የመለስ ወይም የአቶ ኢሳይያስ ሞት ለምድራችን መፍትሄ አያመጣም – አደፍርስ ተሰማ
እንደ ሃገራሽን የሃምሌ ዝናብ ያለማቆም የሚወርደው የወሬ ናዳ አእምሮአችንን ሲያሳምመን ቀናት ቆጥረናል። በጦርነት ጊዜ ቀዳሚ መስዋዕትነት የምትከፍለው እውነት እንደ መሆኑዋ ሁሉ በወሬ ናዳም እውነት ትሞታለች። ሞታም ትነሳለች። ቀደም ባለው የወሬ ነፋስ የሻቢያው አለቃ አረፉ ተብለን ነበር። እሳቸውም ጊዜ ቆጥረው ብቅ በማለት ለወዳጅና ለጠላታቸው አለሁ አርፋቹሁ ተቀመጡ በማለት ፊታቸውን አሳዩን። በመሰረቱ የኤርትራው መሪ ሞት ለሃገሪቱ የሚያመነጨው ተስፋ የለውም። ችግርንና መከራን እንጂ! የኤርትራ ህዝብ አንድነትና ሰላም አደፍራሾች የውጭ ሃይሎች እንጂ የወያኔ ድንፋታ አይደለም። የወያኔና የሻብያ ፍትጊያና ፍጥጫ ሌሎች የሚገፉትና እሳቱ ደምቆ እንዲነድ ነዳጅ የሚያቀብሉት የጭፍን ግብግብና ማለቂያ የሌለው ትግል ነው። ወንድሙን እህቱን ገድሎ የሚፎክር ወታደር በዓለም ዙሪያ ተሰምቶ አይታወቅም። የሻብያና የወያኔ ወታደሮች ግን ጀግና የሚባሉት ስንት ኤርትራዊና ስንት ኢትዪጵያዊ እንደገደሉ ተሰልቶ ነው። አንድ የሚያረገንን ነገር ሁሉ እያፈረሱ የጥል ግድግዳ የሚያቆሙት እነዚህ አፍራሽ ሃይሎች ዛሬም የሚተነፍሱት ከበረሃ ይዘው በመጡት ልብና ሳንባ ነው። ለውጥ የሚባለ ነገር ለእነርሱ ማፍረስ ነው።
አሁን እንሆ የአቶ መለስ መታመም በተቃዋሚ ድህረ -ገጾች ላይ በየቀኑ እየተነገረን ነው። አንድ ሞተዋል ሲለን፤ ሌላው ደግሞ በጽኑ ታመዋል፤ የቀረው ደግሞ ግባተ – መሬታቸውን ፈጽሞ ወደፊት ስለሚሆነው ያስነብበናል። እውነቱ ግን ከዚህ ሁሉ ውስጥ አይደለም። በመሰረቱ የአቶ መለስም ሆነ የሻብያው መሪ ሞት ህዝባችንን ከጫኑበት ሰቆቃና ስቃይ አያድነውም። የዘረጉት አጥፊና ከፋፋይ ድልድይ መፍረስ ብቻ ነው ለህዝባችን ጠቀሜታ የሚያመጣው። የምንቃወመው ሃሳባችውን፤ ድርጊታችውን መሆን አለበት እንጂ የልቡ እንዳልደረሰለት የመድሃኒት መተተኛ ሞታቸውን መመኘት የለብንም። ሞት ለማንም አይቀርም። ጭቁኑም ተጨቋኙም በጊዜአቸው ያልፋሉ። ታዲያ በዚህ ሁሉ የወሬ ናዳ ውስጥ አቶ መለስ ብቅ ብለው አዎን አሞኝ ነበር። አሁን ግን ተሽሎኛል ወደሥራም ተመልሻለሁ ቢሉን የውሽት የወሬ ጆንያ ተሸከመው ወሬውን ሲያናፍሱ የነበሩ ሁሉ ምን ይሉን ይሆን? አበው ሲተርቱ “ማን ያርዳ የቀበረ፡ ማን ይናገር የነበረ” እንዲሉ አጉል የይሁንልን ምኞታቸውን የሚነግሩን ሁሉ አስበውና አመዛዝነው የእውነት ወሬ ቢያካፍሉን ለድህረ- ገጻቸው መታመኛ ጉልበት ያክልላቸዋል። ለዛሬ ደርሰናል። የተለየ ወሬም የለም። ነገ የሚያመጣውን ጠብቀን እንይ!