በአቶ መለስ የሚሸበሩት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች

ከመ/ር ቀለሙ ሁነኛው | ፍኖተ-ነጻነት

ዛሬ ካለው የአለማችን ተጨባጭ ሁኔታ የየትኛውም አገር መሪዎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የሚደረገው ጥበቃ እጅግ የጠነከረ ነው፡፡ ተራ ሰው በነበሩ ጊዜ እንዳሻቸው በህዝብ መሀከል የሚንቀሳቀሱ ሁሉ የሥልጣን ማማው ላይ ሲወጡ ዙሪያገባቸው በጦር መሣሪያ ይከበባል፡ በሚያልፉባቸው መንገዶች ወፍ እንኳን ዝር አትልም፡፡ በተለይ በሚመሩት ህዝብ የሚጠሉ መሪዎች ከሆኑማ ሽርጉዱ አይጣል ነው፡፡ ጠባቂዎቻቸው መርዝ እንደበላች ውሻ ሲክለፈለጉ ይታያል፡፡ በእርግጥ በህዝባቸው ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ዴሞክራት መሪዎች እንደልብ መንቀሳቀስ ቢችሉም ለደህንነታቸውና ለአገሪቱ ክብር ሲባል ተገቢው ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ የሚደረግላቸው ጥበቃ ግን የህዝብን የየዕለት ኑሮ የሚያስተጓጉልና በሽብር የሚንጥ አይደለም፡፡ ሕዝቡ ራሱ በነፃነት የመረጣቸው በመሆኑ የሚመሩትን ሕዝብ አይፈሩም፡፡

የሚመሩትን ሕዝብ የሚፈሩ መሪዎች ግን ዕድሜ ልካቸውን በሥጋት ይኖራሉ፡፡ ለህዝብ የመጡ ሳይሆኑ በህዝብ ላይ የወጡ አምባገነኖች ናቸው፡፡ ዜጎች አይደለም በአካል ሊያዩዋቸው
ድምፃቸውን እንኳን መስማት አይፈልጉም፡፡ በተለይም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአፍሪካ መርገም ሆነው የተነሱት መሪዎች በሚመሩት ህዝብ ዘንድ የማይታመኑና እነሱም የሚመሩትን
ህዝብ የማያምኑ ህዝባቸውን በዴሞክራሲና በፍቅር ሳይሆን በጠብመንጃ አፈሙዝ መግዛት የሚቀናቸው ናቸው፡፡ ለዜጎች ህይወት ግድ የላቸውም፡፡ ደም በማፍሰስና በማፋሰስ ይረካሉ፡፡ የሕዝቦቻቸው መጎሳቆል ጉዳያቸው አይደለም፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የዚህ እኩይ ዕጣ ፈንታ ተጋሪ ናት፡፡ በየዘመናቱ የተነሱት መሪዎቿ በጠብመንጃ እንጂ፣ መቼም ቢሆን በህዝብ ድምጽ ተመርጠው ሥልጣን ላይ አልወጡም፡፡ ኢትዮጵያውያን እስከ አሁን ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ አልታደልንም፡፡ ዛሬም የምዕራቡን ዓለም ዴሞክራሲ ለመቀላወጥ ተገደናል፡፡ ያለፈውም ሆነ የዛሬው ትውልድ በመሪዎቹ ላይ እንዳቄመ፣ መሪዎቹም በህዝቡ መሀከል በነፃነት ለመንቀሳቀስ እንደሰጉ እስከ የት እንደምን ዘልቅ ግራ ቢያጋባም የነፃነት መሻታችንን እውን ለማድረግ በጽናት መታገልን ይጠይቀናል፡፡

አፄ ኃይለ ሥላሴ በግማሽ ምዕተ ዓመት የንግስና ዘመናቸው ከኮሎኔል መንግስቱ እና ከአቶ መለስ ዜናዊ በተሻለ መልኩ በህዝብ መሀከል በነፃነት ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ይህን ስል ንጉሱ ዴሞክራት መሪ ሆነው ሳይሆን “ሥዩመ-እግዚአብሄር” በሚል የማስፈራሪያ ንጉሱ ከእ/ር ዘንድ እንደ ዳዊትና ሰለሞን ለመሪነት የተቀቡ ተደርጎ ስለሚሰበክ ህዝቡ ካደረበት ፈሪሀ እግዚአብሄር የተነሳ ንጉሱ ሲወጡና ሲገቡ እንኳን ሊተናኮላቸው ቀና ብሎ ለማየት ይፈራል፡፡ ንጉሱም የህዝቡን የውስጥ ስሜት ስለሚያውቁ እንደልባቸው ይወጣሉ ይገባሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የ1966 አብዮት ንጉሱን ከሥልጣን
ሲያሽቀነጥራቸው ህዝቡ መሬት ትንቀጠቀጣለች በሚል ይጠባበቅ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ እንኳንስ መሬት ልትንቀጠቀጥ ንፋስም ሽው አላለ፡፡

