ወያኔና የሴቶች መብት በኢትዮጵያ

ኢህአዴግ የሴቶች ጉዳይን በየቦታው እየደነቀረ ለራሱ እርዳታ ለማግኛነት ከመጠቀም ውጭ ለሴቶች ያደረገው ነገር አለመኖሩ ተነገረ፡፡

የዛሬው ስብሰባችን ወደፊት ለሚነሳው የህዝባዊ ንቅናቄ ማዕበል እርሾ ነው” – ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ

ይህ የተነገረው የመድረክ ሴቶች አለምአቀፍ ቀንን ባለፈው እሁድ በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ግቢ ውስጥ ባከበሩበት ወቅት ነው፡፡ በመድረክ ሴቶች በተዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም ላይ የመድረክ አባል ፓርቲዎች አባላትና አመራሮችን ጨምሮ የመኢአድ፣ የብርሀን ለአንድነትና ለዲሞክራሲ፣ የከምባታ ህዝቦች ኮንግረስ ፓርቲና የሌሎች ፓርቲዎች ተወካዮችም ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ የማርች 8 ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢና የአንድነት ፓርቲ የሴቶች ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት ወ/ሮ ላቀች ደገፋና ምክትላቸው ወ/ት ልዕልና ጉግሳ ፕሮግራሙን የመሩ ሲሆን ወ/ሮ ላቀች የመድረክ ሴቶችን በመወከል የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

ወ/ሮ ላቀች በንግግራቸው ወቅት ገዢው ፓርቲ የሴቶችን መብት አክብሮ እንደሚያስከብር ብዙ ጊዜ ቢለፍፍም በተግባር ግን ጠብ ያለ ነገር አለመኖሩን ገልፀዋል፡፡ በመቀጠል መድረክን በመወከል የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ደግሞ የመድረክ የወቅቱ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት ናቸው፡፡ አቶ ገብሩ “ኢትዮጵያ ሴቶች አሁንም ከአህያ እኩል ተጭነው የሚሄዱባት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ኢህአዴግ ሴቶችን በተመለከተ አሳሳች የሆኑ ለውጥ የሚመስሉ ነገሮችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አባባላቸውን ሲያብራሩም ሴቶች ከቀበሌ አንስቶ እስከፓርላማ ድረስ እንዲገቡ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ቢኖርም እነዚህ ሴቶች ግን ወሳኝ ድምፅ ያላቸው እንዲሆኑ አይደረግም፡፡ መብታቸውን የሚጠይቁ እንዲሆኑ ኢህአዴግ አይፈልግም፡፡ ነፃ ህሊና ያላቸውን ሴቶች ኢህአዴግ እንደማይፈልግ ማወቅ ከፈለጋችሁ በብርቱካን ላይ ያደረሰውን ተመልከቱ፡፡” ብለዋል፡፡ አቶ ገብሩ ከሰሞኑ ኢህአዴግ በሁለት የትግራይ ሴቶች ላይ የደረሰውን በደል በመጥቀስም “ለሴቶች መብት እሰራለሁ” የሚለው ከንቱ መደለያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአቶ ገብሩ የጠቀሱት ሴቶች ወ/ሮ ሀዳሽና ወ/ት ለተገብርኤል የተባሉ የትግራይ ነዋሪዎች ሲሆኑ የሴፍትነት አሰራሩ አድሏዊ መሆኑን ስለተቃወሙና መከልከላቸውን ስለገለፁ አዲስ አበባ ለአንድ ሳምንት ያህል እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡

