ዳንኬራ የለመደች መበለት አባይ ዳር ቅበሩኝ አለች!

ጥሩ አጋጣሚ ነው ዛሬን ያገናኘን! (እየዘፈንኩ አይደለም) ሰሙኑ ዲቅ/እልል ያለ ሐሴትና ፌሽታ ላይ ነኝ (በመንፈስ):: ባይሆን እህት አዜብ ደንገጥ ቢጤ በማለት “ምን ተገኘ?”
ማለትሽ አይቀርም ውሎ አድሮ ደም አስቀምጦ እርር ኩምትር አድርጎ ቢገድልሽም:: ዝርዝር ሐተታውን ማተቱ አስፈላጊ ባይሆንም ሀገሩ አሜሪካ ነውና በተቋሙ የትምህርት ዘርፍ ህግና ደንብ መሰረት አንድ የ”ግሎባል ስተዲስ/ፖለቲካ ሳይንስ” ተማሪ “የጁኒዬር” ዓመቱን አጠናቅቆ ወደ “ስንዬር” ከመሸጋገሩ በፊት በተቋሙ ቦርድ የሚቀርበውን የአቅም መመዘኛ የቃልና የጽሑፍ ፈተና ማለፍ ይጠበቅበታል:: የምስራቹ  ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን፥ ይህን ምዕራፍ በደማቅ ድል መጠናቀቁ ነው:: እንግዲህ በ12/13 ዲያቆኑ በ28 ዓመታቸው ሃይማኖት: ፖለቲካ: ኢኮምኖሚና ማህበረ ሰብአዊ ጉዳዮችን በሚዳስስ በግሎባል ስተዲስ የትምህርት ዘርፍና በተጨማሪም በፖለቲካ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ዲግሪያቸውን ያገኛሉ ተብሎ
ይታመናል:: በዚህ አጋጣሚ እህት አዜብም በዕለቱ ተገኝተው የደስታዬ ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ ጥሬን አቀርባለሁ:: ከምሬ ነው! የሃሳብ ልዩነት ጠላትነት አይደለምና:: (ቦታውና ዕለቱ በአድራሻዎ ይላካል)::

ከአንድ ዓመት አምስት ወር አከባቢ በላይ ሆኖሽ ነበር የገባሽበት ሳይታወቅ ያዘመምሽው “ለበድን ክብሩ ዝምታው” ብለሽ እንደሆነ አላውቅም:: ያም ሆነ ይህ ግን አመጣጥሽ በማዘናጋት አልያም ነውረኛ/ነገረኛ ታሞ አይተኛ ከሆነም ሃሳብን በሃሳብ ለመመልስ በሞከርሺባቸው ቦታዎች ላይ በሃሳብ፤ ከስነ ጽሁፍ ስነ ምግባር በማፈንገጥ ወርደሽ ለወረወርሻቸው ሰንካላ ቃላት ደግሞ አንዲሁ በተመሳሳይ “ዳንኬራ የለመደች መበለት አባይ ዳር ቅበሩኝ አለች!” ስል በሰፈርሺው መስፈሪያ እሰፍርልኝ ዘንድ ሁኔታዎች አስገዳጅ ሆነው ተገኝተዋል:: በነገራችን ላይ ምንም አዲስ ይዘሽ የመጥሽው ነጥብ እንደሌለ ሳልዘነጋ ነው:: ያው ከአንድ ዓመት በሃላም ይዘሽው ብቅ ያልሽው የትናንትና የተለመደ ደንቃራ አመለካከት የወለደው ተራ ቃላት ነውና:: [1]
[2]

ክፉ አመልሽ አለ “ከላይ በድርብ መታወቂያ ያስተዋወቅኩት ጸሃፊ ፤ ዲያቆን ሙሉጌታ በሚል ስም የሚያወጣቸው መጣጥፎቹ፤ ከመንፈሳዊ አባት የሚጠበቁ አለመሆናቸውን በመግለጽ ወይ ፖለቲካውን ወይ ካህንነቱን ያዝ! የሚል መልዕክት ያዘለ አስተያየት መስጠቴን አስታውሳለሁ። ይህን አስተያየት ከሰጠሁ ከጥቂት ግዜ በኋላ ባቀረበው ጽሁፍ ላይ ሁለቱንም አቆራኝቶ መያዙን ለማመላከት ይመስላል፤ ከዲያቆንነቱ በተደራቢ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ የሚል ተቀጽላ አስገብቶ በማየቴ እንደፈቃዱ ይሆን ዘንድ እኔም (ዲያቆንና የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ) ብዬ አስተዋውቂያለሁ። ለማስተዋወቅ ያህል ማለቴ ነው።”

