ኢጃ በና ወሬ፤ በእውቀቱ ስዩም ወደ እንግሊዝ ተሸኘ!

በዚህ ወሬ ውስጥ ተሜ ባይኖርበትም በሽኝቱ ላይ ተካፋይ ስለነበር፤ ይህንን ፎቶ ለጥፌዋለሁ!

ሰላም ወዳጄ ዛሬ ብዙ ወሬዎች ሳይኖሩኝ አይቀሩም፤ ታድያ  ከየትኛው ልጀምር!? ብዬ ሳስብ ይቺ “ኢጃ በና” ትሁን ብዬ አካፈልኳችሁ። “ኢጃ በና” ማለት ቃሉ ኦሮሚፋ ሲሆን የአይን መክፈቻ! ማለት ነው። ብዙ ጊዜ ቃሚዎች ዋናውን ጫት “ቂማህ”  ከመጀመራቸው በፊት ትንሽ ነከስ ነከስ የሚያደርጓትን አይን መክፈቻ ወይም ኢጃ በና! ይሏታል።

ተጀመረ፤

ደራሲ በውቀቱ ስዩም ትላንት በጣይቱ ሆቴል አድናቂዎቹ፣ የጥበብ ቤተሰቦች እና የተለያዩ የክብር እንግዶች በተገኙበት ሽኝት ተደርጎለታል።

በእውቀቱ እንግሊዝ የሚሄደው በለንደን ኦሎምፒክ ላይ ግጥም እንዲያቀርብ ተወዳድሮ በማሸነፉ ሲሆን ከእርሱ ጋር በርካታ ስማቸውን የማላስታውሳቸው የአለማችን ታላላቅ ፀሀፍት ስራ ይቀርባል። በተጨማሪም ፅሁፎቹ ታትመው በኢሊኮፍተር ወይም በአንዳች ነገር ከሰማይ ለህዝቡ እንደሚበተኑ ሰምቻለሁ።

ይህ ለበውቀቱ እና ለሁላችንም ታላቅ ውጤት ነው። በተለይ ደግሞ ለሞያ አጋሮቹ እና ለቀድሞ ጓደኞቹ… እልና፤ (ጓደኛው እንደነበርኩ እገልፃለሁ!) እዝች ጋ የሽሙጥ ሳቅ ሲስቁ እየታዩኝነው።

ይልቅስ በሽኝቱ ወቅት እንዲህ ሆነላችሁ፤

የደራሲያን ማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ሆዬ ንግግር ሲያደርጉ…

“ለበእውቀቱ የለንደን ጉዞ መሳካት የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን እና መንግስትን ማመስገን እወዳለሁ…! በእውቀቱ በጉዞህ የሀገሪቱን መልካም ገፅታ እንድታስተዋውቅም አደራ እልሃለሁ!” ብለው እንደ ደራሲ ሳይሆን እንደ ካድሬ አልተናገሩም መሰልዎ…!? ቆይማ አንድ ጊዜ የአርቲስት እሸቱ ጥሩነህ ንግግርን ደግሞ ልቀንጭብላችሁና ወደ በእውቄ መልስ እናሳልጣለን፤

“ይህ ልጅ ድሮ ሳውቀው ቀጫጫ ነበር አሁን ግን በጣም ወፍሯል… መጀመሪያ ያየሁት ጊዜ ኮት እንደሰጠሁት አስታውሳለሁ…!” ብለው ሌላም ሌላም ጨምሩ ሰዓሊው እሸቱ… ሲያበቁ፤ (ነገረኛ ታዳሚዎች፤   “አሁን ያቺ ኮት ለዚህ ጉዞ ያላት አስተዋፅኦ ምን ይሆን…!?” እያሉ በሆዳቸው ጠየቁ…!)

በእውቀቱም ተራው ደርሶ ዝግጅቱን እና ንግግሩን ሲያቀርብ እንዲህ አለ፤

“በመጀመሪያ አቶ ጌታቸው ባሉት አልስማማም። መንግስትም ሆነ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ምንም አላደረጉልኝምና አላመሰግናቸውም። ትብብር ያደረገለኝ የደራሲያን ማህበር መመስገን ካለበት እርሱን አመሰግናለሁ።

ሌላ… “የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ገንባ አደራ” ለተባልኩት፤ ጋሽ እሸቱ እንዳለው እውነትም በፊት በጣም ቀጫጫ ነበርኩ። አሁን ግን ወደ ውጪ ሀገር ስሄድ፤ “እነዚህ ሰዎች ምግብ አይበሉም እንዴ!?” እንዳይሉን በመስጋት ይኸው ወፍሪያለሁ!” (ታዳሚው ሆዬ በሳቅ መሞት… እኔስ ብትሉ…! እርስዎስ ብል…!?)

በውቀቱ ሲቀጥልም፤ “ጋሽ እሸቱ “ኮት ሰትቼዋለሁ” ያሉት እውነታቸውን ነው። ግን አሁንም የምሄደው ብርድ ሀገር ስለሆነ ጃኬት ይሰጡኛል!?” በማለት አርቲስት እሸቱንም ታዳሚውንም እኛ በሩቅ የሰማነውንም በሳቅ አንፈራፍሮናል!

አብዛኛውን ታዳሚ በተለይ የደራሲያን ሊቀመንበሩ አቶ ጌታቸው ካድሪያዊ ንግግር አሸማቋቸው እንደነበር ወሬ አቀባዬ ሹክ ብላኛለች!

በእውቀቱ ስዩም በዛሬው እለት ወደ ለንደን ይበራል የተባለ ሲሆን፤ መልካም ጊዜ እንዲኖረው እመኝለታለሁ!

Filed under: Uncategorized