አቶ ገብሩ በአሁኑ ወቅት ያለው የሴቶች መብት አያያዝ በ1966 ዓ.ም ከነበረው የሚያንስ መሆኑን በዛ ወቅት ሰራተኛ ሴቶች የሚከፈላቸው ደሞዝ ዝቅተኝነትን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነት እንደነበራቸውና አሁን ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያዘጋጇቸው ፕሮግራሞች ላይ እንኳን የመገኘት ነፃነት እንደሌላቸው በመግለፅ አነፃፅረዋል፡፡ አቶ ገብሩ ንግግራቸውን የቋጩት ሴቶች ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን አስፈላጊሆኖ ሲያገኙት መድረክንም መቃወም እንዲችሉ መድረክ ዲሞክራት ሊሆን እንደሚገባው በመግለፅ ነበር፡፡ ወ/ሮ ሙሉ የተባሉ የአንድነት አባል ሁለት ግጥሞችን ካቀረቡ በኋላ መድረኩን የያዙት ዶ/ር ሀይሉ አርአያ የሴቶች መብት ጥያቄ እስካሁን ያልተመለሰበት አንዱ ምክንያት ሴቶቹ ራሳቸው ጥቃቱን እየተቀበሉ በመኖራቸው መሆኑን ገልፀዉ “ሴቶች እምቢ ማለት ጀምሩ፡፡ እምቢታችሁን ደግሞ በተግባር አሳዩ” ብለዋል፡፡ ቀጣይ ግጥም አቅራቢ የነበረችው ወ/ት መስተዋት ስመኝ በግጥሞቿ ኢህአዲግ የሴቶችን መብት የሚያከብረው ቀዩን መስመር እስካላለፉ ድረስ መሆኑን አሳይታለች፡፡ ቀይ መስመር በማለት የገለፀችው የተቃውም ፖለቲካ ውስጥ መግባትን ነበር፡፡

ከተጋባዥ እንግዶች ውስጥ አንዱ የሆኑት የኦፊዴን ሊቀመንበር ዶ/ር ሞጋ ፋሪሳም “በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ሴቶች የመንግስትን መደለያ ረግጠው የመጡ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባል” ካሉ በኋላ በገዢው ፓርቲ በኩል መድረክን ለመከፋፈል በርካታ ሙከራዎች እየተደረገ ቢሆንም እኛ ግን በአዲስ መንፈስ መድረክን በመምራት ለሀገራችን ለውጥ እናመጣለን” ብለዋል፡፡ ከተጠቀሱት ተናጋሪዎች በኋላ ፅሑፍ ለማቅረብ ወደ መድረክ የመጡት የቀድሞ የህወሓት ታጋይና የአቶ ገብሩ ባለቤት የሆኑት የውብማር አስፋው ሲሆኑ ከህወሓት ምስረታ ጀምሮ የነበሩ የሴቶች ጥያቄዎችና ምላሾቻቸው ምን እንሚመስሉ አስረድተዋል፡፡ ወ/ሮ የውብማር ሴቶች በብዛት ወደተቃውሞ እንቅስቃሴ የማይገቡበት ምክንያት ያሏቸውን ከተሞክሯቸው በመነሳት አስቀምጠዋል፡፡

በህወሓት ምስረታ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት አመታት ውስጥ የታጋይ ሴቶች ማህበር ቢመሰረትም የህወሓትን አላማ ከማስፈፀም ያለፈ ሴቶችን የተመለከተ የጠራ አላማ እንዳልነበረው ገልፀው ሴቶቹ ባልጠነከረ አደረጃጀት ውስጥም ሆነው ግን መብታቸውን ይጠይቁ እንደነበር አስታውሰዋል፡ ከሚያስታውሷቸው ጥያቄዎች መሀልም በበረሀ የወሊድ መከላከያ ፒልስ እየተጠቀሙ ለመዋጋት የማይመች በመሆኑ ወንዶቹ በወሲብ ግንኙነት ወቅት ኮንዶም ይጠቀሙና ሴቶችን በስራም ያግዙ የሚል የነበረበት ሲሆን ለጥያቄዎቻቸው የህወሓት ፓሊት ቢሮ የሰጣቸው ምላሽ ያመለኩት የነበረው ህወሓት ላይ ጥያቄ ለማንሳት እንዳስገደዳቸው ገልፀዋል፡፡ ወ/ሮ የውብማር የሴቶቹን ጥያቄ ለማፈን ለሶስት ሳምንት የፈጀ ግምገማ ከመደረጉ በተጨማሪ “ፌሚኒዝምና አደጋው” የሚል ፅሑፍ ከህወሓት አመራሮች ቀርቦ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ “የታጋይ ሴቶች ማህበር አመራሮች ቁጥር ከ15 ወደ 3 እንዲቀንስ ተደርጐ ኢዲምክራሲያዊ በሆነ መንገድ ህወሓት ያልፈለጋቸውን ሴቶች ከአመራር ለማውረድ ቢሞከርም ተመልሰን ከማንፈልገው ውስጥ የነበርነው እኔና አረጋሽ በመመረጣችን የሴቶቹን መብት ወደኋላ ብለው ራሳቸው የሚፈልጉትን ሾመዋል” ያሉት ወ/ሮ የውብማር “ኢህአዴግ ከጫካ ጀምሮ ከዲሞክራሲ በላይ ማዕከላዊነትን መከተሉ የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ይመስለኛል” ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢህአዴግ ከጫካ ጀምሮ የተጠናወተው ሁሉን ነገር የመቆጣጠር አባዜ ዛሬም ቀጥሎ ነፃ የሴት ማህበራት እንዳይኖሩ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ የውብማር ኢህአዴግ ለሴቶች የሚሰጣቸው የሀላፊነት ቦታዎች የሴቶች ጉዳይ፣ ቱሪዝም፣ ማህበራዊ ጉዳይና የመሳሰሉት አይነቶች መሆናቸውን ጠቅሰው በምንም አይነት እንደመከላከያና ፋይናንስ የመሳሰሉትን ለሴቶች እንደማይለቅ አስረድተዋል፡፡ ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል በተደጋጋሚ የሚቀርበው ምክንያት ሴቶች ትምህርትና ልምድ የሚያንሳቸው መሆኑ ቢሆንም ይሄ ግን ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ምክንያት መሆኑን “ዕድሉ ተሰጥቶን እስኪ እንሞክር” በማለት አስረድተዋል፡፡

