የምግብ ዋስትና አለም አቀፍ ስብሰባ፤ ጠቃሚነቱ ለኢትዮጵያዊያን ነውን?
ክፍል፡ አራት
ዶ/ር አክሎግ ቢራራ
ዛሬ፡ ሃገራችን፡ ኢትዮጵያ፤ የምትታወቅበት፡ አበይት፡ መለኪያ፡ የነጻነት፡ መዲና፤ የመላው፡ ጥቁር፡ ህዝቦች፡ የነጻነት፡ መኩሪያ፤ የአፍሪካ፡ አንድነት፡ ማህበር፡ ዋና፡ መናገሻ፤ የክርስቲያንና፡ የእስልምና፡ ተከታዮች፡ በሰላም፡ መኖሪያ፡ ሳይሆን፡ ህወሓት፡ ሆነ፡ ብሎ፡ በዘር፡ የከፋፈላት፤ የህግ፡ የበላይነት፡ የሌለባት፤ከአስር፡ እስከ፡ አስራ-ሶስት፡ ሚሊዮን፡ የሚሆኑ፡ ኢትዮጵያዊያን፡ በለጋስ፡ ሃብታም አገሮች፡ የሚመገቡባት፡ መሆኗ፤ ለም፡ መሬቷና፡ ወንዞቿ፡ በልማት፡ ስም፡ በሳንቲም፡ የሚሸጡባት፤ እስከ፡ ዘጠና-ዘጠኝ፡ አመታት፤ ለውጭ፡ መንግስታትና፡ ሃብታሞች፤ ለተወሰኑ፡ ታማኝ፡ የሆኑ፡የትግራይ፡ ተወላጆች፤ የሚቸረቸሩባት፡ አገር፡ መሆኗ፡ ነው። ህወሓትና፡ ደጋፊወቹ፡ ይህን፡ ሃቅ፡ ይክዳሉ። እንዲያውም፡ የገጠር፡ እኮኖሚው፡ አስደናቂ፡ መዋቅራዊ፡ ለውጥ፡ አሳይቷል፤ የገጠር፡ ሚሊየነሮች፡ ተፈጥረዋል፡ ይላሉ። እነሱ፡ በሚሉትና፡ በአብዛኛው፡ ህዝብ፡ ያለው፡ አመለካከት፡ ሊገናኝ፡ አልቻለም። የህወሓት፡ ባለስልጣኖች፤ “በሬ፡ ወለደ፡ ብሎው፡” እኛን፡ ብቻ፡ ሳይሆን፡ አለምን፡ ለማሳመን፡ ይሞክራሉ። ለታዛቢወች፡ አስደናቂ፡የሆነው፡ ህወሓት፡ አመኔታ፡ የሌላቸውን፡ ማስረጃወች፡ እንደ፡ እውነት፡ ማቅረቡ፡ ሳይሆን፡ ሌሎቻን፡ ማመናችን፡ ነው። ለምሳሌ፡ እድገቱ፡ ፍትሃዊ፡ ነው፡ ሲሉን፤ ዲሞክራሲ፡ አለ፡ ሲሉን፤ እርሃቭ፡ የለም፡ ሲሉን፡ ያለ፡ ጥያቂ፡ እንቀበላለን። ድሃው፡ ህዝብ፡ የሚያየውን፡ እኛ፡ አናይም። ድህነት፡ እየጠፋ፡ ነው፡ ሲሉን፡ እንቀበላለን። ድህነት፡ ከጠፋ፡ ለምን፡ እንሰደዳደለን፡ ብለን፡ አንጠይቅም። አገራችን፡ ከምርጫ፡ ዘጠና፡ ሰባት፡ በኋላ፡ አስራ፡ አንድ፡ በመቶ፡ አድጋለች፡ ከተባለ፡ ይህ፡ እድገት፡ የአብዛኛውን፡ ህዝብ፡ ኑሮ፡ እንዴት፡ አለወጠውም፡ ብለን፡ ስንጠይቅ፡ ህወሓትና፡ ደጋፊወቹ፡ ለውጦታል፡ ይላሉ። እኛም፡ ይህ፡ እውነት፡ እንደሆነ፡ የብልጭልጭ፡ እድገቱን (ቪላ፣ ህንጻ፤ መንገድ፡ ወዘተ፡ መሰራቱን) እንደ፡ ፍትሃዊ፡ ልማት፡ ማየታችን፡ ቀጥሏል። ለዚህ፡ ነው፤ ዛሬ፡ በኢትዮጵያ፡ ውሸቱንና፡ እውነቱን፡ ለመለየት፡ አይቻልም፡ ለማለት፡ የሚያስደፍረው።
እድገቱ፡ ማንን፡ ጠቀመ? ማን፡ ሃብት፡ እያካበተ፡ ነው?
የእድገቱ፡ ውጤት፡ ለማን፡ ጠቃሚ፤ ለማን፡ ጎጂ፤ መሆኑን፡ ለማየት፡ የተራውን፡ ህዝብ፡ ኑሮ፡ ማየቱ፡ ብቻ፡ ይበቃል። የዋጋ፡ ግፍሸት፡ ጥሩ፡ ኑሮ፡ ይኖሩ፡ የነበሩትን፤ ወደ፡ ድህነት፡ እየመራ፡ ነው። ሌላው፡ የዛሬይቱ፡ ኢትዮጵያ፡ መገለጫ፡ ፍትህ፤ ነጻነት፤ የህግ፡ የበላይነት፤ የህዝብ፡ ድምጽና፡ ተሳትፎ፡ የሌለባት፤ በአንድ፡ ጠባብና፡ ትምክህተኛ፡ የንኡስ፡ ብሄርተኛ፡ የበላይነት፡ የሚመራ፡ ፓርቲ፡ የሚገዛት፤ ለሃያ፡ አንድ፡ አመታት፡ ጠቅላይ፡ ሚኒስትሯ፡ መለስ፡ ዜናዊ፡ የተባሉ፡ አምባ፡ ገነን፡ እንደ፡ ቤታቸው፡ የሚያዙባት፡ አገር፡ መሆኗ፡ ነው። የችግሩ፡ እምብርት፡ ይህ፡ ነው። መለስ፤ ይህንም፡ እንደ፡ ሌለ፡ ይነግሩናል። የማይቀበሉት፤ ኢትዮጵያ፡ እድገት፡ እየታየ፡ ድህነት፡ የሚሰፋባት፤ የእርሻ፡ እድገት፡ አለ፡ እየተባለ፤ እርሃቭ፡ በጥልቀት፡ የሚታይባት፡ አገር፡ መሆኗን፡ ነው። ሌላም፡ የማይቀበሉት፡ አበይት፡ ጉዳይ፡ አለ። የህወሓት፡ መንግስት፡ በተከታታይ፡ ምርጫን፡ በግድም፡ ሆነ፡ በውድ፡ አሸንፋለሁ፡ ብሎ፡ ሲነሳ፡ በኢኮኖሚው፡ በኩል፡ ውጤት፡ ማሳዩት፡ እንዳለበት፡ የተገነዘበው፡ ከምርጫ፡ ዘጠና፡ ሰባት፡ በኋላ፡ መሆኑን፡ የሚያሳዩ፡ ማስረጃወች፡ አንዳፈር፡ ናችው። ክዚያ፡ በፊት፡ በመዋእለ፡ ንዋይ፡ መልክ፡ በብዙ፡ ቢሊየን፡ ብር፡ የፈሰሰው፡ ክልል፡ አንድ፤ ትግራይ፡ ነበር። ይህ፡ የማያዋጣ፡ መሆኑን፡ የተረዳው፡ አመራር፡ መሰረተ፡ ልማት፡ ያሰፋፋው፡ ከምርጫ፡ ዘጠና፡ ሰባት፡ በኋላ፡ ነው። የዚህን፡ አዲስ፡ አቅጣጫ፡ ጥቅም፡ ቢያንስ፡ ከሁለት፡ ጎኖች፡ እንየው። አንዱ፡ ስልጣንን፡ ለማቆየት። ሌላው፡ ሃቭትን፡ አገር፡ አቀፍ፡ በሆነ፡ መንገድ፡ ለገዡ፡ ፓርቲና፡ ለደጋፊወች፡ ለማስፋፋት፡ ነው። ይህ፡ ደግሞ፡ ለይስሙላም፡ ቢሆን፡ ሌሎችን፡ ማቀፍ፡ ነበረበት። ከታቀፉት፡ መካከል፡ በግልጽ፡ የሚታየው፡ የውጭ፡ ባለ፡ ሃብቶችና፡ ምርጥ፤ ታማኝ፤ የትግራይ፡ አዲስ፡ ሃብታሞች፡ አገር፡ አቀፍ፡ ሚና፡ ማግኘታቸው፤ ከመንግስት፡ ጥበቃ፡ መጎናጸፋቸው፡ ነው። የጥቅም፡ ሰንሰለት፡ እየጠነከረ፡ የሄደው፡ ለዚህ፡ ነው።ይህ፡ ሰንሰለት፤ ህወሓት፡ በሚፈልገው፡ ደርጃ፡ የሚያስተጋቡ፡ ተጠቃሚወችን፡ አስፍፍቷል። ይህ፡ የመሰረተ፡ ልማት፡ መስፋፋት፡ ግን፡ መዋቅራዊ፡ ለውጥ፡ አላመጣም። ግብርናን፡ እንይ።
