እርቅ፣ ይቅርታና ብሔራዊ ንስኃ ያስፈልገናል
በፍቅር ለይኩን
ከዛሬ ወር በፊት አንድ ሰው በጎንደር በደባርቅ ከተማ በአንዲት ቀበሌ ውስጥ ድል ያለ ድግስ ደግሶ ብሉልኝ ጠጡልኝ በማለት የመንደሩን ሰው ሁሉ በደስታና በፈግግታ ተውጦ ቁጭ ብድግ እያለ ያስተናግዳል፡፡ የዚህ ደስታና ድግስ ምክንያቱ ደግሞ ድግሱን ያዘጋጀው ሰው በደርግ ዘመን ጸረ አብዮተኛ ተብሎ ተይዞ ከሌሎች ሰዎች ጋር እግራቸውና እጃቸው በእገረ ሙቅ/በእግር ብረት ተጠፍሮ በአቀርቢያቸው ወደሚገኘው የሊማሊሞ ገደል ውስጥ ሊጣሉ ይወሰዳሉ፤ ወደ ገደሉ እንደደረሱም የወሰዷቸው አብዮታዊ ታጣቂ ጓዶች እያደፉና እያዋረዱ ወደ ገደሉ ያለምንም ርኅራኄ ይወረውሯቸዋል፡፡
የዛሬው የዚህ ድግስ ባለቤትም ወደዚህ ገደል ሲጣል ባላወቀው ተዓምር የፊጥኝ ከታሰረበት እግር ብረት የተነሳ ከአንድ ዛፍ ላይ ይንጠለጠልና ወደ ገደሉ ቁልቁል ከመወረድ ይድናል ግና በዛፉ ላይ ሆኖ ራሱን ማዳን የሚችልበት አማራጭ አልነበረውም፤ ምክንያቱም እግሮቹም ሆኑ እጆቹ የፊጥኝ በእግር ብረት ታስረዋልና ያለው አማራጭ በዛው እንደተንጠለጠለ ሞቱን መጠበቅ ወይም በሆነ ተዓምር ሰዎች ደርሰውለት እንዲያድኑት ተሰፋ ማድረግ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ጅው ካለ ገደል ቁልቁል ተፈጥፍጦ ከመሞት አሊያም ደግሞ እንደ ውሻ ክራንቻ ጥርስ ከሾሉት የሊማሊሞ ዐለቶች የሞት ፍርድና ከገደሉ በታች ከሚገኙት እንደ ነብርና ጅብ ካሉት አውሬዎች መቦጫጨቅ መትረፉ ለአፍታ እረፍትን ቢሰጠውም እንዲህ በዛፍ ላይ እንደተንጠለጠለ ከሞት ጋር ተፋጦ ምን ያህል ሰዓታትና ቀናት መቆየት እንሚችል ግን እርግጠኛ አልነበረምና ጭንቀቱ በቃላት የሚገለጽ አልነበረም፡፡
ከለሁለት መራር የመከራና የነፍስ ውጭ የነፍስ ግቢ ቀንና ሌሊት በኋላ ሁለት የደባርቅ ሽማግሌዎች በዛ መንገድ ሲያልፉ ያዩታል እናም ቀረብ ሲሉት በሕይወት ያለ የሚንቀሳቀስ ሰው ነው፡፡ ራብና የውሃ ጥም ባደከመውና ባሰለለው ድምፅ እባካችሁ አድኑኝ ይላቸዋል፡፡ እነዛም ሰዎች ከተንጠለጠለበት ዛፍ ላይ አውርደው ከቋጠሩት ስንቅ አቃምሰውና ውኃ አጥተውት ካረጋጉትና ነፍሱን ከመለሱት በኋላ በምንም ምክንያት በዚህ ዛፍ ላይ እንደተንጠለጠለ ይጠይቁታል እርሱም ጸረ አብዮተኛ በሚል ሰበብ ወደ ገደል ሲወረወር በተዓምር በዛፉ ተንጠልጥሎ መትረፉን ይነግራቸዋል፡፡
እነዛም ሰዎች ዥው ባለው የሊማሊሞ ገድል የወደቁ ወጣቶችን እያሰቡ ልባቸው በሐዘን እየደማ ‹‹አይ ኢትዮጵያ ልጆችሽ እንዲህ የገደል፣ የአውሬ፣ የጥይትና የአሞራ ሲሳይ ይሁኑ…!