ገበያ ሲያመች
ከዳንኤል ክብረት
በድሮ ዘመን ነው አሉ፡፡ ልጂቱ ምጣድ ልትገዛ ገበያ ትወጣለች፡፡ ጥሩ ምጣድ መርጠው እንዲገዙላት እናቷን አስከትላለች፡፡ ገበያ ስትገባ እንዴው ሁሉም ነገር ቀልጧል፡፡ የማይሸጥ የማይለወጥ ነገር የለም፡፡ «ምነው?» «ስትል ጦር ሊመጣ ነው ተብሎ ሁሉም ነገር ተወዷል» ይሏታል፡፡ «ምን ምን ይሸጣል?» ብላ ትጠይቃለች፡፡ «ምን የማይሸጥ ነገር አለ፡፡ ከብት ይሸጣል፣ ወርቅ ይሸጣል፣ እህል ይሸጣል፣ ልብስ ይሸጣል፣ ሰውም ይሸጣል» ይሏታል፡፡
«ደግሞ ሰው ለምን ይሸጣል?» ብላ ትጠይቃለች፡፡ «ባርያ መሸጥ መለወጥ ሊቀር ስለሆነ ሁሉም አሁን እየገዛ ነው» ትባላለች፡፡ እናቷን አንድ ጥላ ሥር አሳርፋ ሄዳ ስታይ እውነትም ልጅ ዐዋቂው፣ ባልቴት ሽማግሌው ሁሉ በባርያ ፈንጋይ እየተያዘ ይሸጣል፡፡ ስትሮጥ ሄደችና እናቷን ይዛ መጥታ በአራት ከብት ለወጠቻት፡፡ ነገሩን የሰማው የሀገሬ ሰው ጉድ ጉድ ብሎ ሲያበቃ «ገበያ ቢያመቻት እናቷን ሸጠቻት» የሚል ተረት አወጣላት፡፡
የሁኔታዎች መመቻቸት የሚያመጡትን ኢሞራላዊነት ከገለጥንባቸው ነባር አባባሎቻችን አንዱ ነው ይኼ፡፡ «የአንዳንዱ ሰው ትክክለኛነት፣ ቆራጥነት፣ ሞራላዊነት፣ ጥንካሬ፣ የዓላማ ጽናት፣ እምነት፣ ገበያው እስኪ ያመቸው ድረስ ነው፤ ገበያ ካመቸው ሁሉንም ሽጦ ለማትረፍ ዝግጁ ነው» ነው የሚሉን ቀደምቶቻችን፡፡
ገበያ ሲመች የማይሠራ ኢሞራላዊ ሥራ የለም፡፡ ገበያ ሲመች ሀገር ይሸጣል፣ ኅሊና ይሸጣል፣ መሬት ይሸጣል፣ ቅርስ ይሸጣል፣ ስም ይሸጣል፣ ባህል ይሸጣል፣ ፍትሕ ይሸጣል፣ እናት ይሸጣል፣ አባት ይሸጣል፣ ልጅ ይሸጣል፣ አካል ይሸጣል፣ ሞያ ይሸጣል፣ ሰርተፊኬት ይሸጣል፣ ክህነት ይሸጣል፣ እምነት ይሸጣል፡፡ ምን የማይሸጥ ነገር አለ፡፡
አንዳንዶች ለመኖር ኅሊናን መሸጥ የሚያዋጣ ከመሰላቸው ከመሸጥ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ገበያ ካመቸ ኅሊናን ይሸጡታል፡፡ መመዘኛቸው ትክክል ነው አይደለም፣ ሞራላዊ ነው አይደለም፣ እውነት ነው አይደለም፣ ሕጋዊ ነው አይደለም የሚለው ሳይሆን ያዋጣል ወይስ አያዋጣም የሚለው ብቻ ነው፡፡ እየሠሩ ያለው ነገር ከሚያምኑበት ነገር ጋር ቢጋጭም ባይጋጭም፣ ትናንት ሲያስቡት ከነበረው ነገር ጋር ቢለያይም ቢስማማም፣ ቀድሞ ከተናገሩት ነገር ጋር ቢሠመርም ባይሠምርም ዋናው ነገር አሁን ያዋጣል ወይስ አያዋጣም ብቻ ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የሚሞቱለት አቋም፣ ሃሳብ፣ ርእዮተ ዓለም፣ መሥመር፣ እምነት፣ ማንነት፣ ራእይ የላቸውም፡፡ እንኳንስ ሃሳባቸውን እና አቋማቸውን የሚያዋጣ ሆኖ ካገኙት የትውልድ ቦታቸውን፣ ብሔረሰባቸውን እና ወላጆቻቸውን ጭምር ለመቀየር ዝግጁ ናቸው፡፡ ትናንት አዋጥቷቸው ጎጃም ተወልደው እንደሆነ የዛሬውን ገበያ አይተው ጎንደር ሊወለዱ ይችላሉ፡፡ ጎንደር መወለዳቸው የረከሰ ከመሰላቸውም ትግራይ ወይንም ወለጋ ከመወለድ ወደ ኋላ አይሉም፡፡
እነዚህ ሰዎች አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ሶማሌ ወይንም ጉራጌ የሚሆኑት ከዚያ ማኅበረሰብ ስለተወለዱ ወይንም እዚያ ስላደጉ፣ ያለበለዚያም ቋንቋውን ስለሚናገሩ አይደለም፡፡ ያዋጣል ወይስ አያዋጣም? ነው መመዘኛው፡፡ ገበያው ካመቼ ማንነትም ይቸበቸባል፡፡
ሰው አመለካከቱን፣ አቋሙን ወይንም ርእየቱን ሊቀይር ይችላል፡፡ ነገር ግን ተአምራዊ በሆነ ድንገቴ መንገድ ሰው እነዚህን ነገሮች ሊቀይር አይችልም፡፡ የሰው ኅሊና እንደ ኮምፒውተር በፈለጉት ጊዜ የፈለጉትን ሶፍትዌር በፍጥነት የሚጭኑበት አይደለምና፡፡ ማሰብ፣ ማብሰልሰል፣ ከራሱ ጋር መሟገት፣ መረዳት፣ ማስረዳት፣ መመዘን፣ ማመዛዘን ይፈልጋል፡፡ ሲያምንም በምክንያት ነው፣ ሲለወጥም በምክንያት ነው፡፡
የገበያ ሰዎች ግን እንደዚህ አይደሉም፡፡ አንድን አቋም ወይንም አስተሳሰብ፣ አመለካከት ወይንም ርእዮተ ዓለም የሚመዝኑት ከአቋማቸው እና ከአስተሳሰባቸው አንፃር አይደለም፡፡ ትክክል ነው ወይንስ ስሕተት፣ ያስኬዳል ወይስ አያስኬድም፣ ያሳምናል ወይስ አያሳምንም፣ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም፣ ሕጋዊ ነው ወይስ አይደለም፣ የሚል መመዘኛ የላቸውም፡፡ ይሸጣል ወይስ አይሸጥም ነው ጥያቄአቸው፡፡
ያለ ምንም አሳማኝ ምክንያት ሰው ይዞት ከነበረው አቋም በድንገት በተቃራኒው ከተገኘ አንዳች የሚያዋጣ ገበያ አግኝቷል ማለት ነው፡፡ ሰው እንዴት በድንገት ከተቃዋሚነት ወደ ደጋፊነት ከደጋፊነትም ወደ ተቃዋሚነት ሊቀየር ይችላል፡፡ አስተሳሰብ ሂደት እንጂ ተአምር አይደለማ፡፡
በሀገራችን የየከተማውን መሬት ቸብችበው ቸብችበው የጨረሱት እነማን ናቸው? ለገበያ እንጂ ለኅሊናቸው የማይሠሩ ናቸዋ፡፡ መሬት ውድ ነው? አዎ፡፡ ሚሊየን ብር ያስገኛል? አዎ፡፡ የተቀመጡበት ቦታ ሊያስቸበችብ የሚያስችል ነው? አዎ፡፡ እነ እገሌ የከበሩት መሬት ሽጠው አይደለም? አዎ፡፡ ታድያ እኔስ የምችለውን ያህል ሽጬ የድርሻዬን ብወስድ ምናለ? እንዴ ኅሊና የለም እንዴ፡፡ ገበያው ያመች ይሆናል፡፡ ግን ገበያ ስላመቸኮ እናት አትሸጥም፡፡
