ለስርዓት ለውጥ ዝግጅት ወሳኝ ምዕራፍ ተከፍቷል
ከኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክርቤት የተሰጠ መግለጫ
ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም
ዘረኛውና ጨቋኙ የህወሓት አገዛዝ በሃገራችንና በህዝባችን ላይ እየፈጸማቸው ያለው ህዝብ የማሰቃየት፤ የማሰር፤ የመግደል፤ ከቀየ የማፈናቀል፤ ጋዜጠኞችን ማሰር፤ የመናገር፤ የመሰብሰብና የመቃወም ነጻነትን ማፈን፤ ታሪካዊ የሃይማኖት ተቋማትን ማፈራረስ፤ የስርዓቱን ካድሬዎች በሃይማኖት አመራር ላይ መመደብ፤ ህዝቡን በሀይማኖትና በዘር በማከፋፈል ማጋጨት፤ እህቶቻችንን በአረብ ሀገሮች ለባርነት መሸጥ፤ ሌሎችም እጅግ በርካታ በደሎች የቀጠሉ ሲሆን፥ በቅርቡ ደግሞ የአምባገነኑ ስርአት ቁንጮ የአቶ መለስ ዜናዊን የጤና መታወክ ተከትሎ እየደረሱን ያሉ መረጃዎች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወዴት አቅጣጫ እየተጓዘ እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑን እያለመለከቱን ነው። ከዚህም አንጻር ለሀገራችን ይህ ወቅት በአንድ በኩል እጅግ ፈታኝ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ደግሞ መልካም አጋጣሚዎች ሊፈጥር ይችላል ብለን እናምናለን።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ም/ቤትም ከሚደርሱት መረጃዎች በመነሳትና የሁኔታዎችን አሳሳቢነት በመገንዘብ፤ ከዚያም በላይ የሽግግር ም/ቤቱ የተመሰረተበትን ሰላማዊና የኢትዮጵያን አንድነትንና ሉአላዊነት፤ የዜጎችዋን መብት የሚያስጠብቅ የሽግግር ሂደት የማመቻቸትን ተልእኮ በተመለከተ ይህንን ወቅታዊ መግለጫ አውጥቷል።
- በአምባገነኑ አቶ መለስ ዜናዊ የጤና ሁከት ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን የስልጣን ሽኩቻ ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ አለመረጋጋት ሊከሰት እንደሚችል ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ፤
- በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ሊከሰት የሚችለው አለመረጋጋት የራሱ የሆነ አሉታዊ ወይንም አወንታዊ ውጤቶችን ሊያመጣ ስለሚችል መላው ህበረተሰብ ለውጡ ዘወትር ሲመኘው የኖረውን ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ያመጣ ዘንድ እንዲታገል፤
- ተቃዋሚ ሀይሎች ሁሉ በአስቸኳይ ተሰባስበንና ተመካክረን፤ ሃገራችንና ህዝባችንን የሚታደግ አማራጭ እቅድ በመንደፍ፤ ሃይላችንን አስተባብረን ሁሉን አቀፍ የሽግግር ስርአት እንዲፈጠር የሚጠበቅብንን ሀገራዊ ሀላፊነት እንድንወጣ፤
- የመከላከያ ሃይሉም የኢትዮጵያን ሉአላዊነትን በማስከበር ሚና ላይ በማተኮር ከህዝብ ጎን በመቆም የህዝብ ወገናዊነቱን እንዲያሳይ፤
- ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ሳይሆን ለራሳቸዉ የስልጣን ጥም፤ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለውጭ ሃይሎች በተገዙ ቡድኖች እጅ የሀገሪቱ ሕልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅና መንግስታዊ ስልጣን በጸረ-ኢትዮጵያ ሀይሎች እጅ እንዳይወድቅ ሁሉም ሀገር ወዳድ ነቅቶ እንዲጠብቅ፤
- ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ህዝቡን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል አላስፈላጊ ወደሆነ ግጭት ለመውሰድ የሚጥሩትን አፍራሽ ሀይሎች ህዝቡ በቆራጥነት በመታገል የሀገሩን ሉአላዊነትና የህዝቡን አንድነት እንዲያስጠብቅ፤
- በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያን እንወክላለን የሚሉ አምባሳደሮች ለአምባገነኖች ተገዥ ከመሆን እንዲታቀቡና ከህዝቡ ጎን በመቆም የህዝብ ወገናዊነታቸውን እንዲያሳዩ፤
- የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ሁኔታዎች ሳይባባሱ የተፈጠረውን የሽግግር ሂደት በመደገፍ ድርሻቸውን እንዲወጡ፤
- በስማቸው የሚነገደው ነገር ግን የስርአቱ ተጠቃሚ ያልሆኑት አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በዚሁ አጋጣሚ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ጎን በመቆም የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ጥቅም የሚያስከብር ስርዓት እንዲመጣ የትግል አጋርነታቸውን በተግባር እንዲያረጋግጡ፤
የሽግግር ም/ቤቱ አመራር ጠቅላላው ጉባኤ በሰጠው ሃላፊነት መሰረት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር መወሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በአፋጣኝ ምክክር ለመጀመር ያስችል ዘንድ ለሁሉም ተቃዋሚ ሃይሎች የትብብር ጥሪ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ያቀርባል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት አመራር