ወያኔ በሐይማኖት ተቋማት ላይ የከፈተውን የጥፋት ዘመቻ የሚያወግዝ ሰልፍ በዲሲ ተካሄደ

“……ሁሉም ነገር ተወሰደ፣ ሁሉንም ነገር አጣን….”  አባ ገብረማርያም

በዛሬው ዕለት (ማርች 26, 2012) በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሐይማኖት፣ ዘር፣ጾታ ሳይለዩ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሚገኘው የወያኔ ኢምባሲ ፊትለፊት በመገኘት፤ ወያኔ በቅርቡ በተቀነባበረ ሁኔታ የሃይማኖት ተቋማት ላይ የከፈተውን የማፈራረስና የማውደም ዘመቻ ላይ የተሰማቸውን ቁጣና ተቃውሞ በጋለ መንፈስ ገልጸዋል።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን በመለስ ዜናዊና በታጋይ ጳውሎስ (አባ ገብረመድኅን) አማካይነት ለብዙ ምዕተ ዓመታት ታፍረውና ተከብረው የነበሩ ገዳማትን የማፈራረስና በእሳት  የማጋየት ሴራን አበክረው አውግዘዋል። በዚህም መሠረት ታላቁን የዋልድባ ገዳምን በ”ልማት” ስም የማፍረስና የአባቶችን የመቃብር ሥፍራ የማርከስና በዶዘር የማረስ እኩይ ተግባርና እንዲሁም ታሪካዊዎቹን የአሰቦትና የዝቋላ ገዳማት ላይ እሳት ሆን ብሎ በመለኮስ ገዳማቱን የማጥፋት መሰሪ ተግባር በጽኑ ሁኔታ ተቃውመዋል። ከዚህም በተጨማሪ  ተሰላፊዎቹ ሙስሊሞች ሐይማኖታቸውን ለማዳን በማድረግ ላይ ያሉትን እርምጃዎችን እንደሚደግፉ አበክረው ገልጸዋል። በዚህ ትዕይንተ ሕዝብ ላይ በፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ መርቆሪዎስ በሚመራው በህጋዊው ሲኖዶስ ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ተገኝተዋል። ትዕይንተ ህዝቡን በጸሎት የከፈቱትና ሲፈጸምም በጸሎት የዘጉት የህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የሜሪላንድ ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ  ፊሊጶስ ናቸው።