የዘመነ ወታደራዊው ደርግ ፊታውራሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን በስበብ አስባቡ ካስወገዱ በኋላ “ቆራጡ መሪያችን” የሚል ካባ ደርበው ብቅ አሉ፡፡ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች (ህቡዕ ድርጅቶች) የመስመርና የአላማ ልዩነት ሳቢያ በእነ ኢህአፓ ጅምላ ጭፍጨፋ እሳቸውም በላንድሮቨር መኪና አዲስ አበባ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ በጥይት መቁሰላቸው ይታወቃል፡፡ ከዚያ በኋላ የሚደረግላቸው ጥበቃ እንደ ብረት እየጠነከረ መጣ፡፡ አገሪቱን በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሥር ጠቅልለውና ሥልጣናቸው እጥፍ ድርብ ሆኖ እያለ የሚመሩትን ህዝብ አጥብቀው ስለሚፈሩ የጥበቃ አጀባቸው ጠንካራ ነበር፡፡ በቤተ መንግሥት ጠባቂዎቻቸው ላይ ፍፁም እምነት ነበራቸው፡፡ ኮሎኔሉ ምንም እንኳን ጨቋኝና የለየላቸው አምባገነን ቢሆኑም በውስጣቸው የሚንቦገቦገው የኢትዮጵያዊነት ስሜትና የሀገር ፍቅር ፅናታቸው ዛሬም ቢሆን በጨቆኑት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ እንዲታወሱ አድርጓቸዋል፡፡ “እናት ሀገር ወይም ሞት” የሚለው መፈክራቸው መለያቸው ነበር፡፡ በየጊዜው በሚያደርጓቸው ረጃጅም ንግግሮች መሀከል “እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ . . .” ማለት ይቀናቸው ነበር- ኮሎኔሉ፡፡ አምባገነንነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለነገሩ ለ17 ዓመታት ከሻዕቢያና ከህወሓት ጋር ያደረጉት ጦርነት ኤርትራን ያለማስገንጠል ትንቅንቅም እንደ ነበር አይካድም፡፡

ኢትዮጵያ ከኮሎኔል መንግስቱ እጅ ተነጥቃ ለአቶ መለስ ዜናዊ ከተቸረች ይኸው ድፍን 21 ዓመት ተቆጠረ አቶ መለስም ኮሎኔሉን በ4 ዓመታት ብልጫ እየመሩ ነው፡፡ 21 ቁጥር ማሊያ ለብሰው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ክለብ አጥቂ በመሆን ይጫወታሉ፣ ሲያሻቸውም ግብ ጠባቂ በመሆን ከመሀል ሜዳ ኳሷን አፈፍ በማድረግ ፋዎል ይፈፅማሉ፡፡ በአጠቃላይ ሀገሪቱን በራሳቸው ፖለቲካ እያተራመሷት ይገኛሉ፡፡ በ1994 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት አንድ ምሁር አቶ መለስን “ኳሷ በእግርዎ ስር ናት ሲፈልጉ ይጠልዟታል፣ ሲያሻዎትም ጎል ያገቧታል . . .” ሲል የተናገራቸው በእርግጥም እውነት ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ነጠላ ወረቀት የሚያጥፉና የሚዘረጉ አንድ እና አንድ እሳቸው ብቻ ናቸው ያልገባው አንድ ሰው ካለ የሃያ አንድ አመቷን ኢትዮጵያን አያውቃትም ማለት ነው፡፡

በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ የአቶ መለስ ተክለ-ስብዕና በመላው አገሪቱ እየገዘፈ እንዲመጣ በተለያየ መጠን የህዝብ ግንኙነት ስራ በመሰራት ላይ ነው፡፡ እንደ መከለሻ ቅመም በየሥፍራው
እየተገኙ የሚያደርጉት ዲስኩርና በጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎች አንገት ላይ በሚያጠልቁት ሜዳሊያ የራሳቸውን ሰብዕና እንዲሰቅል ታስቧል፡፡ ፎቶግራፋቸው “ብልህ መሪ፣ አስተዋይ መሪ፣ የአፍሪካ ጠበቃ፣ አባይን የደፈረ መሪ፣ ምርጥ ነውና ምረጡት . . .” በሚሉ ‹‹አማላይ›› ቃላት ተዥጎርጉሮ በየአደባባዩ መሰቀል ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ እሳቸው ግን ከህዝቡ ልብ ውስጥ ውልቅ ብለው የወጡት ዛሬ አይደለም፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው የምርጫ 97 የህዝብ ድምጽ ነው፡፡ የዴሞክራት መሪዎች መገለጫ በየአደባባዩ የሚሰቀለው ፎቶ ግራፋቸው ሳይሆን በሕዝብ ልብ ውስጥ መስረጋቸው ነው፡፡

