ሙስናና ህገወጥነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

(ከዘቢባ ሳልህ)

ባለፈው ወር፣ January 24, 2011፣ በ“ethiomedia” እና በ“ETHIOPIAN REVIEW” ድረ ገጾች ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለተንሰራፋው ሙስናና አድሎአዊ አሰራር አንድ መጣጥፍ “Rise against delinquency, charlatanism and neo-patrimonial bondage at Addis Ababa University” በሚል ርእስ መቅረቡ ይታወሳል:: ያ መጣጥፍ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለአብዛኛው ሰው ከሌሎች መረጃዎች ጋር እየተባዛ ደርሶታል:: ያንን ተከትሎ ዶ/ር እንድርያስ እሸቴ በፕሮፌሰር ጥሩሰው ላይ፣ “አንተ ነህ የጻፍከው” በሚል ትልቅ የማጥቃት ዘመቻ ጀምሮአል:: (በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር ጥሩሰው የእንድርያስን ቦታ ይይዛል ተብሎ በስፋት የተወራለት ሰው ነበር::) መንግስትም፣ ችግሩ በውነት አለ ወይስ የለም የሚለውን ለመመርመር ብዙም የተጨነቀ አይመስልም:: በዚህ መጣጥፍ ባለፈው መጣጥፍ የተጠቀሱትን ነጥቦች ከተጨማሪ መረጃዎች ጋር እያነሳሁ የችግሩ ስር መስደድ ከአገሪቱ ስርዓት መጓደልና ለዚህም ተጠያቂ ከሆነው ከመለስ ቤተሰብ ጋር ያለውን ቀጥተኛ ግንኙነት ለማሳየት እሞክራለሁ:: በጽሁፌም በሙስና ውስጥ እጃቸው ያለበትንና በዩኒቨርሲቲው ለሰፈረው ብልሹ አሰራር ተጠያቂ የሆኑትን ቀንደኛ ሰዎች ስም አነሳለሁ – ህዝብ እንዲያውቃቸው በማለት:: ማን ያውቃል…? ወደውጭ ስለተላኩ የኮንትራት ሰራተኞች ጉዳይ ወደውጭ ዩኒቨርሲቲው ዶላር እየከፈለ ካስተማራቸውና እያስተማራቸው ካሉት ውስጥ ባለፈው መጣጥፍ ከተጠቀሱት አቶ አበባው ቢሆነኝና ወ/ሮ ሀውለት አህመድ በተጨማሪ ሌሎችም አሉ፣ ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲው ፕረስ አስተዳዳሪ የነበረው አቶ ካሳና በሪፎርም ቢሮ ይሰራ የነበረው አቶ መሀሪን መጥቀስ ይቻላል:: ከኢህአዴግ አባልነታቸው በተጨማሪ፣ ሁሉንም የሚያመሳስላቸው አንደኛው ነገር፣ አንዳቸውም የአካዳሚክ ወይም ቋሚ የአስተዳደር ስታፍ አባል አለመሆናቸው ነው:: ሁሉም ለአጭር ግዜ በኮንትራት የተቀጠሩ ናቸው። አቶ አበባው ቢሆነኝን ዩኒቨርሲቲው አሁን 54 ሺህ ዶላር ከፍሎ ለማስተርስ አሜሪካ የላከው ለሁለተኛ ግዜ ነው::

ከዚህ በፊትም ከ 60 ሺህ ዶላር በላይ ተከፍሎለት እዚያው አሜሪካ ሌላ ማስተርስ ሰርቷል:: ይህ ሰው ባሁኑ ግዜ በተወካይ ሙሉ ደሞዙ የሚከፈለው ብቻ ሳይሆን የስልክ አበል፣ የቤት አበል፣ … በተጨማሪም የኮሚቴ አባልነት አበል በሚል በሌለበት ይከፈለዋል:: ሌላው በራሱ እጅ የዘረፈውን ከኔ በላይ የፋይናንስ ሰዎች ጥሩ መረጃ አላቸውና እነሱ ቢናገሩት ይሻላል::

