የለውጥ ግርግርና ሊመጣ ያለው ቀቢፀ ተስፋ በዛሬ ዓይን (አደፍርስ ተሰማ)
አንድ ስለ ቀድሞዋ ኮንጎ የተጻፈ መጽሃፍ ሳገላብጥ እንዲህ የሚል አረፍተ ነገር ላይ ዓይኔ አረፈ። ፓትሪስ ሉምባ (Patrice Lumumba) የመጀመሪያው የኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ ተመረጠ ይልና የጊዜው አለቆቹን ቤልጅምን ከካታንጋ እንዲወጡ ትእዛዝ ሰጣቸው። ካታንጋ በመዳብ፤ በወርቅና በጊዜው አሜሪካ እጅግ በምትፈልገው ዮራኒየም የሚገኝባት የሃገሪቱ ክፍል ነበረች። በዚህም የተነሳ የአሜሪካው የስለላ ድርጅት በሃገሪቱ ብጥብጥ በማነሳሳት ደም እንዲፋሰስ አደረገ። በዚህ ሳቢያ Patrice Lumumba ተገደለ ገዳዮቹና አስገዳዮቹም የPatrice Lumumba አስከሬን መኪናቸው ጭነው በሃገሪቱ መዲና ይሽከረከሩ ነበር በማለት የሲ አይ ኤን ክፋት በመዘርዘር ይቀጥላል።
ነጩ አለም ለሌላው አለም ደህንነት ደንታ የለውም። ቆዳቸው በጸሃይ ሙቀት እያጻባረቀ የመልአክት መልክ ያላቸው ቢመስሉም ውስጣቸው ጽልመት የሞላው ነው። ነጩ አለም ነው ለጥቁሩ አለም ከእጣት እጣት ይበልጣል እያሉ እያስተማሩ እርስ በርሳችን እንድንተራረድ የሚያደርጉት። ዛሬ በአለም ዙሪያ ለሚነድ እሳቶች ሁሉ ምንስኤዎቹ እነርሱ ናቸው። የኢራቁን ሳዳምን ስልጣን ላይ እንዲወጣና እንዲጎለብት የረድት እነርሱ ናቸው። በራሱ ማሰብ ጀምሮ እነርሱ ለሚያቀርቡት የይገባናል ጥያቄ አይሆንም በማለቱ ነው ዛሬ አፈር ውስጥ የከተቱት። የኢራቃውያኑ ኑሮም የመከራና ሰቆቃ እንደሆነ ቆመን የምንተነፍስ ሁሉ የምናየው እውነታ ነው። ኢራቅ ውስጥ በአሜሪካና በተለጣፊ ሃሎች ደጋፊነት ሰላም ይመጣል ማለት ድንቁርና ነው። በሃገሪቱ ሰላም ከጠፋ ዘመን አልፎአልና!
አሁን ደግሞ በአፍሪቃ ግርግር እናያለን። እንካቹህ ጡጦ ጥቡም እየተባለን ነው እንደ ህጻን። የዓረቡን አለም እድል ፈንታ የወሰኑት እነዚህ አምባገነን ስዎች በቱኒዚያ በግብፅ በየመን በጆርዳን እና በተለያዪ የዓረብ ሃገራት የአሜሪካው የስለላ ድርጅት የሚጠቀምባአቸው አሻጉሊቶች ናቸው። የህዝብ እንባና ሰቆቃ የሚለካው በዛችው ሃገር ከሚመነጨው የነዳጅ በርሚል ቁጥር ነው። የዘይት ሃበት የሌላቸው ደግሞ ለዘይቱ ሃብት መፋሰስ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አላቸው ይሉናል። አሁን ሰው በግብጽ፤ በቱኒዚያ በሊቢያ ሞተ ተብሎ እየየ ይባላል። ወያኔ በጠራራ ጸሃይ በአደባባይ ህዝባችን ሲረሽን፤ ሃገሪቱን በዘርና በጎሳ ሲሽነሽን ምነው ጸጥ አሉ? የጥቁሩ ሰው ደም ለአሜሪካ ደንታ አይሰጠውም። ወያኔ ለእነርሱ የመገልገያ መሳሪያ ነው። እንደ መስኖ ቦይ በወደዳቸው ጊዜ አቅጣጫ ያስቀይሩታል። ያም በመሆኑ የፈለገውን ግፍ በህዝባችን ላይ ሲፈጽም እያዩ እንዳላዩ ያልፉታል። በአንፃሩ የኤርትራው መሪ ዞር በሉ አልሰማችሁም ሰላላቸው እብድ ነው ይሉታል። ውትብትቡ የነጭ ፓለቲካ! ያበድስ እነርሱ!
