“ማኅበራዊ መገናኛ (Social Media) ለበጎ”?
“ማኅበራዊ መገናኛ (Social Media) ለበጎ”?
በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
ሰኔ ፭ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. (June 13, 2026)
ሙሉውን የቀሲስን ጽሁፍ በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ ማህበራዊ መገናኛ ለበጎ?
የዚህች ጽሑፍ ምንጭ “ማኅበራዊ ሚድያ ለበጎ” በሚል ርእስ ለሚዘጋጀው የውይይት መድረክ የተዘጋጀ የድርጊት ማስፈጸሚያ በኩረ አሳብ” በሚል ርእስ የካቲት 2018 ዓ/ም በአዲስ አበባ ተዘጋጅቶ በውጭ ለሚኖሩት ለተመረጡ ጥቂት ካህናት መነጋገሪያ ሆኖ የቀርበው ይህ ሰነድ ነው፡፡ (ሰነዱን ለማንበብ ይህን ይጫኑ)፡፡ የሰነዱ ዋና ዓላማ “የውይይት መድረኩ በኦርቶዶክሳውያን የማሕበራዊ ሚድያ እውቀት በካህናት እና መምህራን መካከል መግባባትን አንድነትን ሕሊናነትንና ሞራላዊትን በማሳደግ መኅበራዊ ሚድያ ለበጎ ነገር እንዴት “ዕቃ ጦር” ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ለማሳየት ይጥራል” የሚል ነው፡፡
መርሀ ግብሩን የሚመሩት ሳይሆኑ ከተጋባዦች አንዱ ካህን እንድሳተፍ በግላቸው ጋብዘውኝ በጽሑፍም በቃልም የተካሄዱትን ውይይቶች ሶስት ጊዜ ሰማሁ፡፡ አላማው “በኦርቶዶክሳውያን ካህናትና መምህራን መካከል የማሕበራዊ ሚድያ እውቀት መግባባትን፣ አንድነትን፣ ሕሊናነትንና ሞራላዊነትን በማሳደግ መኅበራዊ ሚድያ ለበጎ ነገር እንዴት “ዕቃ ጦር” ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ለማሳየት ይጥራል” የሚለው አሁን በዚህ ጊዜ መቅረቡ ከዚህ ቀደም የተከሰቱትን ታሪካውያን ተመሳሳይ ክስተቶችን አስታወሰኝ፡፡ ያስታወስኳቸው ታሪካውያን ተመሳሳይ ክስተቶች በውስጣቸው የተሸከሟቸው ደባወች ከኛም ከህዝቡ የተሰውሩ ባስደራጊወች ብቻ የሚታወቁ ነበሩ፡፡ ዛሬም ባስደራጊወች ብቻ የሚታወቁ ካድራጊወችና ከሚደረግበት ሕዝብ የተሰወሩ ደባወች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ አሁን “ሶሻል ሚድያ ለበጎ” ተብሎ የቀረበው ከዚህ በታች የማቀርባቸውን ታሪካውያን ትዝታወች ቀሰቀሰብኝ፡፡ በማወቅም ባለማወቅም በጥልቅ ሳይገነዘቡ በተዘረጋው ወጥመድ እንዳይገቡ የማቀርበውን ማሳስቢያ የሚያስተባብል ስለማይጠፋ የማቀርባቸው ማስረጃውች ከራሴ የመነጩ አለመሆናቸውን ለማሳየትና የራሴን ምስክርነት በአጥር ለመከላከል ታሪካውያን ትዝታወችን ማቅረብ ወቅቱ የሚያስገድድ መሰለኝ፡፡
ሁሉም ናቸው ባልልም ባሁኑ ወቅት የሚቀርቡትን ንግግሮችና ምስክርነቶች የሰውን አስተሳሰብ የሚጠመዝዙ በአሉባልታና ከጥራዝ በተነጠቁ ሐሳቦች እያጠለሹ የሚያቀርቡ ቀበያውባጢወች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን ነው፡፡ በሕዝበ ክርስቲያን መጨፍጨፍ ደስ ብሏቸው ለሚስቁና ለሚሳለቁ አረመኔወች ምስክርነቴን ከአሉባልታ የራቀና ከጥራዝ ያልተነጠቀ መሆኑን ማሳየት ግዴታ ስላለብኝ ጌታችን ኢየሱስ ያስቀመጠልንን ምሳሌ ከዚህ በታች ጠቅሻለሁ፡፡ ክርስቶስ ከሊቃውንቱ ከአንዱ ከኒቆዲሞስ ጋራ ሲነጋገር ፡ የሚነጋገረው ከኒቆዶሞስ ጋራ ብቻ ሳይሆን ኒቆዲሞስ ሕብረተ ሰቡ የሚሰማውና የሚከተለው በህዝብ የተከበበ የብዙ ሕዝብ መምህር ነውና የሚነጋገረው ከኒቆዶሞስ ጋራ ብቻ ሳይሆን ከከበበውና ከሚለተለው ሕዝብ ሁሉ ጋራ ነበር፡፡
