የ “ኢሳት” የዜና ማእከል እና “የማህበረ ቅዱሳን ጊዜያዊ ጋብቻ! ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

ሙሉውን የጽሑፉን ይዘት ከማንበብዎ በፊት÷

  1. ጸሐፊው በጽሑፋቸው ውስጥ የጠቀሱትን የዜና ማዕከል “ማህበረ ቅዱሳን” በመባል ስለሚታወቀው መንፈሳዊ ካባ ያጠለቀ ጸረ ቤተ-ክርስቲያን ጸረ ሀገርና ጸረ ትውልድ በተደጋጋሚ ሽፋን በመስጠት ጽድቁን በዜና መልክም ሆነ በሐተታ ተጠቃሹ የዜና ማዕከል ለአድማጮች ያቀረባቸውን ፍጹም ሚዛኑ የሳተና የተንጋደለ ዘገባ ብቻ በማስመልከት ያነጣጠረ ለመሆኑ÷
  2. አሁንም በጽሑፉ ውስጥ የተካተቱ ማናቸውም ሂሶችና ጥያቄዎች “ማህበረ ቅዱሳን” በማስመልከት እጃቸውን የጨመሩ የክፍሉ ሰራተኞች/ግለሰቦች እንጅ የመደብሩ ባለደረባዎች በመላ የማያጠቃልል ለመሆኑ÷
  3. የጸሐፊው ዓላማም ሆነ የጽሑፉ ግብ በማጣመም ሌላ አንድምታ በመስጠትም “በኢሳት” የመጣ በዓይኔ ብሌን” በማለት አካኪ ዘራፍ የሚልም ስለማይታጣ  “ኢሳት” “ማህበረ ቅዱሳን” በተመለከተም ሆነ “ደጀ-ሰላም” በመባል የሚታወቀው በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያንና በተከታዮችዋ ላይ ሁከትን ለመፍጠር ታጥቆ የተነሳ የማህበሩ (“የማህበረ ቅዱሳን’) በአንድ ራስ ላይ ተደራቢ ምላስ/ልሳን ሆኖ የበቀለ ድረ ገጽ ዋቢ እያደረገ የሚዘገባቸው ዘገባዎችና የሚያቀርባቸው ማናቸውም ዓይነት ዘተታዎች ፍጹም ከእውነት የራቁና ነጭ ሐሰት መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በወንጀል የሚያስጠይቅ ስራ እየሰራ ለመሆኑ÷
  4. በተጨማሪም “ኢሳት” ጭራሽ “የማህበረ ቅዱሳን” ልሳን አስኪያስመስልበት ድረስ እየሄደበት ያለውን አካሄድ ማለት ነፍሰ ገዳይን የመታደግ ስራ ትክክል አለመሆኑ ለማሳየት ምንም በማያሻማ ግልጽ በሆነ አማራኛ የቀረበ ጽሁፍ ለመሆኑ÷
  5. በመጨረሻም “ለኢሳት” ለብቻ ተብሎ የሚታለፍ እውነት አለመኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአንደበት የሚወጣ ቃል የሰውን ልብ ከማሸፈት በላይ ህይወትም ይቀጫልና በተለይ የጉዳዩ ቀዳሚ ባለቤቶችና ሰላባዎች ሊሆኑ የሚችሉ/የምንችል የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን እምነት ተከታዮችና ምእመን ሰላም ለመጠበቅ ሲባል ይህን ጽሑፍ ሊዘጋጅ ግድ ብለዋል። ደግሞም ሰው ይከበራል እንጅ ስጋ ለባሽ ሆኖ የሚፈራ፣ አምልኮም የሚገባው አንድስንኳ አለመኖሩን በሚያምን ልብ ተጻፈ።  ጽሑፉ ልዩነትን የሚያሳይ እንጂ የክስ ደብዳቤም ሆነ የስምታ ማመልከቻም አይደልም።

