ህዳሴና መነኩሴ ለማንም ለምንም አይበጁም! ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
የጽሑፉ ዓላማ፥ ህዳሴ እየተባለ እልል ያለ ድግስ ተዘጋጅቶ ይበላል: ይጠጣል: ይጨፈራል ከዚህም አልፎ ከረባት ወልቆ ሱፍ ቀርቶ በምትኩ ቁምጣ ተለብሶ በአደባባይ ለጉድ ይሮጣል ይዘለላል በዚህ ሁሉ ሽርጉድና ወከባ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብን ከማታለልና ከማዘናጋት በዘለለ ይሄ ነው የሚባል ጥቅም/ትርፍ ሲያመጣ ባለመታየቱ ህዳሴም ከመነክሴ ጋር አዛምጄ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ:: ህዳሴና መነክሴ ምን ቢያገናኛቸው ይሆን ያዛመድካቸው? ለሚለው ጥያቄ ከብዙ ሺህ ዘመናት በፊት ለሆዳቸው ባደሩ የእስርኤል ነቢያትና ካህናት የተፈጸመውን ትልቅ መንፈሳዊ ክስረት/ስህተት ዛሬ ደግሞ ምንም ልዩነት በሌለው በተመሳሳይ መልኩ እንደ አዲስ (ካህናትን ከፊት ለፊት እያስቀደምክ የምትነፋዋን ጡሩምባ/ፕሮፓጋንዳ) ፖለቲካዊ ስልት ሆኖ ብቅ በማለቱና ነገሩም ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢ ሆኖ በመምጣቱ እንዲሁም ሀገርና ሕዝብ የከፋ ችግር ውስጥ ከማስገባታችን በፊት ለትምህርታችን ከተጻፈው ህያው ቃል ትምህርት ለመቅሰም በዚህ ስራ የተጠመዱ ወገኖችም ትርፍ ከሌለው ድካም ለመታደግ ነው::
ለመንደርደሪያ ያክል አንድ አስተዋይ ጸሐፊ “መነኩሴ” ሲባል ጥንት ከሚያውቁት ነገር ተለይቶባቸው በሚያዩትና በሚሰሙትም ነገርም ሁሉ ተገርመው “ምንድነው ምንኩስና?” ሲሉ በግጥም መልክ የቋጠርዋትን አብረን እናንብባት::
ምንድነው ምንኩስና?
ስናድግ ያየነው በጦቢያ:
ተቃቅፈው ነበር በጤና:
ሞትና ምንኩስና:
መነኮሰ ሞተ ነውና::
በማለት የሚጀምረው ግጥማቸው፥
የአስራት ገንዘብ እያፈሰ:
ምጽዋትን እየዘረፈ:
እንደ ኮርማ ከደለበ:
አበበ እንጂ መቼ ሞተ:
ዘበነ እንጂ መቼ ሞተ:
እያሉ ይቀጥላሉ:: እኔም ጨመርኩ እንዲህ ስል፥
እውነት ብለዋል በላይነህ አባተ:
መነከሰ ሞተ መሆኑ ቀርቶ ፈለሰ ሆነዋል ነገሰ:
ላሉት “መነኮሰ ማለት ምን ማለት ይሆን?” መልሴ ነው ዓለምን ወደደ ቆብን ጫነ:
ወደ ሀገር ቤት የህዳሴ ዘመቻ ልመልሳችሁ ህዳሴ ማለት ሀደሰ: አዲስ አደረገ: ለወጠ: ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ/የተገኘ ቃል ሲሆን መፎኩሩ ምንድ ነው? ምንስ ማለት ነው? ብለን የጠየቅን እንደሆነም እንደ ፋብሪካ ዕቃ የአንድ ሰው ምላስና የአእምሮ ውጤት ከሆኑት የገዢው ፓርቲ ምልምል ካድሬዎች የምናገኘው መልስ “ኢትዮጵያን ለማደስ” የሚለውን ነው:: ለዚህም ይመስለኛል በእያንዳንዱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ህዳሴ የምትለዋን ቃል ፈልገን የማናጣት:: ታድያ ህዳሴ ማለት እንደ ቃሉ ትርጓሜ መሆኑን ቀርቶ፥