የእርሻ፡ እድገት፡ አስደናቂ፡ ነው፡ በሚባልባት፡ ኢትዮጵያ፤ ባለፈው፡ አመት፡ ህወሓት፤ ስምንት፡ ሚሊዮን፡ ቶን፡ እህል፡ ሸምቷል። ህወሓትና፡ ደጋፊወች፡ ይህን፡ የሽመታ፡ ጥገኝነት፤ ይክዳሉ፤ ወይንም፡ መግለጫ፡ ይሰጡበታል። የሚሉት፤ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ እድገትንና፡ ዲሞክራሲን፡ ከተጎናጸፈ፡ ቆይቷል፡ ነው። ቢያንስ፤ እየተጎናጸፈ፡ ነው። አቅርቦት፡ ከፍላጎት፡(supply and demand) ጋር፡ የማይስማሙት፡ ህዝብ፡ እየጨመረ፤ ፍሎጎት፡ እያደገ፡ ስለሄደ፡ ነው፡ ይላሉ። መለስ፡ ክፍተቱንና፡ የዋጋ፡ ግፍሸትን፡ የእድገት፡ ምልክት፡ ነው፡ ይላሉ። በእድግትና፡ የውጭ፡ እርዳታ፡ ሲታይ፤ ኢትዮጵያ፡ በአመት፡ አራት፡ ቢሊየን፡ ዶላር፡ ታገኛለች። ስለሆነም፤ በመሰረተ፡ ልማትና፡ በፍጆት፡ ላይ፡ የፈሰሰው፡ መዋእለ፡ ንዋይ፡ የተመሰረተ፡ እድገት፡ መኖሩ፡ አያስደንቅም፤ ባይኖር፡ ያስደንቅ፡ ነበር። ቁም፡ ነገሩ፤ የእድገቱ፡ ውጤት፡ የሚያሳየው፡ ፍትሃዊ፤ ተሳትፏዊ፡ አለምሆኑን፡ ነው። የቁጥጥር፡ ፖለቲካው፡ የቁጥጥር፡ ኢኮኖሚን፡ ወልዷል፡ ለማለት፡ ይቻላል። የተወለደው፡ የምጣኔ፡ ሃብት፡ የሚያደላው፡ ለፈጠረው፡ ህወሓትና፡ ለደጋፊወቹ፡ ስለሆነ፡ ፍትሃዊ፡ ለመሆን፡ አይችልም። አብዛኛው፡ የእርዳታ፡ ገንዘብ፡ ይሰረቃል፤ ከሃገር፡ ህገወጥ፡ በሆነ፡ መንገድ፡ ይወጣል። Global Financial Integrity እንዳሳየው፡ በ2000-2008: ብቻ፡ 12 ቢሊዮን፡ ዶላር፡ ተሰርቋል። ቢያንስ፡ በአመት፡ ሶስት፡ ቢሊየን፡ ዶላር፡ ከአገር፡ ይውጣል። በንጥር፡ (Net inflow) ሲታይ፤ እርዳታውና፡ ወደ፡ ውጭ፡ የሚላከው፡ የእቃ፡ ገቪ፡ በሙሉ፡ ይሰረቃል፡ ማለት፡ ነው። ስርቆቱና፡ ሙስናው፡ ቢኖር፡ ባይኖር፤ እርዳታ፡ ያለ፡ ህዝብ፡ ተሳትፎ፤ ያለ፡ ቁጥጥር፤ ያለ፡ ሕግ፡ አገርን፡ ለማልማት፡ አይችልም። ቢችል፡ ኖሮ፤ የአለም፡ ለጋሽ፡ አገሮች፡መለማመጃ፡ የሆነች፡ ኢትዮጵያ፡ አሁን፡ እንደ፡ ምስራቅ፡ ኤዥያ፡ ድንቅ፡ አገሮች፡ መሆን፡ በቻለች፡ ነበር። የሚታየው፡ ሃቅ፡ ግን፤ የውጭ፡ እርዳታ፡ ሙስናን፤ ስርቆትን፤ የሃብት፡ ሽሽትን፤ ኪራይ፡ ሰብሳቢነትን፤ የሃብት፡ ክምችን (concentration of incomes and assets)፤ ጥገኝነትን፡ አጠንክሯል። ተከታታይ፡ ሙስና፤ ስርቆት፤ አድሎ፤ ጥገኝነት፡ የእድገት፡ ምልክት፡ አይደለም። ከጥቅሙ፡ ጉዳቱ፡ ያመዝናል፡፡በኢኮኖሚው፡ በኩል፡ ሲታይ፤ የመለስ፡ መንግስት፡ ያመጣው፡በደል፡ ሙስና፤ ኪራይ፡ ሰብሳቢነት፤ ስርቆት፤ጥገኝነት፤ የመንግስትን፡ ሃብት፡ ወደ፡ ፓርቲው፡ ባለስልጣኖች፡ ምርጥ፡ ግለሰቦች፡ ማዘዋወር፤ ነው። ይህን፡ የአገዛዝ፡ በደል፡ አብዛኛው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ያውቀዋል። እድገት፡ አለ፡ ብለው፤ የሚያመሰግኑት፡ ተጠቃሚወች፡ ናችው። ለጋስ፡ የሆኑ፡ የውጭ፡ መንግስታትና፤ አበዳሪ፡ ድርጂቶችም፡ እድገት፡ አለ፡ ብለው፡ ሲናገሩ፡ ማስረጃውን፡ የሚያገኙት፡ ክህወሓት፡ ነው። ተጠቃሚወች፡ በመሆናችው፤ ለጠፋው፡ ገንዘብ፡ ተጠያቂ፡ እንዳይሆኑ፤ ታክስ፡ የሚከፍለው፡ ህዝባቸው፡ እርዳታ፡ ጥቅም፡ አለው፡ ብሎ፡ እንዲቀበል፡ ጭምር፡ ሙከራ፡ በማድረግ፡ ነው። የቱኒሲያና፡ የግብጽ፡ አመጽ፡ በተካሄደበት፡ ወቅት፡ አለም፡ ባንክና፡ አይ፡ ኤም፡ ኤፍ፡ በእነዚህ፡ አገሮች፡ እድገት፡ አለ፡ ይሉ፡ ነበር። ፍትሃዊ፡ እድገት፡ ቢኖር፡ ኖሮ፡ የብዙ፡ ሰላማዊ፡ ሰወች፡ ህይወት፡ የተሰዋበት፡ ለውጥ፡ ባላስፈለገ፡ ነበር። ለዚህ፡ ነው፤ ዛሬ፡ በአበዳሪ/ለጋስ፡ አገሮችና፡ በኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ መካከል፡ ያለው፡ የአመለካከት፡ ልዩነት፡ ሰማይና፡ ምድር፡ የሆነው። የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ አበዳሪወችን፡ የሚያያቸው፡ ልክ፡ ገዡውን፡ ፓርቲ፡ እንደሚያየው፡ ነው። በሁለቱም፡ ላይ፡ እምነት፡ የለውም። Human Rights Watch: ያወጣውን፡ ዘገባ፡ ማየት፡ ይበቃል። እርዳታ፡ አቅምን፡ ካልገነባ፤ ሰብ አዊ፡ ክብርን፡ ካላስተጋባ፤ ራስን፡ ካላስቻለ፤ አገራዊ፡ እድገትን፡ ጭብጥ፡ ካላስደረገ፡ ጥቅሙ፡ የት፡ ላይ፡ ነው?
የውጭ፡ መንግስታት፡ ሆኑ፡ አበዳሪወች፡ የሚመሩት፡ በራሳቸው፡ ጥቅም፤ ለራሳቸው፡ ጥቅም፡ እንጂ፡ ለኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ሰላም፤ አቅም-ግንባታ፤ ነጻነት፤ ፍትህ-ርትእ፤ ሉአላዊነት፤ ሁለ-አቀፍ፡ ልማት፡ አይደለም። ለዚህ፡ነው፡ የአሜሪካው፡ ፕሬዘደንት፤ ባራክ፡ ኦባማ፡ መለስ፡ ዜናዊይ፡ የሚሰሩትን፡ ጥፋት፡ እያወቁ፡ የስምንቱ፡ ሃብታም፡ አገሮች፡ ስብሰባ፡ ተካፋይ፡ አድርገው፡ ከኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ያላገኙትን፡ ማእረግ፡ ሰጥተው፡ በዋሽንግተንና፡ በካምፕ፡ ዴቪድ፡ እንዲገኙ፡ የጋበዟቸው። ይህ፡ ክብር፡ ከሶስቱ፤ የጋና፤ ታንዛኒያና፡ ቶጎ፡ መሪወች፡ ጋር፡ ሲነጻጸር፡ የመለስ፡ ዜናዊ፡ መሳተፍ፡ ለምእራብ፡ አገሮች፤ በተለይ፡ ለአሜሪካ፡ መንግስት፤ መለስ፡ በአፍሪካ፡ ቀንድ፡ ጠቃሚነታቸውን፡ የሚያሳይ፡ እንጂ፡ ለኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ታዛዥ፡ መሆናቸውን፡ ገላጭ፡ የማይሆነው። ከጋናው፡ ፕሬዘደንት፡ ሚልስ፡ ጋር፡ አይወዳደሩም። ጋና፡ የህዝብ፡ ድምጽ፡ የተከበረባት፤ ኢትዮጵያ፡ አንድ፡ ንኡስ፡ ብሄርተኛ፡ ቡድን፡ የሚገዛት፡ ናት። ይህ፡ ቡድን፡ የፖለቲካ፡ ስልጣን፡ ተጠቅሞ፡ የአገሪቱን፡ ወሳኝ፡ የኢኮኖሚ፡ ክፍሎች፡ (Pillars of the national economy)፤ በሙሉ፡ በቁጥጥር፡ ይዟል። ይቨቃኛል፡ የሚል፡ መንፈስ፡ የለውም። ይህ፡ ከቀጠለ፤ ማን፡ ሃብታም፤ ማን፡ ድሃ፤ ማን፡ ገዥ፤ ማን፡ ተገዥ፤ ማን፡ ስደተኛ፤ ማን፡ አዲስ፡ ተጠቃሚ፡ እንደሚሆን፡ ለመተመን፡ አያስቸግርም። የዘር፡ ማጥፋትን፡ ዘመቻ፡ የማየው፡ ከዚህም፡ አንጻር፡ ነው። ህወሓት፤ የቻይናን፤ የደቡብ፡ ኮሪያን፤ የታይዋንን፤ የቪየትናምን፡ አይነት፡እድገታዊ፡ አመራር፡ (developmental state model)፤ እከተላለሁ፡ ሲል፡ ለእራሱ፡ ሃይል፤ ሃብት፡ ክምችት፤ ቁጥጥር፡ እንጂ፡ ለመላው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ህይወት፡ መለወጫ፡ አይደለም። በልማት፡ ስም፡ ስልጣንን፤ የበላይነትን፡ ለማረጋገጥ፡ እንጂ፡ አገራዊና፡ ፍትያዊ፡ እድገት፡ ለማራመድ፡ አይደለም። እድገታዊ፡ መንግስት፡ ነኝ፡ ሲል፤ የእንዚህን፡ አገሮች፡ ልዩነት፡ ሳያሳይ፡ ነው። ለምሳሌ፡ እነዚህ፡ አገሮች፡ በአምባ፡ ገነኖች፡ በተገዙበት፡ ወቅት፡ እንኳን፤ ተቋሞቻቸው፡ ሆነ፡ መሪወቻቸው፡ አገር፡ ወዳድ፤ ታሪክ፡ ወዳድ፤ ባህል፡ አክባሪ፤ መላ፡ ህዝብ፡ አቀፍ፡ ነበሩ። የግል፡ ክፍሉ፡ ለሁሉም፡ በር፡ ከፋች፡ እንጂ፡ አድሏዊ፡ አልነበረም። በዘርኝነት፡ የታነጽው፡ የህወሓት፡ ስርአት፡ ከማንም፡ አገር፡ ጋር፡ ሊነጻጸር፡ የማይችለው፡ ለዚህ፡ ነው። ዘረኝነትና፡ አድሏዊይነት፤ ብቻ፡ መለያው፡ ሆኗል። ዘረኝነት፡ እድልን፡ አያሰፋም፤ እንዲያውም፡ ያጠባል።
መለስ፡ “ለእድገት፡ ዲሞክራሲ፡ አያስፈልግም፡” ይላሉ። እውነት፡ አይደለም።
መድቭለ፡ ፓርቲ፡ ያላቸው፡ የአፍሪካ፡ አገሮች፡ ፈጣን፡ ፍትሃዊ፡ እድገት፡ እንደሚያሳዩ፡ ማስረጃ፡ አለ። ናይጀሪያ፤ ደቡብ፡ አፍሪካ፤ ጋና፤ ማሊ፤ ኒጀር፤ ቤኒን፤ ሴኔጋል፤ ሲየራ፡ ሊኦን፤ የመካከለኛው፡ አፍሪካ፤ ሞዛምቢክ፤ ታንዛኒያ፤ ቦትስዋና፤ ናሚቢያ፤ ሞሪሽየስ፤ ኬፕ፡ ቬርዲ፤ ሌሶቶ፤ ኮሞሮስና፡ ሴየሽልስ፡ ዲሞክራሳዊ፡ መንግስታት፡ አሏቸው። የእነዚህ፡ አገሮች፡ መካከለኛ፡ የነፍስ፡ ወከፍ፡ ገቪ፤ በአመት፡ US$4,000፤ የሞሪሽየስ፤ ቦትስዋና፤ ሴየሸልስ፤ በአመት፡ የነፍስ፡ ወከፍ፡ ገቪ፡ US$10,000 በላይ፡ መሆኑን፡ IMF: መዝግቦታል። በጠቅላላው፡ ሲታይ፤ ሃያ፡ ስድስት፡ የአፍሪካ፡ አገሮች፡ የነፍስ፡ ወከፍ፡ ገቪያቸው፡ በአመት፡ ከUS$1,000 እስከ፡ US$3, 999: ነው። በአንጻሩ፤ የእርዳታ፡ ተቀዳሚ፡ የሆነችው፡ ኢትዮጵያ፡ የነፍስ፡ ወከፍ፡ ገቪ፡ አሁንም፡ የአፍሪካ፡ መጨረሻ፡ ከሆኑ፡ አገሮች፡ መካከል፡ ነው፤ በአመት፡ US$350. ዝቅተኛ፡ ገቪ፡ ካላቸው፡ ለመድረስ፡ ምን፡ ተአምር፡ ማድረግ፡ እንዳለባት፡ ማስረጃው፡ ያሳያል። ፍትሃዊ፤ በህግ፡ የሚዳኝ፤ መላው፡ ህዝብ፡ የሚሳተፍበት፤ ስርአት፡ ቢመሰረት፡ አልፋ፡ ለመሄድ፡ ትችላለች፡ ለማለት፡ እደፍራለሁ። የተሳትፎ፤ ፍትሃዊ፤ ዲሞክራሳዊ፡ ስርአት፡ የሚያስፈልግ፡ ለመሆኑ፡ የአፍሪካ፡ አገሮች፡ ጥሩ፡ አራያ፡ ናቸው። የአሜሪካ፡ መንግስት፡ እነዚህን፡ ከዲሞክራሲ፡ ስርአት፡ የሚገኙ፡ ጥቅሞች፡ ያውቃል።
ፕሬዘደንት፡ ኦባማ፡ መለስ፡ ዜናዊይን፡ በአሁኑ፡ ወቅት፡ ለታላቅ፡ ስብሰባ፡ የጋበዙበትን፡ ምክንያት፡ ከሌላው፡ ጊዜ፡ ለየት፡ የሚያደርገው፡ አቢይ፡ ጉዳይ፡ የምግብ፡ ዋስትና : (food security) ፡ ውይይት፤ መሆኑ፡ ነው። ችግሩ፤ አርእስቱ፡ አይደለም። ጠቅላይ፡ ሚኒስትሩ፡ስለ፡ ምግብ፡ ዋስትና፡ ኢትዮጵያን፡ ለመወከል፤ በየቀኑ፡ ለሚራቡት፤ በኑሮ፡ ውድነትና፡ የምግብ፡ ዋጋ፡ ግፍሸት፡ ለሚሰቃዩት፡ ወገኖቻችን፡ ድምጽ፡ ለመስጠት፡ ብቃት፡ የሌላቸው፡ መሆኑ፡ ነው። እስከ፡ አሁን፡ ያሳዩት፡ ተግባር፡ድሃውን፡ ህዝብ፡ ለቁጥጥር፡ እንጂ፡ ለብቃት፡ ሲያዘጋጁት፡ አያሳይም። ለወጣቱ፡ ትውልድ፡ በሃገሩ፡ ጥሩ፡ እድል፡ ሲከፍቱለት፡ አይታይም። ትምህርት፡ ቤት፡ ማስፋፋት፡ አስፈላጊ፡ መሆኑ፡ አያከራክርም። ትምህርት፡ ወደ፡ ስራ፡ ካላሸጋገረ፤ ብቃት፡ ካላሳየ፤ ጥራት፡ ከሌለው፡ በፍጥነት፡ ካደጉ፡ አገሮች፡ ጋር፡ ሊወዳደር፡ አይችልም። የህወሓት፡ ትምህርት፡ ወጣቱን፡ ትውልድ፡ ለስደት፡ እየዳረገው፡ ነው። የማሰብ፤ የመንቀሳቀስ፤ እንደልብ፡ ሃብት፤ ጥሪት፡ የመያዝ፡ መንገዶችን፡ ዘግቶበታል። ማንም፡ ኢትዮጵያዊ፡ ለመብቱ፡ ሲነሳ፡ እያሰሩት፤ እያሳደዱት፡ነው። ኦባማ፡ የቁጥጥር፡ መንግስት፡ የአምባገነነት፡ መለኪያ፡ መሆኑን፡ ያውቃሉ። የኢትዮጵያን፡ አምባገነን፡ መንግስት፡ ከግብጽ፤ ከሊቢያ፤ ከየመን፤ ከቱኒሲያ፤ ከሶሪያ፤ ከዝምባብዌ፡ የሚለይ፡ መለኪያ፡ ሊኖር፡አይችልም። ያለው፡ የጭካኔ፤ የመለየት፤ የአድሎ፡ መጠን፡ ለኢትዮጵያ፡ ብቻ፡ ሳይሆን፡ ለአፍሪካ፡ ቀንድ፡ አደጋ፡ እንደሚያመጣ፡ የአሜሪካ፡ ተቋሞች፡ አስምረውበታል። የአሜሪካ፡ የውጭ፡ ጉዳይ፡ መስሪያ፡ ቤት፡ በእየአመቱ፡ ያወጣው፡ ዘገቫ መለስ፡ ዜናዊይን፡ በአለም፡ ፍርድ፡ ቤት፤ እንደ፡ ላይብሪያው፡ ታይሎር፤ እንደ፡ ሱዳኑ፡ ባሽር፤ እንደ፡ ግብጹ፡ ሙባረክ (በቅርቡ፡ የእድሜልክ፡ እስራት፡ በሃገራቸው፡ የተፈረደባቸው) ወዘተ፡ ለማቅረቭ፡ የሚያስችሉ፡ “ወንጀሎች” እንዳሉ፡ ያውቃሉ። መለስ፡ እንደነዚህ፡ አምባገነኖች፡ በሰላማዊ፡ ህዝብ፡ ላይ፡ በተከታታይ፡ ወንጀል፡ የፈጸሙ፡ መሆናቸውንና፡ ተጠያቂነት፡ እንዳለባቸው፡ አያጠራጥርም። በቀጥታ፡ አንድም፡ ወንጀል፡ አልፈጸምኩም፡ ለማለት፡ አይችሉም። ከጀርቫ፡ ሆነው፡ እርሳቸው፡ ያልገቡብት፤ እርሳቸው፡ ትእዛዝ፡ ያልሰጡበት፡ አቢይ፡ ነገር፡ ከስራ፡ ላይ፡ እንደማይውል፡ ኦባማ፡ ያውቃሉ። እነዚህን፡ የወንጀል፡ መሰረቶች፡ የሚሆኑ፡ ጥቂት፡ ምሳሌወች፡ በመስጠት፡ ልለፍና፡ ወደ፡ ዋናው፡ የምግብ፡ ዋስትና፡ ትንተናየ፡ ልሂድ።
ኪራይ፡ ፈላጊውና፡ ሰብሳቢው፡ ማነው?