ባለፈው መጣጥፍ የተጠቀሰችው ወ/ሮ ሀውለት ጋ የሚያስገርመው “ትምህርቴን ጨረስኩ” ብላ ከመጣች በኋላ 24 ሺህ ዶላር ተጨማሪ እንዲከፈላት መደረጉ ነው:: ክፍያውን በተመለከተ የተቃወሙትና ቼክ ላይ አልፈርምም ያሉት የፋይናንስ ክፍል ሹም ወሪ/ት አልጋነሽ በወቅቱ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ፊርማው በቢዝነስና አስተዳደር ምክትል ፕሬዜዳንት አቶ እስጢፋኖስ እንዲሆን ተደርጓል:: ስለወ/ሮ ሀውለት የሚባለውን ብዙ የሙስናና ተያያዥ ነገሮች እዚህ ከማንሳት እቆጠባለሁ፣ የግል ጉዳይ እንዳይመስልብኝ:: እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ማለት የሚገባን በራሳቸው ጥረት ለማስተርስ “SCHOLARSHIP” ያገኙ የአካዳሚክ ሰራተኞች “ለማስተርስ ወደ ውጭ እንድትሄዱ ዩኒቨርሲቲው አይፈቅድም፣ ከፈለጋችሁ ለቃችሁ መሄድ ትችላላችሁ” በመባላቸው ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ለትምህርት መሄዳቸው ነው:: ለዚህ አብነት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል ይሰራ የነበረውን አቶ ከፍያለውን መጥቀስ ይቻላል:: ልብ በሉ የዩኒቨርሲቲውንም ሆነ ያገርን ምንም ገንዘብ ያልጠየቁትን ፍቃድ መከልከል፣ እራሱ ግን የሚፈልገውን ያውም በኮንትራት ቀጥሮ በሌለ ገንዘብ መላክ::

ከውጭ የመጡ የእንድርያስ የዝርፊያ ቡድን አባላት

1. አቶ ባህረ ነጋሽ
ይህ ሰው፣ የመጀመሪያ ድግሪ እንኳ የሌለው ቢሆንም፣ በየስድስት ወሩ በሚታደስ ኮንትራት በየወሩ፣ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር፣ ከ 9 ሺህ 300 ብር በላይ እየተከፈለው የ ICTDO ዳይሬክተር ሆኖ ማስተዳደር ከጀመረ 4 አመት ሆኖታል:: ይህ እንግዲህ በሙያው PhD ያላቸው ሰዎች ባሉበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መሆኑን ልብ ይሏል:: በየግዜው በአበል፣ በትርፍ ስራ ስም የሚከፈለው በአማካይ በወር ከ 10 ሺህ አያንስም:: ሌላም ብዙነገር የሚወራ አለ:: መረጃው በእጄ ስላልገባ ተራ አሉባልታ እንዳይሆንብኝ ያንን አላነሳም።

2. አቢይ ጣሴ (ዶ/ር?)
አቢይ ከአንዲት ትንሽ የፈረነሳይ ኮሌጅ የዶክተሬት ድግሪ አለኝ ቢልም ከዩኒቨርሲቲው እስከለቀቀ ድረሰ ማስርጃ ማቅረብ አልቻለም ነበር:: ይህ ሰው በመጀመሪያ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጣ የዩኒቨርሲቲውን ሪጅስትራር ሙሉ በሙሉ “ኮምፒውተራይዝድ” አደርጋለሁ ብሎ በ 50 ሺህ Euro ኮንትራት ገብቶ ነው:: ይህ ሰው ምንም የተባለውን ስራ ሳያከናውን በወቅቱ የሪጅስትራሩ ሀላፊ የነበሩት ዶ/ር ዘመዴ አገልግሎቱን ተቀብያለሁ በሚል ልዩ ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ ተደርገው አቢይ ክፍያውን ወስዷል:: ይህ ሰው፣ በኋላ የ IT ባለሙያነቱ ቀርቶ የሶሻል ወርክ ባለሙያ ተብሎ የተቀጠረ ሲሆን ትልቁ የሙሰኞች ቁንጮ ነበር:: ግለሰቡ የዘረፈውን ብር መጠን እንድርያስና በቅርብ ምርመራ ያደረገ ብቻ ነው የሚያውቀው:: ምክንያቱም ከመንግስት ቀጥተኛ በጀት ውጭ ከሚመጡት በርካታ የፕሮጀክት እና የእርዳታ ገንዘቦች መካከል “የዩኒቨርሲቲው ፋይናንስ አሰራር አያመችም” በሚል በግሉ የባንክ አካውንት ይቀመጥ ስለነበረ ነው:: በነገራችን ላይ ባሁኑ ግዜ እንድርያስን ጨምሮ በሌሎች ጥቂት ሰዎች ግል አካውንት የዩኒቨርሲቲው ገንዘብ የተቀመጠ አለ:: ይህን መንግስትም ያውቀዋል፤ የፌደራል ጸረ ሙስና ኮሚሽንም ያውቀዋል፤ እኛም እናውቃለን::