ህዳሴ፥ ማለት ዜጎች “በፋታሊዝም” ርዕዮተ ዓለም አመለካከት ጠንገህ በማሰር ያለ አንድ ሰው ሌላ ሀገር የመምራትም ሆነ ሕዝብን የማስተዳደር ጸጋ የታደለ ማንም የለም የሚል አስተሳሰብ የነገሰበት ትውልድ ማፍራት ከሆነ:
ህዳሴ፥ ስልጣኔ/ዕድገት ማለት በአንድም በሌላም በተገኘው ሀብት የተገነቡትን ህንጻዎች እያየ መቃብሩን የሚቆፍርና የሚያስረዝም ትውልድ መፍጠር ከሆነ:
ህዳሴ፥ ለበለጠ ጥፋትና ከምዕራብም ከምስራቅም መሰሪ ቅጥረኞች በሚፈበርኩት የማጭበርበሪያ ስልቶች ሀገርንና ሕዝብን ማወክና ማሸማቀቅ ከሆነ:
ህዳሴ፥ በዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሕዝብም የስልጣን ባለቤት የሚሆንበት መንገድ ከመፍጠር ይልቅ ጨለምተኛ አስተሳሰብ የነገሰባቸውና የተጸናወታቸው ካድሬዎችን በመመልመል የስልጣን ዘመንህን ማራዘም ከሆነ በዚህ ሁሉ ግርግርና ወከባ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምኑ ተጠቃሚ ቢሆን ነው ህዳሴን የምናወድሰው? እንደዚሁም ሃላፊውን ዓለም ትቻለሁ: የማያልፈውንም የዘላለም ህይወት መርጫለሁ ሲል ምሎ በቁሙ ተቀብሮ ተገንዞና በአናቱ ቆብ በሁለመናውም ቀሚስ ለደፋበትና ላጠለቀበት ዓላማ ራሱን ያላስገዛና ያልሆነ: ለቤተ-ክርስቲያን ያልጠቀመ ብልሃተኛ ለሌላ ይተርፋል ብሎ መሰቡም ሆነ በመኖክሴ ፕሮፖጋንዳ ሕዝብን እሰበስባለሁ ደጋፊ አፈራለሁ ማለት በራሱ ዕብደት ነው:: እንደው ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸውን ስለሚያመዝን እቺ የሚናገርቱንና የሚጽፉትን የማያውቁ አደራ በላተኞችን መኖኮሳትን ከፊት ለፊት እያስቀደምክ የምትደረገውን ፖለቲካዊ ቅስቀሳ ትቅርብን ባይ ነኝ::
መነኩሴ የሚለውን ቃል “ሞኖስ” ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ብቻ ወይንም ደግሞ ብቸኛ ማለት ነው። ገጣሚው ምናልባትም ከቃሉ ትርጉም አልፈው የጠለቀ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚችል ከግጥማቸው ይዘትና ከመልእክታቸው አሰካክ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል:: እንዲህ ያስባላቸው ምክንያትም መነኩሴ ሲባል የሚያውቁት … ተደግፈው በቀለጠው መንደር በለምለሙ ስፍራ ሲወጡና ሲገቡ: አንተ ትብስ ቀርቶ አምጣ የሚያሰኘው ተጎናጽፈው የተነሱትን ፎቶ ግራፍ እየለጠፉ ፌስ ቡክ ሲያጣቡ ሳይሆን በገዳም ገድሞ ቅጠል እየማሰ ንፍሮ እየቀቀለ አማኒ መናፍቅ፣ ኃጥእ ጻድቅ፣ ባዕድ ዘመድ፣ ሳይል በፍጹም ፍቅር ስለ ፍጥረት ሁሉ የሚቃትት ነው::
እንግዲህ የምንኩስና አመጣጥ ከወዲህ ነው ተብሎ የሚነገር የተጨበጠ ነገር ባይኖርም የምንኩስና መሰረቱ ከፈጣሬ/እግዚአ ኩሉ ምንነት ጋር የተያያዘ ለመሆኑ ግን ብዙሐኑ የስነ መለኮት ሊቃውንት ይስማማሉ :: የስርዓተ ምንኩስና ቀደምት አራማጆች እምነት ሁለት ፈጣሪዎች የሚል ሲሆን የምንኩስና ህይወት ሊጀመር የቻለውም/የተጀመረውም ከዚህ የተነሳ ነው ተብሎ
