የምድረበዳው አጽም እንቆቅልሽ – አደፍርስ ተሰማ
ገና በጥዋቱ ሰው ሁሉ ተሰብሰቦ መኪና ይጠባበቃል። ይመጣል የተባለው ደላላ ትላንት ብቅ ብሎ በአረብኛና ትግርኛ ሰውን ሁሉ ቀልቡን አሳጥቶት ሄድዋል። ዛሬ የጉዞ ቀን ነው። ሰው ከለበሰውና ከሚጠጣበት የውሃ እቃ ሌላ ምንም መያዝ አይፈቀድም። ደላላው እሄዳለሁ ብሎ ከተሰለፈው ሃበሻ ሁሉ ገንዘብ ወስዶ አስረክብዋል ትላንትና ለበላዪ። ሳይታስብ አንድ በእንጨት የተጠገነ መኪና ሰውን ተጠግቶ ቆመ። ደላለው ወርዶ ቶሎ መኪና ላይ ውጡ እያለ ማጣደፍ ጀመረ። ሥፍራው ወዲያውኑ ስለሞላ አራግፌ እመጣለሁ በማለት ትቶን ተፈተለክ። ደግሞ መጣና ጫነ። በአራተኛው ጉዞው ሁሉን አመላልሶ ጨረሰ።
ሰው ከተጫነበት ሥፍራ እንዲወርድ የተደረገው ምድረ በዳ ላይ ነው። ፀሃዩ ያቃጥላል። አለፍ አለፍ ብሎም መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ቆመዋል። በራሳቸው ላይ ነጭ ነገር ስለጠመጠሙበት በውል ማንነታቸው አይታውቅም። ከሱዳን፤ ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የተሰባሰበው ህዝብ ወደ ሶስት መቶ ይጠጋለ። ይበልጡ ከኤርትራ ውትድርና ሰልቸቶአቸው አምልጠው የመጡ ሴቶችና ወንዶች ናቸው። ሳናስበው ሃያ አምስት ትላልቅ መኪኖች በሽራ ተሸፍነው ብቅ አሉ። ከመኪናው ወስጥ ነጂና ሌላ ሰው በሁሉም ወስጥ አለ። በጣም ዝግ ብለው አለፉን። ትንሽ እንደቆየ አምስት ሎሪና ስድስት ላንድ ክሩዝር መጡና ሎሪው ላይ እንደንወጣ ታዘዘን። እየተደጋገፍን ሁላችንም እንደሰርዲን ታሽገን ጉዞ በቀስታ ቀጠልን። የስደተኛው አላማ እስራኤል መሄድ ስለሆነ የመኪናውን በዛት ስናይ በጣም ደስ አለን።
ይህ በዚህ እንዳለ አስመራና ካርቱም ያለው የሞሳድ የስለላ መረብ ከሳምንት በፊት ለአለቆቹ ከፍተኛ ሚስጥር ያለበት መረጃ አስተላልፎ ነበር። በዛም መረጃ መሰረት የእስራኤል የጦር ስልት መስመር መያዝ ጀምሮል። ሽራ የተሽፈኑት ከባድ መኪናዎች የጫኑት የጦር መሳሪያ በየዓይነቱ ሲሆን መዳረሽው ለሃማስ ነው። የተላከው ከኢራን ሲሆን ወደሱዳን የተላለፈው በኤርትራ በኩል በየብስና በባህር ነበር። ገና የሱዳንን መሬት ሳንለቅ ሰማዬ በአውሮጵላን ድምጽ ተናወጠ። እኛን የጫኑት መኪኖች ከህዋላ ስለነበሩ ከፊታችን ስለሆነው ማየት አንችልም። ግን በሰማይ ላይ ከፍና ዝቅ የሚሉትን ኤፍ- አስራ አምስት አውሮጵላኖች ከጎኔ የተቀመጠ አንድ የድሮ የኢትዮጵያ ፓይለት በድንጋጤ መንፈስ ነገረኝ። ምን ጉድ ነው እያለን ስናወራ ወዲያው የቦንብ ዝናብ መውረድ ጀመረ። እኔና ይህ ፓይለት ከሎሪው ዘለን ወርደን በሆዳችን ተኛን። ዝቅና ከፍ እያሉ በመደጋገም መኪና ላይ የነበረን ሰውና እቃ ሁሉ እሳት ለኮሶበት። የተጫነው እቃም መፈንዳት ጀመረ። አብቅቶአል በማለት የተረፈ እንዳለ ለማየት ስሞክር ያለ እኔ ማንም ያለመኖሩን