3. አቶ ጋሻው
በእንድርያስ ዙርያ የተሰባሰቡ የትምህርት ደረጃቸው አጠያያቂ የሆኑና ከእንድርያስ ስልጣን ጀርባ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ተመስገው የታክስ ከፋዩን ገንዘብ ሲዘርፉ የነበሩና እየዘረፉ ያሉ ከላይ የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም:: አቶ ጋሻው (የማስተርስ ድግሪ እንደሌለው እርግጠኛ ብሆንም የመጀመሪያ ድግሪ ስለመኖሩም ሆነ አለመኖሩ የማውቀው ነገር የለም) በመጀመሪያ የእንድርያስ ልዩ አማካሪ ሆኖ ተሾመ:: እዚያም ባለበት ወቅት በየፕሮጀክቶች ላይ ጣልቃ እየገባ የዘረፈው ገንዘብ እጅግ ብዙ ነው:: ለምሳሌ አቶ ሞገስ ደለለኝ ከ ICTDO ዳይሬክተርነት ከተነሳ በኋላ የ IT Localization ፕሮጀክትን በሃላፊነት ተቆጣጠረ:: እሱ የፋይናንሱን ሀላፊነት ከተረከበ በኋላ 800 ሺህ ብር አካባቢ የት እንደገባ አይታወቅም:: በኋላም በወቅቱ የአስተዳደርና የቢዝነስ ምክትል ፕሬዜዳንት የነበረው አቶ መሀመድ ሀቢብ በሙስና ላይ ሊተባበር ባለመቻሉ ገንዘብ ለማውጣት አስቸጋሪ ስለሆነ ለአቶ ጋሻው አዲስ የአስተዳደርና የቢዝነስ ተባባሪ ፕሬዜዳንት የሚል ቦታ ተከፍቶ ተሰጠው:: በዝያ ምደባ ላይ እንደተገለጸው የአቶ ጋሻው ስራ ትልልቅ ገነዘብ ነክ የሆኑ ነገሮች ላይ ሁሉ ውሳኔ ማስተላለፍ ነበር:: ሆኖም በአዲሱ ሹመት ብዙም ሳይበላ በ 15 ቀኑ ከእንድርያስ በመጣላቱ እንደቅጣት ከቦታው ተነስቶ ምንም ለአስተማሪነት የሚያበቃው ነገር ባይኖርም በ FBE አሰተማሪና ረዳት ዲን ሆኖ ተመደበ:: የሚገርመው ግን ሰውዬው ከተነሳ በኋላ አስፈላጊነቱ ተዘርዝሮ በቀረበው ቦታ ላይ (ማለትም የአስተዳደርና የቢዝነስ ተባባሪ ፕሬዜዳንት) ከሱ በኋላ አንድም ሰው አለመመደቡ ነው:: ይልቁንም አቶ አበባው ቢሆነኝ የመጀመሪያውን የማስተርሱን ድግሪ ይዞ ሲመጣ ሌላ በስም ብቻ የተለየ ተመሳሳይ ቦታ ተፈጥሮለት ተሾመ::

4. ወ/ሪት ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ
ይች ሴት፣ የእንድርያስ እጅግ ቅርብ ሎሌ ነች:: ሴትዮዋ አለምንም የሙያ ብቃት ከ 6 አመት በላይ በተጠባባቂነት IES ን እንድትመራ ተደርጓል:: ሴትዮዋ ስነምግባር የሚባል የምታውቅ አይመስልም:: በተለይ በጽዳት፣ በላይብረሪና በተላላኪነት የሚሰሩ ዝቅተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸውን ሰራተኞች ተራ ስድብ ሳይቀር ስትሰድብ የሰማ እጅግ ማዘኑ አይቀርም:: ይህ የኛ ጉዳይ አይደለምና እዚህ ብዙ ማለት አንፈልግም:: ወ/ሪት ኤልሳቤጥ IES ን የሚያህል ተቋም፣ በህግ ደረጃ ከረዳት ፕሮፌሰር በላይ የሚጠይቀውን፣ በኮንትራት ተቀጥራ ጥቅማ ጥቅሙን ጨምሮ ከ 10 ሺህ በላይ በወር እየተከፈላት እንድታስተዳድር መደረጉ ብቻ ሳይሆን፣ በተልእኮ ለጀመረችው ትምህርት ወደ አሜሪካ ለአንድ አመት ስትሄድ፣ የተጠባባቂ ሌላ ተጠባባቂ (አንድ በመጠጥ ምክንያት ብዙም አእምሮው የማይሰራ ሰው) ተሾሞላት እንደተመለሰች ቦታውን መረከቧ ነው:: ባሁኑ ግዜ ሁለት ስልጣን ደርባ ከመያዟ በተጨማሪ ልዩ አበል በሚል ከ 3 ሺህ ብር በላይ ይከፈላታል:: ይህ ደሞዟንና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር ነው:: አንድ አመት ውጭ በነበረችበት ግዜም ሙሉ ደሞዟ ከነጥቅማ ጥቅሙ ይከፈላት ነበር:: (በኮንትራት/ በግዚያዊነት ለተቀጠረ እንዴት እንዲህ ይደረጋል የሚለውን የየዋህ ጥያቄ ለጊዜው ወደጎን ተዉት):: ሌላው ነጥብ ኤልሳቤጥ ለአንድ አመት ሀላፊነቷን ለሌላ ሰጥታ ኮርኔል፣ አሜሪካ በቆየችበት ወቅት ዶ/ር ተካልኝም እዚያው ነበር:: ወጪ እንዲቀንስላችው ቢሆንም፣ የሚኖሩት አንድ ክፍል ነበር:: ተካልኝ ከአንድ ክፍል ከኤልሳቤጥ ጋር የኮርኔል ቆይታው በኋላ ሲመለስ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዜዳንት ሆኖ ተሾመ።