ይታመናል:: ይህ እምነት ቁስና መንፈሳዊ ፈጣሪዎች በማለት ሁለት ፈጣሪ መሰረት የተጣለ ሲሆን (የኋላ ኋላ ግኖቲሲዝም በመባል የሚታወቀውን)የቁስ ፍጥረት ስጋን ጨምሮ የፈጠረ ክፉውን ፈጣሪ መንፈስን የፈጠረ ደግሞ መልካሙን/ደጉን ፈጠሪ በማለት ክፉን በመጸየፍ ወደ ደጉም በማድላት እምነታቸውን መግለጽ ሲጀምሩ ራሳቸውን ከተቀረው ዓለም በማግለል የገዛ ስጋቸው የሚገባውን ከመንፈግ አንስቶ ከሚገባ በላይ እስከ መጨቆን መጉዳትና ማጎሳቀል የተያያዙት:: እዚህ ላይ ብዙ ጊዜ የግሪክ ፈላስፎችን የግል ህይወት የምንኩስና አብነት ተደርጎ የሚወሰደውን ፍጹም የተሳሳተ ነው:: የግሪክ ፈላስፎችም ሆነ አዋቂዎች ልምምድ ለነገሮች ካላቸው ፍቅር የተነሳ ሃሳባቸው በምንም ነገር ሳይከፋፈል ጊዜያቸውን ለመጠቀም እንጅ ለጽድቅ ተብሎም አይደለምና::
በተረፈ የምንኩስና ህይወት በራሱ አንድ ራሱ የቻለ እምነት ነው:: ምንኩስና ክርስትና ከመምጣቱ በፊት በሌሎች ጥንታውያን ሃይማኖቶች የነበረ ልምምድ ነው:: አሁንም ወደ ስርወ መሰረቱ መለስ ብለን አመጣጡን ያጤንን እንደሆነም የምንኩስና ህይወት ለእኛ ለአዲስ ኪዳን አማኞች ክርስቲያናዊ ትውፊት አይደለም:: እንጥረንና አበጥረን እንየው ከተባለም ጥጉ ሁነኛ ጸረ ክርስትና ልምምድ ሆኖ ነው የምናገኘው::
የክርስትና መጽሐፍ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ክርስትና ማለት በልብህ አምነህ የተቀበልከውን ላልሰሙትን መናገር: ማሰማት: ማወጅ: መመስከር: በቃሉ እውነት ተሞልተህና ታጥቀህም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ወዳልደረሰበት ስፍራና ቦታ በመሄድም ማዳርሰ: መዝመት በአጠቃላይ ክርስትና የማትረፍ ህይወት እንጅ ክርስትና የያዝክ ይዘህ ወደ
ጫካ የሚል ትምህርት የለውም:: በተጨማሪም ክርስትና ከሀገር ከመንደር የሚያርቅ የዛር ድርሳንም አይደለም:: ክርስቲያናዊ ህይወት እንጅ ክርስቲያናዊ ምንኩስና የሚባል ነገር እንደሌለ ማወቁ በራሱም ከበላተኛ ያተርፈን እንደሆነ እንጅ አይጎዳንም::
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መነኮሳቶቻችን እንማን ናቸው ያልን እንደሆነም ሐቁ እንደሚከተለው ነው፥
ü ኑሮ የከበደው/የኢኮኖሚ ጀንደረባ:
ü ከጦር ሰራዊት ያመለጠ:
ü ሚስቱ የሞተችበት* እነዚህዎቹ አይታሙም በመጠኑም ቢሆን ታማኞች ናቸው::
ü ነፍስ አጥፍቶ የኮበለለ:
ü የደርግ መንግሥት ሲወድቅ ሰራዊቱም ሲበተን ወደ ወቤቱም ሆነ ወደ ጎረቤት ሀገር መሄድ ያልቻለውን መንገዶቹ ሁሉ በእሾክ የታጠሩበት ጦረኞች ናቸው:: በተለይ በኢትዮጵያ ምድር ከፈተኛ የማጭበርበር ወንጀሎች እየተፈጸሙ ያሉት በመነኮሳት መሪነት ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም::
