ቃለመጠይቅ፥ ሒሻም ማታር
ሒሻም ማታር በ1970 በኒውዮርክ ተወለደ። ዝናን ያተረፈ እውቅ የሊቢያ ደራሲና ጥበበኛ ነው። «In the Country of Men» በተባለው ድርሰቱ ይህን አስመስከሯል። አባቱ በ1990 በጋዳፊ ሰዎች ታፍኖ ለእስር የተዳረገው ጃባላ ማታር ነው። ዴስሞንድ ቱቱ ስለዚህ ምሁር መፈታት ብዙ ተሟግተዋል፡ (freematar.org) ማታር የአሜሪካንና የብሪቲሽ ዜግነት ቢኖረውም ከቤተሰቡ ጋር በለንደን ይኖራል።
ስፒግል ከተባለው ጋዜጣ ጋር የተደረገ ቃለመጠይቅ
ሓሺም ማታር፥ የወዳጆቼና የኔ የዜና ማሰራጫ ነው፡ በስደት የሚኖሩ ሊቢያዊያን ጓደኞቼ በየቀኑ ወደ ሊቤያ በርካታ ጥሪዎች እናደርጋለን፡፡ ከጥሪያችን የምናገኘውን መልስ በማቀናጀትና በማስተካከል በመምረጥ ለህትመት የሚሆነንን እንመርጣለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ሃኪሞች ጠቃሚ የመረጃ ምንጮች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ከሙያቸው ስርአት የተነሳ ስሜታዊነተትን ይቋቋማሉ።
ስፒግል፥ ጓደኞችሀ መሃል ያለው ስሜትስ እንዴት ነው?
ሓሺም ማታር፥ በመጀመርያዎቹ ጥቂት ቀናት ይህ ጅምር የት ይደርስ ይሆን በሚል መዋለል ውስጥ ነበሩ፡፡ነገሮቹ ሁሉ አካሄዳቸው ፍጥነት ያለው ሲሆን ግን የነሱም ፍላጎትና ተስፋም እየጨመረ መሄድ ያዘ። አሁን የሚነሳው ጥያቄ ታዲያ ‹‹ጋዳፊ አስኪወድቅ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?›› ከዚህም ጋር አብሮ ‹‹የስንት ንጹሃን ሕይወት መጥፋት አለበት›› የሚለው ነው።
ስፒግል፥ ይሄ የጋዳፊ መጨረሻው ነው ብለህ የደመደመከው መቼ ነው?
ሓሺም፥ የነጻነት ሰልፈኞቹ ሊቢያዊያን ቤንጋዚን የያዙ እለት ነው፡፡ ቤንጋዚ ማለት በምስራቁ ያለው ከተማ ነው። ከበፊት ጀምሮ ከሌሎቹ ከተሞች በተለየ የፖለቲካ ባህል የሚታይበት የፖለቲካውም ማእከል ነው፡፡
ስፒግል፥ ገና የ15 ዓመት አድሜ ላይ እያለህ ነው ከቤተሰብህ ጋር ከሊቢያ የወጣኸው። ካይሮ ከተምክ። ከዚያ በኋላ የኮሌጅ ትምህርትህን ለመከታተል ወደ ለንደን ሄድክ፡፡ አባትህ ዲፕሎማትና የታወቁ ምሁር ነበሩ። በኋላም በጋዳፊ ሰላዮች ታፍነው በ1990 ለእስር ተዳረጉ እና ጋዳፊ በሕይወትህ ውስጥ ምን ሚና አለው?
ሓሺም፥ ጋዳፊ አባቴን ሰረቀኝ፤ ቤተሰቦቼን እየሰበሰበና እያደነ አሰረ፤ ብዙ ጓደኞቼን ገደለ ስለዚህም ጠላቴ ነው፡፡ የኔን ግለሰባዊ ጥቃት ትተን መነጋገር ያለብን ሃገሪቱን የኋከልዮሽ እንድትሄድ ያደረገ፤ ሕዝቡም ለዘልዓለማዊስቃይ ኑሮ እንዲዳረግ ያደረገ ነው። ጋዳፊ ሊረሳ የማይችል ክፉና የጭንቅ ቅዠት በመሆኑ ያሁኑ ሁኔታ ከዚያ ቅዠት የነቃሁበት ወቅት ብዬ ነው የምጠራው። በዚህ አጋጣሚ ወይም ሂደት ያልተገረመ የለም፡፡ ሕይወታቸውን ሙሉ የሊቢያን ሁኔታ በማጥናት ላይ ያሉ ምሁራን ሳይቀሩ የተገረሙበት ጉዳይ ነው። አንድ ጊዜ እንቅስቃሴው ከተጀመረ በኋላ ግን አስገራሚ የነበረው ማስገረሙ ሁሉ ፉርሽ ሆነ። ይህን ደሞ አብሬያቸው ከኖርኳቸው ሊቢያዊያን አንደበት የሰማሁት ነው፡፡ ከፍርሃትና ከመሳቀቅ ተገላገሉ፡፡ ሁላችንም በስቃይ ገመድ እንድንታሰር ያደረገ ጋዳፊ ነበር። አሁንም ለእንቅስቃሴው ያስተሳሰረን ያ ስቃይ ነው።
ስፒግል፥ በ2003 ዓ/ም ምእራባዊያን ጋዳፊን ወዳጃቸው ሲያደርጉትና እያቆላመጡት የማር ጨረቃ ሲቋደሱ ምን ተሰማህ?
