የኢትዮጵያን ሪቪው ርዕሰ አንቀጽ

የኢትዮጵያን ሪቪው ርዕሰ አንቀጽ

 ቀዳሚው ትውልድ “አፍንጫን ሲመቱት ዓይን ያለቅሳል” ይላል። ይህ ስነ-ቃል ብሃራዊ ስንቅ ሲሆን  በአንድ ኣካባቢ ያለ ኢትዮጵያዊ አካል ሲነካ በሌላው በኩል ያለው ወገን ያማል! ብሎ እንዲነሳ ይነሽጣል።

ብዙሃዊት ሃገር ኢትዮጵያ በአራቱም ማእዘናት ያሉት ልጆችዋ ለጋራ ፍትህና እድገት ካልቆሙ ሁልጊዜም እንዲሁ እንዳነከሰች ትኖራለች። ባንድ ጎራ ያለው ባህላዊ ቡድን በባህሉ ወይም በሃይማኖቱ ጥቃት ሲደርስበት ዘራፍ! አፍንጫን ሲነኩት አይን ያለቅሳል ብሎ በሌላው የሃገሪቱ ክፍል ያለው ወገኑ ካልተነሳ የአንድነት ወዙ የቱ ጋር ነው? ኣንድነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ወገን እና ሃይማኖት እየለየ ጥቃት ሲፈጸም ሌላው ወገን ለወገን ደራሽ ወገንነቱን በተግባር ሲያሳይ አይደለምን?

ዛሬ የብዙሃዊት ኢትዮጵያ ባህላዊ ቡድኖች አንዴ በባህላዊ ቡድናቸው አንዴ በሃይማኖታቸው ጥቃት ሲደርስባቸው ይታያል። ለአብነት በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጭፍጨፋና ማፈናቀል እንዲሁም በአማራና በአፋር ወንድሞቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትና በእስልምና ተከታዮችና ዘንድ እየደረሰ ያለው የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በገዳማትና በክርስትና ሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚፈጸመው ግፍ ይጠቀሳሉ።

እነዚህ የባህል ቡድንንና ሃይማኖትን እየለዩና እያነጣጠሩ የሚፈጸሙ ግፎች የኢትዮጵያዊያንን የአንድነት መንፈስ ሊፈትኑ የመጡ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው። በመሆኑም እስልምናው ሲነካ ክርስቲያኑ ፣ ክርስቲያኑ ሲነካ ሙስሊሙ፣ ጋምቤላውና አፋሩ ሲነካ ሌላው ኢትዮጵያዊ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ብድግ ሊል ይገባዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህን ግፎችን በትዕግስት በስሎ ጊዜና ሰዓት ለሚጠብቀው ታላቁ ህዝባዊ ንቅናቄ የመነሻ አደባባይ ሊያደርጋቸውና ለሃያ ዓመት የተሸከመውን ትከሻውን ያጎበጠውን ብልሹ አስተዳደር አስፈንጥሮ የሚጥልበትን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ  የሚያቀጣጥልበት አውድ አድርጎ ሊጠቀምባቸው ይገባል እንላለን።

ድል ለኢትዮጵያችን!!