አንድ ብሶት፤ በእውኑ እኔ ማነኝ ፌስ ቡኬስ ምንድነው!? (አቤ ቶኪቻው)
ሰላም ወዳጄ እንዴት አደሩልኝ! እሰይ ሰላምዎ ይብዛልኝ አዳርዎም ሆነ ትዳርዎ ሳንካ አይግጠመው!
ዛሬ በጠዋት አንድ ወዳጄ መለዕክት ሰዶልኝ ነበር። መጀመሪያ አንዳንድ ልማታዊ ዜናዎችን ነገረኝ። ከነዚህም ውስጥ “አንበሳ አውቶቢስ መሻሻሉን፣ ወደ አስር በሚጠጉ “ባሶች” ላይ ተስረቅራቂ ድምፆችን አስገጥሞ ፌርማታዎቹ የሚገኙበትን ቦታ የሚያስከፍለው ክፍያ እና የመሳሰሉትን መረጃዎች ማቀበል ጀምሯል” የሚለው ይገኝበታል። “የመሳሰሉት መረጃዎች” የሚለውን ስገምት፤ “ሃገራችን እያስመዘገበች ያለችው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ በፀረ ሰላም ሀይሎች ሟርት እንደማይገታ፣ ለሚሊኒየሙ ግድብ ከደሞዝ ማስቆረጥ የአውቶብስ ትኬት የማስቆረጥ ያህል ቀላል መሆኑን” እና ሌሎችም ልማታዊ መረጃዎች ይመሰሉኛል። በእውነቱ ይሄ የሚበረታታ እድገት ነው።
ይህንን እያደነቅሁ የወዳጄን መልዕክት ዝቅ ብዬ ተመለከትኩ፤ “ፎርቹን የተባለው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ዘንድሮም ደቡብ ክልል ላይ ረሃብ አደጋ እያደረሰ መሆኑን የሚጠቁም ዜና ይዞ ወጥቷል።” ይላል። እንዴት ነው ነገሩ ከዚህ በኋላ ረሀብ የሚባል ወደ ኢትዮጵያ ምድር ድርሽ እንዳይል አድርገነዋል ተብሎ ሲነገር አልነበረም እንዴ…!? ለነገሩ የመንግስት ኢትዮጵያ እና የእኛ ኢትዮጵያ ለየቅል መሆናቸውን ቀስ በቀስ በቅጡ እየተረዳን ነው!
ጉደኛው ወዳጄ ካስቀመጠልኝ መልዕክቶች ውስጥ ሌላው ደግሞ፤ “ፌስ ቡክ ፕሮፋይልህን እንዳናየው ተከልክለናል!” የሚል ነው። አሁን በጣም ተደነቅሁ…
በእውኑ እኔ ማነኝ? ፌስ ቡኬስ ምንድነው? ስል ጠየቅሁ! እውነቱን ለመናገር ባለስልጣኖቻችን የለየለት “ፉገራ” ጀምረዋል። አረ ጎበዝ ባለስልጣን ስራ እንጂ ፉገራ አያምርበትም! አሁን አሁን ሳስበው ኢንሳ ውስጥ በግል የተጣላኝ ሰው ይኖራል እንጂ፤ መንግስትን ያህል ተቋም በዚህ ደረጃ እንደ ወገብ ቅማል ጠምዶ ይይዘናል ብዬ አላስብም። ለዚህ ግለሰብ፤ “ፍሬንድ” ችግር አለ እንዴ ምነው እንዲህ ጠመድከኝ አረ “አፉ” በለኝ! ብዬ በማን በኩል እንደምልክለት ግራ ገባኝኮ!
ልብ አድርጉልኝ 1፤ ብሎጌ ተዘጋ እሺ ለልማቱ ካልጠቀመ እና መንግስት ካላመነበት ጥርቅም ይበል ብዬ ተደሰትኩ።
ልብ አድርጉልኝ 2፤ በመፅሀፌ ስም የተሰየመው “የአቤ ቶኪቻው ሽሙጦች” የተባለው የፌስ ቡክ ግሩፕ ተዘጋ “መቼስ ማል ጎደኒ” ብዬ ዝም አልኩ!
ልብ አድርጉልኝ 3፤ የገዛ ፌስ ቡኬ ከወዳጆቼ ጋር የማወጋበት፤ ሰዎች ጎራ ብለው “ፕሮፋይሌን” ማየት እንዳይችሉ ተደረገ። እንግዲህ ምን ልበል…? የገዛ ጓዳዬ ቁልፍ በመንግስት እጅ ከሆነ ምን ይባላል!?
ግን የምር እኔ ማን መስያቸው ነው? “ፍሬንዶቼ” እኔኮ ያ ወገኛው ሰውዬ ነኝ! ምነው እንኳ “ቀፈፈኝ” ብዬ ከሀገር የወጣሁ ግዜ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “አንድ የደህንነት ሰው አስፈራራኝ ብሎ እንዴት ከሀገር ይወጣል? አቤ ወይ ጅል ነው ወይ ደግሞ ልጅ ነው! ማለት ነው” ብላችሁ የፎተታችሁኝ! እ… እሱ እኮ ነኝ። ታድያ ለኔ ለምስኪኑ ይሄ ሁሉ ዱላ ተገቢ ነው?
ደሞስ ምን አጠፋሁ!? በመከርኩ…? በዘከርኩ…? የምሬን ነው የምለው ወዳጄ ሌላ ሰው መስያቸው ነው እንጂ እኔን እንደዚህ አይጨክኑብኝም “የወገን ጦር ነንኮ!” አለ ዘላለም ማልኮም ክብረት! “እኛም አልተባልን!” አልኩኝ እኔ!
ለማንኛውም ዛሬ ፎቶዬንም አብሬ ለጥፌዋለሁ! ውድ “ዘጊዎች” ስታዩኝ “እ… አንተማ የኛው ነህ!” ብለችሁ የተዘጉ በሮቼን እንደምትከፍቱልኝ ተስፋ አደርጋለሁ። አለበለዛ በአካል መጥቼ ለማመልከት እገደዳለሁ! (አትሳቁ የምሬን ነው!)
Filed under: Uncategorized
![]()