ከሰርጎ ገቦች የተነሳ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ/ያን አስተዳደራዊ ማእከል ላይ ስለተፈጥረውና ስላለው ችግር በማስመልከት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ዜናዎችን በማቅረብና ሰፊ ሐተታዎችን በመስጠት ይታወቃል። ይህ መቀመጫው ሆላንድ አምስተርዳም ያደረገ እንዲሁም በአሜሪካን ክፍለ ግዛት ዋሺንግተን ዲሲ በመሆን ከሚያሰራጫውቸ ሀገራዊ ዜናዎች በብዙዎቻችን ዘንድ የታወቀ ለመሆኑ አልጠራጠርም። ስለ መረጃው ማእከል ከማንም የተለየ የጠለቀ ቅርበትም ሆነ ስለ ጣቢያው የተሻለ እውቀት ባይኖረኝም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሚኖረኝ የጊዜ ክፍተት አልፎ አልፎ አድማጭ ነኝ። የኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድ ግለሰብ የሃሳብ የበላይነት ከሚንጸባረቅበት ብቸኛ መንግስታዊ የዜና ማሰራጫ ተገላግሎ አማራጭ እድል ማግኘቱም ደስታዬ ወሰን የለውም። ታድያ ይህ መቀመጫው በምእራቡ ዓለም ያደረገ “ኢሳት” በመባል የሚታወቀው የዜና ማእከል በብዙ የአገልግሎት ዘርፎቹ ሁሉንም የሚያስማማና ሁሉንም ያቀፈ ስራዎቹን ውሃ የሚቸልስ ስራዎችን ሲያቀርብ ከአንድም ሁለቴም በተደጋጋሚ መፈፀሙ በተለይ ለጉዳዩ ቅርበት ባላቸው የቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ልጆችና ባለ አደራዎች ዓይን ሲታይ ነገሩ በቀላሉ የማይታለፍ ሆኖ በመገኘቱ ለመተራረማና እርስበርስ ለመማማር ለማስታወሻም ያክል አንድ መለቱ አስገዳጅ ሆኖ ተገኝተዋል።

የነገሩ ስር ተጠቃሹ የዜና ማዕከል ኢ/ት/ኦ/ተ/ቤ/ያን በተመለከተ ለሚያስተላልፋቸው/ለአድማጭ የሚያደርሳቸው በምስል የተቀረጹ ዘገባዎች  በዋናነት “ደጀ ሰላም” በመባል የሚታወቀው ሰምዓ ሐሰት መካነ ድር እንደ ዋቢ መጠቀሙ አንድ ነው። በነገራችን ላይ የዜና ማእከሉ እንደ አንድ የመረጃ ማሰረጫ ማዕከል ሚዛኑን በጠበቀ ሁሉንም በሚያንጽ መልኩ ዘገባዎችን ማቅረብ ሲገባው “ባለቤትነቱ በውል የማይታወቅ” የሰፈርተኞች አሉባልታ ማስተጋባት ምን ይሉት የሞያ ሃላፊነትና ግዴታ ነው ለማለት እንጅ “ኢሳት” ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን በተመለከተ ለምን  ይዘግባል መዘገብ አይገባውም እየተባለ አይደለም ያለው። “ኢሳት” ድምጽ ሆኖ ካልዘገበ ሌላ ማን ይዘግብ!

የመረጃ ማእከሉ ነፃና ገለልተኛ ሲል የዘራውን እያጨደ ስለሚገኘው፣ በብዙዎች ደም ተጠያቄ የሆነው፣ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ጥንታውያንና ታሪካውያን ቅርሶችዋ በማውደማና በመዝረፍም አቻ የማይገኝለት ሕጋዊ ሽፍታ፣ የሰው ለውጥና ዕድገት ደም የሚያስቀምጣቸው፣ ለሀገርና ለወገን ኪሳራ የሆነውን ትውልድ የሚፈለፍል ቆፍቁፎም የሚያሳድግ፣ እነሱ ያልተካፈሉበት ስራ ሁሉ ለመኮነንና ለማፍረስ የማይቀደሙ፣ የእግዚአብሔር እጅ የከበደችበት፣ በሞት አፋፍ ላይ ስለሚገኘው የሰው እባብ ስለ “ማህበረ ቅዱሳን” ጽድቅ መዘገብና ሽንጥህን ገትረህ መከራከር ከሆነ÷

 ዋጋ በከፈልኩበት!

