የ 50 ዓመት የአገር ሽያጭ ውል

ማሳሰቢያ፡- ይህ ዘገባ ከአገዛዙ እጅ ያፈተለከ ባለ 11ገጽ መረጃን በዋቢነት ያጣቀሰ ነው፡፡1

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ‹‹በኢትዮጵያ የመሬት ነጠቃና ነዋሪውን በግዳጅ የማፈናቀል ተግባር››2 በሚል ርዕስ በአገራችን እየተካሄደ ስላለው የመሬት ነጠቃ ሰፋ ያለ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ዘገባ ላይ እንደገለጽነው በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ‹‹መሠረተልማቶችን ለማስፋፋት›› በሚል ሽፋን ነዋሪውን ያለምርጫው ከተወለደበት ቀዬ እንዲነሣ እየተገደደ ወዳልመረጠው ቦታ እንዲሠፍር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመን ነበር፡፡

በዚህ ዘገባ ደግሞ በተለይ የምንዳስሰው በጋምቤላ ክልል በመዠንገር ዞን በጎደሬ ወረዳ በጉማሬ እና በካቦ ቀበሌዎች የሚገኝ በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ 5000 ሄክታር መሬት ‹‹ለኢንቨስትመንት ተመድቧል›› በሚል ደኑ ተመንጥሮ መሬቱ ለባለሃብቱ እንዲሠጥ ለማድረግ የተፈጸመውን ድራማ ይሆናል፡፡ይህ ዘገባ በተለይ በአገዛዙ ውስጥ በኃላፊነት የተቀመጡት ግለሰቦች በአገራችን ሕዝብ ላይ እያደረሱ ያለውን ግፍ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን በአገዛዙ የሥልጣን እርከን ውስጥ ከክልል ቢሮ እስከ አራት ኪሎ በተዋረድ ያለውን መከፋፈልና መናናቅ በማስረጃ የሚጋልጥ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ቀበሌ ነዋሪዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው የሚገኝ 5000 ሄክታር በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ መሬት ተመንጥሮ ለሻይ ልማት እንዲሰጥ መወሰኑን በመቃወም ለፕሬዚዳንት ግርማ አቤቱታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱም ጉዳዩ ተጣርቶ መልስ እንዲሠጥ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን ባዘዙት መሠረት የባለሥልጣኑ መ/ቤት ሚያዚያ 28፣2002 ዓም ለግብርናና ገጠር ልማት ሚ/ር በጻፈው ደብዳቤ ቦታው የተፈጥሮ ደን እንደመሆኑ ለሻይ ልማቱ ሌላ አማራጭ መሬት እንዲሠጥና የተሠጠው ፈቃድ እንደገና እንዲጤን አስተያየት በመስጠቱ ድርጊቱ ይታገዳል፡፡

ሆኖም ግን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡቦንግ ኡሎም ለጎደሬ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ ከ5000 ሄክታር መሬቱ ላይ Verdanta Harvests የተባለ የሕንድ ኩባንያ 3012 (ሦስት ሺህ አስራሁለት) ሄክታር መሬት በ111 ብር (6 ዶላር) በሄክታር ለ50 ዓመት ለመውሰድ ውል የፈረመ ስለሆነ የአንድ ዓመት ቅድሚያ ክፍያ (19ሺህ ዶላር) ከፍሎ ቦታውን እንዲረከብ እንድታደርጉ የሚል ትዕዛዝ ህዳር 10፣2003 ያስተላልፋሉ፡፡ ትዕዛዙም በተዋረድ እንዲፈጸም ቀጣይ መመሪያዎች ይሠጣል፤ ተፈጻሚነቱም ይጀመራል፡፡