ሓሺም ማታር፥ ታመምኩ።፡በጣም አመመኝ። አጥወለወለኝ። የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ምእራባዊያን ገንዘብ ያጡ የሶስተኛው ዓለም ድሃ ሀገሮች አይደሉም፡፡ ስለ አውሮፓና አሜሪካ እኮ ነው የምንነጋገረው። በዓለም ላይ በሃብት የተንደላቀቁ የሚባሉት ሀገራት ናቸው እኮ፡፡የሆነውን ሁሉ እንዳልሆነ አድርገው እያወቁ ሲረሱት በሰብዊነት ላይ ያለህን አመኔታ ሁሉ ያስክድሃል።
ስፒግል፥ ምእራባዊያን የዚህን አምባገነንና የሌሎቹንም መሰሎቹን እድሜ ያራዘሙ ይመስልሃል?
ሓሺም ማታር፥ ምን ያጠራጥራል። ጸሃይ የሞቀውን እውነት? ግን ይህን አመጽ ታሪካዊ የሚያደርገውም እኮ ይሄው የምእራባዊያን ጉድ ነው። ይሄ እርባና ቢስ አምባገነን በዓለም ያለውን ገንዘብ ሁሉ ያለው አውሬ ብቻውን ሳይሆን ዓለምአቀፋዊ እውቅና ተሰጥቶም ስለነበር ነው የጀገነው። እነሱ ከጀርባ ሆነው ‹‹አበጀህ የኛ አምበሳ!›› ሲሉት ጀገነ፤ አጀገኑት።
ስፒግል፥ በአዲሷ ሊቢያ ድርሻህን ለመወጣት የመመለስ እቅድ አለህ?
ሓሺም ማታር፥ እርግጠኛ አይደለሁም። እኔ ደራሲና የጥበብ ሰው ነኝ። የጠበብ ሰዎች ደሞ ህብረተሰቡን የሚያግዙት ለጥበባቸው ታማኝና እውነተኛ ሆነው ሲገኙ ነው፡፡ጥበብ ለጥቅም አይለወጥም፡፡ጠቢብ ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ ለሆዱ ብሎ አይገዛም። ያም ሆነ ወደ ሃገሬ ለመመለስና የሕዝቡ አካል ለመሆን እጓጓለሁ።
ስፒግል፥ አባትህ በህይወት ያሉ ይመስልሃል?
ሓሺም ማታር፥ ተስፋ አለኝ፡፡እንቅስቃሴው ግቡን ከመታ በኋላ እኔና ወንድሞቼ ፍለጋና ማጠያየቅ እንጀምራለን፡፡ለሁሉም ሊቢያዊያን የግልና ሃገራዊ ጉዳይ አለ። የግሉ ጉዳይ መዘግየት አለበት።
ስፒግል፥ ቀጥሎ ምን ይሆን ይመስልሃል?
