“ሙሴ” ፊልም የህወሓት አባላት መካከል ክርክር ፈጠሯል

በብርሀኔ ንጉሴ ተደርሶ የተዘጋጀው እና በቅድመ ምረቃ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲአትር የካቲት 9 ቀን 2003 ዓ.ም ለእይታ የቀረበው «ሙሴ» ፊልም ከህወሃት በወጡ ሰዎች “አድልኦ የታየበት” በመባል ሲወገዝ በተቃራኒው በስልጣን ላይ ባሉት ወያኔዎች ዘንድ ድጋፍ እያገኘ ነው፡፡

ከሕወሀት የወጡት እና በአሁኑ ወቅት የተቃውሞውን ጎራ የተቀላቀሉት አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ከአንድ የአገር ውስጥ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት “ሙሴ” ፊልም የታሪክ ባለቤት የሆኑ እና አሁን ከሕወሃት የወጡ ወገኖችን ታሪክ አልባ በማድረግ በስልጣን ላይ ለሚገኙ ወገኖች ያልሰሩትን ታሪክ ያቀዳጃል፡፡ አቶ አስገደ ለአባባላቸው በአስረጂነት ካቀረቡት መሀል እሳቸው የሰሩትን ጀብዱ አቶ ስዩም መስፍን እንደሰሩት አድርጎ ማቅረብ ይገኝበታል፡፡

ለዚህ ዘገባ አስተያየቱን እንዲሰጠን የጠየቅነው እና ስሙን መግለጽ ያልፈለገ አንድ የቀድሞ የሕወሃት ታጋይ በአቶ አስገደ ሀሳብ እንደሚስማማ ገልፆ እሳቸው ከገለፁት ታሪክን ማዛባት በተጨማሪ ፊልሙ ሌላም ችግር እንዳለበት ያስረዳል፡፡ የቀድሞው ታጋይ “ፊልሙ የሙሴ ታሪክ ላይ የተሰራ ነው ከተባለ የሙሴን ታሪክ በሚገባ ማሳየት አለበት። ሕዝቡ ማወቅ ከሚፈልገው የሙሴ ታሪክ ውስጥ ደግሞ አሟሟቱ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ምክንያቱም እስከአሁንም ድረስ ሙሴ የተገደለው ከሕወሃት በተተኮሰ ጥይት እንደሆነ የሚያምኑ በርካታ ወገኖች አሉና ፊልሙ ይህንን የተድበሰበሰ እውነት ፈልጎ ማውጣት ይጠበቅበት ነበር፡፡ ብርሃኔ ግን ይህንን አላደረገም፡፡ እውነትን መመርመር በመፍራቱ የፊልሙን መጨረሻ ያደረገው ከሙሴ ሕይወት መጨረሻ እጅግ አስቀድሞ ነው፡፡” ብሏል፡፡

ብርሃኔን በተጠቀሰው መለኩ የሚያብጠለጥሉት እንደመኖራቸው የሚያዳንቁትም አልጠፉም፡፡ የካቲት 17 ቀን 2003 ዓ.ም የታተመው የገዢው ፓርቲ “ህዳሴ” ጋዜጣ “እንደአሸን የአሜሪካን “FBI” ፊልሞች የሚያዳንቁ በፈሉበት ትውልድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጨማሪ “FBI” ማቅረብ አይደለም ከኢትዮጵያ ጥበብ የሚጠበቀው” በማለት የደራሲ ነፃነት ወርቅነህን “FBI” የተባለ ፊልም ካብጠለጠለ በኋላ ለኢትዮጵያ ጥበብ የሚያስፈልጉት እንደብርሃኔ ንጉሴ አይነት ወጣቶች መሆናቸውን ይገልፃል፡፡

«ሙሴ» ፊልም መነጋገሪያ የሆነው በተጠቀሱት ጉዳዮች ብቻ አይደለም፡፡ ፊልሙን በነፃ ለማሳየት ባለሀብቶች ስፖንሰር እንዲያደርጉ በመፈለጉም ባለሀብቶች ላይ የስነልቦና ጫና ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑም ታውቋል፡፡ ከነዚህ ጫናዎች ዉስጥ በአፍቃሪ ኢህአዴግነቱ የሚታወቀው የኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ባለቤት ሳምሶን ማሞ ንግግር ይገኝበታል፡፡ ሳምሶን ከላይ ከጠቀስነው ህዳሴ ጋዜጣ ላይ ባደረገው ቃለምልልስ ፊልሙን በነፃ ለማሳየት 2 ሚልዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልፆ ይህንን ገንዘብ ባለሀብቶች እንዲሸፍኑት “በሙሴና ጓደኞቹ መስዋዕትነት በተገኘ ሰላምና ልማት ተጠቃሚ በመሆን ሀብት ያፈሩ ባለሀብቶች ይህንን የተቀደሰ ዓላማ በስፖንሰርነት ሊደግፉ ይገባል” በማለት አሳስቧል፡፡