በፓርላማ ያለውን የሴቶች ውክልና በተመለከተም “አሁን ካሉት ሶስት እጥፍ ያህል እንዲገቡ ቢደረግ እንኳ ኢህአዲግ ባለው ባህሪ ሴቶቹ የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም” ብለዋል በመጨረሻም ወ/ሮ የውብማር ይህንን ጨቋኝ አሰራር ለመለወጥ የኢትዮጵያ ሴቶች በሙሉ ልዩነቶቻቸው ሳያግዷቸው ነፃ ማህበር በመመስረት እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከወ/ሮ የውብማር ቀጥሎ ንግግር ያደረጉት የብርሃን ለአንድነት ለዲሞክራሲ ፓርቲ ተወካይ አቶ ዳምጠው አለማየሁም ከሳቸው በፊት በቀረበው ሀሳብ ሙሉ በሙሉ እንደሚስማሙ አመልክተው በዚህ ወቅት የሴቶችን ጨምሮ አንድም ነፃ ማህበር እንዳይኖር ገዢው ፓርቲ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ የፕሮግራም መርሀ ግብር መሰረት ቀጥሎ በመድረክ ሴቶች የተዘጋጀ ድፎ ዳቦ ለጨረታ ቀርቦ አቶ ደረጄ ተስፋዬ በ2000 ብር ያሸነፈ ሲሆን ዳቦውን የቀድሞ የኦፌዴን ሊቀመንበር ቡልቻ ደመቅሳ እንዲቆርሱት ጠይቀዋል፡፡ በዚሁ መሠረት አቶ ቡልቻ ጨረታውን ካሸነፈው ወጣት ጋር ሆነው ዳቦ ሲቆርሱ በቴዲ አፍሮ “አልሞላውም ኪሴን” በተሰኘው አዲሱ ነጠላ ዜማና በሕዝቡ ጭብጨባ ታጅበው ነበር፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የዕለቱ የክብር እንግዳ ገጣሚና ኢንተርፕሪነር ሙሉ ሰለሞን ወደመድረኩ ቀርበው ጊዜ ከተሰኘ የግጥም መድብላቸው የተለያዩ ግጥሞቻቸውን በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በእንግሊዝኛ ያቀረቡ ሲሆን የሕይወት ልምዳቸውንም ለታዳሚው አካፍለዋል፡፡ ኢንተርፕሪነሯ የሰላም አምባሳደር በመሆናቸው ፖለቲካ ማውራት እንደማይችሉ ከገለፁ በኋላ “ስለምንም ባወራ ፖለቲካ መሆኑ አይቀርም” በማለት ቅኔ የተላበሱ ፖለቲካዊ መልዕክቶችን ተናግረዋል፡፡ ታዳሚውን “ለመብት መከራከር ጥሩ ነው ግድ የላችሁም ዋጋ ያሰከፍላል ግን ማቆም የለባችሁም” በማለትም መክረዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የሚመራቸው ፓርቲዎች አባላትን ማዳመጥ እንዳለባቸው አለበለዚያ የትም እንደማይደርሱ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አመራሮቹ ለረጅም ጊዜ ወንበር ይዘው ከመቀመጥ ይልቅ ለተተኪ ማስረከብ እንዳለባቸው የራሳቸውን ተሞክሮዎች በመዘርዘር አስረድተዋል፡፡ ወ/ሮ ሙሉ የሰው ልጅ ያመነበትን ነገር ከመናገር እና ከማድረግ ወደኋላ ማለት እንደሌለበት ከተናገሩ በኋላ “እኔ የትም ቦታ እንዲሁ ነኝ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተለያዩ ስብሰባዎች እንገናኛለን እዛም የመሰለኝን ከመናገር አላፈገፍግም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እብድ ነች ብለው የተውኝ ይመስለኛል፡፡” በማለት ታዳሚውን አዝናንተዋል፡፡ ከወ/ሮ ሙሉ በመቀጠል መድረኩን የተረከቡት አቶ ገብሩ ገብረማርያም በፓርላማ ቆይታቸው 30 ፐርሰንት የሴቶች ውክልና በመኖሩ ኢህአዴግ ሲኩራራ እንደነበር ገልፀው በ5 ዓመት ውስጥ የተናገሩት ሴቶች ቢደመሩም ከ5 እንደማይበልጡ አስታውሰዋል፡፡ ከእሳቸው በመቀጠል የግጥም ስራዎቿን ያቀረበችው በፓርላማ ውስጥ ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነው የአቶ ግርማ ሰይፉ እህት ወ/ሪት ጥሩዘር ሰይፉ ስትሆን “ዛሬ በሕይወቴ ላይ እጥፍ እድሜ የጨመርኩ ያህል ተሰምቶኛል” በማለት በፕሮግራሙ ላይ ከተገኙት ታላላቅ ሰዎች ጋር አብራ በመታደሟ የተሰማትን የደስታ ስሜት ገልፃለች፡፡ ጥሩዘር “ፖለቲካ ብቻ” በተሰኘ ግጥሟ አማካይነት ኢህአዴጋውያን ከ20 ዓመት በፊት ወደ ስልጣን ሲመጡ ለኢትዮጵያውያን የገቡት የኑሮ መሻሻል የተመለከተ ተስፋ አስታውሳ የተሻሻለው ግን የኢህአዲጋውያኑ ኑሮ እንጂ ሰፊው ሕዝብ በባሰ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ገልፃለች፡፡