ሌሎች ሙስናዎች
በዩኒቨርሲቲው ስላሉት ሙስናዎች በዚች አይነት መጣጥፍ ዘርዝሮ መጨረስ የሚታሰብ አይደለም:: አንዳንዶቹን ብቻ ጠቆም አድርጌ አልፋለሁ፣ ዝርዝሩን በተከታታይ ለማውጣት በማሰብ:: በእንድርያስና በሌሎች የሙስና ተባባሪ ቢሮዎች አንዳንድ ጸሀፊዎች በየወሩ በአማካይ በአበልና በተጨማሪ ስራ ስም 10 ሺህ ብር ይከፈላቸዋል:: ለዚህ አብነት በእንድርያስ ቢሮ ጸሀፊ የሆነችውን ወ/ሪት አምለሰትን መጥቀስ በቂ ይመስለናል:: ይች ሴት ከተቀጠረች 3 አመት ያልሆናት ቢሆንም፣ በ 1200 ብር የጀመረው ደሞዟ ዛሬ PhD ላለው ከሚከፈለው በላይ ነው:: በአበልና በየጊዜው በትርፍ ስራ ስም የሚከፈላትን ከፋይናንስ መረጃውን በቀላሉ ማግኘት ስለሚቻል እዚህ አላነሳውም። ባነድ ወቅት ከግምሩክ ሁለት የጭነት መኪናዎች እቃ እንዲያመጡ ይላካሉ:: አንዱ ከገባ በኋላ ሌላኛው ቢጠበቅ አይመጣም:: በዚህ የተገረሙት አንዳንድ ሰራተኞች ተስፋቸውን ሳይቆርጡ እዚያው ይቆያሉ:: መኪናው ቆይቶ ባዶውን ይመጣል:: የተጫነውን እቃ ቢጠይቁ ባጭር ቃል የነሱ ጉዳይ እንዳልሆነ ይነገረቻዋል:: ይህን በወቅቱ የአስተዳደር የበላይ ሃላፊ ለነበሩት ለአቶ ብዙነህ ዳዲ ሪፖርት ያደርጋሉ:: አቶ ብዙነህ ይህን ግልጽ ዝርፊያ ለማውጣጣት ጥረት ያደርጋሉ:: በዚያው ሙከራቸው ወቅት በርካታ ሌሎች ጉዳዮችን መስማት ይጀምራሉ:: አሁን ትንሽ ጋብ ያለ በሚመስለው የዩኒቨርሲቲው ጋራዥ ከሁለት አንዱ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ግቢ ሳይገባ እዚያው አየር በአየር እንደሚሻገር፣ ግቢ ከደረሰም ለማስመሰል ትንሽ አራግፎ የቀረውን ይዞ እንደሚወጣ፣ ይህም የተለመደ ተግባር እንደሆነ ይረዳሉ:: ጉዳዩን ለሚመለከተው ክፍል አስታውቀው፣ የዘረፋውን ቀንደኛ ተዋናኝ አቶ ወንድሙን ከሀላፊነቱ ያነሱታል:: ሆኖም፣ ሰውዬው በእንድርያስ ቀጭን ትእዛዝ ቦታው እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ በተገላቢጦሹ አቶ ብዙነህ ይመሩት የነበረው ቦታ ለሁለት ተሰንጥቆ ከስልጣናቸው ዝቅ እንዲሉ ተደረገ:: ይህ አልበቃ ብሎ ከፍተኛ የተንኮል ቡድን ዋንኛ ተዋናኝ የሆነችው በወቅቱ የግቢው የጸረ ሙስና ቢሮ ሃላፊ የነበረችው ሂሩት ወልደማርያም በአቶ ብዙነህ አስተዳደር ላይ ቅሬታ አለ በማለት ኮሚቴ አቋቁማ ዘመቻ ተጀመረባቸው:: አቶ ብዙነህ ምንም እንኳን የማስተርስ ድግሪ ቢኖራቸውም የህግ ትምህርት በዲፕሎማ ፕሮግራም ማጥናት ጀመሩ:: ይህን ያደረጉት ራሳቸውን ለመከላከል እንደሆነ ይናገራሉ:: (በነገራችን ላይ አቶ ወንድሙ ወንጀሉ እየበዛ በመምጣቱ የጥቅም ተካፋዮቹ ከማያድኑበት ደረጃ ደረሰና እነሱ ሳያውቁ/ ሳይካፈሉ ያደረሳቸው ወንጀሎች ብቻ ተዘርዝረው ዛሬ ከርቸሌ ወርዷል::)

