ትኩረት ለኢትዮጵያ!

በኤርምያስ ህሩይ

የግሪጎሪያኑ አዲስ ዓመት 2011 ከገባ ገና ሁለተኛ ወር ባይገባደድም አመቱን ልዩና ታሪካዊ ሊያሰኙ የሚይስችሉት በርካታ አስገራሚ ክስተቶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በመከናወን ላይ ናቸው። ከታሪካዊ ክስተቶቹ መካከል በከፍተኛ ደረጃ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት የሳበውና ፈርጀ ብዙ አንድምታ ያለው ሕዝቦች ለነጻነታቸው እያደረጉት ያለው ሕዝባዊ ትግልና ውጤቱ ነው። የኑሮ ውድነትና አምባገነናዊ አስተዳደርን በመቃውም ገና በዓመቱ የመጀመሪያ ወር በቱኒዝያ የተጀመረውና የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ለስደት የዳረገው ሕዝባዊ ተቃውሞ በወሩ የመጨረሻ ሳምንት ወደሌላዋ የሰሜን አፍሪካ ሃገር ወደ ግብጽ  በመዛመት ከቱኒዝያዊያኑ ባሻገር ግብጻዊያን የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ መሆናቸውን በተጨባጭ ያረጋገጠና ለጨካኝ አምባገነን መሪዎች ሁሉ መቀጣጫ የሆነ ሕዝባዊና ፍጹም ሰላማዊ ተጋድሎ ፈጽመዋል በመፈጸምም ላይ ናቸው።

ላለፉት 30 ዓመታት በግብጽና በግብጻዊያን እጣፈንታ ላይ ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው አልፎ ተርፎ በጎረቤት አገሮች ጉዳይ ጣታቸውን ሲነከሩ የኖሩት ሙባረክ ህዝባዊ አመጹን እንደ ልማዳቸው ከጅምሩ ለማፈን ደፋ ቀና ለማለት ቢሞክሩም የዘመናት ግፍና በደል ያንገሸገሸውን የግብጽን ህዝብ አንድነት ሰባብሮ ተቃውሞውን ማስቆም ተስኗችው በተቃራኒው ራሳቸው የአፍረት ካባቸውን ተከናንበው ስልጣናቸውን የስልጣን ባለቤት ለሆነው ህዝብ ማስረከብ ግድ ሆኖባቸዋል። ለጊዜው ሀላፊነቱን የተረከበው የሚሊቴር አካል ነጻና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አስፈጽሞ ህዝቡ በመረጠው መሪ እንዲመራ ለማደርግ የተጣለበትን አደራ በአግባቡ ይወጣል ወይስ ሌላ ታሪክ ይፈጠር ይሆን ለሚለው ጥያቄ ከወዲሁ ትምቢታዊ መልስ መሰጠት አዳጋች ቢሆንም ለጊዜው ግን ለ17 ቀናት ያለመታከት አደባባይ በመውጣት ተቃውሞውን ላሰማውና የህይወት መስዋትነት እስከመክፈል ለተጋደለው የግብጽ ህዝብ አያስፈልጉኝም ያላቸው የሙባረክና የግብረአበሮቻቸው ስልጣን መልቀቅና የህዝቡ የስልጣን ባለቤትነት መረጋገጥ አንጸባራቂ ድል ነው።

የሕዝቡ በአንድነት መቆምና ሰራዊቱ ከሕዝብ የወጣ የህዝብ አካል መሆኑንና የለበሰው ዩኒፎርም ያነገበው ጠብመንጃ ሕዝብና ሀገርን ማገልገያ እንጂ የባለሰልጣኖች ወንበር መጠበቂያ አለመሆኑን በማጤን ወገንን በጥይት ለመቁላት ባለመተባበር የሰጠው ጨዋነትና ታማኝነት የተሞላበት አገልግሎት ለውጤቱ መገኘት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱ ምክንያቶች ቢሆኑም ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ በተለይም የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረትና የኃላ ኃላ ከህዝቡ ጎን መቆማቸውን ለማሳየት የተጫወቱት ሚና ሕዝባዊ ትግሉ ከተገኘው ውጤት አንፃር እጅግ ብዙ የማይባል ጉዳት ሳያደርስ በሳምንታት ዕድሜ ጫፍ እንዲደርስ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል የሚድያዎችም ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።