ጠቅላይ፡ ሚንስትር፡ መለስ፡ ሃያ፡ አንድ፡ አመታት፡ የመሩት፡ የአንድ፡ አናሳ፡ ብሄርተኛ፡ ቡድን፡ መንግስት፡ በእርሻ-ላይ፡ የተመሰረተ፡ እድገት፡ የአብዛኛውን፡ የድሃ፡ ህዝብ፡ ኑሮ፡ አላሻሻለም። የአሜሪካ፡ መንግስት፡ ይህን፡ ያውቃል። መለስ፡ እድገታዊ፡ መንግስት፡ ብለው፡ የሚጠሩት፡ ስርአት፡ የፖለቲካ፡ ሆነ፡ የመዋእለ፡ ንዋይ፡ የበላይነትን፡ ከያዘ፡ መቆየቱን፡ ፕሬዘደንት፡ ኦባማ፡ያውቃሉ። ምሳሌወችን፡ ላቅርብ።
የኢትዮጵያ፡ ኢኮኖሚ፡ እንደ፡ ሌላው፡ አመራር፡ በምስጢር፡ የሚሰራ፡ ነው። የገበያው፡ ስርአት፡ ግልጽነት፡ የለውም። በህግ፡ አይተዳደርም። በኮንትሮባንድ፡ የሚንቀሳቀሰው፡ ዘርፍ፡ በህግ፡ ከሚንቀሳቀሰው፡ ያላነሰ፡ ወይንም፡ አመዛኝ፡ እየሆነ፡ ነው። ተቋሞችን፡ ከመንግስት፡ ቁጥጥር፡ ስር፡ አናውጣ፡ በሚል፡ ዘይቬ፡ ህወሓት፡ ስልጣን፡ ከያዘበት፡ ጀምሮ፡ እስካሁን፡ ቀስ፡ በቀስ፡ የሃገሪቱን፡ የምርትና፡ የአገልግሎት፡ ዘርፎች፡ ወደ፡ ፓርቲውና፡ ምርጥ፡ ባለስልጣኖች፤ የትግራይ፡ ታማኞች፤ ሌሎች፡ ተባባሪወች፡ አስተላልፏል፤ እያስተላለፈ፡ ነው። በሚያስገርም፡ ሁኔታ፤ ምንም፡ በስማቸውና፡ በስራቸው፡ ካፒታል፡ የሌላቸው፡ ግለሰቦች፡ ነጥረው፡ ሃብታም፡ የሆኑበት፡ ምስጢር፡ ከዚህ፡ የመነጨ፡ ነው። የፖለቲካ፡ ስልጣን፡ ለግል፡ ሃቭት፡ ማጠራቀሚያ፡ ከሆነባቸው፡ በእጂ፡ ከሚቆጠሩ፡ አገሮች፡ መካከል፡ ኢትይጵያ፡ ከፍተኛ፡ ደረጃ፡ ይዛ፡ ትገኛለች። የህወሓት፡ ባለስልጣኖች፡ ይህን፡ ታሪክ፡ የመዘገቨው፡ ዘረፋ፡ የሚያካሂዱት፡ በሚስት፡ ስም፤ በልጂ፡ ስም፤ በዘመድ፡ ስም፤ በወዳጂ፡ ስም፤ በድርጂት፡ ሰም፤ በውጭ፡ ኢንቬስተሮች፡ ስም፡ ነው። አገር፡ ውስጥ፡ የሚፈሰውን፡ መዋእለ፡ ንዋይ፡ ብቻ፡ ማየት፡ አይቨቃም። በዱባይ፤ በደቡብ፡ አፍሪካ፤ በምእራብ፡ አፍሪካ፤ በአሜሪካ፤ በደቡብ፡ ሱዳን፡ ወዘተ፡ የሚፈሰው፤ የሚሸሸው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ሃቭት፡ ሰፊ፡ ነው። ምርምርና፡ ክትትል፡ ይፈልጋል። ይህ፡ የካፒታል፡ ማዘዋወር፡ ዘመቻ፡ የሚደረገው፡ በዘዴና፡ በምስጢር፡ ነው። ባጭሩ፤ የፖለቲካ፡ የበላይነት፤ ስልጣንና፡ ቁጥጥር፡ ለኪራይ፡ ሰብሳቢነት፡ አመችቷል። የመንግስት፡ የነበሩ፡ አትራፊ፡ የምርት፤ የአገልግሎት፡ ድርጂቶች፡ ለግለሰቦች፤ ለከፍተኛ፡ ባለስልጣኖች፡ ሲተላለፉ (Transfer of real resources from Ethiopian society to TPLF core and supporters)፤ ኪሳራውን፡ የሚሸከመው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ነው። ትርፉን፡ የሚያገኙት፡ የህወሓት፡ ባለስልጣኖችና፡ ታማኝ፡ ግለሰቦች፡ እንደሚሆኑ፡ አያጠራጥርም። በቅርቭ፡ የተገኙ፡ ማስረጃወችን፡ እንይ።
1. የጣይቱ፡ ሆቴል፤ ያለ፡ ምንም፡ ወጭ (ካፒታል) ከህዝ፡ ሃብተነት፡ ወደ፡ ምርጥ/ታማኝ፡ ግለሰብ፡ ተሸጋገሯል፡
2. የጉለሌ፡ የሳሙና፡ ፋብሪካ፤ ከመንግስት፡ ሃያ፡ ሚሊዮን፡ ብድር፡ በመጠቀም፡ ፋብሪካው፡ ከኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ወደ፡ ግለሰብ፡ ተሸጋገረ። ይህ፡ ፋብሪካ፡ በአመት፡ ሃያ፡ ሚሊዮን፡ ብር፡ ትርፍ፡ ያስገኝ፡ ነበር። ትርፍ፡ የሚያስገኝ፡ ተቋም፡ ለግል፡ ተጠቃሚ፡ ለምን፡ እንደተሰጠ፡ ምስጢር፡ ሊሆን፡ አይችልም፡
3. የጉለሌ፡ ልብስ፡ ስፌት፡ ፋብሪካ፤ አስራ፡ ሰባት፡ ሽህ፡ ካሪሜትር፡ የሆነው፡ በአንድ፡ ነጥቭ፡ አንድ፡ ሚልዮን፡ ብር፡ ተመን፡ ለታማኝ፡ ግለሰብ፡ ተሽጦ፡ ከኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ወደ፡ ህወሓት፡ ባለስልጣኖች/ግለሰቭ፡ ያለ፡ ውድድር፡ ተዘዋውሯል፡
4. ታሪክ፡ ያለው፡ የባህር፡ ዳር፡ ጊዮን፡ ሆቴል፤ ለእንድ፡ ህወሓት፡ ደጋፌ፤ ታማኝ፡ ግለሰብ፡ ተዘዋውሯል፡
5. የጎንደር፡ ጎሃ፡ ሆቴል፤ በሳንቲም፡ ሂሳቭ፡ አንድ፡ በውጭ፡ ለጥቂት፡ ወራት፡ ለቆየ፡ ካፒታል፡ ለሌለው፤ ታማኝ፡ ለሆነ፡ የትግራይ፡ ግለሰቭ፤ እንደ፡ ስጦታ፡ ተዘዋውሯል። ሌሎች፡ ሊወዳደሩ፡ ቀርቶ፡ አልተጋበዙም።
6. በቻይና፡ ኢንቬስተሮች፡ የተደገፉ፡ የሲሚንቶ፡ ፋብሪካወች (ሞጆ)፤ የጫማ፡ ፋብሪካ፤ ሌሎች፡ ከኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ሃብተነት፡ ወደ፡ ህወሃት፡ ባለስልጣኖች/ደጋፊወች/ታማኞች፡ ተዘዋውረዋል። ህወሃት፡ ይህን፡ ሲያደርግ፡ በመንግስትነት፡ ስልጣኑ፡ ተጠቅሞ፤ የመንግስትን፡ ሃብት፡ ወደ፡ ግለሰብ፡ ማዘዋወር፡ ለእድገት፡ ይጠቅማል፡ በሚል፡ ዘዴ፡ ነው። በገቨያ፡ ውድድር፡ ስም፡ የሃብት፡ ክምችትን፡ አጠናከረ። ኢትዮጵያን፡ እያዳከመ፡ ሃብትን፤ ጥሪትን፡ ወደ፡ ራሱና፡ ደጋፊወቹ፡ አዛወረ፡ ማለት፡ ነው።
7. የደንበል፡ ሕንጻ፤ የሚያወጣው፡ በግምት፡ ከሰቫ፡ እስከ፡ ሰማኒያ፡ ሚልዮን፡ ብር፡ ሲሆን፡ ገዡ፡ ግለሰብ፡ (ከህወሓት፡ ጋር፡ የቀረቨ፡ ግንኙነት፡ ያላቸው፡) ህንጻውን፡ መያዣ፡ አድርገው፡ (collateral) ከመንግስት፡ ካዝና፡ ከሁለት፡ መቶ፡ አምሳ፤ እስከ፡ ሶስት፡ መቶ፡ አምሳ፡ ሚሊዮን፡ ብር፡ አገኙ። ገንዘቩ፡ የት፡ እንደደረሰ፡ አይታወቅም። ሁነኛ፡ ግለሰቦች፡ የነገሩኝ፤ ይህ፡ ገንዘቭ፡ በጥቁር፡ ገበያ፡ ወደ፡ ውጭ፡ ምንዛሬ፡ ተለውጦ፡ ከሃገር፡ ወጥቷል። የጥቁር፡ ገበያ፡ የደመቀበት፡ መርካቶ፡ በአሁኑ፡ ወቅት፡ በቀን፡ ብዙ፡ ሚልዮን፡ ብር፡ ወደ፡ ዶላር፡ ይለወጥበታል። የተለወጠው፡ አገር፡ አይቀርም። አብዛኛወቹ፡ ለዋጮች፡ ገንዘብ፡ በሚልዮን፡ የሚቆጥሩ፡ የህወሓት፡ ባለስልጣኖች፤ የቅርቭ፡ ቤተሰቦች፤ ወዳጆች፤ ታማኞች፡ ናቸው። ሕጉ፤ ደንቡ፡ አይመለከታቸውም። እነዚህ፡ የሚስና፤ የስርቆት፤ የአድሎ፤ የዘረፋ፤ የህገ፡ ወጥነት፡ ማስረጃ፡ ናቸው።