v  እንደ ፌስታል እየተንጠለጠልኩ ወደ እስር በተወረወርኩበት፣

v  ዜግነታዊ መብቴን ተግፎ ከትምህርት ገበታዬ በተፈናቀልኩበት፣

v  በተወልድኩባት እትብቴም ተቆርጦ በተቀበረባትና በገዛ ሀገሬ በተገፋሁበት፣

v  በተዋረድኩበት፣

v  በተንገላሁበት፣

v  በተደበደብኩበት፣

v  በተረገጥኩበት፣

v  በቆሳሰልኩበት፣

v  አባት እንደሌለው በስደት ምድር ቁምስቅሌን ባየሁበት፣

v  በኬንያ ጎደናዎች በወደቅኩበትና በተጣልኩበት፣

v  ወላጅ አባት እናቴ ወንድም እህቶቼ በትልቁም እናት ሀገሬ ጥዬ ለግዞት ህይወት በተዳረኩበት አጀንዳ ላይ እውነት የማይዋጥለትና ሲነገረውም ጆውን የሚያሳክከው ምንስ ቢሆን ማንም ሙሉጌታ ተኝቶ ያድራል ማለት ሲበዛ የዋህነት ነው። ደካማ መስዬ የታየሁት ግለሰብ ሆነ ድርጅትም ቢኖር መፅሐፍ ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሽ ለብርት ሕዝብ ይሆናል እንዲል ጥጉ እንዲሁ ነው። የተደገፍኩትም እንደ ሻምባቆ የሚሰበረው ከሁኔታዎች ጋር የሚለዋወጠውን ሰው ሳይሆን ብቻውን ታላቅ ተኣምራትን ያደረገ/የሚያደርግ፣ ሰማያትን በብልሃት የሠራ፣ ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፣ ለፀሐይ ቀንን ያስገዛው፣ ከበኵራቸው ጋር ግብጽን የመታ እስራኤልንም ከመካከላቸው ያወጣ፣ በጸናች እጅ በተዘረጋችም ክንድ የኤርትራን ባሕር በየክፍሉ የከፈለ እስራኤልን በመካከሉ ያሳለፈ፣ ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ፣ ሕዝቡን በምድረ በዳ የመራ፣ ታላላቅ ነገሥታትን የመታ፣ ለባሪያው ለእስራኤል ርስት የሆነውን እግዚአብሔርን ነው።

እንግዲህ ይህ የመረጃ ማእከል ከተቋቋመበት ዓላማ በማፈንገጥ በተለይ “ማህበረ ቅዱሳን” በተመለከተ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተደጋጋሚ ሽፋን በመስጠት የሚያስተላልፋቸው ዘገባዎች ፍፁም ከእውነት የራቀ፣ ጭብጥ የሌለው፣ ተጠያቂነት በማይፀባረቅበት፣ ሃላፊነት የጎደለበትና ሲበዛም የጋዜጠኝነት የሞያ ስነ ምግባር በሚያጎድፍ መልክ የቀረበ ለመሆኑ ልብ ብሎ ላስተዋለ ሰው ምንም አያጠያይቅም። ቁርጡ “ኢሳት” ለእኔ ለተገፊው ግለሰብ ስለ ሰላቢው ማህበር “ማህበረ ቅዱሳን” እንዲነግረኝ አይጠበቅበትም። (ደጀ ሰላምን በተመለከተ በሚቀጥለው ጽሑፌን እመለስበታለሁ)

ይህ በዋናነት “በኢሳት” ዜና ዘጋቢዎችና አንባቢዎች ሰፈር ዋቢ እየተደረገ የሚጠቀሰው መካነ ድር ፀሐፊው ማን ነው? ለዜናዎቹና ዘገባዎቹ ሐላፊነት የሚወስድ ግለስብም ሆነ ድርጅትስ ማን ነው? ለሚለው እጅግ ቀላል ጥያቄ “የኢሳት” ባልደረቦች በተለይ ማህበሩን በተመልከተ ጊዜያቸውን ሰውተው ብዙና ጥቂት የሚሉትን ለእነዚህ መሰል ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ይዘው እንደመጡ ተስፋ አደርጋለሁ። የሌሎቹን ባላውቅ እንደነ አበበ ገላውና ልጅ ተክሌ የመሳሰሉ በውጭ ዓለም የከፍተኛ ተቋማት ያለፉ ግለሰቦች የሚገኙበት ቤት አንዴት ነው እንዲህ ያለ ነገር በተደጋጋሚ ሊከሰት የሚችለው? ተጨማሪ ጥያቄ ነው (ስለማውቀው ተናገርኩ እንጅ ሌሎቹ አልተማሩም እያልኩ አይደለም)። ማንስ ይዘግበው ማንም የተገኘውን የማቀረብ መብት አለን ከተባለ ደግሞ ከዚህ በሃላ ሙጉቱ ሞያ ነክ መሆኑ ነው። ያገኘኸውን ማግበስበስስ ተገቢ ነው ወይ ባይም ነኝ? ከሆነ ደግሞ የሌላውን ወገን ድምፅስ ለምን አይሰማም? ነፃ የመረጃ ማዕከል ተብሎ የሚነገርለት ፍትሃዊና ሚዛናዊ መሆን አይጠበቅበት? አንድ የመረጃ ማእከል የህዝብ አይንና ጆሮ ነው ሲባልስ የማን ጥቅም ማዕከል አድርጎ ሲሰራ ነው? የሕዝብና የሀገር ወይስ የጥቂት አማፅያን?

