የተስፋዬ ገብረአብ – ማስታወሻዎች
ነቀፋው፤ ስድቡና ምስጋናው ጋብ በማለቱ የተስፋዬን ሁለት ስራዎች (የጋዜጠኛውና የደራሲው ማስታውሻ) የተሰኙትን መጽሃፍት ለማጣጣም ጊዜ በማግኘቴ ስለሁለቱም ያለኝን አስተያየት ባጭሩ ለመጎፈጫጨር ከዚህ በታች ያሉትን መስመሮች እጠቀማለሁ። ተስፋዬ የተዋጣለት ደራሲ ለመሆኑ ጠላቶቹ ሁሉ የሚቀበሉት እውነታ ስለሆነ የእኔ ምስክርነት አያስፈለገውም። የዚህ ጽሁፍ አላማም ምስክርነት ለመቆም አይደለም። የተስፋዬን ሁለቱን መጽሃፍት በሶስት ከፍዬ ለማየት እንጂ።
ሀ. የመጽሃፎቹ አጠራረዝ – ሁለቱም መጽሃፍት በመልካም ሁኔታ የተጠረዙ በመሆናቸው ገጻቸውን ለማገላበጥ ከመቅለሉም በላይ አልፎ አልፎ መጽሃፍትን ሳንብ እንደሚገጥመኝ ገጾች አፍትልከው አይወጡም። በዚህም የተነሳ ሃሳብን አሰባስቦ የመጽፍቶቹን መልእክት ለመከታተል ይቀላል – ማለፊያ ጥረዛ ነው።
ለ. የፊደላቱ አጣጣልና የአጻጻፍ ዜይቤው – በዘመኔ አያሌ መጽሃፍት አገላብጫለሁ። ግማሾቹ የመኖሪያ ብልሃት ፍለጋ የተከተቡ ሲሆኑ የቀሩት ደግሞ ለጊዜው ስርዓት ለማደር የተደበሉ ናቸው። አልፎ አልፎ በተባራሪ በእግራቸው የቆሙ መጽሃፍት ሲገኙ ደግሞ እስየው ያስበለኝ ነበር። አሁን እንሆ መኖሩን እንክዋን ሰምቼው የማላውቅ ተስፋዬ የሚባል ደራሲ መጽሃፍት አወጣ ሲባል በቀጥታ ሁለቱን መጽሃፍት በመግዛት በቅደም ተከተል አነበብኳዋቸው። አዝናንተው ያስተምራሉ። በተለይም የጋዜጠኛው ማስታውሻ ስብጥሩን የወያኔ የበረሃ ትግልና ከተሜ ከሆኑ ወዲህ ያላቸውን እኔ ብቻ የሚለውን ቅራሪ ህይወት አጉልቶ ያሳያል። ተስፋዬ ለሚያቀርባቸው ነጥቦችም እማኝ ስላከለበት ሲፈለግ የሚገኝ እውን ወሬ እንዳካፈለን ጥርጥር የለውም። በቀዝቃዛ ደም ሰውን መግደል ሙያ ብለው የያዙት ወያኔዎቹና ተለጣፊ ድርጅቶች እስከመቼ በሰው ደምና እንባ እየነገድ እንደሚኖሩ ባላውቅም ያለቅጥ የተጣመመና ሽፋፋ የፓለቲካ ዘይቤ እየተከተሉ እንደሆነ ህዝባችን ያውቀዋል። ጉራው፤ስድቡ፤ማስርና መግረፉ በቃ ሲለው ይቆማል። ጊዜ የማይገታው ግፍ የለምና! ሰብዓዊ ክብሩን ያጣ ትውልድ ሲነሳ ምንም ነገር አይገታውም። ያ ቀን ሩቅ አይሆንም። የተስፋዬም መጽሃፍ የሚያመላክተው ይህኑ የውስጥ ሽኩቻና የወያኔ ኢሰብዓዊነትን ነው። መቼ ይሆን ካለፈው ተምረን ለዛሬ በአዲስ ሃሳብ የምንቆመው። በጠራራ ፀሐይ ሰውን በግፍ መግደል፤ ማፈን፤ ሌብነት፤ውሽት፤ከዳተኛነት (ሃገርንና ወገንን)፤ የዘር ፓለቲካ አሳፍሮን የጋሪዮሽ አላማን የምንከተለው? በዘር የተሰመረ ፓለቲካ ለማንም አይበጅም። አሁን በሃገሪቱ ንዋይ እንዳሻቸው የሚዘንጡት የጊዜው ጌቶቻችን የአገሬ አዝማሪ
ያ ሁሉ መዝናናት ያ ሁሉ ደስታ
እልም ብሎ ጠፋ በነነ ባንድ አፍታ
እንዳለው ነው የሚሆነው። ወያኔ ዛሬን ተጠቅሞ ስብዕና የተሞላው ሁሉን ያቀፈ ለአንዲት ኢትዮጵያ ማለት እስካለቻለ ድረስ አወዳደቁ የከፋ ይሆናል።
ሐ. መጽሃፍቶቹ የሚያስተላልፉት መልእክት – ለእኔ ሁለቱም መጽሃፍት ተስማምተውኛል። መልዕክታቸው አንድ ባይሆንም ጥቅል ሃሳባቸው አንድነትን፤ የሃገር ፍቅርንና የህዝባችንን ሃበሳ (በውጭና በሃገር) ውስጥ ያመላክታሉ። ሰው በትላንት አይኖርምና ተስፋዬን በየምክናያቱ ከመወርፍ ይልቅ በርታ፤ አይዞህ ከጎንህ ተስልፈናል ብንለው ተፈጥሮ ከጊዜ ጋር ያደለውን ችሎታውን ለእኛ ጠቀሜታ የበለጠ እንዲያውለው ይገፋፋዋል። ስለሆነም ገምቢ ያልሆነ ብቅልና ጌሾ ያጀበው ዘለፋችንን ተተን እስየው በርታ አይዞህ እንበለው። በሚቀጥለው መጽሃፍትህ እስካገኝህ ፈጣሪ ይጠብⷅህ።
አደፍርስ ተሰማ