›› በማለት እንባቸውን ወደ ጸባዖት ጢቅ በማድረግ ሐዘናቸውን ወደ አምላክ ካሰሙ በኋላ ወደ ትግራይ መንገድ ይሸኙታል፡፡ ይህም ሰው ከትግራይ ወደ ሱዳን ይገባል ከዛም ወደ አሜሪካ ይሻገራል፡፡ በአሁን ሰዓት የዚህ ታሪክ ባለቤት ሰው በአሜሪካ አገር ትምሕርቱን ተምሮ ኑሮውን በዛ አደላድሎ በዴንቨር ኮሎራዶ በሕክምና ሙያ ላይ ተሰማርቶ የሚኖር ነው፡፡ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ይህን አስገራሚ ታሪኩንና ከሞት የተረፈበትን ቀን ለመዘከር ሲል ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ደባርቅ ይመጣል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ወደሊማሊሞ ገደል የተጣለበትና በዛፉ ላይ ተንጠልጥሎ የተረፈበት እለት የተወለደበት ቀን በመሆኑ በሀገሩ በደባርቅ በተወለደበት ቀዬና በወገኖቹ መካከል ሆኖ ሁለቴ የተወለደበትን ቀን በምስጋና ለማሰብ ሲል ነበር ከሀገረ አሜሪካ ወደ ደባርቅ ወደ ትውልድ መንደሩ ከበርካታ ዓመታት በኋላ የተመለሰው፡፡ ይህን አሳዛኝ ታሪክ ደግሞም አስደሳች ዜና የዘገበው በእለተ ሰኞ በማለዳው የፋና ራዲዮ የዘጠና ደቂቃ ፕሮግራም ነው፡፡ ዜናውን ለፋና ያደረሰው ደግሞ የጎንደር ፋና ኤፍ ኤም 98.1 ባልደረባ ነው፡፡
ይህን ዜና በሰኞ ማለዳ በሐዘን በዳመነ መንፈስ ከሰማሁ በኋላ በየጓዳው ስንት ያልተነገሩ እና ያልወጡ ግፎችና በደሎች በኢትዮጵያችን እንዳሉ ተሰማኝ፡፡ እናም በሰማሁት ታሪክ ላይ የተሰማኝን ለማለት ውስጤን አንዳንች ስሜት ገፋፋው እናም ብዕሬን ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ውስጥ ሆኜ አነሳሁ፡፡
በዘመነ ደርግ በዚህ ዓይነት አሰቃቂ ግፍና ሞት የረገፉ የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች ብዙ ሺህ መሆናቸው ብዙዎቻችን የምናውቀው ነው፡፡ በበራቸው ደጃፍ በየመንገዱ በጥይት አረር ረግፈው ደማቸውን እንደ ኤልዛቤል ውሾች የላሱት ወገኖቻችንን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ አስክሬናቸው እንኳን በክብር እንዳይርፍ በጥይት በተደፉበት የአውሬና የአሞራ ሲሳይ የሆኑ ወገኖቻችን ስናስብ ዛሬም ልባችን ያዝናል፣ ነፍሳችንም በሐዘን ይመታል፡፡ ዘጠኝ ወር በማሕጸናቸው ዓለም ለተሸከሟቸው እናቶች ልጆቻቸው ለተገደሉበት የጥይት ዋጋ እንዲከፍሉ በተጠየቁበት፣ ቅጥ የለሽ ግፍና ኢሰብአዊነት በነገሰባት እና የምስኪኗ ኢትዮጵያ እናቶች ወላድ ማኅጸናቸውን በረገሙበት፣ በእንባ ጎርፍ በታጠቡበት በዛ ቀውጢ ወቅት፣ ሀገሪቱ በደም በጨቀየችበትና ምድሪቱ አኬልዳማ በሆነችበት፣ በአራቱም ማእዘናት አስፈሪ ጣእረ ሞት በንዣበበበት የእምዬ ኢትዮጵያ የጣእርና የምጥ ወቅት፡-
የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፣
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ፡፡