የሀገር ሕግ ሊላላ ይችላል፡፡ ሁኔታዎች ሊያመቹ ይችላሉ፡፡ ገበያው ደርቶ ይሆናል፡፡ ዕድል እንደ ትኩስ ኬክ ፊት ለፊት ቀርቦ ይሆናል፡፡ እድሜ ልክ ተሠርቶ የማይገኝ ገንዘብ በካሬ ሜትር ይገኝ ይሆናል፡፡ ግን ኅሊናስ፡፡ አእምሮስ፡፡ ኢትዮጵያ የኛስ ሀገር አይደለችም እንዴ፡፡ ትውልድስ? ነገስ? አይታሰብም እንዴ፡፡
ሰውኮ ከእንስሳ ከሚለይባቸው ነገሮች አንዱ እርሱ ህልው ሆኖ ከሚኖርባቸው ዘመናት በኋላ ላለው ህልውናውም ስለሚያስብ ነው፡፡ በዐጸደ ሥጋ እያለ በአካል ህልው ይሆናል፡፡ በአካልም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዐጸደ ሥጋነት ሲያልፍ ደግሞ በታሪክ ውስጥ ህልው ይሆናል፡፡ ወይንም በዐጸደ ነፍስ ህልው ይሆናል፡፡ ሰውኮ ስለ ሁለተኛ ህላዌውም መጨነቅ አለበት፡፡ እኔ ከሞትኩ ያለችውኮ ማን እንደሆነች እናውቃታለን፡፡
ከጣልያን ጋር አምስት ዓመታት የተዋጉት አርበኞች በዘመናቸው ለመጠቀም አልነበረም መሥዋዕትነት የከፈሉት፡፡ እንዲያውም በዘመናቸው ለመጠቀም ከጣልያን ጋር መሞዳሞዱ የተሻለ ይሆንላቸው ነበር፡፡ ሀገራቸውን እና ክብራቸውን ሽጠው የዕለት ክብር የዓመት ግብር ማግኘት ይችሉ ነበር፡፡ ግን ሌላም ነገር አለ፡፡ ታሪክ አለ፡፡ ማንነት አለ፡፡ ሀገራዊ ክብር እና ኩራት አለ፡፡ የዜግነት ግዴታ አለ፡፡ ይህ ነው አስገድዶ ጫካ ያስገባቸው እንጂ ሀገር ለመሸጥማ እንደዚያ ጊዜ አመቺ ገበያ አልነበረም፡፡ እነርሱ ግን ገበያ አመቸ ብለው እናታቸውን አልሸጡም፡፡
ሰው ጉቦ ለመቀበል መሟገት ያለበት ከኅሊናው ጋር ነው፡፡ ሁኔታዎቹ ጉቦ ለመቀበል ያመቻሉ ወይስ አያመቹም አይደለም መመዘኛው፡፡ ሰው በዘመድ አዝማድ ለመሥራት መመዘኛው የነገሩ ትክክል መሆን እና አለመሆን እንጂ ጊዜው ለዘመድ አሠራር ያመቻል ወይስ አያመችም መሆን አልነበረበትም፡፡
አሁን አሁንኮ ገበያ ኅሊናን እና ልቡናን እየተካ ነው፡፡ የሞራልን እና የእምነትን ቦታ እየወሰደ ነው፡፡ ሁሉ ገበያ መር ከሆነ ለዚህ ሕዝብ የሚያዝንለት ታድያ ማነው? ነጋዴውም ለገበያው፣ ባለ ሥልጣኑም ለገበያው፣ የሃይማኖት መሪውም ለገበያው፣ ገበሬውም ለገበያው ብቻ ከታዘዘ ለኅሊናው የሚታዘዝ ማን ሊሆን ነው፡፡ ይህ እኛ የምናገለግለው፣ የምንሸጥለት፣ የምንወስንለት እና የምንወስንበት ሕዝብ የኛ አይደለም እንዴ፡፡