የአሰራር ብልሹነት
ዛሬ የዲፓርትመንት ሀላፊነት ሳይቀር “ስልጣን” እየሆነ መጥቷል:: ከተወሰኑ ዲፓርትመንቶችና ፋካሊቲዎች በስተቀር አንዴ የተመረጠ ከስልጣኑ የሚወርደው በህጉ መሰረት ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አስተዳደር ከተጋጨ አልያም አልፈልግም ካለ ብቻ ነው:: በተለይ ትልቅ ጥቅማ ጥቅም ባሉባቸው ፋካሊቲዎች ሀላፊነት በቀላሉ የሚለቀቅ ነገር አይደለም:: ለምሳሌ በቀድሞው ስሙ SISA በመባል የሚታወቀው ተቋም ከ 10 ዓመት በላይ አንድ ሰው እስካሁን ዲን ሆኖ ቆይቷል::

በቅርቡ የተደረገው “የመዋቅር ማስተካከያ”ና ያንን ተከትሎ የተደረገው ሹመት ባለፈው መጣጥፍ ብዙ ስለተባለ እዚህ አልደግመውም:: ሆኖም ባሁኑ ወቅት እንድርያስን ከቦ ስላለው በመሰሪነቱ በሚታወቀው በሞገስ ይገዙ ስለሚመራው አዲሱ የዘራፊ ቡድን ትንሽ ማለት ፈለግሁ፣ ግዜ ከፈቀደ በሚቀጥለው ጽሁፌ በዝርዝር የማነሳው ይሆናል:: ባሁኑ ወቅት ካንድ የትምህርት ክፍል አራት ሰዎች በዳይሬክተርነት፣ በዲንነት፣ በምክትል ፕሬዜዳንትነት ሹመት ይዘዋል:: (ይህ መሰሪ ቡድን ለጥቅምና ለሹመት የሚሮጥ ብቻ ሳይሆን ለዚህ ችግር ናቸው ያላቸውን ለማስወገድ ወደኋላ የማይል ነው:: በዶ/ር ግርማ አውግቸው ላይ የደረሰው ግፍ፣ የፖለቲካ ጉዳይ ያለበት ሊሆን ቢችልም፣ በዚህ ቡድን ዋንኛ ተዋናኛንነት የተቀነባበረ ለመሆኑ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተሰወረ አይደለም:: ስለጉዳዩ በቁምነገር መጽሄት ቅጽ 9 ቁጥር 104 ጥቅምት 2003 እትም ላይ ታዋቂው ገጣሚና ጋዜጠኛ ታገል ሰይፉ የዘገበውን ይመልከቱ::) ስለሌሎቹ የሹመት አይነቶች ከዚህ በላይ በተለያዩ ቦታዎች ያነሳሁትን ይመልከቱ::

የተማሪዎች ሁኔታ
እዚህ ስለተማሪዎች ብዙ መናገር ባልችልም ከንጽህና ጋር ከተያያዘ ችግር በተጨማሪ ድሮ ለአራት ተማሪ ያገለግል የነበረው አንድ መኝታ ክፍል ዛሬ ከ 8-10 ተማሪዎች ያገለግላል:: በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በማታ በየጥጋጥጉ ሴትና ወንድ ተኝተው ማየት የተለመደ ነው:: ባንድ ወቅት ይህን ሪፖርት ያደረጉ የግቢው የጥበቃ አባላት ከእንድርያስ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ብቻ ሳይሆን ማንም የፈለገውን ቢያደርግ ማስቆም እንደሌለባቸው ተገልጾላቸዋል። ይህ ልቅነት በተወካዮች ምክር ቤት የባህል ዘርፍ ሀላፊ ለሆኑት ለወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ የመለስ ሚስት፣ ሪፖርት መደረጉ ትዝ ይለኛል:: ለችግሩ መፍትሄ ተብሎ በእንድርያስ የተወሰደው በሴት ተማሪዎች መኝታ ቤት ህንጻ መግቢያ ላይ የኮንደም መሸጫ ሱቅ መክፈት ነው:: ዩኒቨርሲቲ እውቀት የሚገበይበት ቦታ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች በስነምግባር ታንጸው የሚወጡበትም ተቋም ነው:: (የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከ 18 ዓመት በላይ በመሆናቸው በፍላጎታቸው ለይ ጣልቃ ማንም እይገባ እንዳልሆነ የምትረዱ ይመስለኛል፣ በየሜዳው ለሚደረገው ነው ተቃውሞው::) ተማሪዎችን ስነምግባራቸው የተበላሸ የማድረግ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይሆንልኝም፣ በዩኒቨርሲቲውና በአገሪቱ እየተደረጉ ያሉትን ሌሎች ነገሮች ሳስተውለው የተቀነባበረ ትውልድ የማጥፋት ዘመቻ ይመስለኛል:: ከርእሴ እንዳልርቅ ለዚህ ጥርጣሬዬ ሁለት ክስተቶችን ብቻ ልጥቀስ:: ባንድ ወቅት የደህንነት አባል በተማሪ ተመስሎ ኦሮሞን የሚያጥላላ ጽሁፍ ያለበት ካናቴራ ለብሶ የዘር ግጭት በተማሪዎች እንዲነሳ አድርጓል:: ከሶስት ዓመት በፊት ቁራን እተማሪዎች ሽንት ቤት ተቀዶ በመገኘቱ ከፍተኛ ግጭት ሊነሳ ነበር:: ሆኖም ባለፈው መጣጥፍ የተጠቀሰው የጥበቃ ሀላፊ ድርጊቱን እንደፈጸመ ተማሪዎች ስለደረሱበት በሙስሊምና በክርስትያን ተማሪዎች መካከል እንዲነሳ የታሰበው ግጭት ሳይሳካ ቀርቷል:: ዛሬ አብዛኛው የዩኒቨርሲቲው ዲፓርትመንት በድህረ ምረቃ ፕሮግራሙ ተማሪውን በራሱ ማስገባት አይችልም፤ መንግስት (ትምህርት ሚኒስቴር) መልምሎ የሚልካቸውን ብቻ ነው:: ከእነዚህ ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የኢህአዴግ አባሎች ብቻ ናቸው:: ይህ ወደ ሌላ ነጥብ ስለሚወስደኝ በሌላ ግዜ ብመጣበት ይሻላልና እዚሁ እተወዋለሁ::