ዕቃ አይደለሁም እንጅ እንደ አያያዝሽ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ዕቃ ማስታወቂያ አይሻውም እልሽ ነበር:: ለበለጠ ግን ለአሿፊ ማንነትሽ መልሱ በመግቢያዬ በግርድፉ እንዳተትኩት ነው:: በነገርሽ ግር ለሚሰኘት አንባቢያን ግን ከዚህ ቀደም የተጻፈውን ይመለከቱ ዘንድ በጽሑፉ ግርጌ አባሪ ተደርገው የተቀመጠውን ይመለከቱ ዘንድ  እጠይቃለሁ:: ክፉ አመልሽ አለ ከዚህ በህዋላ ግን ስም ሲረዝም አንባቢን እንደሚያሰለች ከጓ.ሊ.መ.መ.ኃ.ማ ትውስታ አለኝና አልደጋግመውም። ባይሆን ዲ.ሙሉጌታ እያልኩ ልቀጥል።”

ከዚህ በፊትም እንደሆነ ግልጽ አድርጌአለሁ ጓድም በያቸው ጉዳም ስለ ተጠቀሱ ግለሰብ (የሀገር መሪ) ከቀድሞዋ ሶቭየት ህበረት/ሩስያ በለመኑት ዱቄት ወልደው ያሳደጉሽ: አስተምረውም ለቁምነገር ያበቁሽና የዳሩሽን: በጻበላቸው የተጠመቅሽ እንዳሻሽ አምጥተሽ ብትመልሺው: አንስተሽ ብትጥዪው ባንቺ ያምራልና ጊዜዬን አላባክንበትም ባይሆን ግን ክፉ አመልሽ ያልሰጠሽኝኝ ለመንሳት ዳድቶታልና ጥጉ ልንገርሽ: ዲያቆን ሙሉጌታ በመንፈሳዊ ቃል እያዋዙ የሚጽፍዋቸው ጽሕፎች ጣመኝ ድገመኝ እየተባለ የሚነበቡና ከፍተኛ ተቀባይነትና ተነባቢነት ያላቸው ብዕርተኛ መሆናቸውን ከዚህ ቀደም የገለጽሽውን የሚታወስ ሆኖ አሁን ደግሞ ያልበረደልሽን ጥላቻሽ ለመወጣት አልያም ጥረትሽ ሁሉ  ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘና ያለው ሰውን በማሳደድ ከፈተኛ ተቀባይነት ለማግኘት ከሆነ ህልምሽ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ/እየተናገሩ ቤቶችን በሞላው ስለ ሚገለብጡ፥ አፋቸውን መዝጋት ይገባል እንዲል “ዲያቆኑ ጥሩ የቃላት ማዋቀር ችሎታ እንዳለው በመጀመሪያ አንቀጽ ያስቀመጣቸው የስነ-ግጥም ዜማዊ ቃና ያላቸው ሃረጎቹ ዋቢ ናቸው።” (ስለ መልካም ምስክርነትሽ ሳላመሰግን አላልፍም እግዚአሔር ይስጥልኝ!) በሚለው አዳላጭ ሳልሸነገል ነውራምነትሽን በሚገባሽ ቋንቋ መታተቱ አንደቀጠለ ነው::

ክፉ አመልሽ አለ “በነኚህና በሌሎች መሰል ሃረጎች ተገነባው የመጀመሪያውን አንቀጽ እንደጨረስኩ ዲያቆኑ ዛሬ ሊያብጠለጥላቸውና እከደከ ….. ርግማን ሊያቀርብባቸው የፈለገው ሰው
ቁልጭ ብለው ታዩኝ፡፡ ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ … ዶ/ሩ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ኃላፊነት መቀጠል ሲያቅታቸው ወደ ፖለቲካው ዘው ብለው ገቡ ለማለት ተፈልጎ እንደሆነ አልጠፋኝም፡”
ታጉል ጥንቆላ የሊቁ መላ! ብያለሁ::