ገበያው አመቼ ተብሎ የአንድ ብር ጨው አሥር ብር፣ የሁለት መቶ ብር በግ ሦስት ሺ ብር፣ የአሥር ብር ዘይት መቶ ብር፣ የሰባት ብር ስኳር ሃምሳ ብር፣ የሦስት መቶ ብር ጤፍ ሁለት ሺ ብር፣ የሁለት ብር ሽንኩርት ስድሳ ብር መሸጥ አለበት እንዴ፡፡ ይህኮ ዕቃ መሸጥ አይደለም የገዛ ሕዝብን መሸጥ እንጂ፡፡ እንዴት ባህል አንድ ያደረገንን፣ እንዴት ታሪክ አንድ ያደረገንን፣ ገበያ ይለያየናል፡፡ እንዴት እምነት ያፋቀረንን፣ ኢትዮጵያዊነት ያስተዛዘነንን ገበያ ያጨካክነናል፡፡
እንዴው ለመሆኑ እኛ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ ፓስተር፣ ቄስ፣ ሼክ፣ አስመላኪ፣ አስዘማሪ፣ አስ ሰጋጅ፣ ነቢይ፣አጥማቂ፣ መጋቢ፣ አለቃ፣ መልአከ እገሌ፣ ጳጳስ፣ የተባልነው ሰዎች እውነት እንነጋገርና ለቦታው ተገቢ ስለሆንን፣ ዕውቀቱ ስላለን፣ ቦታውን የሚመጥን ጸጋ እና ቅድስና ስላለን ነው ወይስ ገበያው ስላመቼ ነው የተቀመጥነው፡፡ ለመሆኑ የያዝነው ቦታ ክብር፣ ዝና፣ ገንዘብ እና ጥቅም፣ የማያስገኝ ቢሆን ኖሮ አሁን ባለንበት ቦታ ተለምነን እንኳን እንቀመጥ ነበር? ገበያ ስለሚያመች ግን ለቦታው የተሠራውን ሥርዓት ሸጥነው፤ መመዘኛውን ቸበቸብነው፡፡ የፈጣሪን ጸጋ በገንዘብ ለወጥነው፡፡ እኛ ወደ ቦታው መሄድ ሲገባን ቦታውን ወደ እኛ አመጣነው፡፡
ይኼ በየቤተ እምነቱ የምንሰማው ትርምስ፣ ግርግር፣ ውጣ ውረድ፣ ትግትግ፣ ጭቅጭቅ፣ ሙግት በዋናነት የገበያ ግርግር ነው፡፡ ዛሬ ገበያው ከሚገባቸው ሰዎች ይልቅ ለጮሌዎች ያመቻል፡፡ ዛሬ ገበያው ኅሊናቸውን በጥሩ ዋጋ መሸጥ ለሚችሉ ሰዎች ያመቻል፡፡ የሚገባቸው ሰዎች በየጓዳው እና በየፍርክታው ቀሩና የማይገባን ሰዎች ቦታውን ያዝነው፡፡ እነዚያ ለምን ቀሩ? ኅሊናቸውን መሸጥ ባለመቻላቸው፡፡
«በከንቱ የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ» ያለውን የፈጸሙትማ ኩርማን እንጀራ በልተው፣ አጎዛ ላይ ተቀምጠው፣ መደብ ላይ ተኝተው ለፈጣሪ ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡ እነዚያማ እውነትን ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ ለያዙት እውነት መሞትን መረጡ፡፡ እነዚያማ በአቋማቸው ላይ ከመደራደር ይልቅ ከነ አቋማቸው መሰቃየትን መረጡ፡፡ እነዚያማ ጥያቄያቸው ስንት? የሚል ሳይሆን ለምን? የሚል ሆነ፡፡ እውነተኞች እንጂ ገበያተኞች መሆን ስላቃታቸው ከገበያ ውጭ ሆኑ፡፡
ገበያ ካመቸ ልጅም ትዳርም እንደሚሸጥ በዘመናችን አየንኮ፡፡ እዚህ አሜሪካ ብቻቸውን ለሆኑ እናቶች መንግሥት የሚሰጠው የተለየ ክብካቤ እና የገንዘብ ርዳታ አለ፡፡ ታድያ አንዳንዱ ባለ ትዳር የሀገሬ ሰው ተስማምቶ በፍርድ ቤት ይለያያል፡፡ ከዚያም ባልም ለብቻ ሚስትም ለብቻ በመኖር ይህንን ርዳታ ይቀበላሉ፡፡ ባህል ደኅና ሰንበት፣ ይሉኝታ ደኅና ሰንብት፣ ሃይማኖት ደኅና ሰንብት ማለት ይኼኔ ነው፡፡