የአጊት ልጅ አዶንያስ ንጉሥ እሆናለሁ ብሎ ተነሳ ሰረገሎችና ፈረሰኞችን በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ አባቱም ከቶ በሕይወቱ ሳለ እንዲህ ለምን ታደርጋለህ? ብሎ ልተቆጣውም ነበር እርሱ ደግሞ እጅግ ያማረ ሰው ነበረ ከአቤሰሎም በኃላ ተወልዶ ነበር፡፡ ሴራውም ከጹሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ነበረ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ይረዱት ነበር፡፡ አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዓይንሮጌል አጠገብ ባለቺው በዞሔለት ድንጋይ ዘንድ ሠዋ የንጉሥንም ልጆች ወንድሞቹን ጠራ ነገር ግን ነቢዩን ናታን በናያስንም ኃያላኑም ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም፡፡
አዶንያስ የእኔ ናቸው በማለት ያሰባሰባቸው ካህናትና 50 የሚያክሉ አጫፊሪዎች ድግስ ደግሶ አብልቶና አጠጥቶ አፋቸው የዘጋቸው ወንዝ የማያሻግሩ ምናምንተዎች ነበሩ፡፡ ልብ ይበሉ! አዶንያስ ያዘጋጃቸው ሰዎች ተራ ሰዎች አልነበሩም:: ንጉስ እሆናለሁ ሲል በአባቱ መንግስትነት ላይ ለጠነሰሰው መፈንቅለ መንግስት የማድረግ ሴራ ይደረዱኛል/አቅሙ አላቸው ብሎ የሚያምንባቸው ሰዎች ነበሩ ከእነዚህ መካከልም ካህናት ይገኙበታል ይህ ያደረገበት ምክንያትምን ስመ ጥሩ አዶንያስ የእስራኤል ሕዝብ ልብ (ለካህናት ያለው የላቀ አመለካከት) አሳምሮ ስለሚያውቅ ነበር:: ታድያ አጀንዳው ማንም የሚጠቅም አልነበረምና ለከፋ ኪሳራና ውድቀት ተዳረገ:: ካህናቶችሁም እንደሆነ ሊያተርፉት አልተቻላቸውም:: ተው! አካሄድህ ቅንነት ይጎድልበታል በማለት ፈንታ ሀሳቡን በመደገፍ በለው! ድፈነው! ሲሉ ነበር ገደል የከተቱትና መክሊቱን የቀበረ: አደራውን የበላ: ያለ እውቀት ምክርን የሚያጨልም ሀኬተኛ “ባሪያ”/የመነክሴ መንገድ እንደሆነም ወደ አራት ኪሎ ሳይሆን ወደ ለማሊሞ ነው የሚያመራና አይበጅኋሁም ባይ ነው መጽሐፉ::
በመጨረሻ መንፈሳዊያን በተለይ የሃይማኖት መሪዎች አንደ ዜጋ ሀገራዊ እንደ አማኝ ደግሞ ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው/ይገባቸዋል ሲባል ጸጋው: ጥሪውንና እውቀቱን ያለው ተባለ እንጂ የጠመጠመ መስቀል የጨበጠ ሁሉ አካኪ ዘራፍ ይበል ያለ ማን ነው? በተጨማሪም አንድ ሰው/አማኝ እንደ ዜጋ የፖለቲካ ፓርቲ የመደገፍም ሆነ የመቃወምም መብት ቢኖረውም ቤተ-ክርስቲያን እንደ ተቋም ግን የማንም ፓርቲ ደጋፊ አይደለችም ልትሆንም እንደማትችል ሊሰመርበት ይገባል::
ጸሐፊው “መነኮሳት” ሁሉ እንዲህ ናቸው: መስረታቸውና ግባቸውም ይህ ነው አላሉም:: የጽሑፉ መኸል ከፖለቲካውም ከመንፈሳዊ እውቀቱም ያይደሉ በለብታ ሕዝብ የሚያውኩ ያተኮረ ነው:: በድጋሜ በድንግልና ህይወት በጾም ጸሎት የሚተጉ አባቶችን አይመለከትም::
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
United States of America