ክፉ አመልሽ አለ “ዲያቆኑ ከዚህ ቀደም ባለው ጽሁፉም ሆነ በዚህኛው ላይ አጎልቶ የንጸባረቀው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀውስ ትልቁ ችግር ዘረኛውን የወያኔ መንግስት ሳይሆን (የተሰመረበት
ዲያቆኑ ወያኔ ዘረኛ መንግስት አይደለም ማለቱን ለማስታውስ ነው) በተቃውሞ የቆመውን ክፍል መሆኑን በማስረገጥ ይሳቀመጠው ትንተና ነው።አብረን እንየው፦”

  • ለዜጎችም ግፍና ውርደት ደግሞ የፖለቲካ መሪዎች ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ስብእና ተጠቃሽ ነቀርሳ ነው::

ክፉ አመልሽ አለ —– ምነውሳ ዘለልሽው x

  • ፖለቲካ በዚህ ስላልተሳካ እስቲ በዚህ ደግሞ ይሞከር ተብሎ የሚገባበት ዓይነት የስራ መስክ ስላይደለ::

ክፉ አመልሽ አለ (ዶ/ር ፍስሃ እሸቱን መሆኑ ነው) አላልኩም!! ዶክቶሩ አዜብ ጌታቸው በሚል ስም የተገለጡ  እንደሆነ ደግሞ ሲሆን መልስ ይኖረኛ!!

  • ፖለቲካ ነገሮችን የመያዝና የመልቀቅ ሂደት እንጂ አቅጣጫ ሳይለይ የሚነፍሰውንን ነፋስ እየተከተልክ ሕዝብንና ሀገርን ማወክም አለመሆኑ::

ክፉ አመልሽ አለ (የዶ/ር ፍስሃን ሃሳብ ለሚጋሩት ወገኖች) መልሱ በትክክል አልተመለሰም! ጊዜ አለሽ: ደግመሽ መሞከርም ትችያለሽ::

  • ፖለቲካ ሕዝብን የማገልገል ሽክም/የአደራ ስልጣን እንጅ ስምህን የምትገነባበት መድረክም አለመሆኑ::

ክፉ አመልሽ አለ (ለሁሉም ይሆናል) ግድ የለም ጥያቄ እየጠየቅኩ አይደለም ያለኹተይ ተረጋጊ!

  • በተጨማሪም በትርፍ ሰዓት ለመረበሽ/ለማወክ ካልሆነ የትርፍ ሰዓት ብሎ ፖለቲከኛ (መሪ) አለመኖሩ ነው::

ክፉ አመልሽ አለ (የግንቦት 7 መሪዎች ላይ ያነጣጠረ) ይህንስ አላውቅም ነበር!

ክፉ አመልሽ አለ ዲያቆኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቀጨጨው ይላል ቀጥሎ በሚዘረዝራቸው ወገኖች ነው፡”

ባይሆን “ወገኖች” ስትዪ የሰነጠርሽውን ቃል ምን አለበት እንደጻፍኩት እንደዛችው “ነጥቦች” ተብሎ ቢፃፍ። ያልሰፈረው፣ ያልተባለውንና ያልተነገረውን እንደተፃፈ ተደርጎ ማቅረብና ማደናገር አመል መሆኑ ነው? ማለትሽ ካልቀረ ደግሞ ከነጥቦቹ ጉን የምታውቂያቸው ፍሬ አልባ በለሶች (የሰዎቹና የድርጅቶችን) ስም ያላሰፈርሽው ዘንግተሽው ነው ወይስ ነጥቦቹ ላይ አለሽበት? አሁን ገና ተነቃቃን!

ክፉ አመልሽ አለ ለመሆኑ በወያኔ ውስጥ ለማገልገል አቅም አጥተው የተፈነገሉ ወገኖች እነማን ይሆኑ?”