ከእርሷ ቀጥሎ ወደ መድረኩ የመጡት አቶ ስዬ “ሕወሓት ሴቶችን መበደሉን ስትሰሙ መቼም ወደአእምሯአችሁ የመጣነው እኔ እና አቶ ገብሩ ነን አይደል?” ካሉ በኋላ “አዎ አብረን ብዙ ለፍተናል ብዙም አጥፍተናል” ብለዋል፡፡ አቶ ስዬ በ1993 ዓ.ም በተፈጠረው የሕወሓት ክፍፍል በመለስ ዜናዊ ሲባረሩ ወ/ሮ የውብማር “እንደዚህ አልነበር ስታደርጉ የነበረው ይኸው በእናንተም ደረሰ” እንዳሏቸው አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ግን አብረው የኢሕአዴግን ስርዓት ለመጣል እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የመድረክ ሴቶችንም “የማንገናኝ አይነት ሰዎች የነበርነውን ሁሉ ሀረግ በመሆን እየሰበሰቡን ነው፡፡” ካሉ በኋላ የሴቶች መብት መከበር ዋስትና በራሳቸው በሴቶቹ እጅ መሆኑን በመግለፅ መበርታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ከአቶ ስዬ በመቀጠል የመድረክ ሴቶች “ምን ይመክሩናል” በሚል የጋበዟቸው የከንባታ ሕዝቦች ኮንግረስ ፓርቲ ተወካይ አቶ ኤርጫፎ ኤርዴሎ የአፄ ቴዎድሮስ ባለቤት እቴጌ ተዋበችን እና የአፄ ሚኒሊክን ባለቤት እቴጌ ጣይቱን በማስታወስ የእነዚህ ሴቶች ምክር ለሀገር የነበረውን አስተዋፅኦ ከዘረዘሩ በኋላ “እንደውም ልትመክሩን የሚገባ እናንተ ናችሁ” ብለዋል፡፡ አቶ ኤርጫፎ ኢሕአዴግ ሴቶች ያለባቸውን የኢኮኖሚ ችግር በመጠቀም በሴፍቲኔት ዱቄት በመስፈር በመብታቸው እንዲደራደሩ እየሞከረ በመሆኑ የመድረክ ሴቶች ይሄንን መታገል እንዳሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