አንዳንድ ቦታማ ይኼ ተለያይቶ መኖር ይለምድባቸውና በዚያው ተፋትተው የሚቀሩ ብዙ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ገበያ ትዳርን ሽጦ ገንዘብ ያስገኛል፡፡ ገበያ ካመቸ ምን የማይሸጥ ነገር አለ፡፡
በአሜሪካ ምድር የቅንጦት መኪኖችን ከሚነዱ የሀገሬ ልጆች መካከል ጥቂቶቹ ልጆቻቸውን በመሸጥ የገዙት መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ልጅ ለማሳደግ አልቻልኩም ብለው ለአሳዳጊ ሰዎች ያስረክባሉ፡፡ ከዚያም በአንድ በኩል ለልጆቻው ያወጡት የነበረውን ቆጥበው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በልጆቻቸው ቁጥር የታክስ ተመላሽ አሠርተው በሚያገኙት ገንዘብ ደልቀቅ ያለ መኪና ገዝተው ደልቀቅ ብለው ያሽከረክራሉ፡፡ አይቆ ረቁራቸውም፣ አይሰማቸውም፣ አያንገበግባቸውም፣ አያሳፍራቸውም፡፡ ገበያ አመችቷቸው ኅሊናቸውንም ልጆቻቸውንም ሽጠዋልና፡፡
ባህላችን ካቆየልን በጎ ነገሮች አንዱ ለኅሊና መሞት ነው፡፡ በልማዳችን የጠፋ ከብት ያገኘ ሰው እንኳን እስከ ሰባት ዓመት ባለቤቱን ይጠብቅ ነበር፡፡ ሞራላዊነት ከማየሉ የተነሣ ተገፍቶ እና ተጨቁኖ ያደረገው ኢ ሞራላዊ ነገር እየቆረቆረው
ልጅ አሳድግ ብዬ
ካገር እኖር ብዬ
ላባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ
እያለ ያንጎራጉር ነበር፡፡ አንድ ባላባት ተከትሎ የመጣ ጦረኛ በየገበሬው ቤት ይሠማራና ይቀመጣል፡፡ የገበሬው ሚስት ቆንጆ ከሆነች «ይህቺ እኅትህ ናት አይደል» ይለዋል፡፡ አይደለችም ካለ ይገድለዋል፡፡ ወይንም ያሳሥረዋል፡፡ እናም «አዎን» ይላል፡፡ በግድ አዎ አሰኝቶ ሚስቱን ይዞበት ያድራል፡፡ ይህንን ነው በእንጉርጉሮ የገለጠው፡፡
ዛሬኮ ተሰምቶት የሚያንጎራጉር የለም፡፡ እንዲያውም በኩራት ይነገራል፡፡ አራዳነት፣ ቀልጣፋነት፣ ብልጥነት፣ ሆኗል፡፡ ገበያ መር ኢኮኖሚ እንጂ ገበያ መር ማኅበረሰብ በሰላም እና በአንድነት መዝለቅ አይችልም፡፡ የማኅበረሰቡ እሴቶች በሙሉ ለገበያ እየቀረቡ እንዳመቺነቱ ከተቸበቸቡ ያን ሕዝብ አንድ አድርጎ የሚያስተሳስር ምን ነገር ይተርፈዋል?
አንጀቴ ተቆርጦ ከሆዴ ከወጣ
እንግዲህ ሐኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ
አይደል ያለቺው ዘፋኟ፡፡