እዚህ ላይ ቀለል ያለ ነገር ግን በቀላሉ የማይታለፍ ሞያዊ/101 ጥያቄ ማንሳት እወዳለሁ። ይኸውም ይቅር አንድ በተቋም መልክ የተደራጀና በምእራቡ የዓለማችን ክፍል መቀመጫው ያደረገ ቀርቶ ሃላፊነት ወስዶ ለሚሰራዎች ስራዎች አንድ በዋቢም ሆነ በምንጭ ደረጃ ለመጠቀም ቢያንስ ቢያንስ ቀዳሚው የመረጃ አካል ለሚያቀርባቸው ዘገባዎች በሕግ ሃላፊነት የሚወስድ፣ ህጋዊነቱ የተረጋጋጠለት፣ የሪፖርቱ ፀሐፊም ሆነ የዘገባው አጠናካሪ አካል በውል የሚታወቅ፣ ሓላፊነት የሚወስድ፣ ዓላማውና ግቡ በግልፅ የሚታወቅ፣ተአማኝነት ያለው መሆኑን ሳይረጋገጥ እንዲሁ እገሌ እንዳለው ተብሎ ዜና ማለትስ የማን ንቀት ነው? ታማኝ ምንጮች እንደዘገቡት፣ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት፣ ሮይተር እንደዘገበው ማለቱ አይበቃም? አንድ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ያለፈ ሰው ይቅርና እንዲሁ ያደገውን የጋዜጠኝነትን መሰረታዊ ስልጠና የወደሰ ሰው ይህን መሰል መሰረታዊና አንኳር ስነ-ምግባር እንዴት ይስተዋል? በመረጃ የሚያምን ተብሎ የተነገረለት “የቃሊቲው መንግስት” የሚለውን መጽሐፍ የፃፈ ሰው ባለበት (መጽሐፉ ደርሶኝ እያነበብኩት ሰላለሁ ነው) እንዴት ነው እንዲህ ያለ ጉልህ የሆነ ስህተት የዜና ማሰራጫ ማእከሉ ሁነኛ መታወቂያ ሊሆን የሚችለው?

እንግዲህ በዚህ አጋጣሚ አንዳንድ የኢሳት ባለደረቦች ለማህበሩ እየዋለት ያሉትን ውለታና እይደረጉት ያሉት ቅምጥል ህጻን ልጅ የማባበል ያክልም እሽርሩ ማለቱ “ማህበረ ቅዱሳን” መሞቴ አይቀር አጥፍቼ ልጥፋ በማለት ፀሐይ ሳለ በቀን የታወሩት አባላቶቹ አሰልፎ ሊፈጥረው የሚችለውን ግርግር ወደ ምኒልክ ቤተ-መንግስት ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ገና ለገና ከወዲህ ታምኖበትም እንደሆነ በዚህ አጋጣሚ ግምቱ ከቅጀት የማያልፍ ትልቅ ስህተት መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ። ማህበሩም እንደሆነ የሚይዘው የሚጨብጠው በማጣት የተቃዋሚዎች ደጋፊ ስለሆንኩ ነው፣ ለቤተ-ክርስቲያን ስለቆምኩ ነው፣ በዚህ ስለመጣሁና በዛም ስለወጣሁነው፣ የሚለውም አጥቶ ብረት ስለዋጥኩ ነው ቢል ከተዘረጋች የጽድቅ እጅ የሚያተርፈው አንዳች ሃይል የለም። አሜን!! ቁርታችን እንወቅ አይደለም የጥቂቶች ጩኸትና ሁካታ ስድስ ቢሊዮን ሕዝብ ሰልፍ ወጥቶ አይሆንም! ቢል የእግዚአብሔርን እጅ አይመልስም አይከለክልምም።  ታድያ በማወቅም ባለማወቅም ቢሆን በዚህ ሰልፍ መኸል የሚገባ ማንኛውም አካል ቢኖር በግብፅ ምድር የተገለጠውን መልአክ ሰለባ መሆኑን ሳይዘነጋ ያድርገው።

