የሽግግር ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ከጁላይ 1 እስከ 3 ባሉት ቀናት በዳላስ ከተማ ይካሄዳል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ከጁላይ 1 እስከ 3 ባሉት ቀናት በዳላስ ከተማ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት እንደ ድርጅት የተቋቋመው ከጥቂት ወራት በፊት ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ከዳር ቆመው ሲቆጩ የነበሩትን ኢትዮጵውያንን፤ ከአሜሪካ፤ ከካናዳ፤ ከአውሮፓ፤ ከአፍሪካ፤ ከሰላሳ በላይ ባሉ የአካባቢ ቻፕተሮች አሰባስቦ ለማደራጀት ችሏል። ይህ ድርጅት የሚከተሉትን ዋና ዋና አላማዎች ግንባር ቀደም ያደረገ ነው፤
- ባገራችን ጉዳይ ላይ በድርጅት ዙሪያም ሆነ በግለሰብ ያለመሰልቸት የሚታገሉትን ወገኖችን፤ እንዲሁም በምንም ምክንያት ተገፍቶ በአገሩ ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፍ የተገደደውንና ነገር ግን የኢትዮጵያ ስቃይ የሚያንገበግበውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአንድ መርህ ዙሪያ ማሰባሰብ – ይህም መርህ ኢትዮጵያ ባስቸኳይ የስረዓት ለውጥ እንደሚያስፈልጋት በማመንና የሚተካው ስራዓትም የቀድሞ ስህተቶችን መድገሚያ ሳይሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያውያን ነጻነት የሚረጋገጥበት እንዲሆን ማስቻል
- በመላው አለም የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ከላይ ለተገለፀው ግብ መሳካት ሃይላችንን አስተባብረን የምንታገልበትን ስልት በተቀናጀና ዲሞክሪያሲያዊ በሆነ መንገድ መምራት
- ስርአቱ ሲገረሰስ የሽግግሩን ሂደት ፈር የያዘና የኢትዮጵያን ህዝብ እውነተኛ የስልጣን ባለቤትነት የሚያረጋገጥ እንዲሆን ማስተባበር፤ ለዚህም ህዝባዊ ውይይቶችና ቅድመ ዝግጅቶች ከአሁኑ መጀመር
- ከእንግዲህ ወዲያ በአገራችን ስልጣን ለህዝብ አገልጋዮች እንጂ ለጨቋኞች እንደማይውል አረጋግጠን ወደየምንወደው ስራዎቻችን መሰማራት
በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ከመቼውም በላይ በአደጋ ላይ ያለች በመሆኑ የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝነት ይኖረዋል። ኢትዮጵያ ከመቼውም በተለየ ድምጽ ለልጆችዋ የአድኑኝ ድምጽ እያሰማች ነው። ከዳር ቆመን ዜና በመከታተልና በየቤታችን በመወያየትና በመተቸት ብዙ ፋይዳ እንደማይኖር ተገንዝበን የተነጠቅነውን የመኖር መብት ለማስመለስ ለተግባር የምንነሳበት ጊዜ ይሆናል። ከዚህ በኋላ ምንም ሰበብ አይኖረንም – ታሪክ የመስሪያ ጊዜ አሁን ነው!!
ይህ ታላቅ መስራች ጉባአኤ የሚካሄደው ከጁላይ 1 – 3 በዳላስ ማርዮት ሆቴል ይሆናል።
አድራሻ፡
Dallas/Addison Marriott Court Yard Quorum
14901 DALLAS PARKWAY
Dallas TX, 75254
በይበልጥ ለመረዳት በድህረ ገፃችን WWW.ETNTC.ORG
በስልክ ቁጥር፡ 202-735-4262
በኢሜይል፡ [email protected] ልታገኙን ትችላላችሁ።
ኢትዮጵያን በተባበረ ድምፃችንንና ትግላችን ከአደጋ እናድናታለን! እግዚአብሔር አገራችንንና ህዝባችንን ይባርክ!