ሓሺም ማታር፥ ተስፋዬን ያጎለበተልኝ ሁኔታ ሕዝቡ ራሱን ማስተዳደርና መምራት መቻሉ ነው። በፍጥነት ኮሚቴዎች አቋቋሙ፤ አስተዳደር አዋቀሩ፤ የዴሞክራሲ ታጋዮቹ 18 የቅጥር ጦረኞች.ሲይዙ በሚገባ አብልተው ተንከባክበው አልብሰው አክመው ፓስፖራትቸውን ጠረፔዛ ላይ ደርድረው ጠበቃ ጠሩላቸው።
ስፒግል፥ ቂም በቀል አላሳዩም
ሓሺም ማታር፥ እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው ተስፋዬን ያለመለሙት።፡ይህ እንቅስቃሴ ጋዳፊን ከማስወገድ ጋር የተያያዘ ብቻ አይደለም፡፡ያ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ሂደቱ ሊቢያዊያን እራሳቸውን ፈልገው ያገኙበት ሂደት ነው።፡ሰው ማለትና ህዝብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተገነዘቡበት፡፡አብዮት ወይም ይህን መሰል እንቅስቃሴ ስለ አሉታዊነት ብቻ አይደለም። አንድነ ሰው ማንሳት፤የማይፈልጉትን ማጥፋት፤ ሊሆን አይችልም ይልቅስ ልትፈጥር ስለምትፈልገው ነው መሆን ያለበት። ሊቢያዊያን አሁን ለአለፉት ዓመታት ሲያልሙትና ሲመኙት የነበረውን ራዕይ በመተግበር ላይ ናቸው። የጋዳፊ መወገድ የተግባሩ ሁሉ መጀመርያ ቁልፍ ነው።
ስፒግል፥ ጋዳፊ ከወረደ በኋላስ ምን ይከተላል
ሓሺም ማታር፥ የእንቅስቃሴው ውጤት ነው የነገዋን ነጻ የሊቢያውያን ሊቢያን የሚፈጥረው፡፡ ማንም የሀይሞኖት ወይም የፖለቲካ ባነር ያነሳ የለም። በክብርና በነጻነት ዋሰትናው የተረጋገጠ ኑሮ የመኖር ጥያቄ ነው። ሊቢያ ሰላማዊና የፍቅር ሃገር ናት፡፡ለዓለም በሯን ከፍታ የምትኖር ሃገር።
ስፒግል፥ የጋዳፊን መንግስት ሲደግፉና አብረውት የቆሙ ሰዎችስ መጨረሻ ምን ይሆናል?
ሓሺም ማታር፥ ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ያም ሆኖ ቂም በቀል ፍትህን አያስገኝም፡፡ሌላው ቀርቶ አባቴን ባሰቃዩት ላይ እንኳን በቀል የለኝም፡፡ብዙዎች፤ ክፉ እርጉም ስርአት ነበር ቢሉም ሁሉንም በአንድ አይነት ቀለም መቀባት እንደሌለብን ይናገራሉ፡፡ሊቢያ ማገገም አለባት ለዚህ ደሞ ጊዜ ያስፈልጋታል፡፡ያለፈው እንዳይመለስ ማድረግ አለብን።፡ለዚህም ማረጋገጫው ከጋዳፊ ጋር የነበሩት ዲፕሎማቶች በቃን ብለው ወደ ሕዝቡ ሲወግኑ መቀበሉ ነው፡፡ለረጂም ዓመታት አብረውት ሆነው ቢደግፉትም የደረሰባቸው ሂስ ግን መለስተኛ ነበር።
ስፒግል፥ የሃቅ ኮሚሽን የዚህ መፍትሄ ይመስልሃል
ሓሺም ማታር፥ ይመስለኛል። ይህን በተመለከተ ደቡብ አፍሪካ ካሉ ወዳጆቼ ጋር ተነጋግሬያለሁ፡፡ከሂትለር በኋላ የተከተለውን ብሔራዊ እብደት ለመከላከል ምሁራንና የስነአእምሮ አዋቂዎች ያስፈልጉናል። ጋዳፊ ሂትለር አይደለም፡፡ግን ከነበረው የሂትለር ዘመን ጋር ማመሳሰሉ ለሚያጋጥመን ወቅታዊ ችግር ይረዳናል። ከኢጣልያም ልምድ ይለያል፡፡ጥቂት ሰዎችን ለፍርድ አቀረበና በቃ ቀጠለ፡፡እንደእውነቱ ከሆነ በኢጣልያ ከሁኔታው ጋር የተገናዘበ ሂደት አልነበረም።
ስፒግል፥ ‹‹በሰዎች ሃገር‹‹ “In the Country of Men” በሚለው መጽሐፍህ ውስጥ በጋዳፊ ስርአት ውስጥ ስለአሉ ቤተሰቦች ትተርካለህ፤ ስለአሁኑስ እንቅስቃሴ መቼ ብለን እንጠብቅ?
ሓሺም ማታር፥ ኪነጥበብ ለፖለቲካ መልስ የሚሰጠው ወይም የሚናገረው ረጋ ብሎ ነው፡፡ ከ20 ዓመታት በኋላ ጠይቀኝ።