ለማጠቃለል ያክል የጸሐፍትና ፈሪሳውያን ገጽታ በከፊል ላውሳችሁ እወዳለሁ እነዚህ ሰዎች ጌታ ኢየሱስ በነበረበት ዘመን በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ መፈራት፣ ተቀባይነት ያላቸውና የላቀ የክብር ስፍራም የሚሰጣቸው ሰዎች ሲሆኑ በተመሳሳይ ትልቅ ትምክህትም የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። በጥቂቱ የተመለከትን እንደሆነ  ኢየሱስ የመጣበት ዓላማ በሚያከናውንበት/እውነቱን በሚያስተምርበት ወቅት የአይሁድ ስርዓትና ወግ፣ በሙሴ ሕገ ኦሪት ላይ ያነጣጠረ በአጠቃላይ ብሉያት መፃሕፍትን በተመለከተ ቃል ከአፉ ያወጣ እንደሆነ እኛ ጋር ሳይደርስ ሕዝቡ ራሱ እንደተራበ አውሬ ቦጫጭቆ ይገድለዋ፣ ይውጠዋል በማለት ይታበዩና የልብ ልብ ይሰማቸው ስለነበር በዋለበት እየተገኙ ኢየሱስን ለማሳጣትና በወጥመዳችው ውስጥም ለማስገባት  ያላደረጉት ጥረት አልነበረም።

በተጨማሪም የእነዚህ አፅራረ ፅድቅ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ትልቁ መታመኛቸው ሕዝብ እኛ ያልነው ይሰማል ከእኛ እውቅና ውጭ ምንም የሚፈጠር ተአምር የለም አይኖርም! የሚል ፈሊጥም ስለነበራቸው ጊዜው እስኪደርስ ድረስ ደረታቸው ገልብጠውና ምላሳቸውን አስረዝመው ለመዘባበት ተችሎአቸው እንደነበር ከቅድሳት መፃህፍት ለመረዳት ይቻላል። ኢየሱስ ይህን እያወቀ በሕዝብ ፊት የተቃወማቸው እንደሆነ ግን ሊገጥመው የሚችለውን አደጋ ወደ ጆሮው ጠጋ በማለት ትሰማለህ ከእሳት ጋር አትጫወት! እንደማለት ይፍክሩበትም እንደነበር ነው። በተመሳሳይ “የማህበረ ቅዱሳን” ጉዳይም ሆነ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ጊዜያዊ አለመረጋጋት “ደጀ-ሰላም” በመባል የሚታወቀው ጋጠወጥ መካነ ድር ዋቢ በማድረግ እንዲሁ “ነጩን አጥቁረን ማሩንም አምርረን ሲፊ ጊዜም ሰጥተን ደግመን ደጋግመን ያሻን ብንዘግብ እስቲ በእኛ ላይ/በጣቢያው ላይ አፉን የሚከፍትም ሆነ ጣቱን የሚሰድ ማን ሱሪ የታጠቀ ወንድ ነው” በሚል አንድምታ ከሆነ በእውነቱ ነገር መጪው ሰፊ ጊዜ ሱሪ የታጠቀ ማን እንደሆነ ፍርዱ ለሕዝቡ የምንተው ይሆናል በማለት ለዛሬ ጽሑፌን በመስጋና ልቋጭ።

ከጽሑፉ እውነተኝነትና ቀጥተኛነት የተነሳ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ/በብዕር ስም በጸሑፉ አዘጋጅ ላይ ለሚሰነዘረው ማንኛውም ዓይነት የዓይን ቅንድብ ማነቃነቅ የማይቻለውን ዘለፋና መሰረተ ቢስ አሉባልታ ጨምሮ ደቀ- መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥምና ሊመጣ ያለውን ልክና ገደብ ያለው ሁሉ እንደ አመጣጡ በጸጋ እንደሚቀበሉ ሲገልፁ በአክብሮት ነው። በዚህና ተጓዳኝ በሆኑ ርእሰ ጉዳዮች ጸሀፊው በየትኛውም መድረክ ሃሳባቸውንና ተሞክሮአቸውን ለማካፈል ለሚቀርብላቸው ጥሪ ዝግጅነታቸውን እየገለጹ አስቀድመውም ለማመስገን ይወዳሉ።

 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

[email protected]

May 19, 2012

United States of America