ክርስቶስ ራሱ መምህራንና ደቂቀ አዳምን ወክሎ ኒቆዲሞስንም ከብዙ ሰወች ጋራ እንዳለ ቆጥሮ “እውነት እውነት” እልሀለሁ፦ካለ በኋላ “የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውን እንመሰክራለን”(ዮሐ 3፡11) ብሎ ለኒቆዲሞስ ነገረው፡፡ ክርስቶስ በዚህ አቀራረቡ ሁለት ምሳሌወች አስተምሮናል፡፡ የመጀመሪያው ምሳሌነት የምንናገረውና የምንመሰክረው ከፈጠራና ከጥራዝ ነጠቃ የራቀ የምናውቀውና ያየነው ሊሆን የተገባ መሆኑን የሚያስተምር ሲሆን፦ ሁለተኛው ምሳሌ ካህናት ነን መምህራን ነን ካልን የምንነጋገረው ከምናስተምረው ከከበን ሕዝብ የተሰወረ እንዳናደርገው አስጠንቃቂ ቀስት ነው፡፡ ሶሻል ሚድያ ለበጎ የሚለውን መርሀ ግብር ያዘጋጁ መምህሮቻችን በብዙ ሽ በሚቆጠሩ ምእናን ለተከበቡ መምህራንና ካህናት ነው፡፡ እኔም ሰምተው በተግባር ለማዋል የሚጥሩት ጥቂት ቢሆኑም ብዙ ሰሚወች እንዳሉ እረዳለሁ፡፡ እናም የኒቆዶሞስንና የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትለን የምንነጋገረው በራስ ተመክሮ ባየነው ባወቅነው እንዲሆንና ወደከበበን ብዙ ሕዝብ መድረሱንም ከግምት ውስጥ እንዲደርስ መሻትን ልንዘነጋ አይገባም፡፡
ከዚህ በመቀጠል “እባብ ያየ በልጥ በረየ” እንደሚባለው “ሶሻልሚድያ ለበጎ” ተብሎ አሁን መነጋገሩያ ሆኖ የቀረበው ከዚህ ቀደም ከተከሰቱት ዘዴወች፡ ከተከሰቱባቸውም ወቅቶችና ቤተ ክርስቲያንም ከነበረችባቸው ፈታኝ ታሪካውያን ክስተቶች ጋራ አንድ አይነት መስለኝ፡፡ ከዚህ ቀደም የተከሰቱት ፈታኝ ክስተቶች ያልኳቸውም ከዚህ ቀጥየ የምጠቅሳቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በ1968 አካባቢ ፓትርያርክ አቡነ ቴወፍሎስን ያወረደው “ተሀድሶ ጊዜአዊ ጉባዔ” ይባል የነበረው ጥርቅም ቤተ ክርስቲያኒቷ ኋላ ቀር ስለሆነች መታደስ አለባት በሚል ሐሳብ፡ የምትታደስበትን መርሆ ወደ ሕዝብ ለማድረስ በአዲስ አደረጃጀት ማህበራዊ ሚድያ መዘጋጀት አለበት ብሎ ወሰነ፡፡ አማረኛ ቃላት ቢያጥራቸው ከግእዙ ቃላት እየመዘዙ ሐሳብ ማቅረብ የሚችሉ በቅኔና በመጻሕፍት ጉባዕያት ትምህርት የበሰሉትን ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ መዞ ማውጣት የሚያስችል የአቅም መለኪያ ፈተና አዘጋጀ፡፡ የሚፈልጉት ስምንት ብቻ ስለነበረ በክፍተኛ ደረጃ ፈተናውን ካለፉት ከስምንቱ ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ ፈተናውን አልፈን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ስር ይካሄድ የነበረውን ሚድያ ይመራ በነበረው በአቶ ዘመድኩን ብዙ ወርቅ መሪነት ስር ተሰብስበን ቤተ ክርስቲያናችን በረዥም ዘመኗ ያጠራቀመችውን ሰበነክ ታሪኳን ከቀኖናውና ከነገረ መለኮት ባላፈነገጠ መንገድ ስልጠናውን ባመረኛ በኦሮሞኛ በትግርኛን በዑራጌኛ እየተቀበልን በጋዜጣም በራዲዮም ስራውን ቀጥለን ሳለን፡ ለካ መንግሥት ብቃት ያላቸውን ከቤተ ክህነት ጉያ ነጥሎ ወስዶ ለራሱ ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ለማድረግ ኖሯልና፡ የቤተክህነቱን የቀድስት ሥላሴንና ብሥራተ ወንጌልን ወረሰና “voice of revolution” ብሎ በላያችን አወጀ፡፡