8. ህንጻወች፤ ቪላወች፤ ኮንዶሚኒየም፤ የግል፡ ቤቶች፡ በአሜሪካ፤ በዱባይ፡ ወዘተ፡ መሰራታቸው፤ ዛሬ፡ ከፍተኛ፡ ባለስልጣኖች፤ ታማኝ፡ ግለሰቦች፤ የፓርቲው፡ ሃላፊወች፡ ስልጣንና፡ የረቀቀ፡ ግንኙነት፡ በመጠቀም፤ ኢምባሲወችን፡ ለግል፡ አገልግሎት፡ በማዋል፡ በብዙ፡ ሚሊዮን፤ ዶላር፡ የኪራይ/መኖሪያ፤ ማረፊያ፤ የልጅና. የቤተሰብ፤ የወዳጅ፡ መገልገያ፤ የኪራይ፡ መሰብሰቢያ፡ እያደረጉበት፡ ነው። ገንዝብ፡ ሲሸሽ፡ የሚጎዳው፡ ድሃውና፡ የወደፊቱ፡ ትውልድ፡ ነው። በኢትዮጵያ፡ አየር፡ መንገድ፡ የሚጓጓዘው፡ የምግብ፤ ሌላ፤ እቃ፡ በአመት፡ ብዙ፡ ሚሊዮን፡ ዶላር፡ ትርፍ፡ እንደሚያስገኝ፡ ይገመታል። በአብዣኛው፡ ተጠቃሚወቹ፡ የህወሓት፡ ባለስልጣኖች፤ ታማኞች፤ ደጋፊወች፡ ናቸው። እቃ፡ ከቀርጥ፡ ውጭ፡ ለማጓጓዝ፤ ቤቶችን፡ ሆነ፡ ሌላ፡ የጥሬ፡ ሃብት፡ ለማቋቋም፡ የፖለቲካ፡ ስልጣን፤ ግንኙነት፤ ገንዘብ፡ ቁልፍ፡ ናቸው። ገንዘቡ፡ የሚመጣው፡ ከኢትዮጵያ፡ ድሃ፡ ህዝብ፤ ካገሪቱ፡ ባንኮች፤ ወዘተ፡ ነው። የኢትዮጵያ፡ ብር፡ በጥቁር፡ ገበያ፤ በሌላ፡ ማስተላለፊያ፤ እየተለወጠ፡ ወደ፡ ውጭ፡ የሚጎርፈው፡ ለዚህ፡ አመልካች፡ መረጃ፡ ነው። ስልቱ፡ በሚስት፤ በልጂ፤ በቅርቭ፡ ዘመድ፤ በሰራተኛ፤ በወዳጅ፤በኤምባሲ፡ ሰራተኞች፤ በፈረንጆች፡ ስራ፡ ላይ፡ የዋለ፡ ነው።
ጠቅላይ፡ ሚንስትር፡ መለስ፡ በመንግስት፡ ውስጥ፡ “ሌቦች፡ አሉ፤ እናውቃቸዋለን.” ብለው፡ ይናገራሉ።ኪራይ፡ ሰብሳቢወች፡ የህወሓት፡ መሪወች፡ አይደሉም፤ ትግራዮች፤ አይደለም፤ እኔ፡ ወይንም፡ ባለቤቴ፡ አይደለንም፡ ይላሉ። ችግሩ፤ ክህደቱ፡ እውነቱን፡ ሊሸፍነው፡ አይችልም። የመንግስት፡ ሌቦች፡ እንዳሉ፡ ካወቁ (ማወቃቸው፡ አያጠራጥርም)፤ የፖሊቲካ፡ ስልጣንና፡ ሙስና፤ ብልግና፤ ገንዝቭ፡ ማሸሽ፡ የተያያዙ፡ መሆናቸውን፡ ያውቃሉ፤ ማን፡ ሌባ፡ እንደሆነ፡ ያውቃሉ። ሕጉም፤ ፍርዱም፤ ፍርድ፡ ቤቱም፤እስር፡ ቤቱም፡ በእጃቸው፡ ነው። ለምን፡ የመንግስት፡ ሌቦችን፡ ለፍርድ፡ አያቀርቡም፡ ብለን፡ መጠየቅ፡ መብታችን፡ የሚሆነው፡ ለዚህ፡ ነው። እንቅጩ፤ ከማንም፡ በላይ፡ የስልጣን፡ ተጠቃሚው፡ የህወሓት፡ ከፍተኛ፡ ባለስልጣኖች፤ ቤተሰቦች፤ ከፍተኛ፡ የጦር፡ መክኖንኖች፤ ታማኛ፡ የትግራይና፡ ሌሎች፡ ግለሰቦች፡ መሆናቸውን፡ ተራው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ያውቀዋል። ጠቅላይ፡ ሚንስትሩም፡ እንደሚያውቁ፡ አልጠራጠርም። እነደ-ጠቅላይ፡ ሚንስትሩ፤ ይህን፡ ማስረጃ፡ የሚሰጡኝ፡ ግለሰቦች፡ የሚኖሩት፡ ኢትዮጵያ፡ ነው። ሁኔታው፡ ሰለዘገነናቸው፤ ባይሆን፡ ለታሪክ፡ ይጻፍ፤ በማለት፡ በየጊዜው፡ የሚሰጡኝ፡ ማስረጃ፡ ነው።
9. የከተማና፡ የገጠር፡ ለም፡ መሬት፡ አሰረጫጨት፤ ኪራይ፡ አልሰበሰብም፡ የሚለው፡ እድገታዊው፡ ህወሓት፡ ቢፈቅድም፤ ባይፈቅድም፡ ከደሙ፡ ንጹህ፡ ለመሆን፡ አይችልም። ለዚህ፡ ጥሩ፡ ማስረጀው፡ የከተማና፡ ለም፡ የገጠር፡ መሬት፡ ስርጭት/ቅርሚት፤ አስተዳደር፡ ነው። መሬት፡ የሃብት፡ ማከማቻ፡ መሰረት፡ ነው። በቦሌ፤ በዱከም፤ በቡራዩ፤ በሰንዳፋ፤ በሱሉልታ፤ በናዝሬት፤ በደብረዘይትና፡ በሌሎች፡ የአዲስ፡ አበባ፡ ዙሪያ፡ ያለውን፡ የመሬት፡ ስርጭት፤ ማን፡ ምን፡ እንደያዘ፡ በገሃድ፡ ያሳያል። በክልል፡ እርእሰ፡ ከተማወችም፡ ያለው፡ አጠቃቅም፡ ይህን፡ ይመስላል። ታላላቅ፡ የፓርቲውና፡ የመንግስት፡ ባለስልጣኖች፤ ከፍተኛ፡ የጦር፡ መኮንኖች፤ ታማኝ፡ ግለሰቦች፤ የባለስልጣን፡ ሚስቶች፤ (በተለይ፡ ምርጥ/ታማኝ፡ የሆኑ፡ የትግራይ፡ ብሄረሰብ፡ አባላት) ከሶስት፡ እስከ፡ አስር፡ ቁልፍ፡ ቦታወች፡ ተመርተርው፡ የ ራሳቸው፡ አድርገዋል፤ ታላላቅ፡ ፎቆች፡ ሰርተዋል። በዋሽንግቶን፡ የህወሓት፡ አምባሳዶር፡ “የህንጻ፡ ባለጸጋ፡ ናቸው፡” የሚል፡ ማስረጃ፡አንድ፡ ግለሰብ፡ በቅርቩ፡ አሳይቶኛል። እሳቸውም፡ ሆኑ፡ ሌሎች፡ ህንጻ፡ በማስያዝ፡ ከመንግስት፡ ባንኮች፡ ብዙ፡ ሚሊዮን፡ ብር፡ አግኝተዋል።
ባለስልጣኖች፡ ህንጻ፡ ሲሰሩ፡ በራሳቸው፡ ገንዝብ፡ አይደለም። ገንዘቡን፡ ከየት፡ያመጡታል? ከሰቫ፤ እስከ፡ ሰማኒያ፡ ሚልዮን፡ ብር፤ ለጀኔራሎች፡ ታላላቅ፡ ፎቆች፡ እስክ፡ ዘጠና፡ ሚልዮን፡ ብር፡ የሚፈጀው፡ ገንዘብ፡ የሚገኘው፡ ከመንግስት፡ ባንኮች፡ ነው። የመንግስት፡ ካዝና፡ የፓርቲ፤ የግል፡ጥቅም፡ ማካቨቻ፡ የሆነባት፡ አገር፡ ኢትዮጵያ፡ ብቻ፡ ናት፡ ለማለት፡ የሚያስደፍረው፡ ለዚህ፡ ነው። ባንኮች፡ እነደሚታለቡ፡ ላሞች፡ ሁነዋል። ሁኔታው፤ ስልጣንና፡ ዋስትና፤ ብድር፡ የማግኘት፡ አቅም፤ የሃቭት፡ ክምችት፡ የተቆላለፉ፡ መሆናቸውን፡ ይጠቁማል። የከፍተኛ፡ ፎቆችና፡ ህንጻወች፡ ባለቤቶች፡ ተራ፤ ወይንም፡ ከስልጣን፡ ጋር፡ ያልተቆራኙ፡ ኢትዮጵያን፡ አይደሉም። ሊሆኑ፡ አይችልም። እነሱ፡ ድምጽ፤ ስልጣን፤ የላቸውም፤ የበይ፡ ተመልካቾች፡ ናቸው።
10. የኮንትሮባድ፡ ንግድ፡ ለኪራይ፡ ፈላጊወች፡ መሳሪያ፡ ሲሆን፤ በህግ፡ የማይተዳደር፡ ስርአት፡ ከቁጥጥር፡ መውጣቱ፡ አያስገርምም። የሚያስደነግጠውና፡ የሚያበሳጨው፡ የመንግስት፡ ሰራዊት፡ መኪናወች፡የኮንትሮባንድ፡ ንግድ፡ ማንቀሳቅሻ፡ መሆናቸው፡ ነው።ማንም፡ አይፈትሻቸውም፤ ማንም፡ አይቆጣጠራቸውም፤ ኬላ፡ እንደልብ፡ ያልፋሉ። በብዙ፡ መቶ፡ ሚሊዮን፡ የሚታሰብ፡ ሸቀጥ፡ ከህግ፡ ውጭ፡ ያዘዋውራሉ፤ ከሃገር፡ ያወጣሉ፤ “የጦር፡ መሳሪያ፡ ይነግዳሉ፤” ትርፍ፡ ለግል፡ ያከማቻሉ። የስልጣን፡ ብልግና፡ ማለት፡ ይህም፡ ነው። ስርአቱን፡ ስለሚያገለግሉ፡ መንግስት፡ ሊቆጣጠራቸው፡ አይችልም።
የግብር (ቫት) አድሏዊነት፡