ምንነው በጀመርሽው አትጨሪስውም? በነካካው እጅህ እንኳን ይባል የለ በበኩሌ ፅሑፌን በጀመርክኩት መንፈስ ጨርሻለሁ:: ሌባ እንደሆነ እኔ ነኝ አይልም!! አባባልሽ/ህ እኔን ማለትክን ነው ከሆነ ደግሞ ይሄው የጎደለውን ለሞምላት ቦታው ክፍት ነው::

ክፉ አመልሽ አለ ለኔ እስከሚገባኝ ድረስ ወያኔ ውስጥ ለማገልገል ዋናው መስፈርት ወይ ከወርቃማው ዘር መወለድ ያ ካልሆነም ህሊናውን እንደ ትርፍ አንጀት አውጥቶ ለመጣል መፍቀድ ብቻ ነው። አቅም አጥተው የተባረሩት እንግዲህ ሁለቱን መስፈርቶች ያላሟሉ በሌላ አገላለጽ ህሊናቸውን አውጥተው ለመጣል ያልፈቀዱ መሆናቸው ነው። ዲያቆኑ እነኚህ ወገኖች ክፉ ወሬን በመፍተል ፖለቲካችንን አቀጨጩ ይላቸዋል።

ማን ነው ወርቅ ማን ነው ጨርቅ? የምኞት ነገር ሆኖ በኢትዮጵያዊነቱ በሚኮራ የትግራይ ህዝብ ስላለሽ ጥላቻ አማራጭ ፖሊስሽ ነውና አሁን በብዕርና ወረቀት አይመለስም::  እቺ “በወሬ” ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተሽ/ክ ከአንድም ሁለቴ መለስ ቀለስ ማለትና ነገር እያመላለስሽ/ክ ማጠንጠንዋ ግን አላማረችኝም::

ክፉ አመልሽ አለ “ለመሆኑ በምን ምክንያት ይሆን ከወያኔ ጉያ የተባረሩ ወገኖች የተቃዋሚውን ጎራ ፖለቲካ የሚያቀጭጩት?”

ለጥያቄሽ መልሱ ያለው/የሚሆነው በእነዚህ ተወልደን ባደግንባቸው (እኛን- ስለ ደርግ ስለ ጃንሆይ ሳትጠየቂ ብዙ ተመክሮሽን ስለምታወሪ አንቺን አይመለከትም) ረጅም ዓመታት ውስጥ ተንሳፋፊዎቹ ያስመዘገቡትን/ያሳዩትን የውጣ ለውጥ ማስፈር ነው የሚቀለሽ::

ክፉ አመልሽ አለ “(ውኃ አይቋጥርም)” ምጸቱ በእኔ ላይ ሳይሆን ለሁለት ገጽ ጽሑፌን አምስት ገጽ የስላቅ ጽሑፍሽን ላነበበ አንባቢ ነው የሚሆነው:: እዚህ ላይ ጸሐፊው “ማሽላ እያረረ ይስቃል” ሲሉ አንባቢ አሜን! ይልልኛል።

ክፉ አመልሽ አለ “ስሜት የማይሰጥ በድን ትንታኔ”

 

ስድብ ያሳደገኝ: ያነቃኝ: ያበረተኝ: የለወጠኝ:

ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳልል መንገዴን በሚገባ እንድጠበጥብ ዘንድ የረዳኝ:

ላለሁበትና ለደረስኩበት ከፍታ እንደ ድልዲ ይሁንታውን ሰጥቶ ያሸጋገረኝ ልዩ  ባለ ውለታዬ::

በበኩሌ በተቻለኝ መጠን በነገር ሁሉ ሰው አፉ እንዲያላቅቅብኝ ክፍተት የምሰጥ/የምፈጥር ሰው ባልሆነው ባለአመል ግን በደስታ አስተናግዳለሁ:: ጥቅሜ ነውና!

 

ክፉ አመልሽ አለ “ይህ እንግዲህ ዲያቆኑ በተቃዋሚው ላይ እንጂ ለተቃዋሚው እንዳልቆመ ያመላከተ፤”