ተረዳሁና ከፍርሃቴ የተነሳ እንደገና ተደበቁኝ። መላ አካላቴ ሞቆዋል። እሳቱ ከመኪናው ላይ አልጠፋም። የተጫነው ሁሉ መፈንዳት ጀመረ። ወዲያው ሌላ ዙር ደብደባ ቀጠለ። እኔም አልተርፍም በማለት ራቅ ብዬ በሆዴ ተኛሁ። በግምት ከአሥራ አምስት ደቂቃ በህዋላ ሁሉም ጽጥ አለ። አንድም ቆሞ የቀረ ነገር የለም። ሁሉም አመድ ሆንዋል። ይህ ከሆነ በህዋላ እኔም ስውን ወደ ሊቢያ ከሚልኩት ሰዎች በሹፌርነት ተቀጠርኩ። ሲሆን ሊቢያ ካልሆነ ወደ እስራኤል የሚሄድ ሰዎችን አመላልሳለሁ። ታዲያ አንድ ጊዜ ድብደባ በሆነበት ሥፍራ ሳልፍ የጫንኩዋቸው ሰዎች መጸዳዳት ፈለጉና አቆምኩ። አንድ ሃበሻ የምን አጽም ነው የተከመረው አለኝ? እኔም አይ እዚህ ግመል የሚሞትበት ሥፍራ ነው የግመል ነው አለኩት። እርሱም ዓይኔን ትኩር ብሎ አይቶ ግመል የሰው ጭንቅላት አለው እንዴ አለኝ። እኔም እንባየ መጣና አላስችል ብሎኝ አለቀስኩ። ሁሉን ነገርኩት። እርሱም ትክዝ ብሎ ከቆየ በህዋላ ልትመልሰኝ ትችላለህ ወደ ካርቱም አለኝ? እኔም ደንገጥ በማለት ለምን አልኩት? በቃ ሃሳቤን ቀይሬአለሁ አለኝ። እሺ ግን የከፈልከው ገንዘብ አይመለስም አለኩት። ችግር የለም። ብቻ መልሰኝ አለኝ። ከሶስት ቀን በህዋላ ሌሎችን አራግፈን እኛ ካርቱም ገባን። ቆይቶ ስሰማ በመተማ በኩል አዋሳ መመለሱን ሰማሁ። በነገራችን ላይ የታሪኩ ተራኪ – ከሞት የተረፈውና በሾፌርነት ሰው ማመላለስ የጀመረው ካርቱም ወስጥ ባልታወቀ ሰው ተገድⶀል::
ከላይ ያለውን ታሪክ ያጫወተኝ የአዋሳው ልጅ ነው። ይህ ታሪክ ታይም የተባለው መጽሄት በሁለት ሺህ ዘጠኝ ካወጣው ዘገባ ጋር ተቀራራቢነት አለው። ለምሳሌ አውሮጵላኖቹ ተመልሰው የመጡት የመጀመሪያው ድብደባ እንደታሰበው አለመሆኑን ሰው አልባ አውሮጵላን ያነሳው ፎቶ ነግሮአቸው። ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ኪ.ሜትር ርቀት መጥተው ድብደባውን ያደረጉት በአየር ላይ ነዳጅ በመሙላት ነው ይለናል የታይም መጽሄት ዘጋቢ። በዚህ ሁሉ ምንም የማያውቁት ሰዎች ህይወት ጠፋ። ዛሬ በዓለም ዙሪያ ሃበሳውን የሚቆጥረው ህዝብ መሰደድ ቀላል እንዳልሆነ ማስረዳት የግድ ይሆንብናል። በየመን፤ በተለያዬ የዓረብ ሃገራት በሰው ላይ የሚፈጸመው ግፍ ለመዘርዘር ጊዜና ሥፍራ አይኖርም። በሳይናይ በረሃ ዘላኖች (በድዊን) በህዝባችን ላይ የሚፈጽሙት የሰውን አካል በህይወት እያለ ቀዶ ኦርጋኑን አውጥቶ መሽጥ ነው። ስብዕና የላቸውም። እንዲኖራቸውም አይጠበቅም። በእሳት የተቃጠሉ። በህይወታቸው ጉድጓድ የተጣሉ ስንቶች ናቸው።
የሚያዋጣው የሃገራችንን ሁኔታ ለውጦ በዛው ለመኖር መታገል እንጂ ገና ጸሃይ ይወጣልኛል ብሎ መንገድ መጀመር አያዋጣም። የምድረበዳው አጽም ክምር ለእኛ የተወልን ትምህርት ቢኖር ሞት፤ግርፋት፤ እርዛት፤ እስራትና ባርነት በመንገድ ላይና በሰው ሃገርም እንዳለ ነው።