ቤተ ክህነቱም ከምንግሥት ጋራ ተስማምቶ አዋጁን ተከትላችሁ ወደ ማስታወቂያ ምንስቴር ሂዱ አለን፡፡ ስለቀሩት ዛሬ የት እንዳሉ አላውቅም፡፡ ከስምንታችን አንዱ ለትግርኛው ቋንቋ የተሰለፈው ዛሬ በሕይወት ያለው ዘሩባቤል ነበር፡፡ የቀሩት በሕይወት ለመኖራቸው ርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ወደራሴ ልመለስና “የተማርከው ለቤተ ክርስቲያን እንጅ ለምንግሥት መሳሪያ ለመሆን አይደለም” ብለው እነ አቡነ ጎርጎርዮስ፡ አቡነ አብርሃም፡ አለቃ አስፋው፡ ሊቀ ካህናት ጥዑመ ልሳን ካሣ፡ ሊቀካህናት ክንፈገብሬል አልታየ፡ ተቃውመው በቤተ ክህነት እንድቀር አደረጉኝ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ውድቀት በገባችበት በዚያን ወቅት የተፈጸመው ሴራ አሁን ከማየው ጋራ ተመሳሳይ መሰለኝ፡፡ በደርግ ጊዜ ከተዘረጋው ወጥመድ እንዳልገባ ላተረፉኝ በህይወት ለሌሉት አባቶች ያደረጉልኝን ውለታ በዚህ አጋጠሚ ካላቀረብኩት ውለታቸውን መካድ መስሎ ተሰማኝ፡፡ ሁለተኛው ታሪካዊ ምሳሌ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ “A Political History of the Tigray people’s Liberation Front (1975-1991)” በሚል ርእስ ለDoctoral dissertation ባሳተሙት መጽሐፋቸው ከገጽ (page 246 _ page 300) ላይ የገለጹት የወያኔወች ሴራ ነው፡፡ እስካሁን በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ ሚነደው አላባራ ያለው እልቂት ወያኔወች በአቶ ገ/ኪዳን ደስታና በአቶ ስብሀት ነጋ አሰልጣኝነት የዘረጉት የጥፋት መርሆ ነው፡፡
ሶስተኛው ታሪካዊ ምሳሌ፦የወያኔ መንግሥት በብልጽግና ሲተካ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በአማራው ሕዝብ ላይ አሁን እየተካሄደ ያለው ደባ ነው፡፡ ጠ/ም ዓቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በአማራው ላይ የሚቃረኑ ክስተቶች ተፈጽመዋል፡፡ የሚቃረኑ ያልኩት ሲኖዶሱን ሲያስታርቁ አርቀው ያስተዋሉ ሰዎች የቤተ ክርስቲያኗ መሠረቶች ማለት ነገረ መለኮቱና ቀኖናውና ስርአተ ክህነቱ ሳይስተካከሉ አሁን በሁለቱም ጎራ ያሉት ጳጳሳት በዘርና በኮታ የገቡ ናቸው፡፡ እነሱን አስታርቆ አንድላይ በቤተ ክህነቱ ውስጥ ማስቀመጥ ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለጠቅላላው ሕዝብ አደጋ ይሆናሉ፡፡ በግርግር ወደጵጵስናው የገቡ እንጅ ቤተ ክርስቲያኗን ያልተረዱ አንድነቷን ጠብቀው ማስጠበቅ የማይችሉ ይልቁንም በሹመቱና በጥቅሙ ሽሚያ የሚጋጩ ናቸው ብለው የተቃወሙ ነበሩ፡፡ አልተሰሙም፡፡ ይልቁንም ይህን ሐሳብ ባፈለቁት ክርስቲያንች ላይ እየተሽቀዳደሙ በገቡት ጳሳት ከፍተኛ ተቃውሞና ጥላቻ ደረሰባቸው፡፡ ከታረቁ በኋል አዋቂወች የፈሩት ደረሰ፡፡ በመጀመሪያ ሁሉም ለጠ/ም ዓቢይ ሚድያ ሆኑ፡፡ መሳሪያ ሆኑ፡፡ በራሳቸው እስኪመጣባቸው ድረስ ህዝቡን አስገደሉ፡፡እርስ በርሳቸው ተጋጩ፡፡ አሁን የት ናቸው? ፖለቲካው እንዴት እንደተጠቀመባቸው ተመልከቱ!