አንደ አንድ ዜጋ ቅድሳት መጻህፍትን የሚሉት ከማለት ውጭ ራሴን እንደ አንድ ፖለቲከኛ በመቁጠር የተናገርኩት ቃልም ሆነ የፃፍኩት ጽሑፍ እንደሌለ ቢያንስ በሙሉ ስሜ ላለፉት
3 ዓመታት ፅሁፎቼን በተከታታይ በጥሞና ያነበብና የተከታተለ አንባቢ ምስክር ነው። በተረፈ ከዚህ ቀደም “ፈውስ የሚያስፈልገው የሻገተ አእምሮ” በሚል ርዕስ የተጻፈውን በማንበብ የጸሀፊዉን አቋም ለማወቅ ይቻላል። በድጋሜ እውነቱን በእውነትነቱ መናገር መጻፍ በአጠቃላይ የሆነውን እና ያለውን በሚገባ ማሳየት፣ ማሳወቅ ማለት አንዱን መደገፍ ሌላውን ደግሞ መቃወም ማለት እንዳይደለ ሊገባን ይገባል። በአጭሩ አንደ አንድ ብቁና ጭምት ዜጋ ስለ ኢትዮጵያ ምድርና ሕዝብ ፖለቲካዊ አስተዳደርም ሆነ የኑሮ ሁኔታ ከማናቸውም ፖለቲካዊ ተጽዕኖዎች በጸዳ መልኩ በተጨባጭ መፍትሔ አዘል ሐተታዎችን ማተትና ጎልተህ መውጣት ማለት አንዱን ከመቃወምና ሌላውን ከመደገፍ ጋር በምንም ዓይነት መልኩ ሊገናኝና አንድ ሊሆን እንደማይችል ማወቅና መገንዘብ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሆና ማየት የምንሻውን እንድናያትና ሩቅ መንገድ እንድንጓዝ ይረዳናልና እላለሁ!!”[3]

ክፉ አመልሽ አለ ሮጦው መቅደም ሲያቅታቸው የወደቀውን ለመቀጥቀጥ ያደቡ ቀቢጸ ተስፋዎች፥ ይህ ደግሞ ያልገባኝ ነገር ነው! ሮጦ መቅደም ያቃተው የወደቀውን ለምን ይቀጠቅጣል? የቀደመውን እንጅ…የወደቀውማ ወድቋል፡፤ ምን አይነት ፖለቲካ ሳይንስ ነው? አይ ….”

አየሽ እህት አዜብ ነገር በዳኛ ሚዶ በእረኛ እንደሚያምር ቃልሽ ምስክር ይሁንሽ:: በተረፈ ከስራ ብዛት የተነሳ የሚታለመውን የህልም ዓይነት መፍታት የለመደ፣ በነገርና በስልቀጣ
የላሸቀውን አእምሮ የፖለቲካ ሳይንስ ውጤት የሆነውን አነጋገር/ዘዬ እንዲገባውም ሆነ አንዲፈታ ማን ይጠብቀዋል? ባይሆን ለደቀ መዛሙርት በከፊል ፍቺውን ልስጥ “የወደቀው” የተባለው በራሱ ሃይል የሌለው፣ ጥንካሬው የሌሎች ድክመት የሆነለት፣ አገር አንቀጥቅጦ ሕዝብ አጭቆ እየገዛ ያለውን የኢህዴግ መንግስት ገጽታ የሚወክል/የሚያሳይ
ነው።  ነገሩማኮ ሌላ ሳይሆን የጥበብ ቃል ከፊት አይፈታ ሙት አይመታ መሆኑ ነው።

ክፉ አመልሽ አለ (ይሄኛው ሳይንስ አልገባኝም)

ንዴት ይገባሻል? እንዴትስ ይግባሽ እናቴ? ያደግሽው ከእግረ ሰባራ ተረት ለቀማ እየተነገረ ያለው ከጥበብ መዓድ ከእውቀት አውድማ ቢገባሽ ነው እንጂ የሚያስደምመው ባይገባሽ ምን ይደንቃል?

ክፉ አመልሽ አለ ዲ.ሙሉጌታ ገና መነሳንሱን (?) ከግራ ወደ ቀኝ ሳያዞር በአፍላ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪነቱ (ዕውነት ከሆነ) የሚያቀርበው ይህ በጥላቻ የታጀለ የፖለቲካ ትንታኔ የተመሰረተው በሳይንስ ላይ ወይስ ወይስ በዘር …. ? የሚያሰኝ ጥያቄን ያጭራል።”

