ኢቲቪ ተኮር “ግጥም” በጨዋታ (አቤ ቶኪቻው)
ሰሞኑን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “አንድ ሀገር ብዙ ሃይማኖት” በሚል ርዕስ ዶክመንተሪ ፊልም አሳይቶን እንደ ቡና ደጋግመን ጠጥተነዋል።
ዶክመንተሪው ርዕሱ ደስ ይላል። እውነት ነው ኢትዮጵያ አንድ ናት እውነት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሃይማኖት አለ መኖርም አለበት። (በመርህ ደረጃ ይሄ ትክክል ነው! (ወይ መርህ…! አትሉኝም!?)) የኢቲቪ ዶክመንተሪ ግን ሆነ ብሎም ይሁን ሰይጣን አሳስቶት አንዱን በአንዱ ላይ ጭራሽ የሚያነሳሳ ነው። ደግነቱ ሀገሩ ኢትዮጵያ ነው። ደግነቱ ጣቢያው ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው። እንጂ ሌላ “ጠብ ያለሽ በቲቪ ” ያለ ሀገር ቢሆን ኖሮ፤ ወይ ደግሞ ጣቢያው እምነት የሚጣልበት ቴሌቪዥን ጣቢያ ቢሆን ኖሮ አፋጅቶን ነበር! እያለ አስተያየቱን የሚሰጥ ሰው ተበራክቷል።
እስቲ በሰላም እየኖርን ያለንን ሰዎች ያኔ እንዲህ አድርገዋችሁ ነበር፣ ያኔ እንዲህ በድለዋችሁ ነበር እያሉ ማነካካት አግባብ ነው!? በእውነት ይደብራል። ደግነቱ ህዝቡ ነቄ ነው። ሙስሊሙም አብሮት ከኖረ ክርስቲያን ወንድሙ ጋር፣ ክርስቲያኗም ከቡና አጣጪ ሙስሊም እህቷ ጋር በኢቲቪ ቆስቋሽነት የተነሳ ለጠብ የሚጋበዙበት ዕድል የለም! በፈለጋችሁት እምላለሁ። ለማንኛውም አንድ ግጥም ብጤ እንሆ፤
ያኔ በደህናው ወቅት
ቆጥቤ እቁብ ጥዬ፣
የገዛሁት ቲቪ
ያወጋኛል ብዬ፣
አነሆ ዘንድሮ
አመሉን ቀይሮ፣
መረጃ ማቀበል
ማውጋቱንም ትቶ፣
ማዋጋት ጀመረ
ጎራ አስለይቶ።
በእውነቱ ይሄ ጉዳይ ያበሳጫል፣ ያቃጥላል፣ ያሳምማል። ብለን አብዝተን ስንማረር ደግሞ ግጥም ሁለት እንደሚከተለው ትወለዳለች፤
ሲበላሽ ሳስጠግን
ሳሰራው ከርሜ
ሲቃጠል ሳሳክም
በሌለኝ አቅሜ
ይክሰኛል ያልኩት
ይከፍላል ውለታ
ጭራሽ አሳመመኝ
ሰጠኝ ለበሽታ
ይቺኛዋ እንኳ የኔ ፈጠራ ውጤት አይደለችም። የሆነ ቦታ ነው የሰማኋት ወይ ከአዝማሪ ወይ ደግሞ ከእረኛ ነው የቀለብኳት። (ማን ብቻውን ይፎገራል!?) ለማንኛውም ይቺት፤
ማነው ጎበዝ ሰሪ
ማነው ጎበዝ ጠጋኝ
ኢቲቪን ሚያደርገው
እውነት እንዲያወራኝ!?
Filed under: Uncategorized
![]()