“ቅዱስ ቂርቆስ በቅድስና (በጀግንነት) እናቱን መልሶ ወለደ” በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

“ቅዱስ ቂርቆስ በቅድስና (በጀግንነት) እናቱን መልሶ ወለደ” በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

“ቅዱስ ቂርቆስ በቅድስና (በጀግንነት) እናቱን መልሶ ወለደ” በሚል ርዕስ ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ልክ የዛሬ 10 ዓመት በፊት  ካንሳስስ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት ላይ ያቀረቡት ትምህርት ወንጌል እሁን ቤተክርስቲያናችን ካለችበት ሁኒታ ጋር መስተጋብር አለው። በየዓመቱ ሐምሌ 19 ቀን በቅዱስ ገብርኤል ስም የሚከበረውን በዓል ምክንያት በማድረግ፤ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋል በኔ የሚያምን እኔ የምሰራውን ይሰራል። ከዚያም የበለጠ ይሰራል” (ዮሐንስ ወንጌል 14፡12 ) ብሎ ለክርስቲያኖች የሰጠውን መመሪያ መንደርደሪያ አድርገው፤ “ቅዱስ ገብርኤል ባከበረው በዚህ ልዕለ አዕምሮ፤ ቂርቆስ እናቱን ኢየሉጣን መልሶ ወለዳት። ኢየሉጣም ለልጇ ልጅ ሆነች” ብለው ቀሲስ አስተርአየ ይህን ትምህርት አቀረቡት። “እውነት እውነት እላችኋል በኔ የሚያምን እኔ የምሰራውን ይሰራል። ከዚያም የበለጠ ይሰራል” የሚለውን ካብራሩ በኋላ፤ “ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አባቶቻችን፤ ልጅን ወደ አባትነት፤ እናትን ወደ ልጅነት፤ አሰቃይቶ የሚገለውን የፈላውን ውሀ ወደ ክብር ዙፋንነት የቀየረውን፤ የቂርቆስን እምነትና ስነ ልቡና፤ በጽላቱ ላይ ከተጻፉት ከአሰርቱ ቃላት (ሕግጋት) አስማምተውና ከኢትዮጵያዊነት ስነ ባህርይ ጋራ አዋህደው አቅርበውታል።

ዛሬ በከፍተኛ እልቂት፣ጭፍጨፋና ውድመት ላይ ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ኢየሉጣ መልሰው እንዲወልዷትና በቂርቆስ እምነት ሞራልና ስነ ልቡና የተዘጋጀ ህሊና ያላቸውን ጳጳሳት፣ ሲኖዶስና ፓትርያርክ በዕጅጉ ትፈልጋለች። በአሁኑ ጊዜ የኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታዩ ኢትዮጵያዊ በገዛ አገሩ መንግስት በድሮንና በመድፍ አየተጨፈጨፈ ዛፍ ያጣ ጉሬዛ አደን የመመረው ሆኗል። ዐቢይ አህመድም “ቤተ ከርስቲያን ትቃጠላለች” እንዲሁም ለመንግስት ጠላት የሆኑ አካላትን ደብቃለች ብሎ በሃሰት ቤተ ክርስቲያኒቷን ወንጅሎ የሚደርስባትን ጭፍጭፋ እየመራና እያሳለጠ ይኽው 8 ዓመት ገዛ። በሰላም የሚኖረውና ለመንግስት ሰላም የሚጸልየው የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይ ዐቢይ አህመድ ባሰማራቸው ነፍስ ገዳዮች እንደ ከብት በጠራራ ፀሐይ እየታረደ ነው። ከ2,000 ዓመታት በላይ ከተለያዩ ወራሪዎች ጋር እየተጋደለ አገር ያስጠበቀው የኦርቶዶክሱ አማኝ በሚያሳዝን ሁኔታ ደሙ በግፍ ሲፈስ የሚቆረቆርለትና የሚከራከርለት ወገን አላገኘም። ሲኖዶሱና ፓትርያርኩ የግል ምቾታቸውን አስጠብቀው እንደ ከብት እየተቀለቡ ምዕመናኖቻቸውን ሊጠብቁና ሊንከባከቡ ሲገባቸው ዝም ብለው እያዩ አንዳንዴም ለገዳዩ ዐብይ አህመድ እያስተባበሉ በምዕመናን ደም ላይ እያላገጡና እየቆመሩ ይገኛሉ። ከቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ሁኒታ ጋር ተያያዥነት ያለውን የቀሲስ እስተርአየ ትምህርተ ወንጌል እንድትከታተሉ በድጋሚ አቅርበንላችኋል።