ባልገባሽና በማታውቂው ርእሰ ጉዳይ ሁሉ እንደ ዝንብ ጥልቅ ማለትሽ: መንቀልቀልሽና መውተርተርሽ ተጠላ እንጂ  ለማወቅ: ለመረዳት በዝግታ መጠየቅና መትጋትማ ጥበብ ነው:: “ዕውነት ከሆነ”  ላልሽው ተጋብዘሻል ብያለሁ! ከዚህ በተረፈ ደግሞ ይቅር በአደባባይ በጓዳም ውሸት አለመደብኝም:: በዚህ አጋጣሚ በፈሪሃ እግዚአብሔርን: ሰውን በሰውነቱ በማክበርና ክብር ለሚገባቸው ክብርን በመስጠት እንዲሁም በታላላቆች ፊት ዝቅ ማለትን በመልካም ስነ ምግባር ቀርጸው ስላሳደጉኝ ለወላጅ አባቴንና እናቴን ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም ለወለደኝ ልዑል እግዚአብሔር በመቀጠል ለማመሰገን እወዳለሁ:: በሳይንስ ላይ ወይስ ወይስ በዘር ለሚለው ሳይንስ ከልምድ አዋላጅ ሰፈር እድል ፈንታ የለውምና የጥላቻ መነሸርሽኝ እስካላወለቅሽ ብዙ ማለቱ ከንቱ ልፋት ነው የሚሆነው:: ከወንጌል የተገኘ ድንቅ ያልተደረሰበት ፖለቲካ!

ክፉ አመልሽ አለ ሌላው የገረመኝ ነገር ዲያቆኑ ዶ/ር ፍስሃ ከዩኒቲ ዩንቨርስቲ አስተዳዳሪነት ወደ ፖለቲካው መግባታቸውን ለማብጠልጠል ያስቀመጠው ፖለቲካ ምርጫ እንጂ አማራጭ አይደለም የሚለው ርዕስ ራሱንም እንደሚቃረነው አለማስተዋሉ ነው። ዶ/ሩ ከዩኒ አስተዳዳሪነት በቀጥታ ፖለቲካ ውስጥ መግባታቸው የሚያስወቅስ ከሆነ ዲያቆኑ ከድቁና ወደ ፖለቲካ ሳይንስ መግባቱ ምን ያስደርግ ይሆን?”

በበኩሌ ስማቸውን እየጠቅሰሽ ከወዲህ ወዲያ ስለምታመላልሽያቸው ግለሰብ በፃፍኩት ጽሑፍ ላይ/ውስጥ ያልኩት ነገር ባለመኖሩ ስቅላት ይገባቸዋል አልልሽም። ዲያቆኑ ከዲቁኑ ወደ ፖለቲካ ሳይንስ መግባቱ ምን ያስደርግ ይሆን? በማለት ለጠየቅሽው ጥያቄ ግን መልስ ልስጥሽ ይኸውም: ሽልማት እንዳልልሽ ዲያቆኑ በለውጥ: በሚታይና በሚዳሰስ: እንዲሁም በተገለጠ ስራ  የሚያምኑ የለውጥ ሰው በመሆናቸው ለሽልማት ቦታ የላቸውም:: ሽልማታቸው ለተወልዱበት ዓላማ ሳይጨምሩና ሳይሸቃቅጡ በእውነት: በፍትሕና በጽድቅ ሕዝባቸውንና ሀገራቸው አገልግለው ማለፍ ነውና ስለ ሽልማቱ ብዙ ባትጨናነቂ::

ክፉ አመልሽ አለ “መቼም የዶክተሩ ሙያ ምንም ይሁን ምን ከድቁና በተሻለ ለፖለቲካው እንደሚቀርብ ሳይታለም የተፈታ ነውና ዝንጀሮ የራስዋን መቀመጫ ሳታይ ከፊቷ ባለው ዝንጀሮ ሳቀች እንዲሉ ዲያቆን ሙሉጌታም …”   

