የሰማእታቱ ደም ይጮሃል፤ የኢትዮጵያን ሪቪው ወቅታዊ ርዕሰ አንቀጽ

የሰማእታቱ ደም ይጮሃል

የኢትዮጵያን ሪቪው ወቅታዊ ርዕሰ አንቀጽ

በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። የሰማዕታቱ ደም ይጮሃል፣ የኢትዮጵያን ሪቪው ወቅታዊ ርዕሰ አንቀጽ

ግምቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ መብቱን ተጠቅሞ ወያኔን በምረጫ ያባረረበት፣ተስፋም የሰነቀበት ታሪካዊ ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ መለስ ዜናዊ እጅግ ከፈተኛ በሆነ ልዩነት መሸነፉን ሲያውቅ የብዙሃኑን ድምጽ መስረቅና ማጭበርበር ከመረጠ በሁዋላ ድምጻችን ይከበር ብለው ሰልፍ የወጡትን ዜጎች የአጋዚን ነፍሰ ገዳይ ታጣቂዎችን በማሰማራት ንጹሃን ኢትዮጵያዊያንን በጠራራ ጸሃይ ረፈረፈ። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ደግሞ በከባድ ሁኔታ አቁስሎ የተቀሩትን በብዙ ሽህ የሚቆጠሩትን እስር ቤት ወረወራቸው።

መለስ ዜናዊ የአዲስ አበባን፣ የደሴን፣ የአዋሳን፣ የአምቦን፣ የነቀምቴን፣ የድሬዳዋን፣ የአርባምንጭንና የሌሎችም የአገሪቱን ዋና ዋና ከተሞችን በንጹሃን ደም ካጨቀየና የቅንጅት መሪዎችን እስር ቤት ከቆለፈባቸው በኋላ በአጼ ሚኒሊክ ቤተመንግስት ውስጥ ተንሰራፍቶ ተቀምጦ የአጋዚን ነፍሰ በላ ቡድን አባላትን ግብር አውርዶ በአልኮል መጠጦች ይራጭ ነበር።

 በአጋዚ ጦር ጭፍጨፋ እናቶቻቸውንና አባቶቻቸውን ያጡ ልጆች፣ ባሎቻቸውን ያጡ ሚስቶች፣ እህቶቻቸውን ያጡ ወንድሞች፣ ሚስቶቻቸውን ያጡ ባሎች፣ወንድሞቻቸውን ያጡ እህቶች፣ ዘመዶች፣ ጓደኞች፣ ጎረቤቶች፣ አሁንም ድረስ እያነቡ ይገኛሉ። በዛን የጭፍጨፋ ወቅት ታክሲ ነጅዎች “የሙታን ደም ከመንገድ እስኪደርቅ ድረስ መኪናችንን አንነዳም! “ ያሉት ሲታወስ አእምሮ ያደነዘዛል። ይህ የያዝነው ወር የሰኔው ጭፍጨፋ የተደረገበት ሁልቆ መሳፍርት የሆኑ ንጹሃን ኢትዮጵያዊያን በግፍ የረገፉበት ሰባተኛ ዓመት የሚዘከርበት ወቅት ነው ።  ይህ በንጹሃን ዜጎች ላይ በወያኔ የደረሰው ጭፍጨፋ በኢትዮጵያዊያን አእምሮ ለዘመናት በከፍተኛ ሀዘንና ብሔራዊ ቁጭት ሲታወስ ይኖራል።

ያለ ህዝብ ይሁንታና ምርጫ የሚገዛው መለስ ዜናዊ አንድ ቀን ህዝባዊ መነሳሳቱ መቀጣጠሉ እንደማይቀር ስለሚያውቅ በመላው ዓለም ውስጥ በማንኛውም አገር ውስጥ ባልታየ መልኩ በግድያ ወይም በአደጋ የሞቱ ሰዎች አስከሬን የሚመረመርባቸው ሆስፒታሎችን በፖሊስ መስሪያቤቱ ቀጥተኛ ቁጥጥር ሥር አድርጎ የተቃወሙትን ገድሎ ለመቅበር እንዲያመቸው ይህንን የሚያመለክቱ መረጃዎች አፈትልከው  እንዳይወጡ ለማፈን ሴራ ሸርቧል። ሆኖም ይዋል ይደር እንጂ መለስ ዜናዊና ግበረአበሮቹ ለሰኔውና ለህዳሩ ጭፍጨፋዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በ21 ዓመት የአፈናና የአምባገነን አገዛዙ ጊዚያት ለፈጸማቸው ወንጀሎች ተይዞ ለፍርድ መቅረቡ ወይም ከህዝብ ጋር በሚያደርገው ጦርነት መጨረሻ አሸናፊ የሚሆነው ሕዝብ ስለሆነ እንደ ሊቢያው ኮሎኔል ጋዳፊ እሱም ላይ ህዝባዊ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ቅርብ እንጅ እሩቅ ኣይደለም።