11. የሃገር፡ ውስጥ፡ ገቢ፤ ይህን፡ ተቋም፡ ሙሉ፤ በሙሉ፡ የሚመራው፡ የህወሓት፡ ታማኝ፡ የሆኑ፡ የትግራይ፡ ተወላጂ፡ ባለስልጣኖች፡ ብቻ፡ ናቸው። ግንኙነታቸው፡ በቀጥታ፡ ከጠቅላይ፡ ሚኒስትሩ፤ ከፓርቲው፤ ከጠቅላይ፡ ሚኒስትሩ፡ ባለቤት፤ ከስለላ፡ ድርጂቱ፡ ጋር፡ ነው። የኢኮኖሚ፡ የበላይነትን፡ ለመያዝ፤ የአገር፡ ውስጥ፡ ገቢን፤ መቆጣጠር፡ አስፈላጊ፡ ነው፡ ብሎ፡ የተነሳው፡ ህወሓት፡ ይህን፡ ድርጂት፡ አንደ፡ አይን፡ ብሌን፡ ያየዋል፤ ይቆጣጠረዋል። ለምን? አቸናፊውን፡ ይመርጣል፤ መገለል፡ ያለበትን፡ በእርቂቅ፡ ያባርራል፤ ይጎዳል፤ መድረሻ፡ ያሳጣል፤ ያደክማል። የሚያተኩርበትን፡ ብናይ፡ ጎጂነቱን፡ እንረዳለን። አብዛኛው፡ ዘመናዊ፡ የኢትዮጵያ፡ ኢኮኖሚ፡ የሚሽከረከረው፡ በዝቅተኛ፡ ነጋዴወች፡ ነው። ሴቶች፤ አናቶች፡ ይተዳደሩበታል። ከአስራ- አምስት፡ በመቶ፡ በላይ፡ ቀረጥ (Value added tax)፤ የሚደነገገው፡ በእነዚህ፡ ላይ፡ ነው። ለመጠጥ፤ ለቡና፤ ለሻሂ፤ ለዳቦ፤ የሚከፈለውን፡ ስናይ፡ ጎጅነቱን፡ ለመረዳት፡ ይቻላል። ማነጻጸር፡ የሚገባን፤ የህወሓት፡ ጥሪት፤ ከቀረጥ፡ ነጻ፡ የሆኑትን፤ እንደ፡ ኤፎርት፤ በኮንትሮባንድ፡ የሚሰሩትን፡ የመከላከያና፡ የስለላ፡ ድርጂቶች፤ በህግ፡ ያልታወቁ፡ ሌሎች፡ ድርጂቶችን፡ ነው። ባት፡ የማይከፍሉበት፡ ምክንያት፡ ለምንድን፡ ነው፡ ብሎ፡ ለመጠየቅ፡ የማይችለው፡ ህብረተሰብ፤ “ወይ፡ ጉድ” አያለ፡ ሁኒታውን፡ ተቀብሎታል። ቀረጥ፡ እንዳይከፍሉ፡ የተደረገው፡ ከስርአቱ፡ ጋር፡ የጥቅም፡ ግንኙነት፡ ስላላቸው፡ ብቻ፡ ነው፡ ለማለት፡ እንገደዳለን። በሃገር፡ አቀፍ፡ ደረጃ፡ ሲታይ፤ ዋናው፡ የንግድ፡ ስራ፡ በሙሉ፡ ለፖለቲካ፡ ባለስልጣኖችና፤ ታማኞች፡ ተዳርጓል። ዝቅተኛ፡ ነጋዴወች፡ ከፍተኛ፡ ግቭር፡ እንዲከፍሉ፡ ሲገደዱ፤ አቅማቸው፡ ስለማይፈቅድ፤ ቀስ፤ በቀስ፡ ስራቸውን፡ ይዘጋሉ። ሃብት፡ ያላቸው፤ አገር፡ ወዳድ፡ የሆኑ፤ ሲብስባቸው፡ አገር፡ ለቀው፡ ይወጣሉ። የህወሓት፡ ዋና፡ አላማ፡ የፖለቲካ፡ ስልጣኑን፡ ተጠቅሞ፤ የንግዱን፤ ቁልፍ፡ የሆነውን፡ የማምረቻ፡ ክፍል፤ ባንክ፤ መገናኛ፤ ማጓጓዣ፡ ሙሉ፤ በሙሉ፤ የህወሓት፡ የበላይ፡ ባልሰልጣኖች፤ ታማኝ፡ የትግራይ፡ ተወላጆች፤ ተባባሪ፡ የሆኑ፤ የውጭ፡ ባለሃብቶች፡ እንዲይዙት፡ ማድረግ፡ ነው። የማይፈለገው፡ የኢትዮጵያ፡ ስብጥር፡(diverse)፤ ህዝብ፡ የበላይነት፡ አንዳይኖረው፤ አንዳይወዳደር፤ ለማድረግ፡ ነው። የበላይነት፡ ከተረጋገጠ፤ ህወሓት፡ በተከታታይ፤ ለብዙ. አመታት፤ ወይንም፡ ከትውልድ፡ ወደ፡ ትውልድ፡ ለመግዛት፡ ይችላል፡ የሚለውን፡ ግምት፡ መሰረትና፡ ድልድይ፡ ለማመቻቸት፡ ነው፡፡ ችግሩ፤ የመስራት፤ ሃብት፡ የመያዝ፤ የመንቀሳቅስ፤ የተፈጥሮ፡ ሃቭት ፍትሃዊ፡ በሆነ፡ መንገድ፡ የማግኘት፡ እድል፡ ክሌለ፡ ዘላቂነትና፡ በእኩለነት፡ የተመሰረተ፡እድገት፡ ሊኖር፡ አይችልም። የዛሬ፡ ተጠቃሚወች፡ የነገ፡ ኢላማወች፡ ሊሆኑ፡ ይችላል። ኢኮኖሚው፡ እንደ፡ ቦትስዋና፡ ሊሆን፡ አይችልም። የነፍስ፡ወከፍ፡ ገቪ፡ አያድግም፤ ድህነት፡ አይጠፋም።
12. የለም፡ መሬት፡ አያያዝ፤ የዘመናዊ፡ ግብርናውን፡ ክፍል፤ እንደ፡ ሌላው፤ ህወሓትና፡ ታማኞች፡ በኢትዮጵያዊያን፡ ስም፡ እየተቀራማቱት፡ ነው። ለውጭ፡ አገር፡ ታዛቢወች፤ የሚሉት፤ አብዛኛውን፡ ለም፡ መሬት፡ የተመሩት፡ ኢትዮጵያዊያን፡ ናቸው፡፡ ይህ፡ ከእውነቱ፡ የራቀ፡ መሆኑን፤ (Oakland Institute, Human Rights Watch, the Guardian, Survival International, Desalegn Rahamato, etc)፤ ማስረጃ፡ አቅርቨውበታል። ለውስጥ፡ ኢንቬስተሮች፡ ተሰጠ፡ የሚባለው፡ ሰባ፡ አምስት‹ በመቶው፡ ለምርጥ፡ የትግራይ፡ ተወላጆች፤ ለከፍተኛ፤ የጦር፡ መኮንኖች፤ ለፓርቲው፡ ከፍተኛ፡ ሃላፊወች፡ የተሰጠውን፡ ነው። ሌሎች፡ ኢትዮጵያዊያን፡ የሉብትም፤ ወይንም፡ አያገቫቸውም፡ እንደማለት፡ ነው። የአድሎውን፡ ጨካኝነት፡ ያመለክታል። ሌላው፤ ግልጽነት፡ በሌለባት፡ አገር፤ የፓርቲው፡ ባለስልጣኖች፤ ታማኝ፡ የትግራይ፡ ተወላጆች፤ የህንድን፤ የፓኪስታንን፤ የሳውዲ፡ አራቢያን፤ ወዘተ፤ ኢንቬስተሮች፡ በውስጥ፡ ድርድር፡ ተካፋይ፡ እንዲሆኑ፡ አድርጓል። ይህ፡ የጥቅም፡ ውል፡ የኢትዮጵያን፡ ከበርቴወች፤ ዝቅተኛ፡ አምራቾች፤ ወጣቶች፡ ወደ፡ ጎን፡ እየተወ፤ ኢትዮጵያዊያን፡ በአገራቸው፡ ለም፡ መሬትና፡ ወንዝ፡ ተእጠቃሚ፡ እንዳይሆኑ፡ እያደረጋቸው፡ ነው። የመሬት፡ ነጠቃውን፡ በተናጥል፡ አላየውም። ከንግዱ፤ ከዘመናዊ፡ ምርቱና፡ ማጓጓዣው፤ ወዘተ፡ አጣምረን፡ ማየት፡ ይኖርብናል። አንዱ፡ ሌላውን፡ ይደግፋል።
በፍጥነት፡ ያደጉ፡ አገሮች፡ ታሪክ፡ የሚያስተምረን፤ እኔ፤ በአይኔ፡ ያየሁት፤ የታይዋን፤ የደቡብ፡ ኮሪያ፤ የኢንዶኔዝያ፤ የቻይናና፡ የህንድ፡ እድገት፡ ከኢትዮጵያ፡ በጣም፡ ይለያል። እንዚህ፡ አገሮች፡ የሃገር፡ ውስጥ፡ ታዳጊ፡ የኢኮኖሚ፤ የአገልግሎት፤ የንግድ፡ ክፍሎችን፡ ከውጭ፡ አገር፡ አትራፊወች፡ ተንከባክበው፡ እንዲጎለምሱ፡ አድርገዋል። ህወሓት፡ ሌላ፡ ቀርቶ፤ የቻይና፡ አትራፊወች፡ በችርቻሮ፡ ተግባር፡ ገብተው፡ ኢትዮጵያዊያንን፡ እየጎዱ፡ ያያቸዋል፤ ፈቅዶላቸዋል። የምስራቅ፡ ኤዥያ፡ አገሮች፡ የማይፈቅዱትን፤ የሞባይል፡ ስርጭት፤ የምግብ፡ አቅርቦት፤ የንግድ፡ ወዘተ፤ ተግባሮች፤ ህወሓት፡ ፈቅዶ፡ ኢትዮጵያዊያንን፡ እየጎዳ፡ ነው። አንባቢው፡ እንዲገነዘቭ፡ የምሻው፡ መልክት፡ ይህ፡ ነው። ሃላፊነት፡ የሚሰማው፡ መንግስትና፡ አመራር፡ ኑ፡ ብሎ፡ የውጭ፡ ኢንቬስተሮችን፡ ወደ፡ ሃገሩ፡ የሚያስገባው፡ የሃገሩ፡ ህዝብ፡ ለመስራት፡ የማይችለውን፡ እንዲሰሩ፤ አቅም፡ ገንብተው፡ ቶሎ፡ እንዲወጡ፡ ብቻ፡ ነው። የሃገሪቱን፡ አምራቾች፤ ነጋዴወች፤ ለመፍጠር፤ ለማምረት፤ የሚችሉ፡ ኢትዮጵያዊያንን፡ እንዲተኩ፡ አይደለም። በእርሻም፡ በኩል፤ ታናናሽ፡ ገበሬወች፡ ሆኑ፡ ፍላጎትና፤ ችሎታ፡ ያላቸው፡ ኢትዮጵያዊያን፡ መሬቱን፤ ወንዙን፤ ምርቱን፤ ገበያውን፡ እንዲቆጣጠሩት፡ የማድረግ፡ የማእክላዊ፡ መንግስት፡ ሚና፤ ተግባር፤ ነው፤ ሃላፊነት፤ አለበት፤ ተጠያቅነት፡ አለበት። ህወሓት፡ የሚያደርገው፡ ከዚህ፡ የራቀ፤ የኪራይ-ሰብሳቢነት፤ የትርፍ፡ አመቻችነት፡ ተግባር፡ ሆኖ፡ ይታያል። ለዚህ፡ ነው፤ የህወሓት፡ እድገት፡ ፍትሃዊ፡ ለመሆን፡ የማይችለው። አብዮታዊ፡ ዲሞክራሲ፡ በምንም፡ ፍትሃዊ፡ ለመሆን፡ አይችልም። ለዚህ፡ ነው፤ ጠቅላይ፡ ሚኒስትር፡ መለስ፡ መላውን፡ የኢትዮጵያን፡ ሕዝብ፡ ለመወከል፤ የሞራል፡ ብቃት፡ የላቸውም፡ ለማለት፡ የሚቻለው።
