“ከምግብም በላይ ነጻነት እንሻለን!” የኢትዮጵያን ሪቪው ወቅታዊ ርዕሰ አንቀጽ

የኢትዮጵያን ሪቪው ርዕሰ አንቀጽ

“ከምግብም በላይ ነጻነት እንሻለን!”

(በፒ.ዲ. ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)

ጋዜጠኛ ኣበበ ገላው በሃያላኑ መንግስታት ጉባኤ ፊት “ከምግብም በላይ ነጻነት እንሻለን!” ሲል ተናገረ። በርግጥ ይህ አባባል ለአንዳንድ ሰነፎች ብዙም ትርጉም ላይሰጥ ይችላል። በመሰረቱ ግን ነጻነት አንዱ የእኛ የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎት ነው። በተለምዶ የሰው ልጆች ፍላጎቶች ሶስት ናቸው ይባል ነበር። ግን አይደለም አራት ናቸው። ከምግብ፣ ከልብስና ከመጠለያ ጋር ነጻነት አንዱ መሰረታዊ ፍላጎታችን ነው። እንዲያውም የሰው ልጅ ነጻነቱን ከምግብም ሁሉ በላይ ሲሾመው ይታያል። ማን ነው እስቲ ማርና ወተት እየጠጣህ ጮማ እየቆረጥክ ኑሮህን በወህኒ ቤት አድርግ ቢባል እሺ የሚል? ማንም ለዚህ አይመዘገብም። ይልቁን የመንቀሳቀስ፣ የመናገር፣ የመምረጥ መብቱ ተከብሮለት ደረቅ ዳቦውን በነጻነት እየበላ ወይም ቆሎውን እየቆረጠመ በቤቱ ኩርምት ብሎ ቢተኛ ይመርጣል። ይህ የሚያሳየው የሰው ልጅ ለነጻነቱ ታላቅ ክብርና ቦታ እንደሚሰጥ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣን ኮርቻ ላይ ተኮፍሰው ለመዝለቅ የሚያስችላቸውን ቀለብ ለሚቆርጡላቸው ኃያለን መንግስታት ልማታዊ መንግስት የሚያስመስላቸውን ተውኔት ቢሰሩም ሃገራችን ውስጥ  ግን ህዝባችን በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ በመማቀቅ ላይ ይገኛል።  ለዕለታዊ ፍጆታ የሚሆን እንኳ በቂ ዳቦም የለም። ስለሆነም የአቶ መለስ ተውኔት፣ ከተራ ጉንጭ አልፋነት የበለጠ ቦታ የሚሰጠው ቁምነገር አይደለም።

አበበ የገለጸው ይህንን ሃቅ ነው። ነጻነት ያስፈልገናል! ታዲያ፣ ያ…. አበበ የተናገረበት ቅጽበት አቶ መለስን፣  እንደውሻ ጭራ አስቆልፎ፣ አስደንግጦና አዋርዶ በዋሽንግተኑ ኢምባሲያቸው ውስጥ የተደገሰላቸው ግብር ላይ እንዳይገኙ እፍረት ውስጥ ጥሏቸው ወዲያውኑ አስፈርጥጦ  ወደ አገር አስመልሷቸዋል። ደቡብ አፍሪካም ውስጥ በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን እንዲሁ አንገታቸውን ደፍተዋል። የአበበን መልዕክት ለወደፊት ትግላችን መፈክር  አድርገን በተጠናከረ ሁኔት በአንድነት መንቀሳቀስ ይጠበቅብና። ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ እንኳን አገራችን በምትገኝበት የአፍሪካ አህጉር ለዘመናት ተንሰራፍተው የነበሩ አምባገነኖች በቱኒዚያ፣ በግብጽና በሊቢያ በሕዝባዊ አመጽና መነሳሳት ተገርስሰው ወድቀዋል።  በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጭቆና  በእነዚህ አገሮች ውስጥ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር እጅግ የከፋና የተባባሰ ነው።  ከዚህም በተጨማሪ የወያኔ በትር ያላረፈበት ዜጋና የሕብረተሰብ ክፍል ስለማይገኝ ኢትዮጵያውያን ተባብረን የመለስ ዜናዊን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ከስልጣን አውርደን  በምትኩ ሁሉን ኢትዮጵያዊ የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንመሰርትበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ አሁን ነው እንላለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!