መንግሥት አርጅቶና አፍጅቶ የምርጫው ጊዜ ሲቀርብ፡ ተቀናቃኞችን ሳይፈታ ያለ ጠንካራ ተፎካካሪና ተወዳዳሪ ራሱን አዝርጋጅቶ ለመቀጠል ከምርጫው በፊት ካዘጋጃቸው አዳዲስ ሴራወች ሶሻል ሚድያ ለበጎ የሚለውን አዘጋጀ፡፡ አሁን በዚህ ወቅት በአርሲ ክርስቲያኖች ላይ ልቂት በመካሄድ ላይ ሳለ፦ ሶሻል ሚድያ ለበጎ የሚለው እቅድ ወደ ዲሲ ካህናት ተልኮ ውይይቱ እንዲቀጥል ተደረገ፡፡ በዚሁ ወቅት የጠ/ም ዓቢይ አማካሪ ዳንኤል ክብረት ሰለ ሶሻል ሚድያ ለአርቲስቶችና ለጋዜጠኞች ስልጠና ሲሰጥ አየሁና አሁን ለካህናቱ መነጋገሪያ ሆነ የቀረበው ከዳንኤል ክብረተ እንደተላከ ተጠራጠርኩ፡፡ አሁን “ሶሻል ሚድያ ለበጎ” ተብሎ ከቀረበው ሰነድ እንደተረዳሁት በደርግ ጊዜ እነ ዶ/ክነፈርግብ ዘለቀ ዘርገተውት የነበረውንና የትግራይን ካህናት መምህራንና ጳጳሳትን ለማስልጠን ወያኔወች በአቶ ገ/ኪዳን ደስታና ስብሐተ ነጋ ያዘጋጁትን መርሀግብር መሰለኝ፡፡
አሁን በዚህ ወቅት ስለ ሶሻል ሚድያ አሰልጣኞቹ እነማናቸው? ለዚህ አዲስ ስልጠና የተዘጋጁት መምሕርንና ካህናት እስካሁን የት ነበሩ? እስካሁን በንግግራቸው በስብከታቸው ሕዝበ ክርስቲያን ከመበደል ተመልሰው ንስሀ ገብተው የህዝቡን መቃጠልና ስደት በበጎ(ተገቢ መንገድ) እንዲመሰክሩ ነው? ወይስ በአሸብሻቢነታቸውና ባስረጋጭነታቸው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ነው?፡፡ ወይስ መናገር ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ እስካዛሬ የተናገርኳቸው ያላውኳቸውና ያላየኋቸው ያለ ማስረጃ ፈጥሬ የተናገርኳቸው በማስመሰልና ንጹሐን ሰወችን እንደ ጎዳሁ ቆጥረው እኔን ንስሀ እንድገባ ከጠየቁኝ የተለዩ ሰወች “በቤተ ክርስቲያናችሁ ላይ የሚደርሰውን ጸዋትወ መከራ እስካሁን በተገቢው መንገድ ተደራጅታችሁ ለእግዚአብሔርም ለዐለምም አላደረሳችሁምና በቤተ ክርስቲያናችሁ ቀኖና መሠረት ክህነታዊ ተልእኳችሁን ተወጡ” የሚል ጥሪ አቅርበውላችሁ ደርሷችሁ ለመወጣት ነው?
በበኩሌ ንስሀ እንድገባ ለቀረበልኝ ጥሪ “ሰይጣን ሆይ ! እክህደከ ስንልህ በመኖራችን ንስሀ ገብተናልና ይቅር በለን” ብላችሁ እናንተ በህዝብ ፊት ንስሀ ግቡና ምሳሌ ስትሆኑኝ በንግግሬ የበደልኳቸውን በይፋ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብየ መልሻለሁ፡፡ በዚህች ጽሑፍ ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው ያለፍኩባቸው ያየኋቸውና ያወኳቸው ልምዶቼ አሁን “ሶሻል ሚድያ ለበጎ” ተብሎ የቀረበው ለበጎ አለመሆኑን እንድጠራጠር አድርጎኝ ጥያቄ ባቀርብ ኃጢአት ሆኖብኝ የንስሀ ጥሪ ይቀርብልኝ ይሆን? ለእናንተም ተመሳሳይ የንስሀ ጥሪ ቢቀርብላችሁ “ሰይጣን ሆይ! እስካሁን እክህደከ እያልን ስንክድህ ኖረናል፡ ከዛሬ ጀምሮ ‘ንሴብሐከ ወንባርከከ’ በሉና እኛም እንከተላችኋለን” የሚል መልስ ለሚጠይቋችሁ እንድትሰጡ “ሀበነ ንኅበር ወፈውሰነ” እያልን በምንሳተፋት መለኮት በተወሀዳት፡ ነፍስ በተለያት አካል አሳስባችኋለሁ፡፡