አቶ መለስ “99.6% ህዝብ መርጦናል” ቢሉም ሕዝብ ወድዶ እንደመረጠው መሪ በህዝብ መሀከል ለደቂቃ እንኳን ለመንቀሳቀስ አይደፍሩም፡፡ ከቤተመንግስት ወጥተው እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ
ድፍረቱም ሆነ ሞራሉ የላቸውም፡፡ አቶ መለስ ከአገር ሲወጡም ሆነ አዲስ አበባ ውስጥ ለሥራ ጉዳይ ሲንቀሳቀሱ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ይናወጣሉ፡፡ የፖሊስ ሞተሮችና መኪናዎች አዲስ አበባን በጡሩምባ ጩኽት ያተራምሷታል፡፡ የፌደራል ፖሊሶች አገር አማን ነው ብለው የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን እያዋከቡ በየሥርቻው ሲወሸቁ አሊያም ከአስፋልቱ ርቀው ፊታቸውን እንዲያዞሩ ሲያስገድዱ ይስተዋላል፡፡ ላለፉት 21 ዓመታት የአዲስ አበባ ህዝብ በተለይም ከቤተ መንግስት እስከ ቦሌ አየር መንገድ የሚንቀሳቀሱ ዜጎችና አሽከርካሪዎች ይህንን ሰላማዊ መሰል ሽብር በማስተናገድ ተሰላችተዋል፡፡

ውድ አንባቢያን ሃሳቤን የሚያጠናክሩ ገጠመኞችን ላንሳላችሁ፡፡ አንዱ ገጠመኝ የራሴ ነው፡፡ ወሩን በትክክል ባላስታውሰውም ሁኔታው የተከሰተው ከዛሬ 13 ዓመት በፊት ነው፡፡ ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ቦሌ መንገድ በሚገኘው ፊላሚንጎ ሬስቶራንት በረንዳ ላይ ሻይ ቡና እያልን ስንጫወት ድንገት አካባቢው በፖሊስ ተተራመሰ፡፡ መኪናዎችም ሆኑ እግረኛው መግቢያ እስከሚያጡ ተጯጯሁ፡፡ እኔና ጓደኞቼም የተፈጠረውን ነገር ሳናውቅ በጥፊና በእርግጫ ተብለን እግሬ አውጭኝ አልን፡፡ ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ ስንሰማ አቶ መለስ ከውጭ ስለገቡ መሆኑን ተረዳን፡፡ ሰሞኑን አንድ በዕድሜ የገፋ ሰው እንደ እኔው የገጠማቸውን አጫወቱኝ፡፡ ቦሌ አካባቢ ቆይተው መኪናቸውን እያሽከረከሩ ወደ መስቀል አደባባይ ሲጓዙ ድንገተኛ ግርግር ይገጥማቸዋል፡፡ ፌደራል ፖሊሶችና ትራፊክ በቁጣ
ያንቧርቁባቸውና “መኪናህን ይዘህ ከአስፓልት ውጣ” ሲሉ ያዟቸዋል፡፡ ግራ ቀኙን ሲያዩ ከአስፖልት ለመውጣት የሚያስችል አማራጭ ስላልነበራቸው “ወዴት ልሂድ?” ሲሉ በመደናገጥ ይጠይቃሉ፡፡ “ስትፈልግ ገደል ግባ!” በማለት ከደነፋባቸው በኋላ ከኋላና ከፊት መኪናቸውን እየገፉ ከመስመር አውጥተው የሆነ ገደላማ ሥፍራ ላይ ከነመኪናቸው ይወሽቁቸዋል፡፡ ወዲያው ግርግሩ
እንዳለፈ እነዚሁ ፖሊሶች “አሁን መሄድ ይችላሉ” ሲሏቸው መኪናዋን ለማንቀሳቀስ ተቸገሩ፡፡ ፖሊሶቹ ከኋላ እየገፉ ረድተዋቸው አስፋልት ከወጡ በኋላ በመደመም ስሜት ውስጥ ሆነው
“ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ማዋከብ ምን ስለተፈጠረ ነው?” በማለት ይጠይቃሉ፡፡ አንዱ ፖሊስ ወደ ጆሮአቸው ተጠግቶ “ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ከውጭ እየገቡ ስለነበር ነው” እንዳላቸው አጫወቱኝ፡፡ እውነት ነው ህዝብ የመረጠው መሪ የሚመራውን ሕዝብ አይፈራም፡፡ በህዝቡ ላይ ሙሉ እምነት ሊኖረው ይገባል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ለዚህ ክብር አልታደልንም፡፡