በዚህ ድርጊት የተቆጩ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የአገር ሽማግሌዎች ከጉማሬ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ታምሩ አምበሎ ጋር በመሆን ጉዳዩ አስቀድሞ የታገደ በመሆኑ እንዲሁም የሠለጠኑ ባለሙያዎችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደዚህ ያለ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቅ የተፈጥሮ ደን ተጨፍጭፎ ለእርሻ መዋል እንደሌለበት በመጥቀስ ድርጊቱ እንዲቆም መንቀሳቀስ ይጀምራሉ፡፡ ይህ ሲሆን የመዠንግር ዞን ኃላፊዎች የቀበሌውን ምክትል ሊቀመንበር በማስከተል የአካባቢውን ሕዝብ ሰብስበው መሬቱ ለባለሃብቱ እንዲሰጥ ህዳር 16፤2003 ዓም በማስወሰን ለርክክብ መሯሯጥ ይጀምራሉ፡፡ በዚህም ጊዜ የቀበሌው ሊ/መንበር አቶ ታምሩ አምበሎ፣ አቶ አመያ ከሲቶ ከተባሉ የአገር ሽማግሌና አቶ ካሳሁን ከኪሎ ከተባሉ የቀበሌው ነዋሪ ጋር በመሆን ህዳር 30፣2003 በተጻፈ ደብዳቤ የጉዳዩን አሳሳቢነትና አደገኛነት በመጥቀስ ለፕሬዚዳንት ግርማ በድጋሚ አቤት ይላሉ፡፡ በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንቱ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር በመፈጸም፤ የቀደመውን ትዕዛዝ በመጥቀስ እየተደረገ ያለው ተግባር መፈጸም የሌለበት መሆኑን በማብራራት ለግብርና ሚ/ር ያሳውቃሉ፡፡ ሆኖም ግን የወረዳው ም/ቤት ኃላፊዎች ለዕቅዳቸው መሳካት ዕንቅፋት የሆኑባቸውን የጉማሬ ቀበሌ ሊ/መንበር አቶ ታምሩ አምበሎን ያለ ምንም ምክንያት ከኃላፊነታቸው በማገድ በቦታቸው ም/ሊ/መንበሩ የተተኩ መሆናቸውን በመግለጽ ይኸው ተፈጻሚ እንዲሆን ጥር 16፣2003 ዓም ትዕዛዝ በማስተላለፋቸው አቶ ታምሩ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡

ይህ ከላይ የተገለጸው በአገራችን በተለያዩ ክልሎች በ‹‹ልማት›› ሰበብ በከፍተኛ ደረጃ እየተካሄደ ካለው ነዋሪዎችን የማፈናቀልና የመሬት ነጠቃ ተግባር ለአብነት ከሚጠቀሱት አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በበርካታ የአገራችን ክልሎች ምትክ የሌለው የኢትዮጵያ ውድ የተፈጥሮ ሃብት እየተጨፈጨፈ መሬቱ በሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ይህንን ግፍ እየፈጸመ ከሚገኝ አገዛዝ ጋር በማበር የዚህ ጊዜያዊ ጥቅም ተካፋይ እየሆኑ ያሉት የውጪ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ በአገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ጭምር ናቸው፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን የእነዚህን ግለሰቦች ማንነት፣ የወሰዱት መሬት ስፋት፣ አድራሻ፣ ወዘተ ዝርዝር መረጃ ስላለው ጊዜውን ጠብቆ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ያስታውቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሰሜን አፍሪካ አገራት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ወደደቡብ በመውረድ ሰሞኑን ሱዳንን አሁን ደግሞ ጂቡቲን እያናወጠ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን በአቶ መለስ የሚመራው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በውጪ አገራት አፍሪካን እየወከለ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ነኝ በማለት በዓለምአቀፍ መድረኮች ለመታየት ቢሞክርም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ግን ከእኛ ኢትዮጵያውያን የተሰወረ አይደለም፡፡ በመሆኑም አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የአገዛዙ ማክተሚያ ‹‹እንዴት ይሆናል›› የሚለው ሳይሆን ‹‹መቼ ይሆናል›› የሚለው እንደሆነ የብዙዎች ጥያቄ እየሆነ መጥቷል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አገዛዝ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብትን እያወደሙ ለዓመታት ውል እየተፈራረሙ የሚገኙ ሁሉ ልብ ሊያደርጉት የሚገባው ዋንኛ ነገር የተፈራረሟቸው ውሎችና መረጃዎች በሙሉ ከአገዛዙ ህልውና ጋር አብረው የሚያከትሙ መሆናቸውን ነው፡፡‹‹ከዘረኝነት ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በሚሰጥባት›› አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት ውሎች በሙሉ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው በአሁኑ ጊዜ በግለሰብም ሆነ በድርጅት ስም ውል የሚፈጽሙ ሁሉ በጥብቅ ሊረዱ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

አምባገነኖችና ጨቋኝ አገዛዞች ጊዜያቸውን ጠብቀው ይከስማሉ፤ አገርና ሕዝብ ግን ለዘላለም ይኖራሉ፡፡ ስለሆነም ‹‹መልካም የሆነውን ነገር ብታደርጉና ቅን የሆነውን ነገር ብትናገሩ ትድናላችሁ፡፡ ስለዚህ በሥልጣናችሁ ተመክታችሁ ድሆችን በመጨቆን አትበዝብዙ፡፡ ጉቦ ለመቀበል እጃችሁን አትዘርጉ፤ ሰው ለመግደልም ሆነ ሌላ ክፉ ነገር ለማድረግ ዕቅድ ከሚያወጡ አድመኞች ጋር አትተባሩ›› የሚለውን የፈጣሪን መመሪያ በመከተል ከሕዝብና ከሐቅ ጋር እንቁም፡፡

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

(ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ዋና ዳይሬክተሩን ለአቶ ኦባንግ ሜቶ ([email protected]) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡)