜን አሜሪካ በ14 ዋና ዋና ከተሞች ስብሰባ እንደጠሩም ሰምተናል።

ስለሆነም እኛ በሜሪላንድ፣ በቪርጂንያ፣ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የምንገኝ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በማር ጠቅልለው መርዝ ሊያጎርሱን የሚመጡትን የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ጠላት የሆኑትን የመለስ ዜናዊ የጥፋት መልእክተኞች የማጨበርበሪያ ዜዴያቸውን በአደባባይ ወጥተን ለማክሸፍ፣ ለማጋለጥና ለመቃወም ዛሬም እንደ ትላንቱ ሆ! ብለን በመነሳት ለአፕሪል 9 ቀን 2011 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሚደረገው ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እንድትገኙ የአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የሰልፉ አዘጋጅ፡- በዋሽንግተንና አካባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በመተባበር
የሰልፉ ቦታ፡- በዋሽንግተን ዲሲ – በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ
የሰልፉ ቀንና ሰዓት፡- አፕሪል 9 ቀን 2011ዓ.ም በ10፡00am ይጀምራል
የበለጠ ለመረዳት፡-
202 656 8070, Email – [email protected]