በዚህ መጣጥፍም ሆነ ከዚህ በፊት በቀረበው መጣጥፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለተንሰራፋው ሙስናና አድሎአዊ አሰራር ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ላለነና ዩኒቨርሲቲውን በቅርብ ለሚከታተሉ የተሰወረ ጉዳይ አይደለም:: እንደውም የተጠቀሰው በጣም ትንሽና አብዛኛው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የሚያውቀው ጉዳይ ብቻ ይመስለናል:: እንደዚህ አይነቱ ነገር ዝም ብሎ እያለፈ ያለው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስላላወቀው ሳይሆን ብጮህም ምን አመጣለሁ ብሎ ይመስላል:: በርግጥም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ያልቀረበበት ግዜ አልነበረም:: ለምሳሌ ሬድዮ ፋና ከአንድ ከሁለት ዓመት በፊት በመረጃዎች ላይ የተመሰረቱትን ጥቆማዎች ብቻ በመያዝ በተከታታይ ለሁለት ሳምንታት (ምናልባትም ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል፣ ግዜው ስለራቀ ማስታወስ አልቻልኩም) በርካታ የሙስና ተግባራትንና ወንጀሎችን አቅርቦ ነበር:: በወቅቱም ሬድዮ ፋና የኢህአዴግ ጣብያ እንደመሆኑ ችግሩ መፍትሄ ያገኛል የሚል እምነት ነበር:: ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የፌደራል ጸረሙስና ኮሚሽን አንድ ኮሚቴ አቋቁሞ ለረጅም ግዜ ጥናት ካደረገ በኋላ ለእኛ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የጥናቱን ውጤት ሳያቀርብ እንዲቋረጥ ተደርጓል:: ይህ መስሪያ ቤት እኛ እስከምናውቀው ድረስ በየግዜው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ስለሚደረጉት የሙስና ወንጀሎች ጥቆማ ያልደረሰው ግዜ የለም:: ሶስተኛ በተወካዮች ምክር ቤት የትምህርት ዘርፍ ሀላፊ በነበሩት የሚመራ ቡድን ስለጉዳዩ በዝርዝር ጥናት ማድረግ ጀምሮ ነበር – ጉዳዩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዜዳንት ዶ/ር እንድርያስ እሸቴ የተወካዮች ምክር ቤት የዘርፉ ሀላፊ ባሉበት ስብሰባ ላይ የሳይንስ ፋኩልቲውን ዲን ሲሰድብ ቆመ እንጂ:: ጉዳዩን ትንሽ ላብራራ:: በርግጥ እዚህ ትንሽ ያጋነንኩ ይመስለኛል:: እዚያ ስብሰባ ላይ የቀረበ ውሳኔ አልነበረም:: ግን ከዚያ ስብሰባ በኋላ ሁሉም እንቅስቃሴ ቆመ:: ያ ቁጣ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰዎች ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ነበር፣ አርፋችሁ ተቀመጡ የማለት:: በርግጥም ቁጣው አልሰራም ማለት አይቻልም:: ከዚያ ስብሰባ በኋላ በግቢው የታየ የተወካዮች ምክር ቤት የጥናት ቡድን ይቅርና ስለጉዳዩ የሚያነሳ የቡድኑ አባል እንኳን አልተገኘም:: (በነገራችን ላይ እንድርያስ እሸቴ ሰው መዛለፉን ባህል አድርጎ የያዘው ይመስላል:: ለምሳሌ አንድ ስብሰባ ላይ የቀድሞዋን የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ገነት ዘውዴን፣ በሌላ ወቅት ደግሞ የሴቶች የህግ ባለሙያዎች ማህበር ሊቀመንበርን በአደባባይ ዘልፏል::) ለመሆኑ፣ ከላይ ለተገለጸውና ላልተገለጸው የተንሰራፋ ሙስናና አድሎአዊ አሰራር ዋነኛ ተዋናኝ የሆነው እንድርያስ እሸቴ ማነው? ይህን ሁሉ ወንጀል ሲሰራና ሲያሰራ፣ የፈለገውን ባለስልጣን ሳይቀር በየአደባባይ ሲዘልፍ እንዴት ዝም ሊባል ቻለ? ለእነዚህና ተያያዥ ጥያቄዎች በእንደዚህ አይነቱ አጭር መጣጥፍ መልስ መስጠት ከባድ ቢሆንም ፍንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ግን አነሳለሁ::