አሁን ለውጥ ለውጥ የሚባልለት አረብ አመጣሽ ውሽንፍር መሰረት የሌለው ቆይቶ ችግር የሚፈጥር ከጭቆናና ግፍ ብዛት የተነሳ በግብታዊነት የመነጨ ነው። በውል ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስ የሚያውቅ የለም። እኛም ከአሜረካ የወሬ ከረጢት የሚበተነውን ቅንጭብ ዜና ሰምተን ሳናላምጥ እየዋጥን ማወራረጃ አጥተናል። እውነቱ የቀረው በእነዚህ ሃገሮች የአሽዋ ምድር ነው። ማን ቆፍሮ ያውጣው? አፍሪቃ ውስጥ ለውጥ ማለት “የጠገበን አውርዶ የተራበን መተካት ማለት ነው” ህዝብ ያቀፈው፤ ህዝብ የተጠቀመበት ለውጥ ተደርጎ አያውቅም። ሶማሊያ ሲያድ ባሬን አባራ ዛሬ የወንበዴ ሃገር ሆናለች። ኢትዮጵያ መዘበሩን የሉትን የዘውድ አገዛዝ አውርደው ክፋትና መክራን የተላበሰ የወታደር መንጋ ጽልመት አለበሳት፡፤ ኤርትራ ከሰላሳ አመት ደም መፋሰስ በህዋላ ዛሬም ጦርነት ረሃብና ችግር ላይ ናት። ወያኔ የሚፈላሰስባት ኢትዮጵያም ከኤርትራ የተሻለ እደል ፈንታ የላትም። እንሻላለን ሊሉን ይሞክራሉ ግን እውነቱ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ህዝብ ለረሃብ እንደተጋለጠ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ባንጻሩ ወይዘሮ አዜብ (የወያኔው መሪ ግማሽ አካል) አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር እንዳላት አንድ ማድሪድ ውስጥ ታትሞ የሚወጣ ጋዜጣ ጠቁሞናል። በዝምባብዌ፤ በኮንጎ፤ በኡጋንዳ፤ በሱዳን፤ በቻድ፤ በአይቬሪኮስትና በሌሎችም የአፍሪካ ሃገሮች የምናየው አመራር እኔ ከሞትኩ ስርዶ አይብቀል አይነት ነው። ለነገው ዜጋ አስቦ ሃገሪቱን የሚመራ መሪ የለም። ቀን እያለ እንብላና እናስበላ ነው። መፈንቀለ መንግስት ብለን የምናመጣው ከቀድሞው የከፋ ነው። የላይቬሪያው ዊሊያም ቶልበርትን ባንድ ጭቃማ ስፍራ ቀብሮ ራሱን ስልጣን ላይ ያወጣው ሃምሳ አለቃ ዶ ላይቬሪያን አፈራርሶ እርሱን በቀናቸው የተኩት ጠበንጃ አንጋቾች ዓይኑ እያየ በሳንጃ ቆራርጠው ገደሉት ይላል በጊዜው የወጣ ዘገባ። ከክፋት ወደ ከፋት፤ ከጭካኔ ወደ ጭካኔ ነው የምንተላለፈው እንጂ የተሻለ በለውጥ ሳቢያ ተገኘቶ አያውቅም።
አሳዛኙ ነገር ለውጥ ብለን ሰናስብ ቀድሞ የሚታየን የቆመን ማፍረስ፤ ሰውን ማሰር፤ መግደል ነው። ለውጥ በተደረገ ቁጥር ሰውን የምናሰር የምንገድል የቆመን የምናፈርስ ከሆነ መሰረታዊ ጠቀሜታው ለአንዲት ሃገር ምንድን ነው? አንዲት ሃገርስ ስንት ጊዜ ነው አዲስ መሰረት የሚጣልላት? ያለውን አሻሽሎ፤ የቆመውን ጠግኖ፤ ያጠፋውን በህግ ቀጥቶ (የሞት ግድያ በፍጽም መኖር የለበትም) ካለፈው ተምሮ ወደፊት መራመድ እስካልተቻለ ድረስ ለውጥ የምንለው ሁሉ የደንበር ገተር ጉዞ ነው የሚሆንብን። እስካሁን ያዘው ጥለፈው ግደለው በማለት ሞክረነዋል። ምንም አልሰራም። ብቀላ ብቀላን ይወልዳል።
አሁን በዓለም ዙሪያ በተለይም በአረብና በአፍሪቃ ሰሜናዊ ክፍል በመንደድ ላይ ያለው እሳት ቆይቶ መብረድ የተፈጥሮ ህግ ነው። ይሁን እንጂ ትናንሽ እሳቶች እየተኩት ሰላምና ነጻነት የጠማውን ህዝብ የበለጠ ሰቆቃ ይከቱት ይሆን? ሰላም እናመጣለን ተብሎ እንደተዘመተበት ኢራቅና አፍጋኒስታን ሰው ጥላውን የሚፈራበት ወቅት ይተካው ይሆን? አበው “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” እንደሚሉት ይሆን? ለእነዚህ ሃገሮች ሊመጣ ያለው አሁን ካለው ይሻላ ወይስ ይከፋ? እስቲ ወደ ቤይሩት አይናችን እናቅና። መልስ ይገኝ ይሆን? ለውጥ ብቻውን ለዛውም ግብታዊ ለውጥ ለሰው ልጆች ሰላም አምጥቶ አያውቅም። ሰቆቃ እንጂ። ትሻልን ትቼ ትብስን አመጣሁ እንዳይሆን እፈራለሁ።
ሰንብተን እንይ!