በመቀጠል መድረኩን የያዘው የአንድነት ፓርቲ ፀሀፊ አቶ አንዱአለም አራጌ ኢህአዴግ ሴቶች ወደተቃውሞ ፖለቲካው እንዳይገቡና ልጆቻቸውንም እንዲከለክሉ በተለያየ መንገድ እያስፈራራቸው መሆኑን ገልጿል፡፡ ለዚህም በምሳሌነት ባለፈው አመት በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ እሱና ታናሽ ወንድሙ ተወዳዳሪዎች እንደነበሩ ገልፆ የኢህአዴግ ካድሬዎች እናቱጋ በመሄድ ልጆቻቸውን እንዲከላከሉ አለበለዚያ ረሽነው ሬሳቸውን እንደሚያመጡላቸው በመንገር ለማስፈራራት እንደሞከሩ አስታውሶ እናቱ የሰጡት ምላሽ ግን ምንጊዜም እንደሚያኮራዉ ተናግሯል፡፡ የአቶ አንዱአለም እናት ካድሬዎቹን የመለሷቸው “የኔን ልጆች የምታገኟቸው ሲሰርቁ ሳይሆን ለመብታቸው ሲከራከሩ ነው፡፡ ግደሉና ሬሳቸውን አምጡልኝ ከወገን ከሀገር ጋር በክብር ይቀበራሉ” በማለት ነበር፡፡ አቶ አንዱአለም የሴቶችን እምቅ ሀይል “እንደአባይና እንደአዋሽ ለዘመናት በትውልድ መሀከል ዝም ብሎ የሚፈስ ያልተጠቀምንብት ጅረት” በማለት ገልፆታል፡፡ በዕለቱ ንግግር ካደረጉት መሀል የአንድነት የወጣቶች ጉዳይ ተወካይም የሚገኝበት ሲሆን በስራ አስፈፃሚ ውስጥ ያለው የሴቶች ቁጥር መሻሻል ላይ አንድነት አጥብቆ እንዲያስብበት ጠይቋል፡፡ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የአንድነት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ነጋሶ ጊዳዳ ሲሆኑ እምባ እየተናነቃቸው የወ/ት ብርቱካንን “ቅንጅት መንፈስ ነው” የተሰኘ ንግግር አስታውሰው “ሰው ነፃነት ሲኖረው እንዲህ አይነት ጉልበታም ንግግር ያደርጋል፡፡ የጠፋው ይሄ ነፃነት ነው የዛሬው ስብሰባችን ግን ያለንበትን ድባብ የሚገፍና ወደፊት ለሚነሳው የህዝባዊ ንቅናቅ ማዕበል እርሾ ነው” ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ከህዝቡ ለቀረበው አንድ ግጥም በገጣሚ ሙሉ ይደገምልን ጥያቄ ገጣሚዋ ቡና የተሰኝ ጭቆናን እምቢ ማለትን የሚያወሳ ግጥም አቅርበዋል፡፡ ግጥሙ ቡና ሁሌ እየተቆላና እየተወቀጠ ከሚኖር አብሮት ከሚቃጠለው ውሀ ጋር ተባብሮ በመገንፈል እሳቱን ለማጥፋት ምክክር እንዲጀምሩ የሚያሳስብ ቅኔያዊ መልዕክት ያለው ነው፡፡