ኢትዮጵያውየን ግንቦት 20 ለተቃውሞ አደባባይ ለመውጣት ቀጠሮ ይዘዋል
በሰሜን አፍሪካ የተጀመረው የለውጥ አብዮት በርካታ ሃገሮችን ከማዳረሱ ጋር ተያይዞ በከፋ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ስሜት እየተስተዋለ ነው፡፡
በቱኒዚያና በግብጽ የተጋጋለ እንቅስቃሴ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ የሚታይ የተቃውሞ ምልክት ያልነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት ይዞታ ስር ያሉ ሚዲያዎችም በተለይ የግብፁን አመጽ በነፃነት ሲዘግቡ ቆይተዋል፡፡ አሁን አሁን ግን በተለያዩ ሃገራት የተነሱት ህዝባዊ አመፆች በመንግስት ሚዲያዎች ሲዘገቡ በተለይም አሉታዊ ገጽታቸውን በማሳየትና ህዝባዊ አመፆቹ የሚያስከትሉትን ጉዳት በመዘርዘር ላይ ከማተኮራቸውም በተጨማሪ ኢትዮጵያ አመፁ ከተነሳባቸው ሃገሮች በተለየ በኢኮኖሚ ዕድገትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የቀደመች ሀገር መሆኗን በየዘገባዎቻቸው ላይ ሲያትቱ እየተስተዋለ ነው፡፡ ህዝቡ ደግሞ በአንፃሩ በጉዳዩ ላይ በግልጽ ከመወያየት አልፎ በየሃገራቱ የተነሱትን ህዝባዊ አመጾች ሂደት በትኩረት በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡ በየካፌው፣ በየመስሪያ ቤቱና በሌሎችም ቦታዎች ይህ ህዝባዊ አመጽ የሀገሪቱ ትልቅ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ተነሳሽነቱን በወሰዱና በግልጽ ባልታወቁ ኢትዮጵያዊያን አስተባባሪነት በፌስ ቡክ ላይ ቅስቀሳ ተጀምሯል፡፡ “የድል ቀን” በሚል ስያሜ በተጀመረው ቅስቀሳ ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ህዝባዊ አመጽ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ በዚህ ቀን በአመፁ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውን እንዲቀላቀሉ በተጠየቀው መሠረት በጥቂት ቀናት ከ5ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ፈቃደኝነታቸውን እንደገለፁም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህን እንቅስቃሴ ተከትሎ የመንግስት ሚዲያዎችና አፍቃሬ ኢህአዴግ የሆኑ አንዳንድ የግል ጋዜጦች ሂደቱን ለማኮላሸት ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮ ቻናል የተባለው የሳምሶን ማሞ ጋዜጣ በተከታታይ ዕትሞቹ ርዕሰ አንቀፆች ላይ “ኢትዮጵያ ውስጥ አመጽ ፈጽሞ ሊታሰብ አይችልም” የሚል እንድምታ ያላቸውን ጽሁፎች ያስነበበ ሲሆን ሚሚ ስብሃቱ የተባለችው ጋዜጠኛም በራሷ ሬዲዮ በምታዘጋጀው “የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ” በተሰኘ ፕሮግራም ላይ በተደጋጋሚ ለጉዳዩ ሰፊ ሽፋን በመጠት አፍራሽ ቅስቀሳዎችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ ሚሚ ስብሃቱ በግብፅና በቱኒዚያ የተደረገውን ለውጥ በኢትዮጵያ ደርግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ሂደት ጋር በማመሳሰል “ትርፉ ልፋት ነው፡፡ ህዝቡ አርፎ መቀመጥ አለበት” የሚል ሰፊ ቅስቀሳ ስታደርግ ከርማለች፡፡
በአንፃሩ የግል ጋዜጦችና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ አመጽ መነሳቱ እንደማይቀርና አመፁ ሲነሳ ህዝቡ ሊያደርግ ስለሚገባው ጥንቃቄ በስፋት እየተናገሩ ነው፡፡ አቶ ስዬ አብርሃ ማክሰኞ የካቲት 22 ቀን 2003 ዓ.ም “አዲስ ወሬ” ከተሰጠው ሳምንታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ አመጽ እንዲፈነዳ የሚያደርጉ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ስር በሰደደ ሁኔታ ያሉ በመሆኑ ህዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣቱ እንደማይቀርየዘገየውም ገልፀው አመፁ ሲነሳ ግን ኢህአዴግ ህዝቡን በጎሳና በሀይማኖት ለመከፋፈል መሞከሩ ስለማይቀር ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
ሌሎች ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችም ተመሳሳይ አቋም የያዙ ሲሆን በተለይ በአዲስ አበባ የሚታየው ሁኔታ ኢትዮጵያ ቀጣይዋ ሃገር መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