የስኳርና ዘይት ወረፋ እያማረረ ነው

መንግስት “መሠረታዊ ናቸው” ባላቸው የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ቅናሽ እንዲደረግ ካወጀ ወዲህ በርካታ ችግሮች እየተከሰቱ ነው፡፡ 26 ብር እንዲሸጥ የታወጀው ዘይት ከገበያ ፈፅሞ የጠፋ ሲሆን በወቅቱ 33 ብር ሲሸጥ የነበረው የሀገር ውስጥ ዘይት 40 ብር ከመግባቱም በላይ ይህንን ዘይት ለማግኘት በመሸጫ ስፍራው ከሌሊቱ 12 ሰዐት ጀምሮ ሰልፍ መያዝ አሊያም ወረፋውን ቀደም ብለው ከመጡት ሰዎች በ100 ብር መግዛት ግዴታ ሆኗል፡፡ ለስላሳና ቢራ በየሆቴሉ እንደልብ የማይገኙ ሲሆን ደረጃውን የጠበቀ ሳሙና ማግኘትም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

ጥሬ ስጋም ቢሆን ሌላ ዘዴ ተገኝቶለታል፡፡ 1 ኪሎ በ52 ብር መሸጥ ያከስረናል ያሉ ነጋዴዎችና ጥራት ያለው ስጋ መግዛት የሚፈልጉ ሸማቾች የራሳቸውን መግባቢያ ኮድ ፈጥረዋል፡፡ አንድ ሰው ጥሬ ስጋ ለመግዛት ወደ ልኳንዳ ቤት እንደደረሰ “የግል ወይስ የመንግስት” የሚል ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡ መልሱ የግል ከሆነ ልኳንዳ ቤቱ የተመነውን ዋጋ ከፍሎ ጥራቱን የጠበቀ ጥሬ ስጋ ተመርጦ ይሰጠዋል፡፡ የመንግስት ያለ እንደሆነ ግን በተቃራኒው ይሰራለትና ባብዛኛዉ የማይፈለጉ የስጋ ክፍሎችን በ52 ብር እንዲገዛ ይገደዳል፡፡

ከሁሉም በላይ ህብረተሰቡን ያማረረው ግን የስኳር ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ ስኳር በየሱቁ እንደልብ የሚገኝ ነገር አይደለም፡፡ ስኳር ለማግኘት የፈለገ ሰው በጅንአድ ሱቆች፣ በኢትፍሩትና በሸማቾች ማህበራት ሱቆች በራፍ ላይ መሰለፍ ግዴታው ነው፡፡

2 ኪሎ ስኳር ለመግዛት ቢያንስ ለ8 ሰዓታት መሠለፍ የሚያስፈልግ ሲሆን ሌላው አማራጭ ቀድመው ከተሰለፉ ሰዎች ወረፋውን በ20 ብር መግዛት ነው፡፡ ያ ካልሆነም ከአትራፊዎች አንዱን ኪሎ ስኳር በ30 ብር በድብቅ መግዛት ግድ ብሏል፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ስኳር ማግኘት በፍፁም አሞከርም፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች “በእንዲህ ያለ ሁኔታ ህ/ሰቡ አየተማረረ መሆኑን አውቆ መንግስት ሌላ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ሲጠበቅ በተቃራኒው የነዳጅ ዋጋን በመጨመር ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉ እንዳስገረማቸው ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ አዋሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኝ አንድ የሸማቾች ማህበር ሱቅ በመንግስት እየተማረሩና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየጮኹ ያገኘናቸውን አዛውንት “ምን ሆነው ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርበንለቸው ነበር፡፡ አዛውንቷ የሆኑትን ሲያስረዱ “ከጥዋቱ 2 ሰዓት የተሰለፍኩ ይኸው አሁን ድረስ /ከቀኑ 9 ሰዓት ሆኖ ነበር/ ስንቃቃ ቆይቼ ተራዬ ደርሶ ስገባ ኩፖን የለሽም ብለው አባረሩኝ፡፡ እኔ እርዳታ አልጠየኩም፡፡ በገንዘቤ ስኳር ልገዛ ነው የመጣሁት፡፡ ስኳር ለመግዛት ምን አይነት ኩፖን ነው የሚያስፈልገው? ይኼንንስ የት ሄጄ ነው አቤት የምለው? እሺ ልጆቼን ምን ላድርጋቸው? ጠዋት ሻይ ካልቀመሱ ወደ ት/ቤት አይሄዱልኝም! እንደው መንግስት የሚባል ነገር እዚህ ሃገር ላይ ካለ አንድ መፍትሄ ያብጅልን” ሲሉ ምሬታቸውን ገልቸዋል፡፡