አየሁ ያመሳክራል፤ ሰማሁ ያከራክራል – አደፍርስ ተሰማ

በዘመነ ወያኔ የማይሰማ ነገር የለም። ይበልጡ ወሬ እውን ሲሆን ቀሪው ደግም የፈጠራ (የይድረስልኝ) ነፋስ ነው። አንድ ነገር ግን አያከራክርም። ወያኔ ለኢትዮጵያ ህዝብ፤ አንድነትና ዳር ድንበር እንደማይገደው ገና ከመሰረቱ ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ በበረሃ እያሉ የታወቀ እንጂ የከተማ አለቆች ሆነው ድራፍት ቢራ እየጠጡ ጫት መቃም ከጀመሩ ወዲህ የታያቸው እይታ አይደለም። የወያኔ የፓለቲካ ንስሃ አባት አቦይ ስብሃት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚሰብኩልን ስለ ኤርትራ ነጻነት እንጂ ከቁራሽ ስለተረፈችው ውድ ሃገራችን አይደለም። እንደ እኔማ ቢሆን አቦይ ስብሃትን ወደ አስመራ ሄደው እንዲኖሩና የሻቢያ ቃል አቀባይ እንዲሆኑ እመኝ ነበር። ለሃገራችን የማይመቹ ጠማማ ፓለቲከኛ ናቸውና! ለነገሩ ከወይዘሮ አዜብ ጋር ሆድና ጀርባ ሆነዋልና እስዋ ታገላግለን ይሆናል።
ወያኔ ትላንትም ወንበዴ ነበር። ዛሬም ወንበዴ ነው። ትላንት የትግራይን ህዝብ ነጻ እናወጣለን እያሉ ሱቅ ከፍተው ነግደውበታል። አእላፍ የትግራይ ልጆች በግፍ ተገድለዋል። በፓርቲ ሚስጥር ተደብቆ የተያዘውን ዛሬ በወያኔ ውስጥ የነበሩ የግፉ ተሳታፊዎችና የዓይን ምስክሮች ከድርጅቱ ሚስጥር እያወሩን ነው። አንዳንዶቹ ግማሹን ደብቀው ሲያጫውቱን፡ ሌሎች ደግሞ በእውነት የሆነውንና የሚያውቁትን አስረድተውናል። ያ የበረሃ ታሪካቸው ነው። ዛሬስ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ስለሚሰሩት ግፍ ማን ይንገረን?
በዘርና በጎሳ አጥር ተከልሎ ሃበሳውን የሚቆጥረው ህዝባችን ኡኡታ ማሰማት ከጀመረ ቆየ። በዚህ ህዝብ ላይ ግፍ የሚያደርሱትን መሰሪ ሰዎች ስም ዝርዝርና የሚሰሩትን ግፍ ለይቶ ከመረጃ ጋር ማስቀመጥ ተገቢ ነው። የሃገራችን ተረት “አይነጋ መስሎት ደሮ ቆጥ ላይ … “ እንደሚሉት ነው። የዛሬ አለቆቻችን ፍርድ የሚቀርቡበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ይሁን እንጂ በዓይን ምስክር፤ በድምጽ፤ በቪዲዬ ወዘተ… ያልተደገፈ መረጃ ጠቃሚነት የለውም። ዛሬ ዓለማችን በዙ የስለላ መረቦችን በቀላሉ ማጠላለፍን እያሰተማረችን
ነው። አያሌ በልሃቶች አሉ መረጃ ለማሰባሰብ። ዝም ብሎ እከሌ ይህን አለ ያ ይህን ደገመ ማለቱ ለክርክር እንጂ ፍርድ ላይ እግር ኖሮት የሚቆም የክስ ስሌት አይሆንም። መቆም የሚችለው ሰማሁን ትተን አየንን ማመሳከር ስንችል ብቻ ነው። ስለዚህ የወሬ ማናፈሻ ባዶ ጆንያ ከመሆን ይልቅ። የወሬውን ምንጭ ተገን አርጎ በመመራመር መሰረቱን ማወቅ አስፈላጊ ነው።
አደፍርስ ተሰማ