ተብሎ ሙሾ በተደረደረባት ኢትዮጵያችን በአብዮት ጨካኝ ሰይፍ ወንድ ሴት ወጣት አረጋዊ ሳይባል የሺህዎች ደም በከንቱ በፈሰሰባት አገር በዳይም ተበዳይ ከልብ የሆነ ይቅርታ ሳይጠያየቁና ብሔራዊ እርቅና ምሕረትን ለማውረድ በተገደርንበት ሁናቴ ዛሬም የግፍና የበደል ታሪካችንን እሹሩሩ እያልን ለሌላ በቀል ሌላ ግፍ ተረኞችን የምናስተናግድበት የጉድ ምድር ሆናለች ሀገራችን ኢትዮጵያ፡፡ ዛሬም የብዙ ሺህዎች የግፍ እንባና ደም እንደ አቤል ደም የፍርድ ያለህ፣ የፍትህ ያለ እያሉ ወደ ጸባዖት ጩኸታቸውን እያሰሙ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግፍ በተፈጸመባት ምስኪን ኢትዮጵያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዚህ ድርጊት ፈጻሚ የነበሩ ሰዎች በግልፅ በሆነ መንገድ በአደባባይ ይቅርታ የጠየቁበትና ተበዳዮችን ተገቢውን ካሣ ባልካሱበት ሁናቴ አለመኖሩና አንዳንዶችም የሠሩት ነገር ትክክል እንደሆነና ማንም በግፍ የተገደለ ሰው እንደሌለና የተወሰደው እርምጃ ሁሉ አብዮታዊና ፍትሐዊ እንደሆነ ያለ ምንም ኸፍረት እየነገሩንና እየጻፉ ባለበት ሁናቴ ቂም በቀል፣ ግፍ፣ መከራና ጉስቁልና ዛሬም በምድራችን ቀጥሏል፡፡
የዚህ ጹሑፍ ዓላማ ያለፈውን በደልና ግፍ በማውሳት የተገጂዎችን የሐዘን ቁስል እንዲመረቅዝ ለበቀልና ለጥላቻ እንዲነሳሱ ለማድረግ አይደለም፤ ግና ዛሬም በዚህ ድረ ገጽ ላይ ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ የደብቡ አፍሪካውን የቁርጥ ቀን ልጅ የይቅርታና የሰላም አባት የማንዴላን እና የትግል አጋሮቻቸውበደቡብ አፍሪካ ያወረዱትን የይቅርታ መንፈስ በማውሳት የደም ሸማን ጸጎናጽፋ ለምትታይ አኬልዳማ ለሆነች ኢትዮጵያችን ከልብ የሆነ ይቅርታና ብሔራዊ ይቅርታን ማወጅ እንደሚያስፈልግ ለመጠቆም ነው፡፡ ዛሬም ለበቀል ሰይፋቸውን የሳሉ እና ለሞት የሚፈላለጉ ሕዝቦች ባሉባት ሀገር የነገ ፍጻሜያችንና ዕጣ ፋንታችን ሲታሰብን ነፍሳችን በጽኑ የምትደክም ይመስለኛል፡፡
አስገራሚው ነገር ይህ ሁሉ ግፍ በተፈጸመባት ግን ደግሞ ክርስትናንና እስልምናን በሰላም ተቀብላ ለሺህ ዘመን ኖራለች ተብሎ በምሳሌነት በምትነሳ ምድር ያ ሁሉ ግፍና በደል ሲፈጸም፣ እንባና ደም በተቀላቀሉበት እምዬ ኢትዮጵያ እርቅ ሰላምና ፍቅር ይውረድ ብለው በአደባባይ የተናገሩ፣ የገሰጹ የሃይማኖት አባቶችንና የአገር ሽማግሌዎችን ትላንትና የት እንደነበሩና ዛሬስ አድራሻቸው የት ነው ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነው በታሪካችን የሆነው ያየነውና የሰማነው ግፍና በደል፡፡
‹‹አባቶቻችን ሲታጠቡ እስከ ክንድ ከታረቁ ከልብ!›› ይላሉና፤ ይቅርታ፣ እርቅና ሰላም በሕዝቦች፣ በመሪዎች፣ በሃይማኖት ተቋማትና በሃይማኖት አባቶች ሁሉ መካከል ይወርድ ዘንድ ያስፈልጋል፡፡ ብሔራዊ የሆነ የይቅርታ መንፈስም ያሰፈልገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ምሁራንና የታሪክ አጥኚዎች፣ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ የሕግ ተቋማትና በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ተሳታፊ የሚሆኑበት ግልጽ የሆነ በአደባባይ እርቅ፣ ይቅርታና ብሔራዊ ንስኃ ያስፈልገናል፡፡
እግዚአብሔርን ኢትዮጵያን ይባርክ!
ሰላም! ሻሎም!