ይህ የግብጽ ሕዝብ ትግል ውጤት የዜግነት መብታቸውን በአምባገነን መሪዎች ተቀምተው በአያሌ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች ተተብትበው ለሚኖሩ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ዜጎች አስተማሪና ብሩህ ተስፋ አብሳሪ ሲሆን በአንፃሩ የሕዝቦቻቸውን ጥያቄ በማፈን ወንበራቸውን ሙጥኝ ብለው ረጅም ዓመታትን እያስቆጠሩ ላሉ መሪዎች አስደንጋጭና እንቅልፍ የሚነሣ ስጋት መሆኑ ግልጽ ነው። ሥጋት ካደረባቸውም አገዛዞች አንዱ ኢሕአዴግ ነው። ለዚህም ነው ወጣቶችንና ወላጆችን በየቀበሌው አዳራሽ በመሰብሰብ ማስጠንቀቂያ መስጠት የጀመረው። ይህ ሥጋት የሚያመለክተው ነገር ቢኖር አገዛዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ከደረሰበት በደልና ግፍ የተነሣ በአገዛዙ ላይ ሥር የሰደደ ጥላቻ እንዳለበት ማመኑን ነው። ምክንያቱም ሕዝብንና ሀገርን በታማኝነት አገልግያለሁ ብሎ በጥሩ ሥራው የሚተማመን መንግሥት በሕዝቡ ላይ ለዚያውም 99.6 ፐርሰንት የሚሆነውን የምክር ቤት መቀምጫ ሰጥቶኛል በሚለው ወገኑ ላይ ስጋት አድሮበት ጣት አያወዛውዝም!

በርግጥም ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደግብጻውያኑ ሆ ብሎ አደባባይ የሚያስወጣ ችግር የለበትም፣ ተመችቶትና መብቱ ተከብሮለት ነው የሚኖረው ማለት ከቶ አይታሰብም። እንደውም የሕዝቡ ውስብስብ ችግር ቢለካ ከግብጾቹ በእጥፍ ድርብ የሚበልጥ ነው።  ስለሆነም ሕዝባዊ ተቃውሞው እንደተሰጋው ሊፈነዳ አይችልም ማለት አያስደፍርም። በመሣሪያ ታፍኖ እንጂ ትግሉማ ከግብጽ በፊት የተጀመረው በኢትዮጵያ ነበር- በ1997። ነገር ግን የብዙ ንጹሀንን ሕይወት ቀጥፎ ለጊዜው በአገዛዙ አሸናፊነት ተቋጨ። ለጊዜው ነው እንጂ ፈጽሞ ተደመደመ ማለት ግን አይቻልም የሕዝቡ ጥያቄ ገና መልስ አላገኘምና። ችግሩም ቢሆን ተባብሶ ወደ ከፋ ደረጃ ደረሰ እንጂ የተሻሻለ ነገር የለም። ታዲያ የሚበጀው የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ በመሪነትም ባይሆን በዜግነት ኑሮን በሰላም መቀጠል ወይስ በኃይልና በአፈሙዝ እያስፈራሩ የሥልጣን ዕድሜን ማራዘም? ግን እስከመቼ?

በ1997 ሕዝብ አገዛዙን የተቃወመው በዋነኛነት ለዲሞክራሲያዊ መብቱ ነበር። አሁን ግን ትግሉ ለመኖር ነው፤ ሠርቶ፣ በልቶ ለማደር! ሕዝቡ ውስጡ እየደበነና በችግር እየተጠበሰ ብሶቱን ችሎ ቀን የሚገፋው ምናልባት በ97 ከታየው አንፃር ከሕዝብ ጎን የሚቆም ሠራዊት መኖሩና መሪዎቹም ቢያንስ እንደሙባረክ በመጨረሻም ሰዓት ቢሆን ለሕዝብ የሚንበረከኩ መሆናቸው አስተማማኝ ባለመሆኑ አምላክ ዳግም የንጹሃን ደም በከንቱ እንዳይፈስና ትግሉ የዘር፣ የኃይማኖትና የቋንቋ ወደመሆን ተቀይሮ ሀገሪቱ የደም ምድር እንዳትሆን ጠብቋት ይሆናል እንጂ እንደቱኒዚያ እና ግብጽ ወንድሞቹ ሆድ ሳይብሰው ቀርቶ አይደለም። ሕዝቡ ለህልውናው፣ ባለሥልጣን ለሥልጣኑ፣ ደም የጠማውም ለእኩይ ተልኮው መራኮት የጀመረ ዕለት ያኔ ኦባማ ልክ ለግብጽ እንዳደረጉት በየቀኑ ስለኛ ይናገሩልን ይሆን? አውሮፓውያኑስ የሕዝብ ድምፅ ይሰማ ይሉልን ይሆን? ፈጣሪ ይወቀው። እንደኛ እንደኛ ግን ሰውየው ወዳጅ ናቸው ካሉ ያበጠው እስኪፈነዳ ከሚጠብቁ ከወዲሁ ቢመክሯቸውና ለሕዝቡ ጥያቄና ቅጥ ያጣ የችግር ማዕበል ትኩረት ሰጥተው ሀገሪቱን ከጥፋት ቢታደጓት መልካም ነው። ውጥረቱ ካልተነፈሰ ብሎም ከፈነዳ ምናልባት ሥልጣኑን ርስት አድርጎ የሙጥኝ ያለው አገዛዝ በምስኪኑ ሕዝብ ላይ ሊያደርሰው የሚችለው ጭፍጨፋና መከራ ራስምታቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አልፎ ለአካባቢው፣ ለአህጉሩ እና ለቀሪው ዓለም መትረፋ አይቀሬ ነውና ባለው አገዛዝ ላይ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችሉት ምዕራብያኑ ከወዲሁ ቢያስቡበት መልካም ነው። እናም ትኩረት ለኢትዮጵያ!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!