ከሁሉም፡ በላይ፤ “እድገታዊው”፡ የህወሓት፡ አስተዳደር፡ ያበለጸገው፡ እራሱን፤ ታማኝ፡ የትግራይ፡ አዲስ፡ ከበርቴወችን፤ ከፍተኛ፡ የጦር፡ መሪወችን፤ ለይስሙላ፡ ሌሎች፡ ደጋፊወችን፡ መሆኑን፡ ፕሬዘደንት፡ ኦባማ፤ ያውቃሉ። በአሁኑ፡ ወቅት፤ አገራችን፡ “ዘርፎ፡ ለዘራፊ፡” ተዳርጋለች፡ ቢባል፡ ከሃቁ፡ የራቀ፡ አይሆንም። የኢትዮጵያን፡ ስብጥር፡ ህዝብ፡ የሚያንጸባርቅ፡ አገር፡ ወለድ፡ ከበርቴ፡ ገና፡ መሰረት፡ መያዝ፡ ያልቻለው፡ አመራሩ፡ አገራዊ፡ ሳይሆን፡ ወገናዊና፤ ጠባብ፡ ዘረኛ፤ ኪራይ፡ ሰብሳቢወችን፡ የሰበሰበ፤ በመሆኑ፡ ነው። የአለም፡ ባንክ፡ ዘገባ፡ እንደሚያሳየው፡ የግል፡ ክፍሉ፡ በህወሓትና፡ ደጋፊ፡ ተቋሞች፤ በወጭ፡ ከበርቴወች፡ ታንቋል። ይህን፡ የአሜሪካ፡ ባለስልጣኖች፡ ያውቃሉ። ደንቡ፤ ህጉ፤ አስተዳደሩ፡ አድሏዊ፡ ከሆነ፡ አገር፡ ወለድ፡ ከበርቴ፡ በስፋት፡ ሊፈጠር፡ አይችልም። እንደ፡ ቦትስዋና፤ ኒይጀሪያ፤ ጋና፡ መካከለኛ፡ መደብ፡ ሊስፋፋ፡ አይችልም። የኮሪያ፤ ጃፓን፤ ቬትናም፤ እድገት፡ ጎዳናወች፤ የሚያሳዩት፤ አድሎ፡ የሌለበት፡ አገራዊ፡ እኮኖሚ፡ ለሁሉም፤ እድል፡ ከፋች፡ መሆኑንን፡ ነው። ለሴቶች፤ ለወጣቶች፡ እድል፡ ይከፍታል። በጋና፤ ሴኔጋል፤ ታንዛኒያ፡ የሚታየው፡ አገር፡ ወለድ፡ እድገት፡ ኢትዮጵያን፡ እንደሚለያት፡ አሳይቻለሁ። ህወሓት፡ አዲስ፡ የግል፡ ሃብታሞች፡ ተፈጥረዋል፡ የሚለው፡ የተወሰኑ፤ የተመረጡ፡ አብዛኛወቹ፡ የትግራይ፡ ብሄረሰብ፡ አባላት፡ መሆናቸውን፡ የኦባማ፡መንግስት፡ ያውቃል። በኢትዮጵያ፡ የተዛባ፤ ትግሬአዊ፤ በሆነው፤ የመከላከያ፡ እዝ፡ ላይ፡ የአሜሪካ፡ መንግስት፡ ተወካይ፡ ጀኔቫ፡ ያደረጉትን፤ ወቀሳ፡ ኦባማ፤ ክሊንቶን፡ አያውቁትም፡ የሚል፡ ታዛቪ፡ አላገኘሁም።
መለስና፡ ደጋፊወቻቸው፡ እንደሚሉት፡ ከሆነ፡ የዚህ፡ አንዱ፡ የተዛብ፡ የእድገት፡ ውጤት፡ የገጠር፡ ሚሊየኖርችን፡ ማምረቱ፡ ነው። ከምሳሌ፡ ውጭ፡ ግን፤ እነዚህን፡ የገጠር፡ ሃብታሞች፡ ፈልጌ፤ የት፡ እነደሚኖሩ፤የተ፡ እንደሚገኙ፡ ተመራምሬ፡ ልደርስባቸው፡ አልቻልኩም። ምን፡ አልባት፡ ጨረቃ፡ ላይ፡ ይሆኑ? የአሜሪካ፡ ተራድኦ፡ ድርጂት፡ የእርሻ፡ ምርት፡ አለማደጉን፡ ያውቃል። አብዛኛው፡ የምግብ፡ መደጎሚያ፡ የሚጎርፈው፡ከአሜሪካ፡ መንግስት፡ ነው። የአለም፡ ባንክ፡ የውስጥ፡ ዘገባ፤ “Poverty and well-being in Ethiopia: the role of agriculture agency” ያሳየው፡ መለስ፡ ከሚሉት፡ የገጠር፡ ልማትና፡ የምርት፡ እድገት፡ ይጻረራል። የገጠሩ፡ ህዝብ፡ የሚተዳደርብት፡ መሬት፡ ባለቤት፡ ካለመሆኑም፡ በላይ፤ መሬት፤ ምርጥ፡ ዘር፤ ብድር፤ ማዳበሪያ፤ ሌላም፡ የአገልግሎት፡ ግብአት፡(input): ለማግኘት፡ የገዡ፡ ፓርቲ፡ ታዛዥ፡ መሆን፡ አለበት። የአሜሪካ፡ መንግስት፡ ይህንም፡ ያውቃል። የሰብአዊ፡ መብት፡ ድርጂቶች፤ በተለይ፤ (Human Rights Watch): እንዳረጋገጡት፡ ህወሓት፡ የውጭ፡ እርዳታ፡ የሚያዳርሰው፡ በታማኝነት፡ መለኪያ፡ እንጂ፡ ያለ፡ አድሎ፡ የህዝብን፡ ችግር፡ ለመፍታት፤ የግል፡ ክፍሉን፡ አገራዊ፡ ለማድረግ፤ አቅምን፡ ለማጎልመስ፤ ድህነትን፡ በሙሉ፡ ለማጥፋት፤ አለመሆኑንም፡ ያውቃሉ። የግል፡ ክፍሉ፡ ያለምንም፡ አድሎና፤ ተጽእኖ፡ ካላደገ፡ ዘላቂነት፤ ፍትሃዊነት፤ ያለው፡ እድገት፡ አይኖርም። መዋቅሩ፡ አይለወጥም። ስደት፡ ይቀጥላል።
የሀወሓት፡ መሪ፡ እንደሚሉት፡ ከሆነ፡ ኢትዮጵያ፡ የእርሻ፡ ምርቷን፡ በሚያኮራ፡ ደረጃ፤ አሳድጋለች። የአለም፡ ባንክ፡ ባለሙያወች፡ እንደሚሉት፡ ከሆነ፡ ግን፡ “ኢትዮጵያ፡ በእርሻ፡ ምርት፡ አስደናቂ፡ እድገት፡ አሳይታለች፡ የሚለው፡ የመንግስት፡ ወሬ፡” በምንም፡ ማስረጃ፡ የተደገግፈ፡ አይደለም። የፈጠራ፡ ወሬ፡ ነው፡ ማለት፡ ነው። በፈጠራ፡ ወሬ፡ ህወሃትን፡ የሚወዳደር፡ አመራር፡ የትም፡ አይገኝም። አለም፡ ባንክ፡ እንደሚለው፤ በገጠር፡ በብዙ፡ ሚሊዮን፡ የሚቆጠሩ፡ ኢትዮጵያዊያን፡ መሬት፡ አልባ፡ ናቸው። ያላቸውም፡ የተበላ፤ የተቦረቦረ፤ የተቆራረጠ፤ ከእጂ፡ ወደአፍ፡ የሚሆን፡ መሬት፡ ነው። በገጠር፤ ብዙ፡ ሰወች፡ ይራባሉ። ከስምንት፤ እስከ፡ አስራ-ሶስት፡ ሚሊዮን፡ የሚሆኑት፡ በውጭ፡ የምግብ፡ ድጎማ፡ ይኖራሉ። የሚያሳዝነው፤ ደጓሚወቹ፡ አቅምን፡ በመገንባት፡ ፋንታ፡ ጥግኝነትን፡ የመረጡ፡ ይመስላል። በቅርቡ፡ ቢል፡ ጌትስ፡ “የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ከየትኛውም፡ አገር፡ የበለጠ፡ የምግብ፡ እርዳታ፡ ያስፈልገዋል” ያሉት፡ የማያሻማ፡ ድምዳሜ፡ የመንግስቱን፡ ውሸት፡ አጋልጦታል። በተከታታይ፡ በአመት፡ ከ አስራ-አንድ፡ በመቶ፡ ባላነሰ፡ አድጋለች፤ አሁንም፤ እያደገች፡ ነው፡ የሚለውም፡ የመንግስት፡ ፕሮፓጋንዳ፡ ከዚህ፡ አንጻር፡ መታየት፡ ይኖርበታል። እድገት፡ መኖሩ፡ ባያከራክርም፡ እድገቱ፡ የአብዛኛውን፡ ህይወት፡ እንዳለወጠው፡ ማስረጃው፡ ብዙ፡ ነው። ያለፈው፡ አመት፡ የተባበሩት፡ መንግስታት፡ የህብረተሰብ፡ እድገት፡ መለኪያ፡ (Human Development Index 2011)፤ ኢትዮጵያን፡ ከመቶ፡ ሰማንያ፡ አገሮች፡ መቶ፡ ሰቫ፡ አምስተኛ፡ ያደረጋት፡ ለዚህ፡ ነው። ህወሓት፡ ሲፈልግ፡ እየመረጠ፡ አለም፡ ባንክ፤ የተባበሩር፡ መንግስታት፡ የእድገት፡ ድርጂት፡ እድገታችን፡ አመሰገኑ፡ ሲል፡ የሚፈልገውን፡ ዘገቫ፡ መርጦ፤ የማይፈልገውን፡ ትቶ፡ ዋናውን፡ የእድገት፡ መለኪያ፡ እንደሌለ፡ አድርጎ፡ ነው። በማስረጃ፡ መዋሽት፡ የህወሓት፡ ልዩ፡ ተሰጦ፡ ሁኗል፡ ለማለት፡ የሚያስደፍረው፡ ለዚህ፡ ነው። ተደጋግሞ፡ ከተነገረ፡ ውሸት፡ እውነት፡ ይሆናል፡ የሚል፡ ግምት፡ አለው።
እውነቱን፡ በግልጽ፡ እናስቀምጠው። እድገታዊ፡ የሚባለው፡ የህወሓት፡ መንግስት፡ የሚመራብት፡ ስርአት፡ የአንድ፡ አናሳ፡ ዘር፡ ፓርቲን፡ የበላይነት፡ ብቻ፡ የሚያንጸባርቅ፡ ነው። ስለሆነም፤ የታወቁት፡ ተመራማሪ፡ ደሳለኝ፡ ራሃማቶ፡ አንዳሉት፡ ከህወሓት፡ ውጭ፡ ያሉ፡ ሁሉ፡ በእድገት፡ ላይ፡ የመናገር፤ ሃሳብ፡ የማቅረብ፤ የመሳተፍ፤ የመተቸት፤ መብት፡ የላቸውም። መለስ፤ እነዚህን፡ “ኪራይ፡ ሰብሳቢ፡ ስለሆኑ፤ አልሚ”፡ ለመባል፡ የሞራል፡ ብቃት፡ የላቸውም፡ ብለው፡ ደንግገዋል። ኪራይ፡ ሰብሳቢ፡ ማን፡ እንደሆነ፡ በማስረጃ፡ ገልጨዋለሁ። ወደፊትም፡ በማስረጃ፡ የተደገፈ፡ ትንተና፡ አቀርባለሁ። የመለስ፡ ድንጋጌ፡ አገር፡ ወለድ፤ ኢትዮጵያዊ፡ የሆኑ፡ ሁሉ፡ የመፍጠር፤ የማምረት፤ የመንቀሳቀስ፤ የመወዳደር፤ ሃብት፡ አግኝተው፤ አገራቸውን፡ የማልማት፡ ሚና፡ እንዳይጫወቱ፤ የሃብታምና፡ መካከለኛ፡ መደቭ፡ ለመፍጠር፡ እንዳይችሉ፤ ማነቆ፡ ሁኗል። በስልጣን፡ ላይ፡ የመቆየት፡ ጉዳቱ፡ አንዱ፡ መልክ፡ ይህ፡ ነው። መለስ፡ እንደደነገጉት፤ ተቃዋሚወች፤ እድገቱ፡ “ፍትሃዊ፡ አይደለም፤ ሙስናን፡ ያጠናክራል፤ ሰው፡ በሃገሩ፡ ሰርቶ፡ እንዲኖር፡ አያበረታታም”፤ እድገት፡ አለ፤ ግን፡ ዳቦ፡ የለም” ለማለት፡ አይችሉም። ይህን፡ ካሉ፡ ምርጫቸው፡ ወይ፡ ከርቸሌ፤ ወይ፡ ስደት፡ ይሆናል። ተስፋ፡ የቆረጡ፤ በስር አቱ፡ እምነት፡ ስለሌላቸው፡ አማራጭ፡ ሁኖ፡ የሚያዩት፤ ከሃገር፡ መሸሽ፤ ሃቭትን፡ ማሸሽ፤ ወዘተ፡ ሆኗል። ጠቅላይ፡ሚንስትር፡ መለስ፡ እድገታዊ፡ መንግስት፡ ብሎው፡ የሚጠሩት፡ ወሳኝ፡ አመራር፡ ጥቅሙ፡ ለአንድ፡ ቡድን፡ መሆኑን፡ የሚያጠነክረው፡ ተወዳዳሪ፡ አለመፈቀዱ፤ የመንጋር፡ መብት፡ አለመኖሩ፤ እውነቱን፡ መናገር፡ አለመቻሉ፡ ወዘተ፤ነው። የህዝብ፡ ጠበቃና፡ ተወዳዳሪ፡ ቢኖር፤ የቻይና፡ የእድገት፡ ስርአት፡ ያስከተላቸውን፡ አስቃቂ፡ ውጤቶች፡ ማሳየትና፡ የኢትዮጵያን፡ የእድገት፡ መስመር፡ ማረም፡ በተቻለ፡ ነበር።
ለምሳሌ፤ የአካባቢው፡ ውድቅት (massive environmental degradation and social dislocation that threatens sustainability)፤ እያደገ፡ የሄደው፡ በሃብታምና፡ድሃ መካከል፡ ያለው፡ የገቢና፡ የኑሮ፡ ልዩነት፤ የሙስና፡ ስፋትና፡ ጥልቀት፤ የወጣቱ፡ ትውልድ፡ በመሪወች፡ ላይ፡ ያለው፡ አመኔታ፡ እየተናደ፡ መሄድ፤ መልካም፡ የሆኑ፡ የባህል፡ እሴቶች፡ መጥፋት፤ ስርቆት፡ እነደብልጠት፡ ስራ፡ ላይ፡ መዋል፡ ከጥያቄ፡ ላይ፡ ይወድቁና፡ ይታረሙ፡ ነበር። መለስ፤ አመራራቸውን፤ የልማት፡ መሰረታቸውን፡ ጥያቄ፡ ውስጥ፡ የሚያስገባ፡ ትችት፡ ሁሉ፡ አይፈቅዱም። ቢፈቅዱና፡ የእራሳቸውን፡ ህገ፡ መንግስት፡ ስራ፡ ላይ፡ ቢያውሉ፡ ተስፋ፡ይኖር፡ ነበር። እርሳቸውም፡ ሆኑ፡ ደጋፊወቻቸው፤ ፖሊሲያቸውን፡ ከእራሳቸው፡ መለየት፡ አልቻሉም። ተቀናቃይ፡ ሁሉ፡ ጠላታቸው፡ አድርገው፡ ስለሚያዩ። ደጋፊወቻቸውም፡ ጥያቄ፡ አቅራቢወችን፡ “ግለሰብ፡ (መለስን፡ ማላታቸው፡ ነው)፡ ስለጠላችሁ፡ እንጂ፡ ፍትሃዊ፡ እድገት፡ ስለሌለ፡ አይደልም፡” ብለው፡ በጭፍን፡ የሚከራከሩት፡ በዚህ፡ መነጸር፡ ስለሚያዩት፡ ነው።በዛሬይቱ፡ ኢትዮጵያ፡ ሰውንና፡ የመንግስት፡ አመራርን፡ ለመለየት፡ አይፈቀድም። እውንትና፡ ውሸት፡ መለየት፡ሃጢያት፡ ሁኗል።
በቅርቡ፡ አዲስ፡ አበባ፡ በተካሄደው፡ አለም፡ አቀፍ፡ የኢኮኖሚ፡ ስብሰባ፡ ላይ፡ አንድ፡የቻይና፡ ባለስልጣን፡ ለመለስ፡ የተናገሩት፡ የሚከተለው፡ ነው። “ተማሩ፤ በጭፍን፡ ቻይና፤ ቻይና፡ አትበሉ። ችግሮችን፡ ተገንዝባችሁ፡ ሌላ፡ ውብ (beautiful) አማራጭ፡ ተከተሉ።” ለመለስ፡ ይህ፡ ምክር፡ ዋጋ፡ የለውም። በኢትዮጵያዊነታቸውና፡ በመላው፡ ኢትዮጵያዊያን፡ የመስራት፤ የመፍጠር፤ የማደግ፡ ችሎታ፡ የሚያምኑ፡ አይመስልም። በለውጥ፡ አያምኑም። በቃኝን፡ አይቀበሉም። ስኅተት፡ ሰራሁ፡ ብለው፡ ለመናገር፡ አይችሉም። እንዲያውም፤ ሌላውን፡ ማንበርከክ፤ ሰብነቱን፡ መግፈፍ፡ ይቀድማቸዋል። ፈላጭ፤ ቆራጭ፡ መሆናቸውን፡ ከዚህ፡ ልንማር፡ እንችላለን። ስለዚህ፤ ካለፈው፡ ስህተት፡ ለመማር፡ የማይችሉ፤ ለህዝብ፡ ንቀት፡ ያላቸው፤ የሌለውን፡ ፍትሃዊ፡ እድገት፡ አለ፡ የሚሉ፤ ህዝብ፡ እየተራበ፡ አልተራበም፡ የሚሉ፤ ወዘተ፤ ጠባብ፡ ብሄርተኛ፡ መሪ፡ በአለም፡ መሪወች፡ የምግብ፡ ዋስትና፡ ውይይት፡ ላይ፡ ለመገኘት፡ የሞራል፡ ብቃት፡ ሊኖራችው፡ አይችልም። በሃያ፡ አንድ፡ አመታት፡ ያላሳዩትን፡ የእርሻ፡ ምርት፡ ውጤት፡ መለስ፡ እንዴትና፡ በምን፡ ተአምር፡ በሚቀጥሉት፡ አምስት፡ አመታት፡ ለኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ እንደሚያጎናጽፉት፡ ለእኔ፡ እንቆቅልሽ፡ ነው። ሌላው፤ የአንድ፡ አገር፡ መሪ፡ ከሃገሩ፡ ህዝብ፡ የበለጠ፡ የውጭ፡ ለጋሾችን፤ ሃብታሞችን (donors and investors): ሲያቀርብ፡ በእራሱ፡ ህዝብ፡ አይተማመንም፡ ማለት፡ ነው።
በህዝብ፡ የመስራት፤ የመፍጠር፤ የማምረት፡ ሃይል፡ የሚያምን፡ መሪ፤ የሃሩን፡ አምራች፡ ገበሬ፡ አቅም፡ ይገናባል፡ እንጂ፡ ሳውዲ፡ ስታር፤ ካሩቱሪ፤ አርሰው፡ ይመግቡኛል፡ ብሎ፤ በውጭ፡ የትርፍ፡ አምራቾች፡ አይመካም፤ አገሩን፡ ዘርፎ ለዘራፊ፡ አይዳርግም። ለዚህም፡ ጭምር፡ ነው፡ ሁኔታው፡ ከቀጠለ፡ ድሃው፡ ሆነ፡ መካከለኛ፡ መደብ፤ አገር፡ ወለድ፡ ከበርቴ፡ ሆነ፡ የተማረው፡ የስራ፡ እድል፡ የሌለው፡ ወጣት፡ መብቱን፡ የሚያስከብርበት፡ መንገድ፡ መፈለግ፡አለበት፡ ለማለት፡ መድፈር፡ ያለብን። እኛ፡ ካልበርታን፡ ማንም፡ የውጭ፡ ሃይል፡ መብታችን፤ ነጻነታችን፤ ክብራችን፡ ሊያጎናጽፈን፡ አይችልም። ክብራችን፡ ለመጎናጸፍ፡ የምንችለው፡ “የልዩንት፡ ኮፍያ/ባርኔጣ፡” አንግቨን፡ ሳይሆን፡ ተቻችለን፤ ተከባብረን፤ ለአንድ፡ አገር፤ ለአንድ፡ ህዝብ፤ ለአንድ፡ አላማ፡ በአንድነት፡ ስንቆም፡ ብቻ፡ ነው። አብረን፡ ከቆምን፡ ኢትዮጵያ፡ ሃብታምና፡ ዘመናዊ፡ እንደምትሆን፡ አልጠራጠርም።