እንድርያስና የመለስ ቤተሰብ
ባለፈው “Rise against delinquency, charlatanism and neo-patrimonial bondage at Addis Ababa University” በሚል ርእስ በቀረበው መጣጥፍ ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ በ”ETHIOPIAN REVIEW” ድር ገጽ ላይ እንድርያስ እሸቴ አስተማሪያቸው እንደነበረና ሰውዬው “ጂኒየስ” እንደሆነ ግን ሴት ተማሪዎች ጋር ችግር እንደነበረበት ገልጸዋል:: ሁለቱም መሰረት ያላቸው አይመስሉኝም:: ሰውዬው በተማሪነት ግዜው ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎች ውስጥ አንዱ እንደነበረ በወቅቱ ተማሪ የነበርን የምንክደው ጉዳይ አይደለም:: በተማሪዎች የ 60 ዎቹ እንቅስቃሴ ወቅትም አንዳንድ መጣጥፍ ይጫጭር እንደነበረ እናውቃለን:: ሆኖም በትምህርት ዘርፍ፣ ሙሉ ፕሮፌሰርነት ማንም ተቋም ለእንድርያስ አለመስጥቱ ብቻ ሳይሆን አንዲት መጣጥፍ እንኳን ለስሙ የለውም።

ሁለተኛ ይህ ሰው ባህኑ ግዜ የሚታማበት ፈጽሞ በሴት መውደዱ አይደለም:: ያ የግል ጉዳዩ ስለሆነ እዚህ ምንም የምለው አይኖርም:: ከፍተኛ ተቋማት የሚተዳደሩት፣ በመርህ ደረጃ፣ በትምህርት ሚኒስቴር ስር ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንቶችም በቀጥተኛ ለከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ተጠሪ ናቸው:: ሆኖም፣ እንድርያስ እሸቴ የተሾመው በቀጥታ በመለስ ዜናዊ ነው:: ልብ በሉ፣ እንድርያስ እሸቴ ወደሀገር ቤት ከመጣ በኋላ የሰመሀል፣ የመለስ ዜናዊ ልጅ፣ የቤት ውስጥ አስጠኚ ነበር:: በወቅቱ ሌሎቹን ልጆቹን ዶ/ር ሳሙኤል፣ አሜሪካ በኋላ አምባሳደር ተደርጎ የተሾመው፣ ያስጠና ነበር:: (በነገራችን ላይ ሰመሀል መለስ እንግሊዝ ሀገር መማር ከጀመረች 4 ዓመት ሆኗታል:: አሁንም እዚያው ነው ያለችው):: ይህን የማነሳው እንድርያስ ከመለስ ቤተሰብ ጋር ምን ያህል ትስስር እንዳለው ለመጠቆም ነው:: በእንድርያስ አማካኝነት ከዩኒቨርሲቲው የሚዘረፉ ትላልቅ ብሮች (በዓመት በአማካይ 20 ሚሊዮን የእርዳታና የብድር ብር) በቀጥታ ወደ አዜብ መስፍን እንደሚገባ ይነገራል:: በርግጥ ለዚህ ተጨባጭ ማስረጃ የለኝም:: ሆኖም፣ ሴትዮዋ በሌሎች ሙስናዎች ላይ ያደረገችውን በህግ ጣልቃ ገብነት ላስተዋለ ይህ ሀሰት ነው ለማለት ይከብዳል:: ለዚህ ጥርጣሬ ህዝብ የሚያውቃቸውን ሁለት ጉዳዮች ብቻ ላንሳ፣ ከርእሴ እንዳርልቅ በማለት:: 1 ኛ፣ ከ 1.5 ቢሊዮን ብር የቴሌ ፕሮጀክት ላይ 2% አንድ የቴሌ ባለስልጣን ሲደራደር የቻይና የስላላ ቡድን በድምጽ ይቀዳዋል:: ያንንም ከሌሎች መረጃዎች ጋር የዛሬ 2 ዓመት አካባቢ ለየቴሌ ባለስልጣንና ለሚመለከታቸው ሁሉ ተበትኖ ነበር (መረጃው እጄ አለ):: ሰውዬውም ለአንድ ወር ከታሰረ በኋላ በአዜብ ትእዛዝ እንዲለቀቅ ተደርጓል:: 2 ኛ፣ አቶ እያሱ በርሄ (አሎ በሎ)፣ ሳተላይት ጠምዶ ከ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ቴሌ ላይ ኪሳራ በማድረሱ በቁጥጥር ውሏል በሚል በሚዲያ ተላልፎ ነበር:: ይህን ብዙዎቻችሁ ታስታውሱ ይሆናል:: ከዚያ በኋላ የሆነውን ጉዳይ ልንገራችሁ:: በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ይህን ሰው ፖሊስ ልመረምረው አልችልም በሚል ለቴሌ ያሳውቃል:: ቴሌም ግራ ተጋብቶ የተወሰኑ ባለስልጣኖችን ወደፖሊስ ጣብያ ይልካል:: የቴሌ ባለስልጣኑ ፖሊስ ጣብያ እንደደረሱ ለአቶ እያሱ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ይነገራቸዋል:: የሂደቱን ዝርዝር ልተወውና አቶ እያሱ የተባለውን እንዳደረገ፣ ይህን እየሰራ ያለው ግን ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር እንደሆነና ስለጉዳዩ መለስም እንደሚያውቅ ይነግራቸዋል:: አስፈላጊ ከሆነም ደውለው እንዲጥይቁ የአዜብንም ሆነ የመለስን ስልክ ሊሰጣቸው እንደሚችል ያሳውቃል:: የቴሌ ባለስልጣናቱ በመጀመሪያ ደረጃ ፖሊስ መረጃ እስካለው ድረስ ከመስሪያ ቤታቸው የህግ ክፍል ጋር ተነጋግሮ ወደ ፍርድ ማቅረብ እንጅ፣ እነሱ በጉዳዩ ላይ መወሰን እንደማይችሉ፣ የተጠሩትም ለዚህ ከሆነ አግባብ እንዳልነበር ገልጸው ፖሊስ ጣብያውን ለቀው ይወጣሉ:: አቶ እያሱም ወዲያው ይለቀቃል:: ከዚያም፣ ሁኔታው እስኪረሳ ወደውጭ ይቆይ በሚል ዱባይና ሳኡዲ ለ 1 ዓመት ያህል ቆየ:: ይህን ትእዛዝ የሰጥችው ወ/ሮ አዜብ እንደሆነች ይነገራል:: እያሱ ወደሀገር ከተመለሰ በኋላ ከወ/ሮ አዜብ ጋር ግጭት ውስጥ ገባ (“ሌባ ሲካፈል ነው የሚጣላው” እንዲሉ):: ህይወቱ በድንገት ያለፈው በደም ብዛት ነው ቢባልም በአሟሟቱ ላይ የአዜብ እጅ እንዳለበት በሰፊው ተወርቶ ነበር:: ስለ ቴሌ ብዙ ማለት እችል ነበር:: ግን ከርእሴ ያወጣኛል:: ግዜ ከፈቀደ ሌላ ግዜ እመለስበት ይሆናል:: እነዚህን ነጥቦች ያነሳሁት የእንድርያስ በስልጣን ላይ መቆየት ዋንኛው ከመለስ ቤተሰብ ጋር ካለው ቤተሰባዊ ቁርኝት በተጨማሪ የጥቅም ትስስርም እንደሆነ ለማሳየት ነው:: ይህ ባይሆን ኖሮ ቢያንስ ገደብ ያጣው ዝርፊያ ላይ አንድ እርምጃ ይወስዱ ነበር ብዬ እገምታለሁ:: ስለዚህ ባለፈው መጣጥፍ አቅራቢዎች ብሶታቸው ቢገባኝም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ መነሳት ያለበት በእንድርያስ አስተዳደር ብቻ ላይ ሳይሆን በአጠቃላይ በመለስ ዜናዊ ስርአት ላይ መሆኑን ማስተዋል የሚገባ ይመስለኛል – ሁለቱ የሚነጣጠሉ አይደሉምና:: ዘረኛውንና በሙስና የተዘፈቀውን የመለስ ዜናዊን ስርአት ለመገርሰስ መታገል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተንሰራፋውን ብልሹ አሰራርም መታገልም ነው:: “ሰማይ ለመርገጥ የዘለለች ቁንጫ ጣራ ሳትነካ አትመለስም” የሚለውን የሀገራችንንም ብሂል ልብ ይሏል::

ቸር እንሰንብት!