እኔ ደግሞ ያሳቀኝ ልንገርሽ ከሃላዬ ተሰልፈሽ ስታበቂ ከፊትሽ በቆመው ሰው በእኔ ላይ ለመሳቅ መሞከርሽን ነው። ደግሞስ እስቲ ማን ይቀርባል? እውነት ለመናገር የሚቀርበውን ለማወቅ
ከተፈለገ ለሁለቱም እኩል መድረክ መስጠት ነው መድሃኒቱ:: ለተናቀውም ጭምር እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸው ተጠብቆላቸው ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ሲችሉ ለማን እንደሚቀርብ ጥያቄሽ መልስ ያገኛል:: ሌላው ይብላኝ ለአንቺ ማለት ይቀለኛል በመድረክ መቆምና በቴለቭዥን መስኮን መታየት ሁለቴ የመወልድ ያህል ደስታ ፈጥሮልሽ ለሚያቧርቅሽና እንዲህ ለሚያንጣጣሽ እንጅ ዲያቆኑ እንደሆኑ ክብር ለጸጋው ባለቤት ለእግዚአብሔር እያስገቡ የመድረክም ሆነ የስክሪን አረራ እንደሌላቸው ሲገልጽ በአክብሮት ነው:: መድረክ ላይ መቆምም ሆነ በሺዎች ፊት መሻገርን የማያውቁትም ከምትገምቺው በላይ በለጋ የልጅነት ዕድሜአቸው ነው:: ባይሆን እንዲሁ ካሉበት በማሰራጨው በጸጋ የተቀመመ ቃል ተራራ ሳይገታው ርቀትም ሳያቆመው ማይሎችን አቆራርጦ የቤች መሰረት የሆድ ውስጥ እቃሽ ካናጋው ካንቦጫቦጨው ይበቃቸዋል::

ሌላው ቢቀር ዋናውን “ፖለቲካ ምርጫ እንጅ አማራጭ አይደለም”

የሚለውን ጽሑፌ ለማስነበብ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተው ሲያበቁ

“ዲያቆን ሙሉጌታ ዛሬም የእንቁራሪቷ አይነትስጋት አለቀቃቸውም!” የሚለውን ጽሑፍሽን ላስነበቡን ደረ ገጾች

መልሴን እልካለሁ የዲሞክራሲ: የዜጎችን እኩልነትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ውጤቱ ደግሞ አብረን የምናየው ይሆናል!

 

ክፉ አመልሽ አለ “ለመሆኑ ዲ.ያቆኑ በሳምንት ሁለቴ ለንባብ ከሚያበቃው አርቲ ቡርቲ አንዱን እንኳ በወያኔ ዘር ማጥፋት ወንጀልና ግፍ ላይ እንዲያጠነጥን ያልፈቀደው ለምን ይሆን?”

በሳምንት ሁለቴ የሚለውን የሚታፈነውን ሳይጨምር ከ 4-6 በሚለው እንዲስተካከልልኝ:: ይህን ለማረጋገጥ ከተፈለገ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ድረ ገጾች ብቅ ማለት ነው:: ስለ ምታውቂው መናገርሽ ከሆነ ደግሞ በእርግጥ እያንዳንዳቸው ድረ ገጾች ጽሕፎችን ተቀብለው የሚለጥፉበት የየራሳቸውን የሆነ መመዘኛ አላቸው እዚህ ላይ ምንም ተቃውሞ የለኝም:: ዳሩ ግን አስርስ ቢጻፍ ላንቺ ምንሽ ነው? የጽሑፍ አስተማሪነቱ እኮ ልቡንና አእምሮውን ዘግቶ ለሚያነበው ፈሪሳዊ ሳይሆን የአንድ ጽሑፍ አስተማሪነቱና ገንቢነቱና ጥቅሙ ለቅኖች: እውቀትን እንደ
ብር ጥበብ እንደ ከበረች እንቁ: ውሃ እንደተጠማች ዋልያም ለተጠሙና ለውጥን ለሚናፍቁ ነው:: ከዓለት ውሃን ያፈለቀ እግዚአብሔር ብቻ ነው! ስለ የዘር ማጥፋት ወንጀል በማለት ላነሳሽው የጻፍሽውን ቃል ማለት እንደሆነ ትርጉሙን ስትነግሪኝ ከሁለት ዓመታት በላይ ቃሉን ካስተዋወቁን ጠበብት የራሴ ያደረግኩትን ትርጓሜውን/ሰፊ ሙሑራዊ ሐተታዬን እለግስልሻለሁ::

 

ክፉ አመልሽ አለ “ባጠቃላይ ግለሰቡ በተቃዋሚው ጎራ እንደቆመና ነገር ግን የተቃዋሚው ጠንክሮ አለመታገል እንዳስቆጨው በማስመሰል ከሚያቀርባቸው ጽሁፎች ውስጥ እያፈተልኩ ከወጡት መልዕክቶች የተረዳሁት፦ ግለሰቡ ወያኔ በኃይልና በአመጽ እንጂ በሰላማዊ ትግል ሊወገድ አይችልም የሚል ቁርጠኛ አቋም የያዘውን ወገን በማጥላላት ለማስጠላት ፤ በማውገዝ ለማስወገዝ የሚተጋ መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ መለስ ዜናዊን እንጂ ወያኔን የማይቃወሙ፤ ወያኔ በህዝብ ኃይልና አመጽ በተወገደ ማግስት የትግራይ ሕዝብ ላይ ችግር ይፈጠራል ብለው የእንቁራሪቷን ስጋት የሚሰጉ ጥቂት የማይባሉ የትግራይ ተወላጆች አቋምና እንቅስቃሴ መሆኑን ከዚህ ቀደምም ጠቅሼዋለሁ አሁንም እደግመዋለሁ፡፡ ዲያቆኑም የዚህ ጎራ ቁጥር አንድ ተሰላፊ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቶናል።”

ሌላውን ወገን ያጥላላል ላልሽው ልዩ መታወቂያሽና መሰረተ ቢስ ቅጥፈትሽ ቢሆንም በሃይልና በዓመጽ የማላምን: ከዓመጸኛ ጋር ምንም ዓይነት ህብረት የሌለኝ: ዓመጸኛውን ታግሎ መጣል በሰለማዊ መንገድ ነው ብሎ የሚያምን ሰው መሆኔንና በዚህ አቋሜም ግንባር ቀደም ከሚይዙ ግለሰቦች አንዱ ነው ላልሺው ምስክርነት ግን በእክብሮት እቀበላለሁ:: ሌላው በግላጭ እንድታውቂልኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር እኔን ባሰብሽ ቁጥር የሕዝባዊ አስተዳደር የአስተሳሰብና የመርህ ልዩነት እንጂ ከማንም ግለሰብ ጋር ምንም ዓይነት ጸብም አጀንዳም የሌለኝም ግለሰብ እንደሆንኩ ልብ ትይው ዘንድ እወዳለሁ:: ስለ ትግራይ ሕዝብ በተመለከተ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የሚባሉ ካሉ እነሱ መልስ ይስጡሽ:: በተረፈ ሃይማኖት: ጎሳ: ቋንቋ: ባህልና ወግ ሳይገድበኝ አንዲት በሆነች ኢትዮጵያ የማምን ኢትዮጵያዊነቴን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብዬ የምኖር ዜጋ ስለሆንኩ ለርካሽና የዘቀጠ አመለካከትሽ ጊዜዬን አልገድልበትም::  ከተናግሮ አናጋሪ ጠብቀኝ!

ክፉ አመልሽ አለ እኔም እላቸዋለሁ ዲ/ሙሉጌታና ሌሎችም የትግራይ ተወላጆች ሆይ ለዘራችሁ መቆርቆራችሁን ማስቆም ባንችልም ቢያንስ ቢያንስ በአግባቡ ብትቆረቆሩ መልካም ነው የእንቁራሪቷን መሰል ስጋት አትስጉ።

እንደው ካበደ ጋር ልበድ በዬ የእንቁራሪቷን መሰል ስጋት አትስጉ ለምትያት የተበላች አባባል “አይሆንም ማለት ትተሽ ይሆናልን ያዢ” በማለት መልስ ለመስጠት አልሞክረውም አይመለከተኝምም ባይሆን ግን  ፈውስ ለሚያስፈልገው የሻገተ እአምሮሽ በድጋሜ ነገሬን ላስረዳ በጥሞና አድምጢኝ:: እኔ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነኝ:: ስለ የሰው ዘር የጠየቅሽኝ እንደሆነ ደግሞ የነፍስ ዜግነት የላትምና የሰው ልጅ ሁሉ በዘሩ አንድ ነው በሰውነቱም አንድና ሁለት የለውም! ለጊዜው ለጽሑፍሽ ማሳረጊያ ለለገሻት ምክር በሚቀጥለው ፈሊጥ ለማካካስ ልሰናበትሽ:-

ጡ — ጥ! ስማኝ ያገሬ ሰው:

የቁም ሬሳ  እህት አዜብ ነገረኛ ናቸው:

ከወትሮ በተለዬ አጥልቃችሁ ቅበሩዋቸው:

ጡ —ጥ! ብያለሁ የተነሱ እንደሆነ ብዙ ነው ጣጣቸው::

 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

[email protected]

25th April 2012