የፕ/ር መስፍን ወልደማርያም አዲስ መፅሐፍ ነገ ገበያ ላይ ይውላል
“ስልጣን” በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የተፃፈውና ስለባህል፣ አገዛዝ፣ ፖለቲካና ምርጫ የሚያትተው መፅሐፍ የፊታችን ሐሙስ በገበያ ላይ ይውላል፡፡
መፅሐፉን ያተመው ንግድ ማተሚያ ድርጅት ሲሆን የታተመው ኮፒ ብዛት 5000 መሆኑ ታውቋል፡፡ መፅሐፍ ከጀርባው በ1996 ዓ.ም በፕ/ሩ “የክህደት ቁልቁለት” በሚል ርዕስ ተፅፎ የነበረውን መፅሐፍም አብሮ የያዘ ነው፡፡ “የክህደት ቁልቁለት” ወያኔና ሻዕቢያ ታሪክን በመካድ ኢትዮጵያን ቁልቁል እንዳወረዷት በተጨባጭ የሚያሳይና በታተመበት ወቅት በህዝቡ በጣም ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ በአንዴ ከገበያ ያለቀ መፅሐፍ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ፕሮፌሰሩ መፅሐፉን በሚፅፉበት ወቅት የነበራቸውን ስሜት “በኤርትራ መገንጠል ንዴት ውስጥ የተፃፈ” በማለት ይገልፁታል፡፡
የአሁኑ መፅሐፋቸው ጭብጥ ምንነትን አስመልክቶ ላቀረብንላቸው ጥያቄም “ስልጣን ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው” በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡
ይህንኑ ሀሳባቸውን “አገዛዝ ከሀይማኖት፣ ከጎሳ፣ ከባህል፣ ወ.ዘ.ተ. ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ስልጣን ግን ፖለቲካዊ ነው፡፡ በምርጫ ከህዝብ የሚመጣ ነው፡፡ በሀገራችን ያለው ስልጣን ሳይሆን አገዛዝ ነው፡፡ ስልጣንን ኢትዮጵያ ውስጥ አልገነባነውም፡፡ ተቋማዊ አላደረግነውም፡፡ ይህ ስላልሆነ ነው መሪዎቻችን አምባገነን የሆኑት!” በማለት አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ችግር ለመውጣት ኢትዮጵያውያን ማድረግ የለብንን ሊያስረዱም ከአምባገነን ስርዓት በቀላሉ መላቀቅ አይቻልም፡፡ አብዛኛው ሀበሻ ጨቋኝ ነው፡፡ ሲጨቆን አይወድም እንጂ! ባል ሚስቱን፣ ሚስት የቤት ሰራተኛዋን፣ . . . ወ.ዘ.ተ አንዳቸው አንዳቸውን ይጨቁናሉ፡፡ ከዚህ ህብረተሰብ የተገኘ መሪ ደግሞ ህዝቡን መጨቆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ለመውጣት እያንዳንዳችን መለወጥ አለብን፡፡” ብለዋል፡፡
ያለፈ ታሪካችንን በምሳሌነት በመጥቀስም ከተጠቀሰው ውጭ በሆነ መንገድ የሚመጣ ለውጥ ዋጋቢስ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ፕ/ር መስፍን አፄ ሀ/ስላሴን እንጂ ስርዓቱን አለመለወጣችንን፤ መንግስቱ ሀ/ማርያምን እንጂ ስርዓቱን አለመቀየራችንን አስታውሰው አሁንም ከስህተታችን ስላልተማርን የምናስበው መለስዜናዊን እንጂ ስርዓቱን ስለመለወጥ ባመሆኑ መታረም እንደሚገባን አሳሳበዋል፡፡ ስርዓትን መለወጥ ላይ ማተኮር ሰውን መለወጥ ላይ ከማተኮር የለጠ ያለውን ጠቀሜታም “ሲስተሙን ብንለውጥ መለስም ተገዶም ቢሆን ጥሩ መሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አለበለዚያ ሲስተሙ ይተፋዋል፡፡” በማለት አስረድተዋል፡፡
በመፅሐፋቸው ምንአይነት ለውጥ ለማምጣት እንዳሚፈልጉ ላቀረብንላቸው ጥያቄም “በተለይ ወጣቱ መፅሐፉን አንብቦ ራሱን እንዲጠይቅ የምፈልገው እኔ ተለውጫለሁ ወይ? ሌላውስ ተለውጧል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን የኢህአፓና የመኢሶን፤ የደርግና የወያኔ ታሪክ ስናስታውስ ወጣቱ መሳያ እየሆነ ተላልቋል፡፡ አሁን ወጣቱ ለመተላለቅ አይቻኩል፡፡ መታገል ካለብኝ ለምንድነው የታገለው? የሚለውንና የስርዓት ለውጥ ስለማምጣት ማሰብ አለበት” የሚለ መልስ ሰጥተዋል፡፡
መፅሐፉ በ2002 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ኢህአዴግ ያደረጋቸውን ሽፍጦች የሚየጋልጥና በሁለተኛ የምርጫ ሪፖርቶች የፓርላማ ወንበሮችን መያዙን የሚያሳይ ጭምር ሲሆን ከኢትዮጵያም ውጭ በቦስተን ታትሞ በተለያዩ የአለም ክፍሎች በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ መፅሐፍ ለኢትዮጵያ አንባቢያን የቀረበው በ60 ብር ነው፡፡