ግጥም ብጤ፤ ተዉት አትምክሩት (አቤ ቶኪቻው)
ዛሬ የግጥም አዚም በላይ ላይ ሰፍሮ ነበር። (እውነቴን ነው አይሳቁ ወዳጄ…) ታድያ ውረድ አትውረድ ስታገል ከቆየሁ በኋላ በዚህ መልኩ ግጥም ሳይሆን ግጥም ብጤ ሆኖ ወረደ። ታድያ ከእርስዎ ደብቄ አጀንዳዬ ላይ የማስቀምጠው ምን ጉዳይ አለኝ…? አልኩና እነሆ በረከት አልኩኝ…!
ማሳሰቢያ ይህንን ግጥም ለየት የሚያደርገው ግልፅነት እና ተጠያቂነት በተሞላበት መልኩ እርማቱ ፊት ለፊተችሁ መደረጉ ነው…!
ርዕሱ ምን ይሁን…? በነገራችን ላይ ለግጥም ርዕስ ማውጣት ከባዱ ስራ እንደሆነ እውቅ ገጣሚያን ሁሉ ሲናገሩ ሰምቼ አውቃለሁ። ስለዚህ ርዕሱ ቢከብደኝም ብርቅ አይደለም ማለት ነው። “ኦ… ርዕስ ከየት አለህ አንጀት አርስ…” አያችሁልን ግጥም እንዴት እንደሚዥጎደጎድልኝ…! ዛሬማ ወሬዬ በሙሉ በግጥም ሳይሆን አይቀርም። ለማንናውም ርዕሱን ምን ልበለው….? በቃ ባዶውን ከሚሆን፤ “ተዉት አትምከሩት” ብዬዋለሁ። እንጀምር…
ተዉት አትምከሩት
ተዉት አትከልክሉት ያብዛብኝ መከራ።
ችግሬን ያግዝፈው እንደ ዳሽን ጋራ!
ይዝለፈኝ፣
ያሳደኝ፣
ያግዘኝ፣
ይግረፈኝ፣
ዝም በሉት ብቻ፤
ያረገኝ መጫወቻ።
“ይሄን አስተካክል ይሄን ባክህ አርቅ” ብላችሁ አትምከሩት
ብትመክሩም ላይሰማ
ምን አስጨነቃችሁ ለዚህ ለገገማ… (… እዚህ ጋ የምር ሳቄ ነው የመጣው። “በግጥም የተማርናቸው እነ ቃላት መረጣ ምናምን የለም እንዴ…?” ብለው እርስዎ ወዳጄ አጓጉል ሲተቹኝ ታወቀኝ። ሌሎችም “ሆድ ያባውን ግጥም ያወጣዋል” ብለው ሲተርቱብኝ ወለል ብሎ ተየኝ። ይቅርታ ጠይቄ ቀጥሎ የተሻለ ስንኝ ለማምጣት እሞክራለሁ…!
“ይሔን አስተካክል ይሄን ባክህ አርቅ” ብላችሁ አትምከሩት።
ብትመክሩም ላይሰማ፣
የሚያደርገው ሁሉ በርሱ ቤት እውቀት ነው፤
የመሰልጠን ማማ!
ስለዚህ ዝም በሉት ለማረም አትሹ፣
ላይሰማችሁ ነገር፤ አፍ አታበላሹ፣
ቃል አታኮላሹ፣
ለእርሱ ሽብር ወሬ ለእርሱ ድንፋታ፤
መልሱ ነው ፀጥታ፣
ዝም ያለ ዝምታ።
ያንጠባጥብ በደል፤
ያጠራቅም መከራ፤
ፅዋዬ እስክትሞላ፤
ያኔ እርሱን አያድርገኝ!
አይኑን አያሳየኝ።
የበደል ፅዋዬ ሞልታ ከፈሰሰች፣
እንኳን እርሱን እና አለም ታፀዳለች!
(ይሄን እርሱም ያውቃል)
ስለዚህ ዝም በሉት ያብዛብኝ መከራ፣
ጠራርጋ የምትወስደው ፅዋዬ እስክትሞላ!
ትንሽ አመረርኩ አይደል…? እንግዲህ ምንም ማደረግ አይቻለም የግጥም ውቃቢ በላይዎ ላይ ሲያድር በል ያልዎትን ነው የሚሉት። እናም ይህንን የተናገረው በላዬ ላይ ያደረው ነውና! መረረ ጣፈጠ ለእርሱ ትቻለሁ!
Filed under: Uncategorized
![]()