የህትመት ዋጋ እስከ 50% ጨመረ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጦች ሊጠፉ ተቃርበዋል

ከመጋቢት 13 2003 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የተነገረለት የህትመት ዋጋ ጭማሪ ነፃው ፕሬስን እስከመጨረሻው ሊያጠፋው እንደሚችል እየተገለፀ ነው፡፡

የህትመት ዋጋ ጭማሪው እንደየጋዜጦቹ የገፅ፣ የህትመት ብዛትና የቀለም ብዛት የተለያየ በመሆኑ ከ30-50% እንደሚደርስ ታውቋል፡፡ የህትመ ዋጋ መጨመር ከጀመረ ጥቂት ቢቆይም የአሁኑ የህትመት ዋጋ መጨመር ከረጀም ጥቂት ቢቆይም የአሁኑ ግን ነፃው ፕሬስ ከተቋቋመበት ከ18 አመት ወዲህ ከነበሩት ጭማሪዎች ወደር የማይገኝለትና ትልቁ ነው። በመሆኑም የነፃዉ ፕሬስ ባልደረቦች ከቅዳሜ ጀምሮ በወጡ ዕትሞቻቸው በመጥፋት ላይ መሆናቸውን በግለፅ መንግስት የወረቀት ዋጋ ላይ ድጎማ እንዲያደርግ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነውና ባለፈው ቅዳሜ ገበያ ላይ የዋለው ካፒታል ጋዜጣ ሁኔታውን ‘print media on the way to extinction” በማለት ሲገልፀው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በበኩሉ ጭማሪው አስደንግጦናል አስጨንቆናልም” ብሏል፡፡

ሜዲካል ጋዜጣ በዛሬው ዕትሙ ከአሳታሚዎች ኪሳራን ተቋቁሞ ከመቀጠል አንፃር ዋጋ መጨመር ግድ መሆኑን ገልፆ ህብረተሰቡ ከሚገኝበት ከፍተኛ የኑሮ ችግር አንፃር ሲታሰብ ደግሞ ዋጋ መጨመሩ እንደማያስኬድ በማስረዳት ግራ መጋባቱን አሳይቷል፡፡ ጋዜጣው ማተሚያ ቤቶች ከሚጨምሩባቸው ዋጋ አኳያ እነሱም ጭማሪ ካደረጉ የአንድ ጋዜጣ የመሸጫ ዋጋ እስከ 8.00 ብር ሊደርስ እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡

በዛሬው ዕለት ከወጡት ጋዜጦች ውስጥ የሚገኘው አዲስ ወሬ ጋዜጣም በበኩሉ የነፃው ፕሬስ መኖር ጥያቄ ውስጥ መውደቁን የገለጸ ሲሆን ሁኔታውን አስመልክቶም በፓርላማ ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉን አነጋግሯል፡፡ አቶ ግርማም የማሳተሚያ ዋጋ ጭማሪውን “ፕሬሱን ለማሽመድመድ የተደረገ” በማለት ገልፀውታል፡፡

ስለሁኔታው አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ከጠየቅናቸው መሀል አንዱ የሆነውና አምስት ኪሎ አካባቢ ጋዜጣ በማዞር የሚተዳደር አንድ ወጣት የተባለው የዋጋ ጭማሪ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ህብረተሰቡ ዋጋ ጨምሮ ጋዜጦች ለመግዛት የማይችልበት የኑሮ ደረጃ ላይ በመሆኑ ምን ሰርቶ እንደሚኖር በማሰብ እየጨነቀ መሆኑን ነገሮናል፡፡

የነፃው ፕሬስ አባላት ጭማሪውን በተመለከተ አስተያየት እንዲደረግላቸው በመጠየቅ ትላንት ከብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ማተሚያ ቤቱ የጥያቄያቸውን መልስ ነገ ሊያሳውቃቸው ቀጠሮ እንደያዙ ለማወቅ ተችሏል፡፡